Print this page
29 April 2014 Written by  FanaBC

አቶ ቃሲም ፊጤ በነፃ ተሰናበቱ

የፌደራሉ ከፍተኛ  ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር  የመሬት አስተሰዳደር ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም ፊጤ ተከሰው የነበረበትን የሙስና ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ  እንዲሰናበቱ ወሰነ።

ተከሳሾቹ አቶ ቃሲም ፊጤን ጨምሮ  የሊዝ አሰባሰብ ክትትል ባለሙያ አቶ ገብረየስ ኪዳኔ፣ የመሬት አቅርቦት አፈፃፀም ንዑስ የስራ ሂደት መሪ በቀለ ገብሬ እና በአስተዳደሩ የፍትህ ቢሮ የምርመራና ክስ ኤክስፐርቱ ተስፋዬ ዘመድኩን ናቸው።

የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ተከሳሾች በህገ ወጥ መንገድ በመመሳጠር የተሰጣቸውን ስልጣንና  ሃላፊነት በግልፅ ተግባር ያላአግባብ በግድፈት በመገልገል፣ ለሌላ ሰው ህገ ወጥ የሆነ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ  የሙስና ወንጀል ነበር ክስ መስርቶባቸው የነበረው።

ኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ የሚባሉ ግለሰብ በቦሌ ክፈለ ከተማ ወረዳ 3 ክልል የተሰጣቸውን 500 ካሬ ሜትር ቦታ ያለአግባብ ለሌላ አልሚ ተመሳጥረው ባልተገባ መንገድ እንዲተላለፍ አድርገዋል የሚል ነበር ጥቅል ክሱ።

የክሱ ሂደት እስከዛሬ ሲካሄድ ቆይቶ፥ ቀድም ብሎ አቃቤ ህግ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን ያስረዳልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቀረቧል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ይከላከሉ ወይም አይከላከሉ የሚለውን ለመበየን ዛሬ ይዞ በነበረው ቀጠሮ አቃቤ ህግ ክሱን በማስረጃ ማስረዳት ባለመቻሉ፥  አቶ ቃሲም ፊጤን ፣ አቶ ገብረየስ ኪዳኔንና በቀለ ገብሬን ክሱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ ብሏል።

ሌላው በክስ መዝገቡ የተካተቱት የአስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ የምርመራ ክስ ኤክስፐርቱ አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን የተመሰረተባቸው የሙስና ክስ የመንግስትን ስራ በማይመች አኳኋን መምራት በሚል በሌላ አንቀፅ ተሻሽሏል።

ይህ ክስ ደግሞ የዋስትና መብት የሚከለክል ባለሙሆኑ 5 ሺህ ብር በዋስትና አስይዘው መፈታት እንዲችሉ በማለት እንዲከላከሉ ቀጠሮ ቢይዝም፥ ተከሳሹ አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን የማቀርበው የመከላከያ ማስረጃ የለኝም፤ ቅጣት ይሰጠኝ በማለቱ ችሎቱ ለዛሬ ሳምንት ቀጠሮ ይዟል።

Last modified on Tuesday, 29 April 2014 15:59