2ኛ. አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ

        3ኛ. አቶ ሞላ ሻረው

       4ኛ. አቶ ኤጉ በዳሶ

       5ኛ. ወ/ሮ አሰገደች ከበደ

ተከሣሾች ፡- አዲስ የተመረጡ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን

ሰራተኞች ቢዝነስ አክሲዮን ማህበር የቦርድ አባላት፡-

        1ኛ. አቶ ጌታቸው ገ/የስ

        2ኛ. አቶ ናደው ወልደየስ

        3ኛ. አቶ የማነብርሀን መኮንን

       4ኛ. አቶ ማስረሻ ገሰሰ

       5ኛ. አቶ ሞገስ ኩፋሼ

       6ኛ. አቶ አወቀ እርቄ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ብይን ተሠጥቷል፡፡

ብይን

      ከሳሾች በሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ የቀድሞ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሰራተኞች ቢዝነስ አክሲዮን ማህበር በማቋቋም ከሳሾች የቦርድ አባላት ሆነው ተመርጠው ስራ ሲሰሩ እንደቆዩ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ 1ኛ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ/ም ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ምልአተ ጉባኤ ባለመሟላቱ በድጋሚ በጥር 19 ቀን 2011 ዓ/ም ጥሪ ተደርጎ በእለቱ በተገኙ 66 አባላት ስብስባው እንዲቀጥልና አዲስ የቦርድ አባላት እንዲመረጡ እንደተደረገ ሆኖም በተገኙት አባላት ምርጫ ሲደረግ በተገኙት አባላት ስም ዝርዝር ላይ ያላቸው የአክሲዮን ብዛት እንዳልተገለፀ በስብሰባው ላይ የተገኙት 66 አባላት ውስጥ 13 የሚሆኑት የስብሰባው ተካፋዮች የአክሲዮን ማህበሩ አባል ሳይሆኑ ወይም ህጋዊ ውክልና ያላቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ሳይቀርብ በተሰብሳቢነት ተመዝግበው ከመ/ደንቡና ከህግ ውጪ በመውጣት የድምፅ አሰጣጡ በሚስጥር መሆን ሲገባው እጅ ብቻ በማውጣት ያላቸውን አክሲዮን ከግምት ሳይገባ ምርጫ ተደርጎ ካለቀና ጉባኤው ከተበተነ በኋላ ፅ/ቤት ተመልሰው ከመዝገብ ሲያመሳክሩ 13 ሰዎች አባል ሳይሆኑ በምርጫ እንደተሳተፉ እንደተረጋገጠ ይህንን ስህተት እንደገና ስብሰባ በመጥራት ሊታረም ሲገባ ለስብሰባ ከተመዘገበው ዝርዝር ላይ ስማቸውን በመሰረዝ ድምፅ ያልሰጡ ፣ ስብሰባውን ጥለው የሄዱ ታሳቢ ሳይደረግ ቁጥሩን ለተመራጮች በመደልደል ምርጫው በትክክል እንደተካሄደ ተደርጎ ቃለ ጉባኤው በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤትና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደተመዘገበ ይህም ተገቢ አለመሆኑን በዚህም የአክሲዮን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በመ/ደንብና በንግድ ህጉ መሰረት ያልተደረገ በመሆኑ እንዲሻር ውሳኔ እንዲሰተርላቸው ጠይቀው የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

 

        1ኛ ፣ 3ኛ ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ጉዳዩን ለማየት የግዛት ስልጣን ያለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መሆኑን ቃለ ጉባኤው የፀደቀው በጥር 19 ቀን 2011 ዓ/ም በመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ መሆኑን ከሳሾች ክስ ያቀረቡት ራሳቸው የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባል በነበሩበት ወቅት በጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ራሳቸው እየመሩና እየተቆጣጠሩ አወያይተው ያፀደቁት ውሳኔ በመሆኑ ክስ ለማቅረብ የሚችለው ከከሳሾች ውጪ ያሉ ባለአክሲዮኖች እንጂ ከሳሶች ሊሆኑ የማይገባ በመሆኑ ክስ ለማቅረብ የክስ ምክንያት እንዲሁም መብትና ጥቅም እንደሌላቸው የተከራከሩ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ በሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያም በተመሳሳይ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ ከሳሾች በ2ኛተከሳሽ ላይ ያቀረቡትን ክስ ያነሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

      ከሳሾች በበኩላቸው ለተነሱት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች በሰጡት መልስ በቀረባቸው ችሎት ክስ ያቀረቡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን እንዳለው ክስ የቀረበበት ቃለ ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ከሳሾች በስብሰባው ላይ እንደነበሩ ቃለ ጉባኤው የፀደቀው በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ/ም በመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ እንደማይሆን ህግና ደንብ ሳይከበር ስብሰባው የተደረገ በመሆኑ ክስ ለማቀረብ መብትና ጥቅም ያላቸው መሆኑን ገልፀው ተከራክረዋል፡፡

           የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው ወይ? ከሳሾች ክስ ለማቅረብ መብት ወይም ጥቅም እንዲሁም የክስ ምክንያት ያላቸዉ መሆኑን በማረጋገጥ ክስ አቅርበዋል ወይ? የቀረበው ክስስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል ወይ? የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን መርምሯል፡፡

   በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 37/1 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ዉሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን ፍ/ቤቶችም የቀረበላቸውን ክስ ለማየት ስልጣን ያላቸው መሆኑን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያለባቸው መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 9/1/፣ 231/1/ለ ፣ 244/2/ሀ ፣ 245/2/ ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ከሳሾች ክስ ያቀረቡት የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ በመ/ደንብና በንግድ ህጉ መሰረት ያልተደረገ በመሆኑ እንዲሻር ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ሲሆን በዚህ አግባብ የቀረበን ክስ ለማየት ስልጣን ያለው የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት መሆኑን በፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14 ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ተከሳሾች ክሱ መቅረብ ያለበት በፌ/መ/ደ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው በማለት ነው መከራከሪያቸውን ያቀረቡት፡፡ ሆኖም የፌ/መ/ደ ፍ/ቤቶች በየክፍለ ከተማው የተቋቋሙት ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ሲሆን በአንድ ከተማ ላይ ያሉ ፍ/ቤቶችም የግዛት ስልጣንን በተመለከተ ክርክር ሊቀርብባቸው የሚችልበት የህግ አግባብ የለም፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም በማለት ያቀረቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ 

    በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33/2 እና 3 እንዲሁም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 244/2/መ ላይ እንደተመለከተዉ ከሳሽ ክስ ባቀረበበት ነገር (ሀብት) ላይ መብት ወይም ጥቅም ያለዉ መሆኑን ፤ ከተከሳሽ የሚጠይቀዉ መብት ወይም ጥቅም ያለ መሆኑንና የክስ ምክንያት ያለው መሆኑን  በማረጋገጥ ክስ ማቅረብ ያለበት መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ከላይ እንደተመለከትነው ከሳሾች ክስ ያቀረቡት የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ በመ/ደንብና በንግድ ህጉ መሰረት ያልተደረገ በመሆኑ እንዲሻር ሲሆን በዚህ አግባብ ክስ ለማቅረብ ደግሞ በን/ህ/ቁ 416/2 ላይ እንደተመለከተውም ህግን ፣ መተዳደሪያ ደንብንና የመመስረቻ ፅሁፍን ባለመከተል የተሰጠን ውሳኔ ማንኛውም ባለጥቅም ሊቃወማቸው እንደሚችል የተመለከተ በመሆኑ ከሳሾች ከህግ ውጪ ነው በማለት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ክስ ለማቅረብ የሚችሉ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ከሳሾች የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባል በነበሩበት ወቅት በጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ራሳቸው እየመሩና እየተቆጣጠሩ አወያይተው ያፀደቁት ውሳኔ ነው በሚል ብቻ ክስ ለማቅረብ መብትና ጥቅም የላቸውም የሚባልበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ያቀረቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

        በን/ህ/ቁ 416/2 ላይ እንደተመለከተው ህግን ፣ መተዳደሪያ ደንብንና የመመስረቻ ፅሁፍን ባለመከተል የተሰጠን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በሶስት ወር ውስጥ ወይም በንግድ መዝገብ ተመዝግቦ እንደሆነም ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ በሶስት ወር ውስጥ ክስ ካልቀረበበት በይርጋ ቀሪ የሚሆን መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን በያዝነው ጉዳይ ከሳሾች እንዲሰረዝላቸው ክስ ያቀረቡበት የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የተሰጠው በጥር 19 ቀን 2011 ዓ/ም ሲሆን ቃለ ጉባኤው በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት ዘንድ ቀርቦ የተመዘገበው ደግሞ በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ/ም መሆኑን የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ከህጉ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ እንዲሻር ክስ ለማቅረብ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ወይም በንግድ መዝገብ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት በማመልከት የይርጋ ጊዜውን ያስቀመጠ ሲሆን በህጉ ላይ እነዚህ ሁለት አማራጮች በምን አግባብ ተፈፃሚ እንደሚሆኑ በግልፅ ያልተመለከተ ሲሆን ከህጉ አላማ አኳያ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የመጀመሪያው ማለትም ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ማቅረብ ያለበት ውሳኔው በተሰጠ ጊዜ ለነበረ ባለአክሲዮን ወይም በጉባኤው ለነበረ ማንኛውም ወገን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው የይርጋ ጊዜ መነሻ ማለትም በንግድ መዝገብ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ማቅረብ ያለበት ቃለ ጉባኤው ሲደረግ ላልነበረ ፣ ቃለ ጉባኤው ባለመመዝገቡ የተነሳ ቃለጉባኤው የተደረገ መሆኑን ላላወቀ ነገር ግን ከተመዘገበ በኋላ ጥቅሙን የነካበት መሆኑን ላወቀ ማንኛውም ወገን በተለይም የ3ኛወገኖችን መብት ጥበቃ በሚመለከት የሶስት ወር ጊዜ የተቀመጠ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የያዝነውን ጉዳይ ስንመለከት ከሳሾች እንዲሰረዝ ክስ ያቀረቡበትን ቃለ ጉባኤ በተመለከተ ቃለ ጉባኤው በተደረገ ጊዜ የተሳተፉና ቃለ ጉባኤው ስለመደረጉ የሚያወቁ መሆኑን ለፍ/ቤቱ ያስረዱ ሲሆን ይህም ከሳሾች ውሳኔ ከተሰጠ ከጥር 19 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ባለው የሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔው እንዲሰረዝ ክስ ማቅረብ እያለባቸው ያላቀረቡ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም ከሳሾች ውሳኔው እንዲሰረዝ ክስ የማቅረብ መብታቸው በይርጋ ቀሪ ሆኖ ሳለ ክስ ያቀረቡ በመሆኑ ክሱ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ት እ ዛ ዝ

  1. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡
  2. ይግባኝ መብት ነዉ ተብሏል፡፡
  3. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡