Print this page
01 August 2014 Written by  FSC

አገር አቀፍ ነፃ የሕግ ድጋፍ ሰጪዎች ቅንጅት ማቋቋሚ ሰነድ ተፈረመ

አገር አቀፍ ነፃ የሕግ ድጋፈ ሰጪዎች ቅንጅትን ለማቋቋም ሐምሌ 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም.በፍሬንድሺኘ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተዘጋጀው የአውደ ምክክር መርሃ ግብር የቅንጅቱን ማቋቋሚያ ሰነድ በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡

የምክክር መድረኩን በመክፈት ንግግር ያደረጉት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ም/ኘሬዚዳንት አቶ መድሕን ኪሮስ እንዳሉት ፍትህ የማግኘት መብት የአገሪቱ የበላይ ሕግ በሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና አገሪቱ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፉ ሰብአዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ እውቀና ያገኘ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት እንደመሆኑ መጠን በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች በሕግ ባለሙያ ለመታገዝ የመክፈል አቅም በማጣታቸው ፍትህ እንዳይዛባባቸው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት እና የሕፃናት ፍትህ ኘሮጀክት ጽ/ቤት፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጰያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ የተከላካይ ጠበቆች ቢሮዎች፣ የክልል ፍርትህ ቢሮዎች፣ የፌዴራል የሴቶች፣ የሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እና የክልል የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮዎች በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ሥር ያሉ የሕግ ትምህርት ቤቶች ያቋቋማቸው ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሙያ ማህበራትና ማህበረሰብ አቀፍ ተቋማት ቅንጅትን ለመጀመር መነሻ የሚሆን መድረክ ቀደም ብሎ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘጋጀቶ የነበረ ሲሆን በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ለቀንጅቱ መፈጠር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመራው ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ የኢትዮጰያ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሰጪዎች ብሔራዊ ቅንጅት መመስረቻ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በተበታተነና ባልተቀናጀ መልኩ በተለያዩ መንግሥታዊ አና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይሰጠ የነበረው ነፃ የሕግ ድጋፍ ተደራሽ፣ ቀጣይነት እና ተጠያቂነት ያለው የሕግ ድጋፍ አገለግሎት እንዲሆን ቅንጅቱን የሚያስተባብር አካል አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰነዱ ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ነፃ የሕግ ድጋፍ ሲሰጡ በነበሩ ተቋማት ይታዩ የነበሩትን ችግሮች ማለትም የሕግ ድጋፍ ምን ምን አገለግሎቶችን ያጠቃልላል፣ የሚሰጠው አገልግሎት ጥራት የሚቆጣጠር አካል አለመኖር፣ አገልግሎቱን ለማግኘት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ከተቋም ተቋም መለያየታቸው፣ ተመሳሳይ የሆኑ የአሠራር ማኑዋሎች አለመኖር፣ አገልግሎቶቹ በከተሞች አካባቢ ብቻ መብዛታቸው፣ በሐገር አቀፍ ደረጃ አገለግሎቱን የሚሰጡ ጠበቆች የሚያስተባብር አካል አለመኖሩ እና መሠል ችግሮችን በመቅረፍ ተቋማቱ ተናበው እና ተደጋግፈው እንደሰሩ ያደርጋቸዋል ተብሏል፡፡

በአውደ ምክክሩ ላይ የተለያዩ የምርምር ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መሃከል "በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ነፃ የህግ ድጋፍ ሰጪዎች የዳሰሳ ጥናት ግኝቶች ሪፖርት"፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ ቅንጅት ለማቋቋም አና በቅንጅት ከመስራት ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮ እና የረቂቅ ሰነዱ ይዘት ይገኙበታል፡፡ በቀረቡት የጥናት ፅሁፎች ላይ ከተወያዮች የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መሃከል የፌዴራል ሥርዓታችን እንደዚህ ዓይነት የተማከለ የፍትህ ስርዓት ይፈቅዳል ወይ? ዩኒቨርስቲዎቻችን የሕግ ክሊኒኮች የትምህርት ሥርዓቱን ማገዝ እንጂ የሕግ ነፃ ድጋፍ የመስጠት የሕግ ግዴታ የለባቸውም፣ ቅንጅቱ ራሱን የቻለ የሕግ ስብዕና ይኖረዋል ወይ? የሚሉት ሲሆኑ ከተሳታፊዎችና ከአመራሮች ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

የምክክር መድረኩን ሲመሩ የነበሩት አቶ መድሕን ኪሮስ ይህ ቅንጅት ወደፊት ራሱን የቻለ የሕግ ስብዕና እንደሚኖረው እና ይህ መድረክ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ ጠራጊ አንደሆነ አበክረው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጀ አንገብጋቢነቱ እየጨመረ መሄዱን እና በእኛም ሐገር ካለው የፌዴራል ሥርዓት ጋር የማይጣረስ እንዳውም የፌዴራል ሥርዓቱን የሚያጠናክር መሆኑን አክለዋል፡፡

በምክክሩ ማብቂያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅንጅቱን እንደመራ በውይይት መድረኩ ጉባኤ ተመርጧል፡፡

Last modified on Friday, 01 August 2014 16:45