3. አቶ አይደር ሙሰማ ሙሄ

4. ቶ አስራት ስዩም ዘለቀ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍርድ

 ከሣሽ በነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ አሻሽሎ ባቀረበው የክስ አቤቱታ ከሳሽን 14 አባላት በ2005 ዓ/ም መስርተውታል የማህበሩ አባላትም በጉልበትና በእዉቀት በመተጋገዝ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ተከሳሾች ግን ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ከማህበሩ ምስረታ በኋላ በስራ ገበታቸው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ በዚህም ተከሳሾች በማህበሩ መሳተፍም ሆነ መስራት የማይችሉ በመሆኑ ከአባልነት እንዲሰናበሩ (እንዲሰረዙ) ውሳኔ እንዲሰጥለት ጠይቆ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን በፅሁፍ የመከላከያ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀንም ሆነ ክስ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ያልቀረቡ ሲሆን በዚህም ፍ/ቤቱ የመከላከያ መልስ የማቅረብ መብታቸውን በማለፍ ክሱን በሌሉበት ሰምቷል፡፡ 

 ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት ቀንም ከሳሽ ተከሳሾች ማህበሩ ሲመሰረት በወረዳ አስተዳደሩ በኩል ቁጥር ለማሟላት የገቡ እንጂ የማህበሩ አባላት አያውቋቸውም ስራም ሰርተው አያውቁም በማለት በፅሁፍ ያቀረበውን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክሯል፡፡   

   ፍ/ቤቱም ተከሳሾች ከከከሳሽ ማህበር አባልነት እንዲሰናበቱ ሊደረግ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን ከቀረቡት ማስረጃዎች እና አግባብነት ካላቸው ህጐች ጋር በማገናዘብ መርምሯል፡፡

  ከሣሽ በክስ አቤቱታው የጠየቀው ከዳግም አስካለና ጓደኞቻቸው የብሎኬት ማምረቻ ስራ ህብረት ሽርክና ማህበር አባልነት ተከሳሾች እንዲወጡ እንዲወሰንለት ሲሆን ማህበሩ በብር 5,012 (አምስት ሺህ አስራ ሁለከት) ካፒታል በአስራ አራት አባላት እያንዳንዱ አባል ብር 358 (ሶስት መቶ ሀምሳ ስምንት) በማዋጣት በህግ አግባብ የተቋቋመ የንግድ ማህበር ስለመሆኑ፤ ተከሳሾች የማህበሩ አባል ስለመሆናቸው የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ተከሳሾች አባል የሆኑበት ማህበር የሕብረት ሽርክና ማህበር ሲሆን ማህበሩ ግዴታዎችን መግባት፤ መክሰስ እና መከሰስ እንደሚችል፤ ማህበርተኞች እርስ በርሳቸው እንዲሁም ለማህበሩ በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ፣ ከማህበር አባልነት የሚወጣ የማህበር አባልም በነበረበት ጊዜ ለነበሩትና በመሰራት ላይ ላሉት ጉዳዮች ላስገኙት ትርፎችና ኪሳራዎች ተካፋይ ስለመሆናቸው ከን/ህ/ቁ 262 ፣ 280 ፣ 286 እና 294 እና የህግ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በንግድ ህጉ ድንጋጌዎች የንግድ ማህበር አባላት በምን አግባብ ከማህበር አባልነታቸዉ ሊሰናበቱ /ሊወጡ/ እንደሚችሉ ተመልክቶ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ኃ/የተ/የግ/ማህበርና የሽርክና ማህበር ከአባላት የእርስ በርስ ግንኙነት መረዳዳት አብሮ ከማደግ ፍላጎት አኳያ የሚመሰረቱ በመሆኑ የማህበሩ አባል መወጣት ያለበትን ግዴታ ያልተወጣ ለማህበሩ የስራ እንቅስቃሴም አስቸጋሪ የሆነ እንደሆነ የማህበሩ አባል ተገዶ እንዲወጣ ሊደረግ የሚችል ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ. 261 ድንጋጌ ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡

     በተያዘው ጉዳይ ተከሳሾች የማህበሩ አባል ሲሆኑ ከሳሽ ተከሳሾች ከማህበር አባልነት እንዲወጡ ውሳኔ እንዲሰጥለት የጠየቀው ተከሳሾች በማህበሩ ዘንድ ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት የአባልነት ተሳትፎ ሲያደርጉ ያልነበረና በማህበሩ አባላት ዘንድ እንኳን በአካል የማይታወቁ መሆኑን በመግለፅ ሲሆን ተከሳሾች በበኩላቸው ይህንን በተመለከተ ያቀረቡት መከላከያ የለም፡፡ ፍ/ቤቱም በከሳሽ በኩል የተቆጠሩትን ምስክሮች አስቀርቦ እንደሰማው ማህበሩ በአስር አባላት ብቻ ስራውን እየሰራ ያለ መሆኑን ተከሳሾች ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ስራ ሰርተውም ሆነ መጥተው የማያውቁ መሆኑን ከተሰጠው የምስክርነት ቃል ለመገንዘብ የቻለ ሲሆን ይህም ተከሳሾች እንደ ማህበር አባልነታቸው በመረዳዳት አብሮ ከማደግ ፍላጎት አኳያ የተመሰረተውን ከሳሽ ማህበር አላማውን ያሳካ ዘንድ እንደ ማህበር አባልነታቸው እየተሳተፉ አለመሆኑን በዚህም መነሻነትም ከሳሽ ማህበር የስራ እንቅስቃሴው ላይ እክል የፈጠረበት መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ቀሪ የማህበሩ አባላት የማህበር አባልነት ግዴታቸውን እየተወጡ ከሆነና ተከሳሾች ይህንን የማህበር አባል ሀላፊነታቸውን የማይወጡ እስከሆነ ድረስ በማህበር አባልነት ለመቀጠል የሚያስችል ህጋዊ ምክንያት የሌላቸው በመሆኑ  ተከሳሾች ከዳግም አስካለና ጓደኞቻቸው የብሎኬት ማምረቻ ስራ ህብረት ሽርክና ማህበር አባልነት  ሊሰናበቱ ይገባል ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ይህ ውሳኔ 3ኛወገኖችም ሆኑ ተከሰሾች ተከሳሾች የማህበሩ አባል እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ የሚጠይቁት እዳ ወይም መብት ካለ መብታቸውን ከመጠየቅ የሚያስቀር አይሆንም፡፡

ውሳኔ

  1. ተከሳሾች ከዳግም አስካለና ጓደኞቻቸው የብሎኬት ማምረቻ ስራ ህብረት ሽርክና ማህበር አባልነታቸው እንዲሰናበቱ ተወስኗል፡፡
  2. ወጪና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

ትዕዛዝ

  1. ይግባኝ መብት ነው፡፡
  2. የውሳኔው ግልባጭ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ፡፡
  3. መዝገቡ ተዘግቷል ፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡