Print this page
14 May 2014 Written by  Ethiopianreporter

በሽብርተኝነት የተጠረጠሩት እነ አቡበከር አህመድ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት ጀመሩ

የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤትን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ላይ ይግባኝ ተጠየቀ

ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ በማለት ሕገወጥ ኮሚቴ አቋቁመውና የእምነት ነፃነትን የሚቃረን፣ ከራሳቸው አክራሪ አስተሳሰብና አስተምህሮት ውጪ፣

ሌላ እምነትም ሆነ አስተምህሮት እንዳይኖር የሃይማኖት አስተማሪዎች ቡድን በህቡዕ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩት፣ እነ አቡበከር አህመድ መሐመድ (18 ሰዎች) የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ከግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ማሰማት ጀመሩ፡፡

በአወሊያ ኮሌጅና በሌሎች መስጊዶች የተነሳው የሙስሊሙ እንቅስቃሴ መነሻው ምን እንደነበር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃሊቲ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎትና ለከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ስለተከሳሾች ቀርበው የመከላከያ ምስክርነታቸውን ያሰሙት የመጀመሪያው ምስክር እንደገለጹት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት አወሊያ ኮሌጅና መስጊድን የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፍ የእስልምና ድርጅት ነበር፡፡ ድርጅቱ ሲለቅ ደግሞ በቦርድ እንዲተዳደር ተደረገ፡፡ ከቦርዱ በኋላ በ2003 ዓ.ም. መጅሊስ እንደተረከበው ተናግረዋል፡፡

መጅሊሱ ኮሌጁንና መስጊዱን እንደተረከበ የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ኮሌጁና መስጊዱ የአሸባሪዎች መፈልፈያ እንደነበር በመናገራቸው፣ ማኅበረሰቡ ቅሬታ አድሮበት እንደነበር ምስክሩ ገልጸዋል፡፡ በቅሬታ ውስጥ የነበረው ማኅበረሰብ ቅሬታው ሳይፈታ ከስድስት ወራት በኋላ በታኅሣሥ ወር 2004 ዓ.ም. በኮሌጁ ዓረብኛ የሚያስተምሩ መምህራን መታገዳቸውን የገለጹት ምስክሩ፣ የመባረራቸው ምክንያት በአህባሽ ሥልጠና ላይ እንዲሳተፉ በማስታወቂያ ተነግሯቸው ሳይሳተፉ በመቅረታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መምህራኑ ሲባረሩ የኮሌጁና የመስጊዱም ኢማም አብረው መባረራቸውን ምስክሩ አክለዋል፡፡

የመምህራኑን መባረር ተከትሎ ተማሪዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን የገለጹት የመከላከያ ምስክሩ፣ ‹‹የቀረን ስድስት ወር በመሆኑ ከስድስት ወራት በኋላ አዲስ ካሪኩለም ይቀየራል፡፡ በመሆኑም መምህራኖቻችን ተፈትተው የጀመርነውን የዓረብኛ ትምህርት እናጠናቅቅ፤›› በማለት ቅሬታቸውን ለመጅሊሱ ማቅረባቸውን ምስክሩ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹የሚመለከታችሁ ነገር ስለሌለ አርፋችሁ ተቀመጡ›› በማለት ለተማሪዎቹ ጥያቄ መጅሊሱ ምላሽ መስጠቱን የተናገሩት ምስክሩ፣ ተማሪዎቹ በምላሹ በመበሳጨት ‹‹ይኼንን ቀላል ጥያቄ መመለስ ካቃተው መጅሊስ አይወክለንም፣ አህባሽም በግድ አይጫንብንም፤›› በማለታቸው ወደ ውዝግብ መገባቱን የመከላከያ ምስክሩ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩ እያሰጋ በመምጣቱ የተማሪዎቹንና የሙስሊሙ ማኅበረሰብን ጥያቄ የሚያስረዳ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች፣ ከወላጆችና ከአካባቢው ነዋሪዎች የተውጣጣ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን ምስክሩ አስተውሰዋል፡፡ ኮሚቴው ሲቋቋም የመንግሥት ተወካዮችና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ኃላፊዎችም መገኘታቸውን ምስክሩ አብራርተዋል፡፡

ኮሚቴው መጅሊሱን ለማነጋገር ሲሄድ ቀደም ሲል የቀረበውን ጥያቄ በአንድ ወር ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥበት የተናገረውን በማለፍ፣ ምላሽ የሚሰጠው በሁለት ወራት ውስጥ መሆኑንና ይኼም የሚመለከተው ኮሌጁን እንጂ ተማሪዎቹን እንደማይመለከታቸው በመግለጽ ኮሚቴውን እንደመለሰው ምስክሩ ገልጸዋል፡፡

የጉዳዩ አሳሳቢነት እየጠነከረ በመምጣቱ ኮሚቴው ወደ ወከለው ማኅበረሰብ ተመልሶ መጅሊሱ የሰጠውን መልስ በማስረዳት፣ የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩን ይዘው ቢመሩት እንደሚሻል ሲናገር ከኮሌጁ ማኅበረሰብ ጋር መግባባት እንዳልተቻለና ነገሩ እየከረረ መምጣቱን መከላከያ ምስክሩ አስረድተው አብቅተዋል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግም ድርጊቱ ማለትም በኮሌጁና በመስጊዱ የተቀሰቀሰው አለመግባባት መቼ፣ እንዴትና እነማን እንዳስነሱት ላቀረበው ጥያቄ የመከላከያ ምስክሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተጠርጣሪ ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክሮች ከ400 በላይ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ከግንቦት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ለአንድ ወር እንደሚያዳምጥ ያዘዘ ቢሆንም፣ የመከላከያ ምስክሮቹን ፍርድ ቤቱ ባለበት ቀን ከግንቦት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ መስማት አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በመዝገቡ ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤትን ጨምሮ 12 ሰዎች በብይን በነፃ ከተሰናበቱ በኋላ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱና መዝገቡ በመላኩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአቶ ጁነዲን ባለቤት ወ/ሮ ሀቢባ መሐመድን ጨምሮ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ያለባቸው ስምንት ግለሰቦች ቢሆኑም፣ የሁለት ግለሰቦች ይግባኝ ብቻ ውድቅ ሲደረግ ወ/ሮ ሀቢባን ጨምሮ በስድስቱ ላይ የቀረበው ይግባኝ ያስቀርባል መባሉ ተጠቁሟል፡፡