አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገሪቱ የእምነት አኩልነትና ተቻችሎ የመኖር የሃይማኖት እሴትን ሊያጎለብት የሚችል ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም እንዳሉት በሃይማኖቶች ስም የሚደረጉ የፖለቲካና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለመግታት አንዲቻል የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች የሚተገብሩት ረቂቅ ህግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል ፤ በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ ይህንን አሰራር እንደሚያሰፍን ታምኖበታል።
መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በህገ መንግስቱ መካተቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ፥ ይህም በረቂቅ አዋጁ መደገፉን ነው ያብራሩት።
የሃይማኖት ተቋማትና መንግስት በሰላምና በልማት እሴቶች ላይ በጋራ ተባብረው እንዲሰሩም ረቂቅ አዋጁ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።