Print this page
10 February 2014 Written by 

በቀድሞው የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሠራተኛ ላይ የዓቃቤ ሕግ የክስ ማሻሻያን ለማድመጥ ተለዋጭ ቀጠሮ ተያዘ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት በቀድሞው የሀገር ውስጥ ደህንነት ሰራተኛ ላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ ማሻሻያ ለማድመጥ ተለዋጭ ቀጠሮ ያዘ።

የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ፤ በአቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት ወንድማቸው ዘርአይ ወልደሚካኤል፣ እህታቸው ወይዘሪት ትርሃስ ወልደሚካኤልና የቅርብ ጓደኛቸው ዶሪ ከበደ ላይ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ተጨማሪ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሹ በ 2002 ዓ.ም "ቴረሪዝም ኢን ኢትዮዽያ ኤንድ ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ" የተሰኘ መጽሃፍ ያሳተሙ ሲሆን ፥ ይህንን መጽሃፋቸውን በስፖንሰር ለማሳተም ባደረጉት እንቅስቃሴም  የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ በየነ ገ/መስቀል የነበራቸውን ቀና አስተሳሰብ ተጠቅመው ያለአግባብ በልጽገዋል በሚል ተከሰው ነበር።

ተከሳሹ አቶ ወልደስላሴ ባልደረባቸወ የሆኑ አንዲት ሴት ጋር በነበራቸው መቀራረብ የመስሪያቤቱን  መኪና በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ እያስሞሉ ግለሰቧ እንደልባቸው በአዲስ አበበባና ከከተማ ውጪ እንዲጠቀሙበት አስደርገዋል የሚለውም ተጠቅሶባቸዋል።

ተከሳሹ ባለ4 ፎቅ የግል ቤቱን ወንድሙ ለሆነው ሁለተኛ ተከሳሽ ዘርአይ ወልደስላሴ ውክልና ሰጥቶና ከመኖሪያ ቤት ውጭ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል አድርጎ በ14 ወራት ውስጥ 790 ሺህ ብር ገቢ አግኝቷል ፤ ከገቢው 126 ሺህ ብር የሚሆነው የመንግስት ግብርን ለግብር አስገቢው መስሪያቤት ሃሰተኛ መግለጫ በማቅረብ ሳይከፍል መቅረቱም በክሱ ተመልክቷል።

እንዲሁም ምንም አይነት የገንዘብ ልውውጥ ሳያደርጉ ከ3ኛዋ ተከሳሽ እህቱ ትርሃስ ጋር መጋቢት 24፣ 2005 ዓ.ም የብድር ውል ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

1ኛው ተከሳሽ ወልደስላሴ ወደሚካአል ከ1983 እስከ የካቲት 2005 ዓ.ም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የውስጥ ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ ፥ ወርሀዊ ደመወዙ ከ 1,600 እስከ 6,000 ብር የነበር ሲሆን ፥ ነገር ግን ስልጣኑን እና የነበረውን ተሰሚነት በመጠቀም በፈጸመው የሙስና ወንጀል ከባለ4 ደረጃ ህንጻ ውጪ ፣ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በተለያዩ የግልና የመንግስት ባንኮች ተቀማጭ ማድረጉም ተመልክቷል።

2ኛ ተከሳሽ አቶ ዘርአይ ወልደስላሴ ከመከላከያ ሚኒስቴር በጡረታ እስከሚገለል ድረስ ወርሀዊ ደመወዙ 532 ብር የነበር ሲሆን ፥ በክስ መዝገቡ ተከሳሹ በተለያዩ ባንኮች 5 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማስቀመጡ ፣ በአዲስ አበባ ቤቴል ቁጥር 3 በተባለ አካባቢ  በ74 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ መሰረት የተጀመረበት ቦታ ፣ በአፋር ክልል ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሁለት የእርሻ  ኢንቨስትመንቶችና 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ሁለት ሎደር ማሽነሪዎችም በስሙ መኖራቸው ተመዝግቧል ።

3ኛዋ ተከሳሽ የአቶ ወልደስላሴ እህት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ፥ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት እንደሆነች ነው በክስ መዝገቡ የተገለጸው።

ግለሰቧ በ 81 ሺ ዩሮ የተገዛ አንድ ስካቫተር ፣ አውቶሞቢል መኪና፣ በአዲስ አበባ ቦሌና የካ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በለገጣፎ ፣ በመቀሌና አክሱም ከተሞች 3 ሺህ 266 ካሬ ሜትር ቦታዎች በስሟ ተመዝግቧል ፤ በተለያዩ ባንኮችም ከ 8 ሚሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብም እንዲሁ ተመዝግቧል።

የአቶ ወልደስላሴ የረዥም ጊዜ ጓደኛ እንደሆነ የሚነገርለት 4ኛው ተከሳሽ ዶሪ ከበደ አቶ ወልደስላሴ በቤተሰቦቹ ስም በሚስጥር የያዘውን ከፍተኛ ሃብት ይዞ በማቆየት የወንጀል ተሳትፎ አድርጓል ነው የሚለው ክሱ።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ንብረትና ገንዘብ ለማፍራት የሚያስችል ምንም አይነት አቅም ሳይኖራቸው በፈጸሙት ምንጩ ያልታወቀ  ንብረትና ገንዘብ ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬ ውሎው በጠበቆች ቅዋሜ መሰረት ፥ የተከሳሽ  ሃብት ተይዟል የተባለበት ጊዜ በክሱ አልተካተተም ፣ የአቶ ወልደስላሴ ሃብት ወደ ሌሎች ተከሳሾች ተሸጋገረ የተባለበት መንገድ ግልፅ አይደለም የሚለውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ዓቃቢ ህግ የክስ ማሻሻያውን ዛሬ አቅርቧል።

የተከሳሽ ጠበቃ ደግሞ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት የቀረበ አይደለም ፤ የመከላከል መብታችንን ያሳጣናል እንዲሁም ግልፅ አይደለም በማለቱ ችሎቱ ይህን አጣርቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 13 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

Last modified on Monday, 10 February 2014 16:33
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)

Website: www.facebook.com/ethiopianlaws