17 August 2014 Written by  EthiopianReporter

መንግሥት ክስ ተመሥርቶባቸዋል ያላቸው ሥራ አስኪያጆችና መጽሔቶች ጉዳይ መታየት ጀመረ

-የፋክትና የአዲስ ጉዳይ መጽሔቶች ተከሳሾች አልቀረቡም

-የሎሚ መጽሔት ሥራ አስኪያጅ የ50 ሺሕ ብር ዋስ ተጠየቁ

ፍትሕ ሚኒስቴር ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ክስ መሥርቼባቸዋለሁ ያላቸው የፋክት፣ የአዲስ ጉዳይ፣ የዕንቁ፣ የሎሚ፣ የጃኖ መጽሔቶችና የአፍሮ ታይምስ ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶችና የድርጅቶቹ ሥራ አስኪያጆች ጉዳይ፣ ከነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀረበው ክስ፣ በፋክት መጽሔት አሳታሚ ዩፋ ኢንተርቴይንመንትና ፕሬስ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ፋጡማ ኑርዬ ላይ ነው፡፡ ክሱ የተመሠረተባቸው ሥራ አስኪያጇ በዕለቱ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ፖሊስ ተጠይቆ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ የግለሰቧን አድራሻ ማግኘት ባይችልም በግል ስልካቸው አግኝቶ እንዲቀርቡ መንገሩን አስረድቷል፡፡ ተለዋጭ ቀጠሮም ተሰጥቶት አፈላልጎ ለማቅረብ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግም በሰጠው አስተያየት በቀጣይ ቀጠሮ ተከሳሿ ታስረው እንዲቀርቡ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ፖሊስ ተከሳሿን ባሉበት አፈላልጎ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ በማዘዝ፣ ክሱን ለመስማት ለነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፋክስ መጽሔት አሳታሚ ድርጅትና ሥራ አስኪያጇ ክስ የተመሠረተባቸው፣ የወ/ሕ/ ቁጥር 32 (1/ሀ/ለ) እና 34 (1)፣ 44 (1)፣ 257 (ሀ) እና 486 (ሀ/ለ) ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ መሆኑ የዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በፋክት መጽሔት ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል በቅጽ 2 ቁጥር 26 ታህሣሥ 2006 ዕትም፣ ‹‹የከተማ አብዮት›› በቅጽ 2 ቁጥር 35 የካቲት ወር 2006 ዓ.ም. ዕትም ‹‹የፈራ ይመለስ››፣ በቅጽ 2 ቁጥር 37 ‹‹የቁልቁለት መንገድ››፣ በቅጽ 2 ቁጥር 6 ሐምሌ 2005 ዓ.ም. ‹‹የግፉአን ዕድሜ ምን ያህል ይረዝማል?›› እና በቅጽ 2 ቁጥር 56 ሐምሌ 2006 ዓ.ም. ዕትም ‹‹የፍትሕ ዕጦት አመፅ ይጠራል›› በሚሉ ርዕሶች ሥር ሰፊ ዘገባዎች ማስፈሩን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ መጽሔቱ ባሰፈራቸው ዝርዝር ዘገባዎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ፣ በአመፅ መንገድ ለማፍረስ፣ አመፅ የሚያነሳሱ ጽሑፎችን ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ቅስቀሳ በማካሄድ፣ በመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳት ወንጀል እንደተከሰሱ የመጀመሪያው ክስ ያስረዳል፡፡ 

በፋክት አሳታሚ ድርጅትና ሥራ አስኪያጇ ላይ ሁለተኛ ክስ ሆኖ የቀረበው፣ በመጽሔቱ ቅጽ 2 ቁጥር 48 ግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ዕትሙ፣ ‹‹ሽብርተኝነትና የቀለም አብዮት የኢሕአዴግ ሥጋት ወይስ የምርጫ መጨፍለቅ ቅድመ ዝግጅት?›› በቅጽ 2 ቁጥር 30 ጥር 2006 ዓ.ም. ዕትም፣ ‹‹ዘመቻ ሰላማዊ ትግል ግባት››፣ በቅጽ 2 ቁጥር 38 መጋቢት 2006 ዓ.ም. ዕትም ‹‹ፍትሕ በሌለበት የፍትሕ ሳምንት ማክበር ፍትሕ የተነፈገባት አገር መሆኗን ያወሳል›› በሚሉ ዝርዝር ዘገባዎች፣ ‹‹በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለተጠያቂነት የማይገዙባት አገር ናት›› የሚል ሐሰተኛ ዘገባ በማሰራጨት፣ በሥርዓቱ ላይ ሕዝቡ እምነት እንዲያጣ ሐሰተኛ ወሬዎችን አትመዋል፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት የሐሰት ወሬዎችን በማውራት፣ ሕዝብን ማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 

ሌላው ነሐሴ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በተመሳሳይ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦ የታየው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት አሳታሚ፣ ሮዝ አሳታሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የሥራ አስኪያጁ  የአቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ጉዳይ ሲሆን፣ ሥራ አስኪያጁ ባለመቅረባቸው ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ሮዝ አሳታሚ ድርጅት መዘጋቱንና ሥራ አስኪያጁን ባድራሻቸው ቢፈልጋቸውም ሊያገኛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ፣ በቀጣይ ቀጠሮ አፈላልጎ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግም በሰጠው አስተያየት፣ ፖሊስ ሥራ አስኪያጁን በአድራሻቸው ፈልጎ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ አስታውሶ፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ተጠርጣሪው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠርተው እንዲቀርቡ፣ የማይቀርቡ ከሆነ ጉዳዩን በሌሉበት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

በአዲስ ጉዳይ መጽሔት አሳታሚ ድርጅትና ሥራ አስኪያጅ ላይ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ እንደተገለጸው፣ ተከሳሾቹ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 192 ህዳር 2006 ዓ.ም. ዕትሙ ‹‹እንደማይመለከትህ ስታስብ ይህንን አስታውሳ፣ እውነተኛ ሙስሊም ምንጊዜም ትግል ውስጥ ይገኛል፤ አቅም ካለው ተገቢውን ኃይል ተጠቅሞ የሚፈጸመውን ነገር ያስቆማል፤›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ዝርዝር ዘገባ፣ ሕዝበ ሙስሊሙን ለማነሳሳት የአመፅ ቅስቀሳ ማድረጉን ክሱ ያብራራል፡፡ አዲስ ጉዳይ መጽሔት በቅጽ 8 ቁጥር 215 ግንቦት 2006 ዓ.ም. ዕትሙ ‹‹በኦሮሚያ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ ቦምቦች›› በሚል ርዕስ፣ ‹‹መንግሥት የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ለማፈን የኦሮሞ ወጣቶችን የትግል ስሜት ለማኮላሸት ሆን ብሎ የወሰደው ዕርምጃ ነው፤›› በማለት በኦሮሚያ የሚገኙ ወጣቶች በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ እንዲያምፁ የሚያነሳሳ ጽሑፍ በማሳተም አሰራጭተዋል የሚል ዝርዝር ሐተታ በክሱ አካቷል፡፡

ሌሎቹ ክስ የተመሠረተባቸው የሎሚ መጽሔት አሳታሚ ድርጅት ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ ሆርዶፋ፣ የጃኖ መጽሔት አሳታሚ አስናቀ ኢንተርቴይንመንትና ፕሬስ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ አስናቀ ልባዊና የአፍሮ ታይምስ ጋዜጣ አሳታሚ ግዛውና ቶማስ ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቶማስ አያሌው ናቸው፡፡

የሎሚ መጽሔት አሳታሚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ መመልከታቸውንና ክሱ ገብቷቸው እንደሆነ ሲጠይቃቸው ክሱ ከሦስት ቀናት በፊት የደረሳቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከሕግ ባለሙያ ጋር መነጋገር እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያገኙበት ቀን በቂ መሆኑን በመግለጽ ክሱ እንዲነበብላቸውና የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ያመለከተ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ አቶ ግዛው የሕግ ባለሙያ አማክረው በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲቀርቡ እስከዛው ድረስ የ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲጠሩ ወይም እንዲያሲዙ አዟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከአገር ሊወጡ ይችላሉ በሚል፣ የዕግድ ደብዳቤ ለደኅንነት ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ባለሥልጣን እንዲጻፍ የጠየቀ ቢሆንም በወቅቱ ምላሽ አላገኘም፡፡

ድርጅቱንና ሥራ አስኪያጁን ለክስ ያበቃቸው መጣጥፍ በሎሚ መጽሔት ቅጽ 3 ቁጥር 109 ግንቦት 9 እና ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ‹‹በዓለም በጨቋኝነቷ አቻ የማይገኝላት የሚዲያ ምኅዳር በኢትዮጵያ››፣ እና ‹‹ሰብዓዊ መብት የሚባል በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተረስቷል››፣ በቅጽ 3 ቁጥር 91 እና ከጥር 24 እስከ የካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ዕትሞች ‹‹የአሸባሪነት ፈርጦች›› እና ‹‹ኢሕአዴግም ከማን አንሼ በሚል ስሜት  ተቃራኒ ሐሳብ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን ለሥልጣኔ (ወንበሬ) ያስጉኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን እያደነ በአሸባሪነት ስም ወህኒ ያወርዳቸው ከጀመረ ሰንብቷል፤›› በሚሉ ርዕሶች ዝርዝር ዘገባ መስፈሩን በመጥቀስ፣ ድርጅቱና ሥራ አስኪያጆቹ ሐሰተኛ ወሬ አትሞ በማውጣትና ሕዝብን በማነሳሳት ወንጀል በሁለት ክሶች መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለመስማት ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡