የትግራይ ክልል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀምና በሙስና ወንጀል ይከሰሳቸውን አራት ግለሰቦች እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጣ።
ተከሳሾቹ አቶ አብዱልቃድር ኢብራሂም ሁሴን ፣ አቶ ጎይቶም አሰፋ ልጃለም ፣ አቶ ደሱ ሀለፎም ወዳጀ ፣ አቶ ሙሀመድ ብርሀን ሙሀምድ የተባሉ ናችው።
1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በወልቃይት ወረዳ የውሀ መስኖና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሀላፊና የግምጃ ቤት ሰራተኛ ሆነው ሲያገለግሉ ፥ 180 ኩንታል ሲሚንቶ ለግል ኮንትራክተሮች እንዲሰጥ በማድረግ ፣ 72 ሺህ ብር ደግሞ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ክስ ነው የተከሰሱት።
በተጨማሪም ሁለተኛ ተከሳሽ 390 ኩንታል ሲሚንቶ ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሽ በጽህፈት ቤቱ የመስኖና የመጠጥ ውሀ ባለሙያና መሀንዲስ ሆነው ሲያገለግሉ ፤ ሶስተኛ ተከሳሽ 221 ኩንታል ሲሚንቶ ፣ አራተኛ ተከሳሽ ደግሞ 260 ኩንታል ሲሚንቶ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል የእምነት ማጉድል ወንጀል ተከሰዋል።
ተከሳሾቹም ክሱን መከላከል ባለመቻላቸው የክልሉ ምዕራብ ዞን መካከለኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ፥ 1ኛ ተከሳሽ በ6 ዓመት እስራትና በ10 ሺህ ብር ፣ 2ኛ ተከሳሽ በ10 ዓመት እስራትና በ15 ሺህ ብር ፣ 3ኛ ተከሳሽ በ4 ዓመት እስራትና በ8 ሺህ ብር ፣4ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ15 ዓመት እስራትና በ80 ሺ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።