የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህፃናት ሽያጭን፣ የህፃናት የወሲብ ንግድና ህፃናትን በወሲብ ተግባራት ማሳተፍን ለመከላከል የወጣውን የህፃናት መብቶች ተጨማሪ ስምምነትን አፀደቀ።
ህፃናትን በተለየ ሁኔታ ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርገው የወሲብ ቱሪዝም በፍጥነት መስፋፋቱንና ከዚህም በላይ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ለማቆም በማስፈለጉ ተጨማሪ ፕሮቶኮል መዘጋጀቱ በትናንቱ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተመልክቷል።
የህፃናት ገላ ንግድና የወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች እንዲበራከቱ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱትን ሁኔታዎች ኋላቀርነት፣ ድህነት፣ የኢኮኖሚ ልዩነት፣ የፈረሱ ቤቶች፣ ከገጠር ወደ ከተማ ስደት፣ የወጣቶች ሀላፊነት የጎደለው የወሲብ ፀባይ፣ ጎጂ ባህላዊ ልማዶች፣ የህፃናት ንግድና ለመሳሰሉት አፋጣኝ መፈትሄ ለማበጀትም የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ነው።
በፀደቀው ተጨማሪ ፕሮቶኮል መሰረትም ህፃናትን ለወሲብ ብዝበዛ ማዋል፣ ለወሲብ ሽያጭ አሳልፎ መስጠት፣ መቀበል፣ መግዛት፣ ማቅረብ፣ እንዲሁም የወሲብ ፊልም ማሰራት ማከፋፈል፣ ማሰራጨት፣ ወደ አገር ማስገባት፣ ወደሌላ አገር መላክ፣ ማቅረብ እና መሸጥ ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ፕሮቶኮሉ ወንጀል ብሎ የደነገጋቸው ጉዳዮች ቀደም ብላ ካላት የወንጀል ህግ ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው እንድትፈፅም የሚጠበቅባት አዲስ ግዴታ ባይኖርም ፥ ፕሮቶኮሉን ማፅደቅና ተፈፃሚነቱን መከታተል የህፃናትን በስነ ምግባር እና በመልካም ባህሪ ታንፆ ማደግ የሚያግዝ በመሆኑ ተጨማሪ ፕሮቶኮሉ መፅደቁን ነው ያስታወቀው።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ህፃናትን በጦርነት ማሳተፍን በሚመለከት የወጣውን የህፃናት መብት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ስምምነትን አፅድቋል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ህፃናት በግጭትና ጦርነት እንሰዳይሳተፉ ከመከላከል አንፃር ከመንግስት የሚጠበቁ ተግባራት እንደሚገኙበት ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ወይም የክልል ፖሊስ አካላት ህፃናትን ለወታደራዊ አገልግሎት የማይቀጥሩ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፥ በተጨማሪ ፕሮቶኮሉ መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛውን እድሜ መደንገጉ ጠቃሚ ይሆናል ብሏል።