- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
የኮ/መ/ቁ 270687 - አቶ አበራ አግዛ እና አቶ አንድአምላክ ሳህሌ
የመ/ቁ 270687
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ከሣሽ፡- አቶ አበራ አግዛ
ተከሣሽ፡- አቶ አንድአምላክ ሳህሌ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ከሣሽ በታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ተከሣሽ የቼክ ቁጥሩ ኤኤ2899517 የሆነ ብር 50,000.00 (ሀምሳ ሺህ) ያዘዘ ቼክ እንዲሁም የቼክ ቁጥሩ ቢኤፍ3779809 የሆነ ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ያዘዘ ቼክ ባለን የንግድ ግንኙነት ወይም እቁብ አብረን እንሰራ የነበረ በመሆኑ ፈርመው የሠጡኝ ቢሆንም ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ ሳቀርብ ባንኩ በቂ ገንዘብ እንዲሁም ሂሳቡ ተዘግቷል በማለት ቼኮቹ ሣይከፈልባቸው የተመለሱ በመሆኑ ተከሣሽ በቼኮቹ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ተከሣሽ የመ/ማስፈቀጃ አቅርበው ፍ/ቤቱ የመ/መልሳቸውን እንዲያቀርቡ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት በሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ/ም በሰጡት መልስ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መሰረት ከሳሽ ክስ ያቀረቡበት የቼክ ቁጥር ኤኤ2899517 የሆነውን ቼክ በተመለከተ ክስ ለማቅረብ መብታቸው በይርጋ ቀሪ መሆኑን ፍ/ቤቱ ብይን ሰጥቶበታል፡፡
ተከሳሽ በፍሬ ጉዳዩ ላይ የሰጡትን መልስ ስንመለከት ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጠሁት በየካቲት ወር 2007 ዓ/ም በተጀመረው ባለን የእቁብ ግንኙነት ነው ፤ ተከሳሽ ያለብኝን የእቁብ ገንዘብም በከሳሽ ስም በተከፈተ ሂሳብ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም በተከፈተ ሂሳብ ገቢ በማድረግ ጨርሼ ከፍያለሁ ያላግባብ ለመበልፀግ ያቀረቡት ክስ በመሆኑም ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ወጪና ኪሳራ የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት ቀንም ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ለክሱ መነሻ የሆነው ቼክ ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በ2010 ዓ/ም በመጨረሻ ላይ ለወጣው እቁብ ክፍያ ይሆን ዘንድ ለመተማመኛ ነው ፤ ያቀረቡበት የሰነድ ማስረጃ በ2008/9 ዓ/ም ለወጣ እቁብ የተከፈለበት ነው ያሉ ሲሆን የመዝጊያ ክርክር ባቀረቡበት ጊዜ ደግሞ ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጡት ተከሳሽ ሊጥሉት ይገባ የነበረውን የእቁብ ገንዘብ ከሳሽ እከፍልላቸው የነበረ በመሆኑ ለዚህ ክፍያ ይሆን ዘንድ ነው ካሉ በኋላ ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በእቁብ ምክንያት ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 200ሺህ ለተከሳሽ ያበደርኳቸው በመሆኑ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ተከሳሽ በበኩላቸው ከከሳሽ ጋር የእቁብ ግንኙነት የለኝም ቼኩ ከሳሽ እጅ ሊገባ የቻለው ከሳሽ በ2009 ዓ/ም እቁብ ይሰበስቡ የነበረ በመሆኑ ለዋስትና ቀን ሳይፃፍበት የተሰጠ ሲሆን በወቅቱም እቁቡ አልቆ ተለያይተናል፤ ከሳሽም በወቅቱ ቼኩን ሊመልሱ አልቻሉም በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡
ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሽ ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ ሂሳቡ የተዘጋ መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡
በያዝነው ጉዳይ ተከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ቼኩን ለከሳሽ የሰጠሁት በየካቲት ወር 2007 ዓ/ም በተጀመረው ባለን የእቁብ ግንኙነት ነው ፤ ተከሳሽ ያለብኝን የእቁብ ገንዘብም በከሳሽ ስም በተከፈተ ሂሳብ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም በተከፈተ ሂሳብ ገቢ በማድረግ ጨርሼ ከፍያለሁ ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን ያቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃዎችም በተለያየ ቀን በከሳሽ ስም በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም ወ/ሮ ሰልፍነሽ ግዛው ስም በወጋገን ባንክ በተከፈተ ሂሳብ ገንዘብ ገቢ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከሳሽ በፅሁፍ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ላይ ለክሱ መነሻ የሆነው ቼክ በእቁብ አማካኝነት በተከሳሽ የተሰጣቸው መሆኑን የገለፁ ሲሆን ክስ በተሰማበት ቀን ደግሞ በአንድ በኩል ቼኩ በእቁብ አማካኝነት ለክፍያ ይሆን ዘንድ የተሰጠኝ ነው ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጡት ተከሳሽ ሊጥሉት ይገባ የነበረውን የእቁብ ገንዘብ ከሳሽ እከፍልላቸው የነበረ በመሆኑ ለዚህ ክፍያ ይሆን ዘንድ የተሰጠ ነው ያሉ ሲሆን እንዲሁም በድጋሚ ለፍ/ቤቱ ሲያስረዱም ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በእቁብ ምክንያት ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 200ሺህ ለተከሳሽ ያበደርኳቸው በመሆኑ ነው በማለት እርስ በርሱ የሚጣረስ ክርክር አቅርበዋል፡፡ ይህም በከሳሽ የቀረበው መከራከሪያ ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ያገኙት ከተከሳሽ ጋር በነበራቸው የንግድ ግንኙነት አማካኝነት ክፍያ ይፈፀምበት ዘንድ የተሰጠ መሆኑንም ሆነ ከከሳሽ ጋር የብድር ውል ግንኙነት የነበራቸው ስለመሆኑም የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ያስረዱበት አግባብ የለም፡፡ በዚህም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ በተመለከተ ከተከሳሽ ጋር ባላቸው ግንኙነት የተሰጣቸው መሆኑን ያስረዱበት አግባብ በሌለበት ሁኔታ በቼኩ የተመለከተው ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ሊጠይቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ በመስጠት ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ውሳኔ
- ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም፡፡
- ተከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡