1. ከወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ለውጦች

  • ረቂቁ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ከግምት በማስገባትከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢየሚል አዲስ የገቢ ዓይነት በግብር ሥርዓቱ ውስጥ አካቷልይህ ገቢ ግለሰብ ወይም ድርጅት የቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎቶችን፣ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን፣ የድምጽ ማስተላለፊያ (ፖድካስት) አገልግሎቶችን እና የቀጥታ ስርጭት መድረኮችን ጨምሮ በኦንላይን መድረኮች ላይ ዲጂታል ይዘትን በመፍጠርና በማሰራጨት የሚያገኘውን ማንኛውንም የገንዘብ ወይም የገንዘብ ነክ ያልሆነ ገቢ ያካትታልይህም የማስታወቂያና ስፖንሰርሺፕ፣ የምርት ስም ስምምነቶች፣ የአጋርነት ግብይት፣ የደጋፊዎች አስተዋጽኦ እና የዲጂታል/አካላዊ ሸቀጦች ሽያጭ ገቢዎችን ይጨምራል።
  • ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚያስተላልፉት መረጃ (ለምሳሌ በኬብል፣ በሬድዮ፣ በኦፕቲካል ፋይበር፣ በቴሌቪዥን ማሰራጫ፣ በቪሳት፣ በኢንተርኔት ሳተላይት) አማካኝነት የሚያገኙት ገቢ፣ መረጃው ከየትም ይምጣ የኢትዮጵያ ምንጭ ገቢ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚደነግግ አዲስ አንቀጽ (6(6)) ተካቷል።

2. የቃላት ፍቺዎች፣ ምድቦችና የማብራሪያ ማሻሻያዎች

  • የቃላት ፍቺዎች:ድርጅትለግብር አላማ ምን እንደሆነ ትርጉሙ ተብራርቷል፤ ይህም ኩባንያ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ወይም ሌላ በኢትዮጵያ ወይም በውጭ ሀገር የተመሠረተ የሰዎች ድርጅት እና በሌሎች ሕጎች የሂሳብ ሰነድ እንዲይዝ የሚገደድ ድርጅትን ይጨምራል።የቴክኒክ አገልግሎትምን እንደሆነም በስፋት ተዘርዝሯል፤ ይህም የሂሳብ አያያዝ፣ ኦዲት፣ ኢኮኖሚ፣ ፋይናንስ፣ ሕግ፣ አስተዳደር፣ ኢንጂነሪንግ፣ አርኪቴክቸር፣ ቅየሳ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሙያ አገልግሎቶችን ያካትታል።በጠቅላላ ገቢ ላይ የሚከፈል ግብርማለት በአንቀጽ 49 የተመለከቱት አነስተኛ ግብር ከፋዮች ከንግድ ስራቸው ባገኙት አመታዊ ጠቅላላ ገቢ ላይ ተሰልቶ ግብር የሚከፈልበት ቀለል ያለ የግብር ስርአት እንደሆነ ተብራርቷል።
  • የግብር ከፋይ ምድቦች (አንቀጽ 3): እንደሚከተለው ተሻሽለው ተለይተዋል፤

o   ደረጃ ግብር ከፋይ: ማንኛውም ድርጅትወይም ጠቅላላ አመታዊ ገቢው ብር 2 ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ማንኛውም ሌላ ሰው።

o   ደረጃ ግብር ከፋይ: ድርጅትን ሳይጨምር አመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከብር 2 ሚሊዮን የሚያንስ ሰው ነው።

  • ቋሚ ተቋም (Permanent Establishment - አንቀጽ 4): የቴክኒክ አገልግሎትና የምክር አገልግሎት ወይም የግንባታ ስራ በአንድ የግብር አመት ወይም በማናቸውም አንድ አመት ጊዜ ውስጥ 91 ቀናት በላይ ከተከናወነ ቋሚ ተቋም እንደሚፈጥር ተደንግጓል።
  • ከግብር ነፃ የሆኑ ገቢዎች (የተሻሻለው አንቀጽ 68): በዝርዝሩ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ አዳዲስ ነፃ ገቢዎች ተካተዋል፤ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ ፈንድ የሚሰበስበው አረቦንበስራ ላይ ያሉ ኩባንያዎች አዲስ ከሚያወጡት አክሲዮን የሚገኝ የካፒታል ዋጋ እድገት ጥቅም (ፕሪሚየም)፣ እና አንድ ኩባንያ በኩባንያው ውስጥ 12.5% ያላነሰ ድምጽ የመስጠትና የመቆጣጠር መብት ላለው በኢትዮጵያ ነዋሪ ለሆነ ሌላ ኩባንያ የሚፈጽመው የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ክፍያ ይገኙበታል።

3. የገቢ ማጠቃለልና የሂሳብ አያያዝ (በአንቀጽ 8 የተሻሻለው)

  • በሠንጠረዥ መሠረት ግብር የሚከፈልባቸውና ከአንድ በላይ የሥራ መስክ ገቢ ያላቸው ግብር ከፋዮች ለእያንዳንዱ የተለየ የሥራ መስክ የሂሳብ መዝገቦችን እና ደጋፊ መረጃዎችን በተናጠል መያዝ እንዳለባቸው ተደንግጓል።
  • አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ ቀጣሪወይም በአንቀጽ 49 ስራ ከሚወድቅ የንግድ ስራ ገቢ በስተቀር በሰንጠረዥ ሀ፣ ወይም መሰረት ግብር የሚከፈልበት ገቢ ያለው ከሆነየግብር ባለሥልጣኑ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘውን ታክስ የሚከፈልበት ገቢ በአንድነት በማጠቃለል ግብሩን እንዲያሰላ ይደነግጋል።
  • በዚህ አግባብ ግብሩ ከተሰላ በኋላ ግብር ከፋዩ በዚሁ ገቢ ላይ ለሌላ በሕግ ስልጣን ለተሰጠው አካል ግብር የከፈለ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ የከፈለው ታክስ ሊከፍል ከሚገባው ታክስ ጋር እንዲካካስ ይደረጋል።
  • ተቀጣሪ ከተለያየ ምንጭ ገቢ የሚያገኝ ከሆነ በመቀጠር ካገኘው ገቢው ላይ ተቀንሶ የተከፈለው ግብር የመጨረሻ እንደማይሆንና የተጠቃለለ ገቢውን የማስታወቅ ግዴታ እንዳለበት ተመልክቷል።

4. የሕግ ተገዢነትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች

  • የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ገደቦች እና የሚያስከትሏቸው ውጤቶች:

o   ለተቀባይ (አዲስ አንቀጽ 80): ማንኛውም ግብር ከፋይ፣ ከተወሰኑ በሕግ ከተፈቀዱ የክፍያ መንገዶች (ቼክ፣ የባንክ ድራፍት፣ የባንክ ዝውውር፣ ፈቃድ የተሰጣቸው የኤሌክትሮኒክ ዘዴዎች) ውጪበአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ሰው ጋር በተደረገ ጠቅላላ ግብይት፣ ከአንድ ግብይት ጋር በተያያዘ ወይም ከአንድ ሰው ጋር ከተፈጸመ አንድ ግብይት ጋር በተያያዘ ከብር 10,000 በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ መቀበል እንደማይችል ይከለክላል። ይህ ድንጋጌ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና በገንዘብ ሚኒስቴር በሚወሰኑ ሌሎች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።

o   ለከፋይ (በተሸጋሸገው አንቀጽ 29(1)() የተጨመረው): አንድ ግብር ከፋይ ከላይ በተጠቀሱት ከተፈቀዱ የክፍያ መንገዶች ውጪ በአንድ ቀን ውስጥ ለአንድ ሰው ከብር 10,000 በላይ በጥሬ ገንዘብ የፈጸመው ክፍያ ከታክስ የሚከፈልበት ገቢ ላይ ተቀናሽ እንደማይደረግ ይደነግጋል።

o   ቅጣት (አዲስ አንቀጽ 88): የአንቀጽ 80 ድንጋጌ በመተላለፍ ከተፈቀደው መጠን በላይ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ የተቀበለ ግብር ከፋይበብልጫ የተቀበለውን ገንዘብ እጥፍአስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

  • የመረጃ ልውውጥ ግዴታዎች (የተሻሻለው አንቀጽ 12):

o   የግብር ባለስልጣን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በውጭ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን ዝርዝርና አድራሻ ለግብር ዓላማ የሚያገኝበት ሥርዓት እንዲያቋቁም ይደነግጋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህንን መረጃ የመሰብሰብና የማስተላለፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

o   ለሎች ዜጎች ማንኛውንም ዓይነት የሥራ ፈቃድ የሚሰጡ ወይም የሚያድሱ ሁሉም የመንግሥት አካላት፣ ስለዚህ ጉዳይ ወዲያውኑ ለታክሱ ባለሥልጣን እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ድንጋጌ ተካቷል።

o   የዲጂታል ይዘት ክፍያ የሚያስተላልፉ መድረኮች ገቢያቸው በደንብ ከሚወሰነው ገደብ በላይ የሆኑ የይዘት ፈጣሪዎችን ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ለእያንዳንዱ ፈጣሪ በየዓመቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ይገደዳሉ (አንቀጽ 20(4))

  • የተዘዋዋሪ የሀብት ሽያጭ (Indirect Transfer Rules - አዲስ አንቀጽ 62): የአንድ ሰው ወይም ድርጅት የአክሲዮን ወይም የአባልነት መብት ዋጋ 20% በላይ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ሌላ ሀብት ጋር የተያያዘ ሆኖ ይህን አክሲዮን ወይም መብት በመሸጥ የተገኘ ትርፍ ላይ ግብር የሚጣልበት ዝርዝር ሥርዓት ቀርቧል። ይህንን ንብረት ያስተላለፈ ሰው ወይም ድርጅት ለታክሱ ባለስልጣን የገቢ ማስታወቂያ የማቅረብ ግዴታ አለበት።

5. የግብር ተመኖችና አዳዲስ የግብር አይነቶች

  • የኪራይ ገቢ ግብር (የተሻሻለው አንቀጽ 14): በድርጅቶች የኪራይ ገቢ ላይ 30% የግብር ተመን ተፈጻሚ እንደሚሆን ተደንግጓል። ለግለሰቦች ተራማጅ የግብር ሰንጠረዥ ቀርቧል (ዝርዝር ተመኖቹ በረቂቁ ላይ አልተካተቱም)
  • የንግድ ሥራ ገቢ ግብር (የተሻሻለው አንቀጽ 19): በድርጅቶች የንግድ ሥራ ገቢ ላይ 30% የግብር ተመን ተፈጻሚ እንደሚሆን ተደንግጓል። ለግለሰቦች ተራማጅ የግብር ሰንጠረዥ ቀርቧል (ዝርዝር ተመኖቹ በረቂቁ ላይ አልተካተቱም)
  • ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ ላይ የሚጣል ግብር (አዲስ አንቀጽ 20): የተወሰኑ ሁኔታዎችን ካሟላ (ትርፍ የማግኘት ዓላማ፣ ሙያዊ ወይም የተደራጀ አሰራር፣ የንግድ መዝገብ መያዝ) እንደ ንግድ ገቢ ተቆጥሮ ግብር ይጣልበታል። ካልሆነ እንደ ሌላ ገቢ ይመደባል።
  • አማራጭ አነስተኛ ግብር (AMT - አዲስ አንቀጽ 21): አንድ ድርጅት ወይም ሰው ከንግድ ስራ ባገኘው ትርፍ ላይ ሊከፍል የሚገባው ግብር በዚሁ የግብር አመት ካገኘው ጠቅላላ ገቢ 2% በታች ከሆነ፣ በጠቅላላ ገቢው ላይ 2.5% አማራጭ አነስተኛ ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል። ለባንኮች (ከባንክ ስራ በተገኘ የተጣራ ገቢ 2.5%) ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች (ከጠቅላላ አረቦን 2.5%) እና ዋጋቸው የተወሰነ እቃዎችን ለሚያቀርቡ ድርጅቶች (ከኮሚሽን ገቢ 2.5%) የተለዩ ተመኖች ተቀምጠዋል። ይህ ግብር እስከ 15 ዓመታት ድረስ ከመደበኛ የንግድ ትርፍ ግብር ጋር የሚታሰብ ይሆናል። በኪሳራ ምክንያት መፍረስ ላይ ያሉ ወይም በእዳ ማሸጋሸግ ላይ ያሉ ድርጅቶች ከዚህ ግብር ነፃ ናቸው። ይህ ድንጋጌ የግብር እፎይታ በተሰጣቸው ላይም ተፈጻሚ ይሆናል።
  • ነዋሪ ባልሆኑ ላይ የሚጣል የተቀናሽ ግብር (WHT on Non-Residents - የተሻሻለው አንቀጽ 53): ለኢንሹራንስ አረቦን ወይም ሮያልቲ፣ ለትርፍ ድርሻ (ዲቪዴንድ) እና ለወለድ ገቢ፣ ለአስተዳደር ወይም ለቴክኒክ አገልግሎት እንዲሁም በአንቀጽ 6(6) ለተዘረዘሩ የሳተላይት ቴሌቪዥንና መሰል አገልግሎቶች ከጠቅላላ ገቢ ላይ 15% ግብር እንዲከፈል ሃሳብ ቀርቧል።
  • የመዝናኛ አገልግሎት ግብር (የተሻሻለው አንቀጽ 55): በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ወይም ቡድን ከመዝናኛ አገልግሎት በሚያገኘው ጠቅላላ ገቢ ላይ የወጪ ተቀናሽ ሳይደረግ 15% ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል።
  • የቅርንጫፍ ትርፍ ግብር (Branch Profits Tax - የተሻሻለው አንቀጽ 65): ነዋሪ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ቋሚ ተቋም (ቅርንጫፍ) አማካኝነት ከሚያገኘውና ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ከሚልክ ትርፍ ላይ 15% ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል።

6. ከተለያዩ ሕጎችና አሰራሮች ጋር የተያያዙ ማስተካከያዎች

·        የተሻሩ ሕጎች (የተሻሻለው አንቀጽ 106):የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 308/1995 እና ማሻሻያዎቹእንዲሻሩ በረቂቁ ቀርቧል።

·        የግብር ማበረታቻዎች (አዲስ አንቀጽ 95): በኢንቨስትመንት ሕጉ መሰረት የሚሰጡ የገቢ ግብር ማበረታቻዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት እንዲተገበሩ የተደነገገ ሲሆንበዚህ አዋጅ ከተቀመጡት ውጭ በሌሎች አዋጆች፣ ደንቦች፣ እና መመሪያዎች የተሰጡ ማናቸውም የገቢ ግብር ነፃ የመሆን መብቶች በዚህ አዋጅ እንዲሻሩ ሃሳብ ቀርቧል።

·        የግብር ተመኖች ማስተካከያ:

o   ደረጃ ግብር ከፋዮች (የተሻሻለው አንቀጽ 49 በተሸጋሸገው አንቀጽ 51): በጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ ከብር 0 - 100,000 (2%) ከብር 100,001 - 500,000 (3%) ከብር 500,001 - 1,000,000 (5%) ከብር 1,000,001 - 1,500,000 (7%) እና ከብር 1,500,001 - 2,000,000 (9%) ተራማጅ የግብር ተመን ተቀምጧል። ይህ የሂሳብ አያያዝ፣ አርክቴክቶች፣ አማካሪዎች፣ የግንባታ ስራ ተቋራጮች፣ መሃንዲሶች፣ የፋይናንስ፣ የጤና እና የሕግ ባለሙያዎችንየተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎችን እና የሂሳብ መዝገብ በማቅረብ በሠንጠረዥመሰረት ግብር ለመክፈል የመረጡትን አይጨምርም።

o   የቅጥር ገቢ (የተሻሻለው አንቀጽ 11): አዲስ ተራማጅ የግብር ማስከፈያ ሰንጠረዥ እንዲኖር መዋቅር ቀርቧል (ዝርዝር ተመኖቹ በረቂቁ ላይ አልተካተቱም)

o   የሮያሊቲ ገቢ (የተሻሻለው አንቀጽ 55 (የቀድሞ 54)): ለነዋሪዎች ከጠቅላላ ገቢ 10% (የሮያሊቲ ገቢው ከስነጥበብ እና ባህላዊ ስራዎች ከሆነ 5%)፣ ነዋሪ ላልሆኑት (በቋሚ ተቋም በኩል) ከጠቅላላ የሮያሊቲ ክፍያ 10% የተቀናሽ ግብር እንዲጣል ሃሳብ ቀርቧል።

o   የወለድ ገቢ (የተሻሻለው አንቀጽ 58 (የቀድሞ 56)): በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ከገንዘብ ተቋማት ቁጠባ ካገኘ 5%፣ በሌላ ሁኔታ ካገኘ 10% ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል። በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰውም በተመሳሳይ ሁኔታ (በኢትዮጵያ ነዋሪ ከሆነ የገንዘብ ተቋም በቁጠባ ከሆነ 5%፣ በሌላ ሁኔታ 10% ) ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል። አንድ የፋይናንስ ተቋም ከሌላ የፋይናንስ ተቋም የሚያገኘው ወለድ በንግድ ሥራ ገቢ ግብር ሥር ይያዛል።

o   የካፒታል ትርፍ ግብር (የተሻሻለው አንቀጽ 61 (የቀድሞ 59)): መጠኑ 15% እንዲሆን ተወስኗል።የማይንቀሳቀስ ሃብትለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም ህንጻው ከመተላለፉ በፊት ለሁለት አመታት ሙሉ በሙሉ ለመኖሪያነት ያገለገለ ህንጻን እንደማይጨምር ተብራርቷል።

7. ሌሎች ድንጋጌዎች

  • ያልተከፋፈለ ትርፍ (የተሻሻለው አንቀጽ 64 (የቀድሞ 61)): ትርጉሙ ተብራርቶ፣ አንድ ኩባንያ ትርፉን መልሶ ኢንቨስት እንዳደረገ የሚታሰበው የተጣራ ትርፍን ያህል የባለአክሲዮኖቹን ድርሻ እና የኩባንያውን ካፒታል ሲጨምር ወይም የተጣራ ትርፉን ባለአክሲዮኖች ለአመለከቱት አክሲዮን ያልተከፈለውን ቀሪ ሂሳብ ለመክፈል ሲጠቀምበት እንደሆነ ተደንግጓል።
  • አንቀጾችን በድጋሚ ቁጥር መስጠት (አንቀጽ 30): በአዲሶቹ አንቀጾች መጨመር ምክንያት ከነባሩ አዋጅ አንቀጽ 19 ጀምሮ እስከ አንቀጽ 102 ድረስ ያሉት የአዋጁ ድንጋጌዎች እንደቅደም ተከተላቸው ከአንቀጽ 19 እስከ 107 በሚል እንደተስተካከሉ ተገልጿል።

አጠቃላይ ምልከታ: ረቂቅ አዋጁ በነባሩ የገቢ ግብር ሥርዓት ላይ መጠነ ሰፊ ለውጦችን ያካተተ ሲሆን፣ እነዚህም የግብር መሰረቱን፣ የግብር አይነቶችን፣ የግብር ተመኖችን፣ የአፈጻጸም ሂደቶችንና ከሕግ ተገዢነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ድንጋጌዎችን ይዟል።

Download the draft proclamation