Print this page
24 March 2014 Written by  addisadmassnews

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ተነሱ

12 ዳኞች በስነ-ምግባር ጉድለት ከኃላፊነት ተነስተዋል

ለበርካታ ዓመታት የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታረቀኝ አበራ አይዶ ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ምክትላቸው የነበሩት አቶ ሙሉጌታ አጎ፤ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል፡፡ በክልሉ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሲያገለግሉ የነበሩ 12 ዳኞች፤ በስነ-ምግባር ጉድለት ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ታረቀኝ ለበርካታ ዓመታት ጠቅላይ ፍ/ቤቱን በመሩበት ወቅት ባሳዩት የሥራ ክፍተትና የስነ-ምግባር ጉድለት ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ምንጮቻችን ቢጠቁሙም፣ የክልሉ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ ሃሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታረቀኝ፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ወደ ኔዘርላንድ ለመሄድ ባመለከቱት መሰረት፣ተፈቅዶላቸው መሄዳቸውን ነው የማውቀው” ብለዋል፡፡

ከክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ጀምሮ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በዳኝነት ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ 12 ዳኞች በስነ-ምግባር ጉድለት ከኃላፊነት መነሳታቸውን በተመለከተ የጠየቅናቸው አቶ ሙሉጌታ አጎ፤ ዳኞቹ ባሳዩት የስራ ክፍተትና የስነ-ምግባር ጉድለት በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ተወስኖባቸው ከሃላፊነት እንደተነሱ አስረድተዋል፡፡ 

ቀደም ሲል “ቡታጅራ ላይ በድንጋይና በዱላ ተደብድበው የሞቱት ኢ/ር ጀሚል ሀሰን ቤተሰቦች፤ አቶ ታረቀኝ አበራ ባስቻሉት የይግባኝ ችሎት፣“የገዳዮቹን ፍርድ ያለአግባብ ቀንሰዋል” በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ጉዳዩ እንደገና በሰበር ሰሚ ችሎት ታይቶ፣ በወንጀለኞቹ ላይ ከፍተኛ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡