የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15 ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል ክስ በተመሰረተባቸው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገቦች ላይ የተለያዩ ትእዛዞችን ሰጠ።
የፌዴራል የስነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በሁለተኛ መዝገብ በቁጥር 14፣ 13 54 ከዘረዘራቸው 18 ተከሳሾች መካከል የሰባቱ ክስ እንዲቋረጥ እና የሌሎቹ ባለበት እንዲቀጥል ማመልከቻውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም ህግ በማጣቀስ ኮሚሽኑ ክስ የመሰረተባቸውን ወገኖች በማናቸውም ጊዜ የመሰረትኩት ክስ ይቋረጥ የማለት መብቱን በመጥቀስ፤ የክሳቸው ይቋረጥልኝ ማመልከቻውን ተቀብሎ ትዝዛዝ ሰጥቶበታል።
ክሳቸው እንዲቀረጥ የቀረቡት ግለሰቦችም አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ አቶ አምሃ አባይ ፣ አቶ ግርማ ታፈሰ፣ አቶ ተስፋዬ መርጊያ፣ አቶ አስፋው ወሰን አየለ፣ አቶ አማረ ገብረ ወልድ እና አቶ ሙሉጌታ ባልቻ ናቸው።
ግለሰቦቹ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በመሆን እና በመመሳጠር ከሰባት የሚበልጡ የንግድ ድርጅቶች የሚፈለግባቸውን የመንግስት እዳ እንዲቀነስላቸው እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንዲቀር በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል፤
እንዲሁም የመንግስትን ስራ በማይመች አኳዃን በመምራት ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ባለፈው ሳምንት የኮሚሽኑን መጥሪያ ተቀብለው ፍርድ ቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸው እንደተከለከለም አይዘነጋም።
በዚሁ መዝገብ 15ኛ ተከሳሽ የሆኑት እና ባለፈው የፍርድ ቤት ውሎ ችሎት ያለቀረቡት አቶ መስፍን አህመድ፥ ዛሬ ተይዘው ቀርበው የተመሰረተባቸው ክስ ተነቦላቸው ግለሰቡ በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን በተለያየ የስራ ሀላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ የመንግስትን ስራ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው፤
ከተለያዩ ደርጅቶች ጋር በመመሳጠር ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ805 ሺህ ብር በላይ በማጉደል ለግል ጥቅማቸው በማዋል፤ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ቶሚ እንተርናሽናል ሬስቶራንት፤ ሀሰተኛ ደረሰኝ አሳትሞ በቸልታ የመንግስት ገቢ እንዲጓደል አድርገዋል የሚሉና ሌሎች የሙስና ወንጀሎች መፈማቸው በክስ ዝርዝሩ ተካቶ ቀርቧል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የጠየቁተን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ትእዛዝ ሰጥቷል፤
ከሰነድ ማስረጃዎች አቀራረብ ጋር ተያይዞ በተነሱ ጉዳዮች፤ ማስረጃው የተሟላ አይደለም፣ ያልተተረጉሙ ማስረጃዎች ቀርበዋል የማይነበቡ ከቁጥር አንጻር የሚጎሉ ተመላሽ መሆን ያለባቸው የሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮችም ተነስተው ፍርድ ቤቱ ተመልክቷቸዋል።
ፍርድ ቤቱም በሶስቱም መዝገቦች የቀረቡ የማስረጃ ጉዳዮች ሀሙስና አርብ ተሟልተው እንዲቀርቡ ተዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የሰጠባቸው ጉዳዮች ተሟልተው እንዲቀርቡ ለህዳር 9 ቀን 2006 አመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ በመያዝ የእለቱን ችሎት አጠናቋል።