የመ/ቁ 275249                

ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም

 

ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ

ሣሽ፡- አቶ አብደና በቀለ ቀነአ- ጠበቃ ደጀኔ

ተከሳሾች 1ኛ. አቶ ጠቀሳ ባይሳ ቀልቤሳ        ጠበቃ ጋሻሁን

        2ኛ. ወ/ሪት ገልገሌ ባይሳ ቀልቤሳ    

መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ተገቢውን ለመስራት ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

      በመዝገቡ ላይ ተከሳሾች ያቀረቡት የመከላከያ ማስፈቀጃ ውድቅ ተደርጎ ውሳኔ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን የፌ/ከ/ፍ/ቤት የመ/ቁ 242914 በሆነው መዝገብ ላይ ተከሳሾች ያቀረቡትን ይግባኝ ቅሬታ መርምሮ ተከሳሾች የመከላከያ መልሳቸውን እንዲያቅርቡ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ እንዲወስን በሰጠው ውሳኔ መሰረት መዝገቡ ወደ ስር ፍ/ቤቱ የቀረበ ነው፡፡ በመዝገቡ ላይ የቀረበውን ክስ ስንመለከት ከሣሽ በግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከሳሽ ከተከሳሾች ጋር በጥር 4 ቀን 2011ዓ.ም ባደረግነው የእርቅ ስምምነት ቀድሞ በነበረን የሽርክና ማኅበር ግንኙነት የድርሻዬን በተለያዩ የጊዜ ገደብ ገንዘብ ከፍለውኝ ከሽርክና ማህበሩ እንደምወጣ የተስማማን ሲሆን በዚሁ መሰረት ከማህበሩ የወጣሁና በስምምነታችን መሰረትም የመጀመሪያውን ክፍያ ብር 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) በቼክ ቁጥር ኢጂ 25014011 የተቀበልኩ ሲሆን ሁለተኛው ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቂርቆስ ቀበሌ ቅርጫፍ በቼክ ቁጥር EG 25014012 በጥር 04 ቀን 2011ዓ.ም የሚመነዘር ተከሳሾች ቼክ ቆርጠውና ፈርመው ሰጥተውኛል፡፡

      ተከሳሾች እንዲከፈል በማለት የጻፈውን ቼክ ለክፍያ ዝግጁ በሆኑበት ቀን ክፍያውን ለመቀበል ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቂርቆስ ቀበሌ ቅርንጫፍ ብመላለስም በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ እንደሌለ በ21/08/2011ዓ.ም በማረጋገጥ ማስረጃ የሰጠኝ ከመሆኑም በላይ የተከሳሾች ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆንም ከሳሽ ግን በሆደ-ሰፊነት ወደ 1ኛ ተከሳሽ በመደወል የባንኩ ሂሳብ በቂ ስንቅ እንደሌለውና ገንዘቡን እንዲከፍል ለማሳወቅ ጥረት ቢያደርግም እንቢተኛ የሆነ ሲሆን ከእኔም አልፎ የቅርንጫፍ ባንኩ ማናጀር ጭምር ደውሎለት ቼኩ ከተመታ በኋላ ገንዘብ ገቢ ያደረገ ቢሆንም ክፍያ እንዲፈጽም ቢጠይቀውም ፍቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲሁም ወጪና ኪሳራን ጨምሮ እንዲከፍሉ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

    ተከሳሾች በህዳር 24 ቀን 2012 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ክስ የቀረበበት ቼክ በተከሳሾች የተፃፈ ቢሆንም ጥር 24 ቀን 2011 ዓ/ም እንዲመነዘር የተሠጠ አይደለም፡፡ ቼኩ የተሰጠው ለዋስትና ሲሆን የጉዳዩ መነሻም ተከሳሾች ከከሳሽ ጋር የመሰረትነው አብደና እና ገልገሌ የኤሌክትሪክ ሜካኒካል ሶሉሽን ሽርክና ማህበር ነበር፡፡ ከሳሽ ማህበሩ እንዲፈርስ የመ/ቁ 265253 በሆነው መዝገብ ላይ ክስ አቅርበው የነበረ ሲሆን ጉዳዩ ክርክር ላይ እንዳለ ጉዳዩ በእርቅ አልቋል፡፡ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ/ም ከከሳሽ ጋር በተደረገው ስምምነትም ተከሳሾች በአጠቃላይ ብር 1,300,000 (አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ) ለከሳሽ ከፍለን ከሳሽ ከማህበሩ እንዲሰናበቱ የተስማማን ሲሆን በውሉ መሰረትም ክፍያው የሚፈመው በሶስት ዙር ሲሆን የክፍያው ጊዜ አልተገለፀም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ተከፋዩ ገንዘብ ቀጥታ ከማህበሩ ወይም ተከሳሾች የሚከፈል ሳይሆን ኦሮሚያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ከተባለው መንግስት ተቋም በተለያዩ ጊዜያት የሚለቀቅ በመሆኑ ነው፡፡ በውሉ መሰረትም የከሳሽን መብት ለማስጠበቅ ክስ የቀረበበትን ቼክ ጨምሮ ሶስት ቼኮች በሽማግሌ እጅ የነበሩ ሲሆን ይህ ሶስተኛ የሆነው ወገን ገንዘብ ሳይለቅ የቼኮቹ የመክፈያ ጊዜ ሊያበቃ ቢሆን በግራ ቀኙ ቃለ ጉባኤ ተይዞ  ተለዋጭ ቼክ እንደሚሰጥም ተስማምተናል፡፡

       ከሳሽ ይህንን ስምምነት በመጣስ ከአስታራቂ ሽማግሌዎች ጋር በመመሳጠር ቼኮቹን በመውሰድ ክስ ያቀረቡ ሲሆን ክፍያውን የይለቃል የተባለው ተቋምም የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ክፍያውን ሲያዘገይ ከቆየ በኋላ የተወሰነ ገንዘብ የለቀቀ ሲሆን ይህ ገንዘብም ለሰራተኞች ደሞዝ ፣ ለመኪና ኪራይና ለመንግስት ግብር ወጪ ተሰርቶ የሚቀረው ገንዘብ በቼኩ ላይ እንደተገለፀው ለመክፈል ባለመቻሉ የተወሰነ ገንዘብ ወስደው ቀሪውን በትእግስት እንዲጠባበቁ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆን ክስ አቅርበዋል፡፡

     ከሳሽ እንደውሉ ያልተፈፀመላቸው ከሆነ ውሉን መሰረት በማድረግ በአፈፃፀም መጠየቅ ከሚችሉ በስተቀር ለዋስትና የተሰጠውን ቼክ መነሻ በማድረግ ክስ ማቅረብ አይችሉም፡፡ እንደ ውሉ ያልተከፈለ ገንዘብ አለ ካሉም ለወደፊት ከሚለቀቅ ክፍያ ከሚወስዱ በስተቀር በቼኩ ላይ የተመለከተውን ገንዘብ በውሉ መሰረት እንድንከፍል አንገደድም፡፡ በዚህም ከሳሽ   ወጪና ኪሳራ እንዲከፍሉ ተወስኖ ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡      

    ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት ቀንም ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ቼኩ ከሽማግሌ እጅ ለከሳሽ የተሰጠው በውሉ መሰረት ሁለተኛ ክፍያ ከብር 1.9 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ የተለቀቀ በመሆኑ ሲሆን በውሉ ላይ ክፍያ ሲከፈል የሚከፈል በመሆኑ ያለ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ነው፡፡ ለሰራተኛ ለመብራት የሚል ስምምነት በውሉ ላይ የሌለ ሲሆን ክፍያ የተለቀቀ መሆኑንም ተከሳሾች አምነዋል በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሾች ባቀረቡት ክርክር ሁለተኛ ክፍያ ብር 1.9 ሚሊየን ተከፍሎናል ነገር ግን በውሉ ላይ ስንት ገንዘብ ሲለቀቅ ክፍያ እንደሚፈፀም አልተገለፀም በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

     በግራ ቀኙ በኩል የተነሱት የመከራከሪያ ነጥቦች ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡

   ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ  አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት 

 በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡

    ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሾች ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡

    በያዝነው ጉዳይ ከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሾች ለከሳሽ የሰጡት ከተከሳሾች ጋር በጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረጉት የእርቅ ስምምነት ውል መሰረት ቀድሞ በነበራቸው የሽርክና ማኅበር ግንኙነት የድርሻቸውን በተለያዩ የጊዜ ገደብ ገንዘብ ተከፍሏቸው ከሽርክና ማህበሩ እንዲወጡ የተስማሙ በመሆኑ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ይህንን በከሳሽ የቀረበውን መከራከሪያ በማጠናከር ነው ተከሳሾችም የተከራከሩት፡፡ ሆኖም ተከሳሾች ቼኩ ለዋስትና የተሰጠ ኦሮሚያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ከተባለው መንግስት ተቋም በተለያዩ ጊዜያት ክፍያ ሲለቀቅ እንዲከፈል በሽማግሌ እጅ እንዲቀመጥ የተደረገ ሆኖ ሳለ ይህ ቅድመ ሁኔታ ባልተሟላበት ቼኩ ለከሳሽ እንዲሰጥ የተደረገ መሆኑን የገለፁ ናቸው፡፡

   በዚህም ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነው ጉዳይ ግራ ቀኙ በጥር 4 ቀን 2011 ዓ/ም ያረጉት የእርቅ ስምምነት ውል በመሆኑ የውሉን ይዘት መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ በውሉ ላይ ከሳሽ ብር 1,300,000 (አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ) ተከፍሏቸው ከተከሳሾች ጋር ካቋቋሙት ማህበር ለመውጣት የገንዘብ አከፋፈሉን በተመለከተ በሶስት ዙር ሆኖ በመጀመሪያ ዙር ብር 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) በቼክ የተሰጣቸው ሲሆን 2ኛ ዙር ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) አሰሪው ተቋም በሁለተኛ ዙር ከኦሮሚያ ሪጅን አ/አ/ኤ/አ/ፕ ከሚከፈለው ክፍያ ውስጥ ሊከፈል እንዲሁም ቀሪው 3ኛው ዙር ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ደግሞ ተቋሙ ለሶስተኛ ዙር ከሚለቀቅለት ክፍያ የሚከፈል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

       እንግዲህ ይህንን ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ በተመለከተ ግራ ቀኙ ካደረጉት የውል ስምምነት አኳያ ክፍያ ሊፈፀምበት የሚገባ ነው ወይ ክፍያ ሊፈፀም የሚገባው ከሆነስ መቼ ነው? የሚለውን ነጥብ ፍ/ቤቱ እንደመረመረው ከላይ እንደተመለከትነው በውሉ ድንጋጌ ላይ ተከሳሾች ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ለመክፈል የሚገደዱት ማህበሩ ለሰራው ስራ የሁለተኛ ዙር ክፍያ ሲለቀቅለት መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ተከሳሾች ለፍ/ቤቱ እንዳስረዱትም ይህ የሁለተኛ ዙር ክፍያ ብር 1.9 ሚሊየን ብር የተለቀቀላቸው ሲሆን በውሉ ላይ ተከሳሾች ምን ያህል ገንዘብ ሲለቀቅላቸው ይህንን ገንዘብ ለከሳሽ እንደሚከፍሉ የተገለፀበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህም ከሳሽ የሁለተኛ ዙር ክፍያ የተለቀቀ እንደሆነ ክፍያ የሚፈፀምላቸው መሆኑን ግራ ቀኙ የተስማሙ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን ምን ያህል ገንዘብ ሲለቀቅና ተከሳሾች ይህንን የተለቀቀውን ገንዘብ ምን ምን ላይ አውለው ሲተርፍ ለከሳሽ የሚከፍሉ ስለመሆኑ በውሉ ላይ ያልተመለከተ በሆነበት ሁኔታ ተከሳሾች ሁለተኛ ዙር ገንዘብ የተለቀቀ መሆኑን በማመን እየተከራከሩ ባለበት ሁኔታ የተለቀቀው ገንዘቡ ለሰራተኞች ደሞዝ ፣ ለመኪና ኪራይና ለመንግስት ግብር ወጪ ተሰርቶ ለከሳሽ ገንዘቡን ለመክፈል ያልበቃ መሆኑን በመግለፅ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ሊከፍሉ የማይገባ መሆኑን ያቀረቡት መከራከሪያ ግራ ቀኙ ያደረጉትን የውል ስምምነት ቼኩ እንዲከፈል ከተሰጠበት ምክንያት ውጪ በመሆኑ መከራከሪያቸውን ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነው ግራ ቀኙ ያደረጉት የእርቅ ስምምነት ውል መሆኑ በግራ ቀኙ በኩል ያለውን የቼክ ግንኙነት ከሚያመለክት በስተቀር ቼኩን መሰረት በማድረግ በቀጥታ ክስ ሊቀርብ አይገባም ሊባል የሚችልበት የህግ አግባብ የሌለ ሲሆን በዚህም ተከሳሾች ከሳሽ በአፈፃፀም መጠየቅ ከሚችሉ በስተቀር ለዋስትና የተሰጠውን ቼክ መነሻ በማድረግ ክስ ማቅረብ አይችሉም በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡

   በዚህም ተከሳሾች በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ሊከፍሉ የማይገባበት ምክንያት ያለ መሆኑን ያላስረዱ በመሆኑ ገንዘቡን ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡  

 

ውሳኔ

  1. ተከሳሾች ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ) ቼኩ ለክፍያ ባንክ ከቀረበበት ከሚያዚያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
  2. ወጪና ኪሣራ በተመለከተ ከሣሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 7,850 ፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 30 ፣ የጠበቃ አበል በጥብቅና ውሉ መሰረት ብር 50,000 ፣ ልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 1,000 ተከሳሾች ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

 

ትዕዛዝ

  1. ይግባኝ መብት ነው፡፡
  2. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡