Print this page
23 April 2014 Written by  EthiopianReporter

ለፍርድ ቤት አልታዘዝ ባለው ክፍለ ከተማ ምክንያት የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ጥብቅ ትዕዛዝ ደረሰው

-ክፍለ ከተማው ለሕግ ተገዥ አለመሆኑ ትልቁ ሥጋት መሆኑም ተጠቁሟል 

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲና የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ የደረሳቸውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊቀበሉ ባለመቻላቸው፣ የአስተዳዳሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ጥብቅ ትዕዛዝ ደረሰው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ መጋቢት 17 እና መጋቢት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኤጀንሲውና ለጽሕፈት ቤቱ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ተግባራዊ ሊሆን ባለመቻሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቢታዘዝም፣ እሱም ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ በክፍለ ከተማው ሁለት ተቋማትና በከንቲባው ጽሕፈት ቤት የተበሳጨው ፍርድ ቤት፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ባስተላለፈው ጥብቅ ትዕዛዝ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርቦ፣ መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ያልፈጸመበት ምክንያት ከበቂ ማስረጃ ጋር እንዲያስረዳ በድጋሚ አዟል፡፡

የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤትና የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ መርካቶ ሲኒማ ራስ አጠገብ ከሚገኘውና ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ካስቆጠረው ሐረር ሆቴል ሕንፃ ጋር በተያያዘ ጉዳይ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ባለሦስት ፎቅ በሆነው ሐረር ሕንፃ ላይ ከ11 በላይ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሆኑ ሱቆች ወይም 15 ነጋዴዎች በአክሲዮን ይደራጁና ‹‹ወሎ የገበያ ማዕከል አክሲዮን ማኅበር›› የሚል ማኅበር ያቋቁማሉ፡፡ በ4.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ2004 ዓ.ም. የተቋቋመው አክሲዮን ማኅበር በፍትሕ ሚኒስቴር የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሕጋዊነቱ ተረጋግጦ በጅምላ አከፋፋይነት፣ በፋብሪካ ውጤቶች አከፋፋይነት፣ በጉዞ ወኪልና አስጎብኚ ድርጅትነትና በሆቴል አገልግሎትና ችርቻሮ ንግድ ሥራ መሰማራቱን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ማኅበሩ የአስተዳዳሩ ፕላን በሚፈቅደው መሠረት ደረጃውን የጠበቀ ሕንፃ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ እያለ፣ ከመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ነጋዴዎቹ የግል ንብረታቸውን ባስቸኳይ በማውጣት የሚሠሩበትን ሕንፃ እንዲለቁ ዳብዳቤ ይደርሳቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዘመናዊ የሲኒማ ሕንፃ (ለራስ ቴአትር ቤት) ለመገንባት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጠይቆ ቦታው በከተማ አስተዳደሩ (በአቶ ኩማ ደመቅሳ ጊዜ) መሬት ልማትና አስተዳደር ቦርድ በቃለ ጉባዔ ቁጥር 18/2003 ዓ.ም. ሰኔ 15 ቀን 2003 ዓ.ም. ተፈቅዷል በሚል ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ኃይሌ ፍስሐ ሰብሳቢነትና በእነ አቶ ቃሲም ፊጤ አስረጅነት ቦርዱ ውሳኔ ያሳረፈበት ቃለ ጉባዔ እንደሚያስረዳው፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለዘመናዊ ሲኒማ ቤት መገንቢያ 3,000 ካሬ ሜትር ቦታ ጠይቆ ተወስኖለታል፡፡

በሲኒማ ራስ አካባቢ የሚገኙትን 13 የመንግሥት ቤቶች ንብረት የሆኑ መኖሪያ ቤቶችና ሁለት የግል ቤቶችን ጨምሮ የተገኘው ቦታ ሥፋት 2,995 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ አሁን ውዝግብ ያስነሳው ሐረር ሆቴል ሕንፃን እንደማይጨምር ወይም እንሚጨምር የቦርዱ ውሳኔ ያለው ነገር የለም፡፡

በመሆኑም ወረዳው 2,995 ካሬ ሜትር ቦታን ከማስረከብ ባለፈ፣ የሐረር ሆቴል ሕንፃን ማፍረስ ሲጀምር የወሎ ገበያ ማዕከል እክሲዮን ማኅበር ባለድርሻዎች ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱም አቤቱታውን ተቀብሎ ለመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ፣ ቦርዱ በቃለ ጉባዔ ቁጥር18/2003 ከሰጠው ውሳኔ አኳያ ለማኅበሩ ምላሽ እንዲሰጠው የከንቲባው ማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪና የሊዝና ኅብረተሰብ ጉዳዮች የሥራ ሒደት መሪ በአቶ እሸቱ አየለ ፊርማ 76 ገጽ ያለው ሰነድና በደብዳቤ ልኳል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ትዕዛዝ ምንም ያልመሰለው ኤጀንሲው ለማኅበሩ በሰጠው ‹‹ንብረታችሁን አውጡ›› ትዕዛዝ መሠረት ጊዜውን ጠብቆ ሕንፃውን ካናቱ ማፍረስ ሲጀምር፣ የማኅበሩ አባላት ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ የዕግድ ትዕዛዝ በማምጣታቸው፣ በመፍረስ ላይ የነበረው ሕንፃ በጅምር ሊቆም መቻሉምንም የማኅበሩ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ቀርቦ እንዲያስረዳ በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ባለመቅረቡ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ቢታዘዝም እሱም ሳይቀርብ መቅረቱ ታውቋል፡፡ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ሁለቱ ተቋማት ለምን እንዳልቀረቡ እንዲይስረዳ ቢታዘዝም፣ እሱም በመቅረቱ ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ምክንያቱን በማስረጃ አስደግፎ እንዲያስረዳ በጥብቅ ታዟል፡፡

ቤተሰቦቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን ጭምሮ ከ1,500 በላይ ሰዎችን እያስተዳዳሩ መሆናቸውን የሚናገሩት የማኅበሩ አባላት፣ የአስተዳደሩ ቦርድ ከወሰነው ውጪ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሕጋዊ ድርጅታቸውና ማኅበራቸው እንዳይፈርስና ወደ ሥራ አጥነት እንዳይገቡ መንግሥት እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሰነዶች ማስረጃ በተጨማሪ ለምን በቦርድ ከተወሰነው ውጪ ወረዳው የማኅበሩን ሕንፃ ለማፍረስ እንደፈለገ ለማነጋገር የከተማ ማደስ ኤጀንሲውንና የመሬት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም፣ እንዳተለመደው ‹‹አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ናቸው›› በመባሉ አልተሳካም፡፡ 

Last modified on Wednesday, 23 April 2014 11:56