የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ አንድ እንጀራ ደረጃውን አሟልቷል ሊባል የሚችልበትን የደረጃ መስፈርት አዘጋጀ ።
በዚህም መሰረት በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም እንጀራን በማቅረብ የተደራጁ ሌሎች ማህበራት የተቀመጠላቸውን ደረጃ በማሟላት ወደ ውጭ ሀገር መላክ የሚያስችል ስርአት ተዘርግቷል ።
ኤጀንሲው አንድ እንጀራ ሊያሟላ ይገባል ብሎ ያስቀመጠው መስፈርት ፥ ሙሉ በሙሉ ከጤፍ የተጋገረ ሆኖ 310 ግራም የሚመዝን መሆን አለበት ፤ ዲያሜትሩ ወይም ከጫፍ እስከ ጫፍ ሲለካ እንጀራው 52 ሳንቲ ሜትር በተጨማሪም ሲተጣጠፍ መሰባበር የማይችል ሊሆን ይገባል።
ሌላው እንጀራው ጀርባው ልሙጥ ሆኖ ከፊት ለፊት አይኖቹ ጎላ ጎላ ብለው የሚታዩ መሆን አለባቸው።
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት አገልግሎት ሀላፊ አቶ ዳንኤል ዘነበ ይህ ደረጃ ሊወጣለት የቻለው በአምራቾች ጥያቄ አማካኝነት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ሀገራዊ ምርት የሆነውን እንጀራን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት አጋዥ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ትልልቅ ተቋማት እነዚህን ደረጃዎች ካሟሉ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የተመቻቸ አሰራርን ሊዘርጉ እንደሚችሉም ነው የጠቀሱት።