ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተዘረፈ የተባለው ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ባንኩ በሰጠው ማስተባበያ አስታወቀ
በባንኩ ሠራተኞች የተዘረፈውን የገንዘብ መጠን አስር ሚሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችልና ከሶስት የተላያዩ ቅርንጫፎች መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ካስነበበ በኋላ ባንኩ ባወጣው ማስተባበያ የገንዘቡን መጠን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ የተዘረፈው የገንዘብ መጠን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንደማይደርስ ፣ ተዘረፉ የተባሉትም ቅርንጫፎች ሶስት ሳይሆኑ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ቅርንጫፎች ብቻ መሆናቸውን እና 450 ሺሕ ብር ማስመለሱንም ገልጿል፡፡
በባንኩ ማስተባበያ እንደተገለጸውበ ተጠርጣሪዎቹ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን በወላይታ ቅርንጫፍ ግን ማጭበርበሩ እንዳልተፈጸመ ጠቁሟል፡፡
የባንኩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች አሠራራቸውን በመፈተሽ ቀዳዳዎችን ከመድፈን ይልቅ ‹‹የተዘረፍነው የገንዘብ መጠን ትንሽ ነው›› በማለት ማስተባበያ መስጠታቸው የባንኩ ደንበኞች እምነት እንዳያጡና ያስቀመጡት ገንዘብ በዚህ መጠን እየተዘረፈ እንደሆነ የተሳሳተ ግምት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ነው መባሉን ስማቸው ያልተጠቀሰ የስራ ሃላፊን በመጥቀስ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
በአዲስ አበባ ቅርንጫፍና በፊንፊኔ ቅርንጫፍ ላይ የተፈጸመውን የማጭበርበር ወንጀል ሙከራም ሆነ በሌሎች ቅርንጫፎች ላይ የተሞከሩትን በማክሸፍና ተጠርጣሪዎችንም ለሕግ በማቅረብ አሠራሩን እያጠራ እንደሚሄድ እንዲሁም የተፈጸመው የዝርፊያ ሙከራ የከሸፈ ቢሆንም ድርጊቱ ግን እውነት መሆኑን ኃላፊው መናገራቸውን ጋዜጣው አስነብቧል፡፡