Print this page
13 February 2014 Written by 

ለመሬት ጉዳዮች ወጥተው የነበሩ 13 መመርያዎች ሊሻሻሉ ነው

በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአሠራር ችግሮችን ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 13 መመርያዎችን ለማሻሻል ረቂቅ እያዘጋጀ ነው፡፡

እየተዘጋጁ ካሉት መመርያዎች መካከል የሊዝ አዋጅን ለማስፈጸም የወጣው መመርያ፣ ሕገወጥ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቶ የነበረው መመርያ፣ የካሳና ምትክ ቦታ መመርያ፣ ከቤት ውጭ በተለያዩ ቦታዎች የሚሰቀል ማስታወቂያ መመርያና የይዞታ አስተዳደር ማሻሻያ መመርያ ይገኙበታል፡፡ 

የከተማው አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች ከ13 መመርያዎች ውስጥ አምስቱን አዘጋጅተው መጨረሻቸውንና የአዲስ አበባ ከተማ ፍትሕ ቢሮ አስተያየት እንዲሰጥበት መላኩን፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሐሰን አቡዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የተቀሩትን ስምንት መመርያዎች ለፍትሕ ቢሮና ለከተማው ካቢኔ አቅርቦ ይሁንታ ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን አቶ ሐሰን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኅዳር 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅና የከተማው አስተዳደር አዋጁን ለማስፈጸም ያወጣው መመርያ እርስ በርሳቸው እንደሚቃረኑ ታምኗል፡፡ 

አዋጁን በሚመለከት የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከመመርያው ጋር ያለውን ተቃርኖ አጥንቶ ለመንግሥት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በመነሳት የከተማው አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የከተማው አስተዳደር ያፀደቀውን የሊዝ አፈጻጸም መመርያ ለማሻሻል እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

በሁለተኛ ደረጃ እየተስተካከለ የሚገኘው ሕገወጥ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ በቀድሞው የከተማው አስተዳደር የተዘጋጀው መመርያ ነው፡፡ ይህ መመርያ በአስተዳደሩ የተለያዩ የሥልጣን ወቅቶች በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ እየተዘጋጀ የነበረ ነው፡፡ የሊዝ አዋጅ እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ ያሉ ሕገወጥ ባለይዞታዎችን ሕጋዊ እንዲደረጉ ከደነገገ በኋላ፣ ይህ ረቂቅ መመርያ በዚህ መንፈስ መዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡ 

ነገር ግን ይህንን መመርያ ማፅደቁ ሕገወጥ የመሬት ወረራን ያበረታታል በሚል የተለያዩ አስተያየቶች በመሰንዘራቸው መመርያው በረቂቅ ደረጃ እንዳለ በድጋሚ እንዲከለስ በመወሰኑ፣ ቢሮው ይህንኑ መመርያ በመከለስ ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ከዚህ ጋር ሕገወጥ ባለይዞታዎች የሚባሉትም ሆኑ ነባር ሰነድ አልባ ባለይዞታዎች የያዙት የመሬት ልኬትም በዚሁ መመርያ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡

ሌላው የተካሰና የምትክ ቦታ መመርያ ነው፡፡ በልማት ምክንያት ለሚነሱ ባለይዞታዎች የሚከፈለው የቦታ ካሳ ቀደም ሲል የወቅቱን የገበያ ሁኔታ በማገናዘብ  በየሁለት ዓመቱ እየተጠና ይከለስ ነበር፡፡ ነገር ግን በአፈጻጸም በኩል ችግር በመታየቱ   ይህንን መመርያ በድጋሚ ማስተካከል አስፈልጓል ተብሏል፡፡  

ሌላው የሚሻሻለው መመርያ ከቤት ውጭ የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የተዘጋጀው መመርያ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው የተለያዩ ቦታዎች የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች የከተማውን ውበት እያሳጡ ናቸው በሚል እንደ አዲስ ለማስተናገድ አዲስ መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙስና መፈልፈያ ናቸው ካላቸው ዘርፎች አንዱና ዋነኛው የመሬት ዘርፍ ነው፡፡ አስተዳደሩ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ይህንን ዘርፍ ለማስተካከል በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን ሲያወጣ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የወጡት ሕግጋቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ይገባባቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ከሁለት ዓመት በኋላ ወጥተው የነበሩትን መመርያዎች በድጋሚ በመከለስ ሥራ ላይ ማተኮሩ እንዳልተዋጠላቸው የአስተዳደሩ ነባር ሠራተኞች ይገልጻሉ፡፡ ሠራተኞቹ አንድ አሠራር ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በቂ ጥናትና ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

Last modified on Thursday, 13 February 2014 09:40
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)

Website: www.facebook.com/ethiopianlaws