Print this page
23 April 2014 Written by  EthiopianReporter

ለአክሰስ ሪል ስቴት ተጐጂዎች የቆሙ ጠበቃ ፈቃዳቸው ለሁለት ዓመት ታገደ

አዲስ ደንበኛ ለሆኑዋቸው የአክሰስ ሪል ስቴት ተጐጂዎች ጠበቃ በመሆን፣ በቀድሞ ደንበኛቸው ላይ ክስ መሥርተዋል የተባሉ የሕግ አማካሪና ጠበቃ የጥብቅና ፈቃዳቸው ለሁለት ዓመት ታገደ፡፡ 

በጥብቅና ፈቃዳቸው ላይ ለሁለት ዓመት እግድ የተጣለባቸው ጠበቃ አቶ ሲሳይ ተፈራ ናቸው፡፡ እግዱን የጣለባቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ የእግድ ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች የዲሲፕሊን ጉባዔ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎ ነው፡፡ 

በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፊርማ የፀደቀውና ተፈጽሟል የተባለው ጥፋት፣ እሳቸው የሕግ አማካሪ ሆነው ሲሠሩበት በነበረው ፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ ሪል ስቴት ላይ ሲሆን፣ ድርጅቱን ሳያማክሩ ወይም ፈቃድ ሳይጠይቁ፣  አማካሪ የነበሩበትንና ከአራት ዓመታት በላይ የሚያውቁትን የድርጅቱን ሚስጥር ተጠቅመው አዲስ ደንበኛ ለሆኗቸው የአክሰስ ሪል ስቴት ተጐጂ ነን ለሚሉ ግለሰቦች ጠበቃ በመሆን ክስ በመመሥረታቸው ነው፡፡ 

ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ከጠበቆች ማኅበር የተውጣጡ ስምንት አባላት ላሉት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች ዲሲፒሊን ጉባዔ አቤቱታ ያቀረበው ፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ በአቤቱታው እንደሚያስረዳው፣ ከጠበቃ ሲሳይ ተፈራ ጋር ከኅዳር 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ውል ፈጽመው አማካሪ በመሆን መሥራት ጀምረዋል፡፡ ከድርጅቱ ጋር በሠሩባቸው ዓመታት አክሰስ ሪል ስቴት ከፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ ሪል ስቴት አክሲዮን ለመግዛት ሲደራደር ጠበቃው በአማካሪነት የሠሩ ቢሆንም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 57/1992 አንቀጽ 10 እና 12 ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ፣ አዲስ ደንበኛቸው ለሆኑት የአክሰስ ሪል ስቴት ተጎጂዎች በኩል ሆነው በድርጅቱ ላይ ክስ መመሥረታቸው የዲሲፕሊን ግድፈት መሆኑን በማመልከቻው ጠቅሶ ለጉባዔው አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ 

ጠበቃ ሲሳይ በበኩላቸው ለቀረበባቸው የዲሲፕሊን ጉድለት ክስ ለጉባዔው በሰጡት ምላሽ፣ ከፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ ሪል ስቴት ጋር የአሠሪና ሠራተኛ ውል ባይኖራቸውም ከድርጅቱና ከእህት ድርጅቶች ጋር ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በውል የሕግ ምክርና የጥብቅና አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን አልካዱም፡፡ ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ከድርጅቱም ጋር ሆነ ከሠራተኞቹ ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁ የተናገሩት ጠበቃው፣ ከጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ  ውል ማቋረጣቸውን በመግለጽ ያልተከፈለ ክፍያ መጠየቃቸውንም በምላሻቸው ጠቁመዋል፡፡ 

ሁለቱ ሪል ስቴቶች አክሲዮን ለመግዛት ሲደራደሩ አለማማከራቸውን፣ ምክር የሰጡት አክሰስ ካፒታል ሰርቪስና ምቾት ሪል ስቴት በሰኔና በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ከፓስፊክ ሊንክ ጋር ሲደራደሩ መሆኑን ጠበቃ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

የአክሰስ ሪል ስቴት ተበዳይ የሆኑ 137 ሰዎችን በመወከል ክስ የመሠረቱ መሆኑን የገለጹት ጠበቃ ሲሳይ፣ ከፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ ጋር ሲሠሩ ግለሰቦቹ (ከሳሾቹ) ግንኙነት እንዳላቸው (ከፓስፊክ ጋር) እንደማያውቁ በመልሳቸው አስረድተዋል፡፡

ከሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች በኩል የቀረቡ ማስረጃዎች ጠበቃውና ድርጅቱ የነበራቸውን ግንኙነት የሚያስረዱ በመሆናቸው፣ የሰዎች ምስክሮችን መስማት አስፈላጊ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ጉባዔው የሁለቱንም ክርክር መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ጠበቃው ‹‹በቀድሞ ድርጅቱ ላይ አዲስ ደንበኞቹን በመወከል ክስ ማቅረብ ይችላል ወይስ አይችልም?›› የሚል ጭብጥ ይዞም መርምሯል፡፡

አቶ ሲሳይ የፓስፊክ ሊንክ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሆነው ሲሠሩ፣ የድርጅቱንና እህት ኩባንያዎች እንዲሁም የዋና ሥራ አስኪያጁን ንብረቶች በሥራ አጋጣሚ ስለሚያውቁ፣ አዲስ ደንበኛ ለሆኗቸው የአክሰስ ሪል ስቴት ተጐጂዎች ንብረቶቹን ሁሉ በመዘርዘር እንዲታገዱ አድርገው ትልቅ የጥቅም ግጭት መፍጠራቸውን አመልካች ያስረዱትን ሐሳብ ጉባዔውም አረጋግጧል፡፡ ጠበቃው የፓስፊክ ሊንክ ሚስጥርን አዋቂ መሆናቸውን ከሁለቱም ወገኖች የቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ ፍንትው አድርጐ እንደሚያሳይ ጉባዔው አክሏል፡፡ 

በመሆኑም ‹‹ጠበቃው በሥራ አጋጣሚ ያወቀውን ሚስጥር በመጠቀም ፓስፊክ ሊንክን አዲስ በመሠረተው የክስ ሒደት አልጐዳም ማለት አይቻልም፤›› በማለት፣ ከፓስፊክ ሊንክ ኢትዮጵያ ሪል ስቴት ፈቃድ ሳያገኙ ለሌላ ደንበኛ ክስ መመሥረታቸው ተገቢ አለመሆኑን ጉባዔው በውሳኔ ሐሳቡ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም ጠበቃው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ሥነ ምግባር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 57/1992 አንቀጽ 13 ሥር የተመለከተውን በመተላለፋቸው ጥፋተኛ ማለቱን አስታውቋል፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ አዋጅ ቁጥር 199/1992 አንቀጽ 24(3ለ/2/ መሠረት የጥብቅና ፈቃዳቸው ለሁለት ዓመት እንዲታገድ ጉባዔው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ የፍትሕ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በተሰጠው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ተግባራዊ ይሁን፤›› በማለት አፅድቀውታል፡፡

Last modified on Wednesday, 23 April 2014 11:55