Print this page
27 May 2014 Written by  EthiopianReporter

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ውሳኔው በፍርድ ቤት ተሻረ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ካካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ጋር በተያያዘ በኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ታኅሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ተጽፎ በተመሠረተበት ክስ በመረታቱ፣ የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔና ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተሻሩ፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻና የቦርድ ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ለረዥም ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ በነበሩት በአቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ምክንያት፣ በኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የተመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ምክር ቤቱ ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ያስተላለፈው ውሳኔ መሻሩን ያሳወቀበት ውሳኔ የተሰጠው ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩና ምክር ቤቱ የተካሰሱበት ጉዳይ መነሻ የሆነው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. መካሄዱን አስመልክቶ፣ የምክር ቤቱ አባል የሆነው ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በጉባዔው ላይ የሚሳተፍ አባል እንዲወክል ደብዳቤ በመጻፉ ምክንያት ነው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የድርጅቱን ከፍተኛ ባለድርሻና የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን መወከሉን በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡ ምክር ቤቱ ግን በድጋሚ ደብዳቤ ጽፎ አቶ ኢየሱስወርቅ ምክር ቤቱ በሚያደርጋቸው ማናቸውም ስብሰባ ላይ እንዳይወከሉ የምክር ቤቱ ቦርድ ውሳኔ ያሳለፈባቸው መሆኑን ጠቅሶ ሌላ ተወካይ እንዲልክ ለአክሲዮን ማኅበሩ ያሳውቃል፡፡

የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 16/4/ ማንኛውም አባል በጠቅላላ ጉባዔ ላይ በአካል ወይም በውክልና በመገኘት ድምፅ የመስጠት መብት እንዳለው በግልጽ መቀመጡን በመጥቀስ፣ ደንቡን በመፃረር መከልከሉ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ አክሲዮን ማኅበሩ ምላሽ መስጠቱን ክሱ ያስረዳል፡፡ አንድ አባልን ለመከልከልም ጠቅላላ ጉባዔው ስም ጠቅሶ ለቦርዱ ሥልጣን መስጠት እንዳለበትም በደንቡ መደንገጉን በክሱ አክሏል፡፡

ሌላው አክሲዮን ማኅበሩ ያነሳው ጥያቄ ደንብ ሊሻሻል የሚገባው ከጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሁለት ሦስተኛው ድምፅ ስምምነት ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ ቢደነገግም፣ ምክር ቤቱ ጥቅምት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ የአባላቱ ቁጥር 14 ሺሕ ሆኖ ሳለ፣ በጠቅላላ ጉባዔው 860 አባላት ብቻ የተገኙ ቢሆንም፣ ‹‹መተዳደሪያ ደንቡን አሻሽያለሁ›› በማለት ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቷል በሚል ጉባዔውን ማካሄዱ የሕግ ጥሰት መሆኑን በክሱ አካቷል፡፡ ከአዋጁ ውጪ ተሻሽሏል በተባለው ደንብ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው ሳይሟላ በመሆኑ ያስተላለፈው ውሳኔም እንዳይፀና በክሱ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ አክሲዮን ማኅበሩ ተወካይ እንዲልክ ከጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ማሳወቁን ጠቅሶ፣ የሚወክለው አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን መሆኑን ኅዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዳሳወቀውም ጠቅሷል፡፡ አቶ ኢየሱስወርቅ የምክር ቤቱን ስም በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና መገናኛ ብዙኃን ስም የማጥፋት ተግባር በመፈጸማቸው፣ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ ዕግድ እንደተጣለባቸው በመግለጽ፣ ሌላ ተወካይ እንዲልክ ለአክሲዮን ማኅበሩ በድጋሚ ደብዳቤ መጻፉን ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ማስታወቁን የውሳኔው ግልባጭ ያስረዳል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች የቃል ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ምክር ቤቱ ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ በታኅሳስ ወር 2001 ዓ.ም. የፀደቀውን መተዳደሪያ ደንብ ያሻሻለው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያካሄደው 9ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና ያስተላለፈው ውሳኔ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ መመርመሩ በመዝገቡ ገልጿል፡፡

 አክሲዮን ማኅበሩ በዋነኛነት ምክር ቤቱን የሚከሰው፣ ምክር ቤቱ በ2001 እና 2003 ዓ.ም. ያደረገው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ ሳይሟላ ነው በማለት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ሲመረምር ምክር ቤቱ ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ይተዳደርበት የነበረውን በታኅሳስ ወር 2001 ዓ.ም. ያፀደቀውን የ1999 ዓ.ም. መተዳደሪያ ደንብ እንዳሻሻለ ማስረጃ ማቅረቡን ጠቅሷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ማስረጃዎችና ተሻሽሏል ስለተባለው መተዳደሪያ ደንብ በስፋት አትቶ፣ ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ሕገወጥ እንዲባልለት ያቀረበውን ጥያቄ ምክር ቤቱ ያሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ሕገወጥ አለመሆኑን ጠቅሶ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያደረገው 9ኛ መደበኛ ጉባዔና ያስተላለፈው ውሳኔ እንዲሻርለት ያቀረበውን ክስ ፍርድ ቤቱ መርምሮታል፡፡

ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው አክሲዮን ማኅበሩ የምክር ቤቱ አባል ነው፡፡ በመሆኑም በመተዳደሪያ ደንቡ የተሰጡት የተለያዩ መብቶች አሉት፡፡ ምክር ቤቱ በሚያደርገው ጉባዔ ላይ መገኘት፣ ድምፅ መስጠት፣ መምረጥ፣ መመረጥና በአመራር ቦታ የመወከል መብት ያለው መሆኑን በደንቡ አንቀጽ 9/2/ሀ ሥር መደንገጉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አባሉ ከአባልነት እንዲሰረዝ እስካልተደረገ ድረስ ሁሉም መብቶቹ እንዲጠበቁለት በደንቡ አንቀጽ 11 መሠረት መደንገጉን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ 

ከላይ የተገለጹትን የአንድ አባል መብቶች ምክር ቤቱ ካላሟላ፣ የሚያካሂደው ጉባዔ በሕጉና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት አባሉ ጉባዔው እንዲሻር የመጠየቅ መብት እንዳለው ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

አቶ ኢየሱስወርቅም በአክሲዮን ማኅበሩ ተወክለው ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በምክር ቤቱ 9ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ ቢሆንም በጉባዔው እንዳይገኙና ድምፅ እንዳይሰጡ፣ በብዙ ትግል በጉባዔው ቢገኙም ድምፅ እንዳይሰጡ መከልከላቸው፣ የተከለከለው ግለሰቡ ሳይሆን አክሲዮን ማኅበሩን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በሕግ አግባብ ከአባልነት እንዲታገድ ካልተደረገ በቀር፣ ራሱ መቅረብ የማይችል (Fictious Person) በመሆኑ ተወካዩን በመላክ በጉባዔው ድምፅ የመስጠት መብት ያለው መሆኑን፣ የተወከሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ መከልከላቸው የሕግ አግባብነት እንደሌለው ገልጿል፡፡

አቶ ኢየሱስወርቅ በመጨረሻ በጉባዔው እንዲሳተፉ መደረጉን ምክር ቤቱ ቢገልጽም፣ ፍርድ ቤቱ ከምስክሮቹ ሲያጣራ ከብዙ ውዝግብ በኋላ ወደ ጉባዔው መግባታቸውን፣ የድምፅ መስጫ ካርድ እንዳልተሰጣቸውና እንዳልተመዘገቡ ማረጋገጡን ጠቁሞ፣ ከመጀመርያውም መከልከላቸው አግባብ እንዳልሆነ፣ ድምፅ የመስጠት፣ የመመረጥ፣ የመምረጥ፣ ሐሳብና አስተያየት የመስጠት መብት መነፈጋቸውን፣ የመምረጫ ካርድ እንዳልተሰጣቸው ወይም ስለመስጠቱ ምክር ቤቱ ማስረጃ አለማቅረቡን ፍርድ ቤቱ አትቷል፡፡

በመሆኑም ምክር ቤቱ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያደረገው 9ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጉንና መተዳደሪያ ደንቡን ባልተከተለ ሁኔታ የተደረገ በመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባዔውና በጉባዔው የተላለፈው ውሳኔ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 273 መሠረት መሻሩን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በሚመለከት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት አቶ ኢየሱስወርቅ እንደገለጹት፣ ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ መረጃ ባገኘበት ጉዳይ ላይ አጥጋቢና አርኪ የሆነ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ለእኔ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤት መሄድ ምን ያደርጋል እያሉ ተስፋ ለሚቆርጡ ጥሩ ማሳያ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በቂ መረጃ የመሰብሰብና ነገሮችን የመከታተል አቅም ያለው እንደማይመስላቸው የተናገሩት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ ምክር ቤቱ የተሳሳተ መረጃ ሲሰጠው እስከ መጨረሻው ሄዶ ባለማረጋገጡ ካቀረቡዋቸው ሁለት ክሶች አንዱን ክስ ብቻ ትክክል ነው ሊል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ ከጀመረበት ጊዜ ማለትም ከነሐሴ 26 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ምልዓተ ጉባዔው ያልተሟላ ጉባዔ አድርጎ አያውቅም፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ ምክር ቤቱ እውነታውንና በቃለ ጉባዔ ተጽፎ የሚገኘውን መረጃ በመደበቁ፣ ፍርድ ቤቱ መንገዱን የሳተ ፍርድ እንዲሰጥ መገደዱን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሁሉንም ነገር እንደሚያውቁና እስከ 5ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ያለው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ በምልዓተ ጉባዔ መካሄዱን የሚያሳይ ቃለ ጉባዔ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ዋናው ክሱ ‹‹እኔ ወኪል ነኝ›› ሳይሆን የምክር ቤቱ ሕግ እየተጣሰ በመሆኑ ሕግ ይከበር መሆኑን የገለጹት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ ላለፉት አራት ዓመታት የተጣሰው ሕግ ሊስተካከል እንደሚገባውና ይግባኝ ብለው ሕግ እንደሚያስከብሩ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በውክልና መጥራት ሲገባው በነፍስ ወከፍ እየጠራ የሚፈለገው ሕጋዊ መንገድ ሊያዝ እንዳልቻለ የሚናሩት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ በተወካዮች ምክር ቤት በወጣው አዋጅ ቁጥር 341/95 አንቀፅ 9 (2) መሠረት የወጣውን መተዳደሪያ ደንብ ሙሉ በሙሉ እንደተሻረ ምክር ቤቱ መናገሩ፣ አስደንጋጭና ፍፁም ከአገሪቱ ሕግ ውጪ በመሆኑ ዝም ብሎ መታየት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ንግድ ምክር ቤቱን እየመራውና እያንቀሳቀሰው ያለው ተመራጩ ሳይሆን ተቀጣሪው ነው፤›› ብለው፣ ይኼ ደግሞ ለምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ጉዳይ አደገኛ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡