የሻዕቢያ መንግስት በኢትዮጵያ ለመፈጸም ላቀደው የሽብር ተግባር ተባባሪ የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተከሳሾች በ18 እና 20 አመት ጽኑ እሰራት እንዲቀጡ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ተከሳሾቹ አብርሀ ኪዱ ማሞ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ሀብቶም ገብሩ ወልደኪድ የተባሉ ሲሆኑ ፥ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን እገላ ወረዳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመሰለል ለሻዕቢያ መረጃ ያቀብሉ የነበረና ለሽብር ተግባር የሚሆኑ የተለያዩ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በማጓጓዝ ስራ ላይ የተሰማሩ ነበሩ።
ተከሳሾቹ ሶስት የወንጀል ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን የመጀመሪያው የአገርን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ፣ሌላው ደግሞ በህገወጥ መንገድ የአትክልት ውጤቶችን ከአገር ሲያወጡ እና ሲያስገቡ እንዲሁም ሲሸጡ መገኘት ሲሆን ፥ ሶስተኛው ክስ ደግሞ ለሻዕቢያ ተላላኪዎች መረጃ በማቀበል እና በሽብር ድርጊት ተባባሪ ሆነው በመገኘታቸው ነው።
አምስት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበው የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአደዋ ተዘዋዋሪ ችሎትም ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ በ18 ዓመት እስራተ እንዲቀጣ ሲወሰን ሁለተኛ ተከሳሽም የአገር ክህደት በማክበጃነት ተይዞበት በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ችሎቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ወስኗል። (sourceአዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2006(ኤፍ.ቢ.ሲ.))