- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
የኮ/መ/ቁ 181609 - ጎስፕላ ትሬዲንግ ኃ. የተ.የግል.ማህብር እና አቶ ፍቃዱ ተስፋሁን
መ/ቁ 181609
ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- ጎስፕላ ትሬዲንግ ኃ. የተ.የግል.ማህብር ስራ አስኪያጅ ፡- ሽመልስ አበበ፡- ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አቶ ፍቃዱ ተስፋሁን፡- ጠበቃ በላይነዉ አሻግሬ፡- ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርማራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ/ም በተፋጠነ ስነ ሰርዓት ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ ዕቁብ በሚሰበሰቡበት አቤነዘር ብራንድ የህጻናት አልባሳት ስም በተዘጋጀ የዕቁብ ደብተር ከሳሽ በመ/ቁ 01 መደቡ የብር 440/አራት መቶ አርባ/ ለሆነዉ 22 ጊዜ፤ በመ/ቁ 02 መደቡ የብር 2,200(ሁለት ሺህ ሁለት መቶ) ለሆነዉ 32 ጊዜ፤ መ/ቁ 03 መደቡ የብር 2,200 (ሁለት ሺህ ሁለት መቶ) ለሆነዉ 32 ጊዜ፤መደቡ የብር 1,100(አንድ አንድ መቶ) ለሆነዉ 22 ጊዜ እንዲሁም እንጎቻ ባህላዊ ምግብ ቤት ዉስጥ ተከሳሽ ለሚሰበስበዉ ባለ 440 (አራት መቶ አርባ)15 ጊዜ በአጠቃላይ ብር 181,000.00 (አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ከላይ ለተጠቀሱት የዕቁብ መደቦች የጣሉ መሆኑን ከሳሽ በዕቁቦቹ ተሳታፊ የሆኑት ተከሳሽ የዕቁቡን 2ኛ ዕጣ ያለውድድር የሚሰጧቸዉ መሆኑን ቃል ስለገቡላቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ቃል በገባላቸዉ መሰረት የ2ኛዉን ዙር ዕቁብ ሊሰጣቸዉ ያልቻለ በመሆኑ ዕቁቡን ያቋረጡ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ብር 181,000.00 (አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) እንዲከፈላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥሯል፡፡ ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አአባሪዎቹ ለተከሳሽ ደርሶ ተከሳሽ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ ያቀረቡትን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኃላ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡትም የመከላከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቧል በፍሬ ነገሩ ላይ መልስ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ከሳሽ የህዳር ወር የ30 ቀናት የእቁብ ክፍያ ሳይፈጽሙ የበሰለ ክፍያ በተከሳሽ ላይ ያላቸዉ በማስመሰል በተፈጠነ ስነ ሰርዓት ክስ ማቅረባቸዉ አግባብብነት የለዉም የቀረበዉ ክስም ውልን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ክሱ መቅረብ ያለበት ዉሉ በተደረገበት ወይም በሚፈጽመበት ስለሆነ የተከሳሽ የንግድ ቦታ ቦሌ ክፍለ ከተማ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል የግዛት ክልል ስልጣን የለዉም እንዲሁም ከሳሽ በእቁቡ ደንብ መሰረት የእቁብ ተመላሽ ገንዘብ ሊጠይቁ የሚገባዉ እቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወር በኃላ በመሆኑ የቀረበዉ ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸዉን ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስም ደግሞ ከሳሽ ለመጀመሪያዉ ዕጣ መክፈል የነበረበት ብር 191,400(አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ ከሳሽ የከፈለዉ ብር 181,000(አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) መሆኑን ተከሳሽ ምንም እንኳን የእቁቡ ደንብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዕጣ ለእቁቡ አከፋፈል ዋስትና እንዲሆን የሚደነግግ ቢሆንም ከሳሽ የነበረበትን ችግር ከግምት ዉስጥ በማስገባት የባለ 1,100/አንድ ሺህ አንድ መቶ) የሆነዉን ዕቁብ ሁለተኛዉን ዕጣ ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ መሆኑን፤ከሳሽ ለ2ኛ ዕጣ የሚሆነዉን ክፍያ በየቀኑ መክፍል የነበረበት መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ ይህን ክፍያ ከሳሽ ያልፈጸሙ መሆኑን ፤ከሳሽ የህዳር ወር የ30 ቀናት የዕቁብ ክፍያ የሆነዉን ብር 191,400( አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) ያልከፈለ ቢሆንም ከሳሽ ክፍያዉን ቢፈጽም ኖሮ ከሚያገኘዉ ብር 240,000.00(ሁለት መቶ አርባ ሺህ) ላይ ያልከፈለዉን ብር 191,400(አንድ መቶ ዘጠኛ አንድ ሺህ አራት መቶ) ተቀናሽ በማድረግ ብር 60,000.00 (ስልሳ ሺህ) እንዲወስድ ሲጠየቅ አምቢተኛ የሆነ መሆኑን፤ከሳሽ የዕቁብ ተመላሽ ገንዘብ መጠየቅ የሚቻለዉ በዕቁብ ደንብ መሰረት ዕቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወር በኃላ መሆኑን ከሳሽ በአሁኑ ጊዜ የእቁቡ ገንዘብ ሊመለስለት ይገባል እንኳን ቢባል በዕቁቡ ደንብ አንቀጽ 6 መሰረት ብር 36,200.00( ሰላሳ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ) ቅጣት እንዲሁም የሰብሳቢ የአግልግሎት ክፍያ ብር 139,200(አንድ መቶ ሰለሳ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ) በድምሩ ብር 175,400.00( አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ አራት መቶ) ከሳሽ በአጠቃላይ ከከፈለዉ ብር 181,000.00(አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ላይ ተቀናሽ ተድርጎ ለከሳሽ ሊከፈል የሚገባዉ ብር 5,600/አምስት ሺህ ስድስት መቶ) ብቻ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሱን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ተከሳሽ የዕቁቡን ዕጣ 2ኛ ዙር ያለውድድር ሊሰጣቸዉ ቃል የገባ መሆኑን ተከሳሽ በገባዉ ቃል መሰረት የ2ኛዉን ዙር ዕቁብ እንዲሰጣቸዉ ሲጠይቁ ተከሳሽ እምቢተኛ የሆነ መሆኑን የ2ኛዉን ዙር ዕቁብም ለማግኝት ከሳሽ መክፍል የሚጠበቅበት ብር 33,000.00(ሳላሳ ሶስት ሺህ) መሆኑን ከሳሽ ብር 35,200(ሰላሳ አምስት ሺህ) የከፈለ መሆኑን በቀንም መጣል ይጠበቅባቸዉ የነበረዉ ብር 1,100 (አንድ ሺህ አንድ መቶ ) መሆኑን የሰብሳቢ የአገልግሎት ክፍያ የተባለዉን የማያውቁ መሆኑን፤ በማስረጃነት የቀረበዉንም የእቁብ መተዳደሪያ ድንብ የማያውቁት መሆኑን ተከሳሽም ዕቁቡን ሲቀላቀሉ ያላሳያቸዉ መሆኑን የሰብሳቢ የአግልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ሊከፍሉ የማይገባ መሆኑን በመግለጽ ሲከራከሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ዕቁቦቹ አምስት መደቦች ያላቸዉ መሆኑን በአያንዳንዱ ዙርም ከሳሽ ብር 191,400.00(አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መከፍል የሚጠበቅባቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ የመጀመሪያዉን ዙር እንኳን ሙሉ ክፍያ ያልከፈሉ መሆኑን 2ኛዉን ዙር ምንም አይነት ክፍያ ያልከፈሉ መሆኑን ነገር ግን ሙሉዉን ክፍያ የመክፍል ግዴታ ያለባቸዉ መሆኑን እንዲሁም ከሳሽ የዕቁቡን መተዳደሪያ ድንብ አናውቀዉም በማለት ያቀረቡት ክርክር አግባብነት የሌለዉ መሆኑን በመግለጽ ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡
የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ተከሳሽ ያቀረባቸዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ክርክሩ ወደ መደበኛ ክርክር የተለወጠ በመሆኑ ጉዳዩ በተፋጠነ ስነ ስርዓት መቅረቡ አግባብነት የለዉም በማለት ተከሳሽ ያቀረበዉ መቃወም አግባብነት ያለዉ ባለመሆኑ እንዲሁም ይህ ፍርድ ቤትም በአዋጅ ቁጥር 25/88 መሰረት ጉዳዩን ለማየት የግዛት ክልል ስልጣን ያለዉ በመሆኑ የተከሳሽን የመጀመሪያ ደረጃ መቃሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል፡፡
በመቀጠል ፍርድ የመረመረዉ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፈል ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ ነዉ፡፡
እንደመረመረዉም ከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን ገንዘብ ክፍያ የፈጸሙ መሆኑን ተከሳሽ ካለመካዳቸዉም በላይ ከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀዉን ገንዘብ የከፈሉ መሆኑን የቀረቡት የእቁብ ክፍያ ደብተሮች ያስረዳሉ፡፡
ተከሳሽ ለከሳሽ በ2ኛ ዙር ባለ 1,100( አንድ ሺህ አንድ መቶ) መደቡን ዕቁብ ያለውድድር ለከሳሽ ለመሰጠት ቃል የገባ መሆኑን በመከላከያ መልሱ ላይ ከማመኑም በላይ ክስ በተሰማ ጊዜም ለችሎቱ ገልጸዋል ፡፡
ተከሳሽ የ2ኛ ዙሩን አቁብ ለከሳሽ ያልሰጠሁት በክሱ ላይ ለተጠቀሱት ለአምስቱም አይነት የዕቁብ መደቦች በአጠቃላይ ብር 191,400 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መክፍል ይጠበቅባቸዋል በማለት የተከራከረ ቢሆንም አምሰቶቹም በክሱ ላይ የተጠቀሱት የዕቁብ መደቦች እራሳቸዉን ችለዉ የሚቆመ መሆኑን ግራ ቀኙ በክርክር ሂደት የገለጹ ከመሆኑ አንጻር እና ተከሳሽም ለከሳሽ ያለውድድር ሊሰጥ የነበረዉ ባለ 1,100 የሆነዉን መድብ ከመሆኑ አንጻር ተከሳሽ በ2ኛ ዙር ዕጣዉን ያለውድድር ለማገኝት ብር 191,400 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መከፈል ነበረባቸዉ በማለት ያቀረበዉ ክርክር እርስ በእርሱ የሚጣርስ ነዉ፡፡
በተለመደዉ የዕቁብ አሰራርም ከሳሽ የሚጠበቅባቸዉ ያለውድድር ለሚያገኙት የዕቁብ ክፍያ ዕጣዉ እስኪሰጣቸዉ ድረስ የሚፈለግባቸዉን ክፍያ መክፈል ነዉ፡፡ ከሳሽ ለባለ 1,100 መደብ ብር 35,200(ሰላሳ አምሰት ሺህ ሁለት መቶ) የከፈሉ መሆኑን ክርክር አቅርቧል በማስረጃም አረጋግጧል ተከሳሽ በበኩሉ ለዚህ መደብ እቁብ በተከሳሽ ብር 35,200 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) ያልተከፈለ መሆኑን በመግለጽ ያቀረበዉ ማስተባበያ የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ባለ 1,100 መደቡን እቁብ ለማገኝነት ተገቢዉን ክፍያ የከፈሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሽ በገባዉ ቃል መሰረት ባለ 1,100 ዉን መደብ ለከሳሽ በ2ኛ ዙር ለመስጠት እምቢተኛ መሆኑን አልካደም፡፡ ይህም የተከሳሽ ተግባር አይነተኛ የውል መጣስ በመሆኑ እና ከሳሽም ተከሳሽ 2ኛዉን ዙር ዕቁብ ያለ ውድድር ለማግኝት በዕቁቡ ታሳፊ የሆኑ በመሆኑ እና ተከሳሽም ባቀረበዉ ክርክር ከሳሽ ወደ ዕቁብ የገቡት 2ኛዉን ዙር ዕቁብ ያለውድድር የሚሰጧቸዉ መሆኑን በማመን መሆኑን ያልካዱ በመሆኑ ከሳሽ ዕቁቡን ማቋረጡ በአገብቡ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ለከሳሽ ተመላሽ ሊደረግ የሚገባዉ ገንዘብ ብር 5,600 ነዉ ከሳሽ አጠቃላይ ከከፈሉት የገንዘብ መጠን ላይ የሰብሳቢ ጠቅላላ አግልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ብር 175,400(አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ) በዕቁቡ ደንብ መሰረት ተቀናሽ ሊደረግ ይገባል በማለት ክርክር አቅርቧል ከሳሽ በበኩላቸዉ በማስረጃነት የቀረበዉን የዕቁብ ደንብ አናወቀወም የሰብሳቢ ጠቅላላ የአገልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ተቀናሽ ሊደረግ አይገባም በማለት ነዉ፡፡
የእቁብ ደንብ የአባላቱን መብትና ግዴታ የሚገዛ እንደመሆኑ መጠን ድንቡ በአባላቱ ላይ አስገዳጅ እንዲሆን የዕቁቡ አባላት ደንቡን አይተዉ ተመልክተዉ ፈቃዳቸዉን መሰጠት ያለባቸዉ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 1678 እና 1679 መረዳት የሚቻል ሲሆን አንድ የእቁብ ደንብ እንደ ውል የሚቆጠር በመሆኑ አባላቱ እንዲገደዱበት ፈቃዳኛቸዉን መስጠት አለባቸዉ፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ተከሳሽ ከሳሽ የእቁቡ አባል ሲሆኑ የዕቁቡን ደንብ ያልተመለከቱ መሆኑን የእቁቡ ድንብ ላይ ፈቃዳቸዉን ሰጥተዉ ያልፈረሙ መሆኑን አልካዱም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ፈቃዳኛዉን ባለሰጡበት ደንብ የሚገደዱበት የህግ መሰረት የለም፡፡በመሆኑም
ተከሳሽ ከሳሽ አጠቃላይ ከከፈሉት የገንዘብ መጠን ላይ የሰብሳቢ ጠቅላላ የአግልግሎት ክፍያ እንዲሁም ቅጣት ተቀናሽ ሊደረግ ይገባል በማለት ያቀረቡት ክርክር የማስረጃ ፤የህግ እንዲሁም የተለመደ አሰራር ድጋፍ የሌለዉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ሌላዉ ተከሳሽ ያቀረቡት ክርክር ከሳሽ የእቁብ ተመላሽ ገንዘብ ሊጠይቁ የሚገባዉ ዕቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወራት በኃላ ነዉ በማለት ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ተከሳሽ ለዚህም መሰረት ያደረጉት በማስረጃት ያቀረቡትን የእቁብ ደንብ ነዉ ይሁን እንጂ ይህ ደንብ በከሳሽ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ ከሳሽ ፈቃዳኛዉን ያልሰጡትበት በመሆኑ ሊስገድዳቸዉ አይችልም፡፡ ይልቁንም ተከሳሽ የገባዉን ቃል በማጠፉ እና የዕቁብ ሂደትም ውልን መሰረት የሚደረግ በመሆኑ እና ተከሳሽም 2ኛዉን ባለ 1,100 ዕጣ ዕቁን ለከሳሽ ለመስጠት እምቢተኛ መሆኑ ሲታይ ተከሳሽ አይነተኛ የውል ጥስት የፈጸመ መሆኑን የሚያስረዳ ስለሆነ እና እንዲህ በሆነ ጊዜም ዉሉ ቀሪ ሆኖ ግራ ቀኙ ወደነበሩበት ሊመሰለሱ የሚገባ መሆኑን መረዳት የሚቻል ስለሆነ ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊመልስ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ ብር 181,000.00( አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ከጥር 27 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታስብ 9% ወልድ ጋር ለተካሳሽ ይክፈሉ፡፡
- ወጪና ኪሳራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 4,545፤ለቴምብር ቀረጥ ብር 30 እንዲሁም የጠበቃ አበል ብር 18,000 ተከሳሽ ለከሳሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ፡፡
መዝገቡ ተዝግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡