በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ያሉት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ እና ሌሎች አራት ተከሳሾች ያቀረቧቸው ሶስት የክስ መቃወሚያዎች ውድቅ ተደረጉ።
የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም ክስ የመሰረተባቸው አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ አቶ ዘሱ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ እዮብ ጌታቸው፣ አቶ በላይነህ ደሴ እና አቶ እሸቱ አጥላው ናቸው።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች በዛሬው እለት ያቀረቧቸውን ሶስት መቃወሚያዎች ውድቅ ያደረገ ሲሆን፥ ክሱን አስመልክተው በሰጡት የእምነት ቃልም ወንጀሉን አልፈፀምንም ብለው ክደው በመከራከራቸው ችሎቱ የአቃቤ ህግን ማስረጃ ለመስማት ለመጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ሆነው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋር አብረው የተደመሩት ባለሀብቱ አቶ ማሞ ኪሮስ ዛሬ በዋስትና 30 ሺህ ብር አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ችሎቱ የበየነ ሲሆን፥ ተመስርቶባቸው የነበረው የሙስና ወንጀል ክስም ወደ ከባድ የማታለል ወንጀል እንዲሻሻል ተወስኗል።
ተከሳሹ ከአገር እንዳይወጡም ለዜግነትና ኢሚግሬሽን ጉዳይ መምሪያ ደብዳቤ መፃፉም ተገልጿል።
ችሎቱ የተከሳሹን የመከላከያ ምስክር ለማድመጥም ለሚያዚያ 2 ፣ 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
በሌላ በኩል የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ባለደረባ የነበሩት አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል ከነቤተሰቦቻቸው ከተመሰረተባቸው የሙስና ወንጀል ክሶች መካከል በ11ኛው ክስ ላይ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ችሎቱ ለመጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።