Print this page
30 April 2014 Written by  EthiopianReporter

ይቅርታ የሚያስከለክሉ በሚል በረቂቅ የይቅርታ ሕጉ የተዘረዘሩት ወንጀሎች ተሰረዙ

የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ይቅርታ የማያሰጡ የወንጀል ዓይነቶችን የሚዘረዝረው አንቀጽ ሙሉ በሙሉ ተሰረዘ፡፡ ሌሎች ማስተካከያዎች የተካተቱበት ይህ የይቅርታ አዋጅ ባለፈው ማክሰኞ ፀድቋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ክፍል ሦስት አንቀጽ 14 ንዑስ አንድ በሕገ መንግሥቱ ይቅርታ የሚያስከለክሉ ተብለው ከተቀመጡት ወንጀሎች በተጨማሪ ይቅርታ የሚያስከለክሉ ወይም የማይጠየቅባቸው በማለት ከአሥር በላይ ወንጀሎችን ዘርዝሮ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ግብረ ሰዶም፣ ሙስና፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነት መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ወንጀል የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡ 

ረቂቅ አዋጁን መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የታዘዘው የፓርላማው የሕግ፣ የፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ማክሰኞ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የተጠቀሰውን አንቀጽ 14 ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ በሌላ ተክቷል፡፡ 

እንደ አዲስ የተተካው የአንቀጽ 14 ድንጋጌ ‹‹በሌሎች ሕጎች የተደነገጉ ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 የተደነገገውን የይቅርታ ዓላማ ለማሳካት ቦርዱ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቀርቡለትን የይቅርታ ማመልከቻዎች ከመንግሥትና ከሕዝብ ጥቅም አንፃር በማመዛዘን ያስተናግዳል፤›› በሚል እንዲተካ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

በፓርላማው ብቸኛ የተቃዋሚ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ‹‹ይቅርታ የማይጠየቅባቸው ወንጀሎችን የሚዘረዝረው አንቀጽ ለምን በዚህ መልኩ ተቀየረ? ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ውይይት ክፍት በተደረገበት ወቅት በሌላ እንዲተካ አልተወሰነም፡፡ በምክር ቤቱም አልተነሳም፡፡ ከተዘረዘሩት ወንጀሎች መካከል የግብረ ሰዶም ወንጀል መጠቀሱ የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ በተለያየ መንገድ እጅ የመጠምዘዝ ሥራ ተሞክሯል፡፡ ግብረ ሰዶም ወንጀል ይቅርታ የማያሰጥ ተደርጎ መግባቱ ከሕገ መንግሥቱና ከሕዝብ ሞራል አንፃር ትክክል ነበር፤›› በማለት ተቃውመዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ መልስ የሰጡት የፓርላማው የሕግ፣ የፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕ አስተዳደር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ አስመላሸ ወልደ ሥላሴ የአቶ ግርማን አስተያየት በመቃወም ‹‹እጅ መጠምዘዝ ማለት ምን ማለት ነው? ነውርና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ንግግር ነው፤›› በማለት ወቅሰዋል፡፡ ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ ሕግ ወንጀል መሆኑን የገለጹት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹እጅ መጠምዘዝ ነው›› የሚለውን የአቶ ግርማ ሰይፉ አስተያየት ተችተዋል፡፡

የተዘረዘሩት ይቅርታ የማያሰጡ ወንጀሎች እንዲወጡ የተደረገው ይቅርታ የማያሰጡ በማለት ዝርዝር ከተጀመረ መቆሚያ ስለማይኖረው፣ ይህንን አዋጅ በየጊዜው የማሻሻል ግዴታ ውስጥ ያስገባል በማለት ምክንያቱን ተናግረዋል፡፡

ለአብነት ያህል ሲያስረዱም፣ ከዚህ በኋላ በሚወጣ ሕግ ከዚህ በፊት በወንጀል ሕጉ ያልነበረ ወንጀል ሊደነገግ ይችላል፡፡ ይህ ወንጀል ይቅርታ የማያሰጥ ከሆነ ይህንን የይቅርታ አዋጅ ማሻሻል ሥራ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ በመርህ ደረጃ ብቻ የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅምን ከግንዛቤ በማስገባት ይቅርታ ሊደረግ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ረቂቅ የይቅርታ አዋጁ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን ይቀንሳል የተባለው አሁን በሥራ ላይ ከሚገኘው የይቅርታ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር እንጂ በሕገ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጠው የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር ተነፃፅሮ አለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የይቅርታ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጁ ፕሬዚዳንቱ በይቅርታ ቦርዱ የሚቀርቡ የይቅርታ ውሳኔ ሐሳቦችን ወደ ጎን በተመው ለምሳሌ ይቅርታ አያሰጥም የሚል የውሳኔ ሐሳብ ቢቀርብ በመቀልበስ ይቅርታ መስጠት የሚያስችላቸው ነበር፡፡ ረቂቅ የይቅርታ አዋጅ ግን ፕሬዚዳንቱ በይቅርታ ቦርድ ተገምግሞ ይቅርታ ይሰጠው የሚለውን የውሳኔ ሐሳብ  በመመርኮዝ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት ብቻ ነው የሚኖራቸው፡፡

ይህንን በተመለከተ በምክር ቤቱ ተነስቶ ለነበረ ጥያቄ አቶ አስመላሽ የሰጡት ምላሽ፣ ይቅርታ ማድረግ የመንግሥት መብት መሆኑንና የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ፕሬዚዳንቱ በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል ብቻ እንደሚል ገልጸው፣ በሕግ መሠረት ማለት ዛሬ የምናውቀው ሕግ ነው ብለዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል የይቅርታ ዓላማን የተመለከተው አንቀጽ አንዱ ነው፡፡ ‹‹የይቅርታ ዋና ዓላማ፣ የመንግሥትና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መንግሥት ጥፋተኞች በጥፋታቸው የተፀፀቱና የታረሙ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች ዜጋ እንደሆኑ ማድረግ ነው፤›› በሚል ተተክቶ አዋጁ ፀድቋል፡፡

Last modified on Wednesday, 30 April 2014 17:45