የመ/ቁ. 270967

ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ/ም

               ልደታ ምድብ 5ኛ ፍ/ብ ንግድ ችሎት

ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ

ከሣሽ፡- መክሊት የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አ.ማ)  

ተከሣሾች፡- 1ኛ. አቶ በፍቃዱ ጋረደዉ መስቀሌ

          2ኛ. አቶ መሐሪ የማነ አብረሃም

           መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የብድር ገንዘብ ለማስከፈል የቀረበ ክስን የሚመለከት ሲሆን ከሣሽ በአጭር ሥነ-ሥርዓት ታይቶ እንዲወሰን ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የክስ አቤቱታ በከሳሽ እና በተከሳሾች  መካከል ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል ስምምነት 1ኛ ተከሳሽ ብር 2,5000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ከከሳሽ ተበድረው የወሠዱ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ  በብድር ለወሠዱት ገንዘብ ዋስ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ በውሉ መሰረት የተበደሩትን ገንዘብ ባይከፍሉ በአንድነት እና በነጠላ በመሆን የማይከፋፈል ኃላፊነት በመግባት ውሉ ፈርመዋል፡፡ 1ኛተከሳሽም ከወሰዱት ገንዘብ ከወለድና ቅጣት ጋር ብር 16,243∙53 የቀሪባቸዉ በመሆኑ የተበደሩትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ፍቃደኛ ሆነዉ ሊከፍሉ አልቻሉም፡፡ በመሆኑ ከተበደሩት ገንዘብ ውስጥ ዋና ገንዘብ ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 4,183∙29  ከወለድ ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 9,703∙38 ከቅጣት ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 2,356∙86  በድምሩ ብር 16,243∙53 (አሥራ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሶስት ከ38/100) እንደሚቀርባቸው በዚህም ወጪና ኪሳራን ጨምሮ ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ የዚህ ክስ ዉሳኔ እስከ ሚሰጥበት ድረስ ያለዉን ከሚታሰብ 17% ወለድ እንዲሁም ቅጣት 7% እንዲከፍሉ እንዲወሰንለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል፡፡

      ተከሳሾች በህግ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው 1ኛ ተከሳሽ ክሱን እንዲከላከሉ በተፈቀደላቸው መሰረት መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የመከላከያ መልሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን  2ኛ ተከሳሽ መጥሪያ የደረሳቸው ቢሆንም የመከላከያ ማስፈቀጃ  ያላቀረቡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ የመከላከል መብታቸውን አልፎታል፡፡

     1ኛ ተከሳሽ በሰጡት መልስ ከከሳሽ ብር 25000(ሀያ አምስት ሺህ ብር) ሊከፍሉ ዉል የገቡ መሆናቸዉን በማመን ከተበደሩት ዋና ገንዘብ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ብር 20,816∙71 (ሀያ ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ስድስት ብር ከ71/100) እና ወለድ ብር 7,825 (ሰባት ሺህ ስምንት ሀያ አምስት ብር) የከፈሉና ቀሪ ዕዳ ብር 4,183∙29 (አረት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) ሲሆን ከዚህም 1ኛ ተከሳሽ ተቀማጭ ቀሪ የተገኘዉን ብር 1,549∙92 ከከሳሽ ካዝነ ያለ በመሆኑ ስቀነስ ከዋና እዳ ቀሪ ብር 2,633∙37 ብቻ የቀረባቸዉ መሆኑን ገልጾ ከሳሽ መጠየቅ የሚችለዉ በዉሉ አንቀጽ 1∙2∙6 እና 2∙7 መሰረት ተከሳሽ ለመክፈል በተስማማበት የጊዜ ገደብ ዉስጥ ሳይከፍል በቀረዉ የብድር ገንዘብ ብር 2,633∙37ና ከግንቦት 22 ቀን 2009 እስከ መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ/ም ያለ የ22 ወራት ወለድ ብር 869 እንዲሁም የዚህ ወለድ ወለድ ብር 286∙77 እና ቅጣት ብር 434∙50 በድምሩ ብር 4223∙64 ብቻ ከሳሽ መጠየቅ ሲገባ ብር 16,243∙53 ተከሳሾችን ለማስከፈል ያቀረቡት ክስ ዉድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ጠይቋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል፡፡

  ፍ/ቤቱ ክስ በሰማበት እለት ከሳሽ ባቀረበው ክርክር 1ኛ ተከሳሽ ብር 20,816∙71 ከፍያለሁ በማለት የገለፁ ቢሆንም ይህ ስለማሆኑ ያቀረቡት ማስረጃ የለም።  ያልተከፈለ ጠቅላላ ገንዘብ ብር 16,243∙53 ነዉ። ወለዱ ፍላት ሬት ነዉ። የሚቀረዉ ገንዘብ አንድ ብር  እንኳን ቢሆን ወለዱ የሚሰላዉ በአጠቃለይ በተበደሩት ገንዘብ ላይ ነዉ።  ወለዱ መታሰብ ያለበት በዉሉ 1∙2∙6 መሰረት ከዋናዉ ገንዘብ ላይ ነዉ። 1ኛ ተከሳሽ በተቋሙ ያለዉ ተቀማጭ ቁጠባ ገንዘብ ለማካካስ 1ኛተከሳሽ ቀርቦ ፎርማሊቲዉን ሟሟለት እያለባቸዉ አልቀረቡም። ለ3 ወር በላይ ያልከፈሉ በመሆኑ ዉሉ ተቋርጣል በማለት የገለፀ ሲሆን 1ኛተከሳሽ በበኩሉ ብር 20,816∙71 በየወሩ በዉሉ መሰረት ስከፍል ነበር። በዉሉ አንቀጽ 1∙2∙6 መሰረት ወለዱ መታሰብ ያለበት በቀሪዉ ዕዳ ላይ ነዉ። በዉሉ መሰረት ያስቀመጥኩት ቁጠባ ገንዘብ ብር 1,549∙92 ለዕዳ ማካካሸነት ሊታሰብ ይገባል። የሚቀረዉ ብር 2,633∙37 ነዉ በማለት አስረድተዋል፡፡

    ፍ/ቤቱም ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርምሯል፡፡

    ከሣሽ በተከሳሾች ላይ ክስ ያቀረቡት 1ኛ ተከሳሽ ተበድረው የወሠዱትን ገንዘብ በብድር ውሉ መሠረት ያልመለሱ ስለሆነ ተበድረው ከወሠዱት ቀሪ ገንዘብ ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት ሲሆን ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል ስምምነት 1ኛተከሳሽ ብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ከከሳሽ ተበድረው የወሠዱ መሆናቸዉን 2ኛተከሳሽ 1ኛተከሳሽ  በብድር ለወሠዱት ገንዘብ ዋስ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ በውሉ መሰረት የተበደሩትን ገንዘብ ባይከፍሉ በአንድነት እና በነጠላ በመሆን የማይከፋፈል ኃላፊነት በመግባት ውሉ የፈረሙ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ ቀርቧል፡፡

      በህግ አግባብ የተደረጉ ውሎች ማለትም በህግ ፊት የሚፀና ህጋዊ ውጤትን የሚያስከትል ውል ለመዋዋል መሟላት አለባቸው ተብለው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1678 ስር የተቀመጡትን መስፈርቶች በሙሉ ባሟላ መልኩ የተደረጉ ውሎች በተዋዋይ ወገኖች ላይ ህግ ናቸው ይህም ከላይ በገለጽነው ህግ በቁጥር 1731/1/ ስር ተመልክቷል፡፡

    ግራ ቀኙ ተዋዋይ ወገኖች ያደረጉት ውል የብድር ውል ከሆነ ተበዳሪው ወገን በብድር ውሉ መሠረት ተበድሮ የወሠደውን ገንዘብ በብድር ውሉ ላይ የብድር ገንዘቡን መክፈያ ጊዜ ተወስኖ ከተቀመጠ ይህ የመክፈያ ጊዜ ሲደርስ፣ በብድር ውሉ ላይ መክፈያ ጊዜው ካልተወሠነ አበዳሪው ወገን ያበደረው ገንዘብ እንዲመለስለት በጠየቀ በ30 ቀናት ውስጥ ተበዳሪው ወገን ለአበዳሪው የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2482፣ 2483 ስር ተመልክቷል፡፡ ተበዳሪው ወገን በዚህ ግዴታው መሠረት ተበድሮ የወሠደውን ገንዘብ ካልመለሰ አበዳሪው ወገን ውሉን እንዲሁም ህጉን መሠረት በማድረግ ተበዳሪው ወገን በብድር የወሠደውን ገንዘብ እንዲመልስለት መጠየቅ ይችላል፡፡

   ከሳሽ እና ተከሳሾች ያደረጉት ውል የብድር ውል ሲሆን በዚህ የብድር ውል 1ኛ ተከሳሽ ከከሣሽ ላይ  ብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ተበድረው ወስደው በውሉ መሰረት ባይከፈል በብድር የወሰዱት ገንዘብ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በአንድነት እና በነጠላ ለከሳሽ ለመመለስ ውል ያደረጉ  ስለመሆኑ የቀረበዉ ማስረጃ የሚያስረዳ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የተበደሩት ከዋናዉ ብድር እንዲሁም ወለዱን በየወሩ ሲከፍሉ የነበሩና ከዋና ቀሪ ዕዳ ብር 4,183∙29 (አራት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) ብቻ ሳይከፈል የቀረ መሆኑን እንዲሁም ተቀማጭ ቀሪ የተገኘዉን ቁጠባ ብር 1,549∙92 ከከሳሽ ካዝና ያለዉ መሆኑን የቀረበዉ የሰነድ ማስረጃ ያስረዳል። በግራቀኙ የተደረገው የብድር ዉል አንቀጽ 1∙2∙6 እና 1.2∙7 መሰረት ተበዳሪዉ ለመክፈል በተስማማበት የጊዜ ገደብ ዉስጥ ክፈያዉን ያላጠናቀቀ እንደሆነ ሳይከፍል በቀረዉ ዋና ገንዘብ በተጨማሪ ዕዳዉን አጠናቅቆ እስከሚከፍል ድረስ በ18% ተሰልቶ ወለድና የወለድ ወለድ ሊከፍል እንደሚገባ ተደንግጓል። ከዚህ አንጻር ተከሳሽ እንድከፍል የሚገደደዉ ሳይከፍል በቀረዉ ከዋና ገንዘብ ቀሪ ዕዳ እና በ18% ተሰልቶ የዚህኑ ወለድና የወለድ ወለድ በመሆኑ መረዳት የሚቻል ሲሆን  ከሳሽ ወለዱ የሚታሰበዉ በፍላት ሬት ከተበደረዉ ዋና ገንዘብ ላይ እንጅ ከቀሪ ዕዳ አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር ፍ/ቤቱ አልተቀበለም።

     ከዚህ በተጨማሪም የዉሉ አንቀጽ 1∙2∙7 መሰረት ተበዳሪዉ በዉሉ መሰረት ያልከፈለዉ ዉዝፍ ዕዳ ቢኖር በተቋሙ ዉስጥ ያስቀመጠዉ ማንኛዉም ቁጠባ ያለምንም ክርክር ለእዳዉ ማካካሸነት የሚዉል መሆኑ የተደነገገ ሲሆን ይህም የባለእዳ ፈቃድ ላይ ያልተመሠረተና ከሳሽ በማንኛዉም ጊዜና ያለቅድመ ሁኔታ ላልተከፈለዉ ዉዝፍ ዕዳ ማካካሸነት መዋል እንደሚችል የሚያስረዳ ሲሆን ከሳሽ ተከሳሽ ቀርቦ ፎርማሊትዉን ማሟላት ስላለበት ከቀሪዉ እዳ አልተቀነሳም በማለት ተከሳሽ በዉሉ መሰረት ከቀሪ ዕዳ ሊቀነስለት የሚገባ በተቋሙ ቁጠባ እያለ ሳይቀነስለት ከዋና ቀሪ ዕዳዉን ከነወለዱ ተሰልቶ ለማስከፈል ያቀረቡት ክርክር ፍ/ቤቱ ተገቢ ሆኖ አላገኘውም። ስለሆነም ክስ የቀረበበት ገንዘብ ከዋና ቀሪ ዕዳ ከብር 4,183∙29 (አራት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) 1ኛተከሳሽ ከከሳሽ ላይ ያሉት የቁጠባ ገንዘብ ብር 1,549∙92( አንድ ሸህ አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር ከ92/100) ቅናሽ ተደርጎ 1ኛተከሳሽ ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ በቀሪነት የሚፈለግባቸው ብር 2,633∙37 (ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ሶስት ብር ከ 37/100) እና የ22 ወራት ወለድ ብር 869 (ስምንት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ብር) እንዲሁም የወለድ ወለድ ብር 286∙77 (ሁለት መቶ ሰማንያ ስድስት ብር ከ 77/100) በድምሩ ብር 3,789∙19 (ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር ከ19/100) የሚሆን ሲሆን ተከሳሾችም ይህንን የገንዘብ መጠን በአንድነት እና በነጠላ ኃላፊነት ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል፡፡   

   በሌላ በኩል ከሳሽ ለ1ኛ ተከሳሽ በብድር ውሉ መነሻነት ባበደሩት ገንዘብ ላይ ስምምነት ያደረጉበት 18% ወለድ አስልተው ዳኝነት ጠይቀው እያለ ገንዘቡ በውሉ መሰረት በወቅቱ ባለመከፈሉ ቅጣት ብር 2,356∙86 (ሁለት ሺህ ሶስት መቶ አምሣ ስድስት ብር ከ586/100) እንዲከፍሉ እንዲሁም ክስ በቀረበበት ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቅጣት 7% እየተሰላ ጭምር ከሳሽ እንዲከፈለው ዳኝነት ጠይቋል፡፡ ተበዳሪው የተበደረውን ነገር ከመመለስ ወይም የሚገባውን ወለድ ከመክፈል የዘገየ እንደሆነ ጊዜ በማስተላለፍ የሚከፈለውን ወለድ እንዲከፍል እንደሚገደድ እና ይህን ግዴታ የሚያከብድ ማንኛውም የውል ቃል ፈራሽ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2489(2) ስር ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም ከሳሽ እና ተከሳሾች ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም ባደረጉት የብድር ውል ተከሳሾች የብድር ገንዘቡ ለመመለስ ስምምነት በተደረገበት ጊዜ ባለመመለሳቸው ወለድ ተሰልቶ ዳኝነት ተጠይቆ እያለ ከላይ የተጠቀሰዉ ቅጣት ተከሳሾች ለከሳሽ እንዲከፍሉ የተደረገው ተከሳሾቹ ሙሉ በሙሉ ባይቃወሙ እንኳን የውሉ ክፍል የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2489(2) ይዘትን ያልተከተለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. ተከሳሾች ክስ ከቀረበበት ገንዘብ ውስጥ ብር 3,789∙19 (ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር ከ19/100) ክስ ከተመሰረተበት ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከ ሚጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር በአንድነት እና በነጠላ ለከሳሽ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
  2. ከሳሽ የብድር ገንዘቡ እና ወለዱ በመዘግየቱ ቅጣት እንዲከፈል ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
  3. በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት የወጣ ወጪና የደረሰ ኪሣራ በተመለከተ ለዳኝነት ፍርድ በተሰጠበት የገንዘብ ልክ ብር 162 ፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 20 እንዲሁም ለልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 500 ተከሳሾች በአንድነትና በነጠላ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

ትዕዛዝ

  1.   ይግባኝ መብት ነዉ፡፡

    2∙ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

                                       የማነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡