- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
የኮ/መ/ቁ 180219 - አቶ ኃይለስላሴ አስርስ ደሳለኝ እና አቶ አብርሃም ጌታሁን ደያም
መ/ቁ 180219
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- አቶ ኃይለስላሴ አስርስ ደሳለኝ ከጠበቃ መለስ ግርማይ ጋር ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አቶ አብርሃም ጌታሁን ደያም፡- ጠበቃ ሳሙኤል ደመቀ ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ መርምሮ ተገቢዉን ለመስራት ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤተታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃልና ምስል በንግድ ምልከትነት ያስመዘገቡ መሆኑን ከ25/1/2009 ዓ/ም እስከ 25/1/2016 ዓ/ም ድርስ የሚቆይ የአዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ የተሰጣቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ያለ እርሳቸዉ ፈቃድ እና እውቅና ያስመዘገቡትን የንግድ ምልክት እየተጠቀሙበት የሚገኙ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ይህን ድርጊታቸዉን እንዲያቁሙ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ እንድ ክስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰንድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡
ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ድርሶ ተከሳሽ ጥር 3 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልሳቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍርሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ያቀረባቸዉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ፍርደ ቤቱ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች መርምሮ ውድቅ ያደረጋቸዉ በመሆኑ ከዚህ ማስፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡
ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ስም Sun land international Hotel የሚል ሳይሆን Sun land Hotel የሚል መሆኑን international የሚለዉ ቃልም በተከሳሽ የንግድ ስም ዉስጥ የሌለ መሆኑን በጋዜጣ ላይ የወጣዉ የከሳሽ የንግድ ምልክት በኢታሊክስ አጻጻፍ Sun land የሚል መሆኑን ነገር ግን የተከሳሽ የንግድ ስም በካፒታል ሌተር SUN LAND HOTEL የሚል በመሆኑ ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተቀራራቢ እንጂ ተመሳሳይ ነዉ ሊባል የማይችል መሆኑን በጋዜጣ የወጣዉ የከሳሽ የንግድ ምልክት ምስል እና ከሳሽ ከክሱ ጋር አያይዞ በማስጃነት ያቀረበዉ ምስል ተመሳሳይነት የሌላቸዉ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልክቱን በስማቸዉ ያስመዘገቡ ስለመሆኑ የምስክር ወረቀት ያላቀረቡ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልከቱን የምስክር ወረቀት ባላቀረቡበት ሁኔታ የንግድ ምልከቱ በሶስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚነት የሌለዉ መሆኑን ተከሳሽ suland hotel የሚለዉን የንግድ ስም ስልጣን ባለዉ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት ያስመዘገቡ መሆኑንአዕምሮዊ ንብረት የንግድ ምልክትን ምዘገባ የሚያካሂድ መሆኑን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደግሞ የንግድ ስም ለመመዘገብ ስልጣን የተሰጠዉ መሆኑን በዚህም ምክንያት አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ ሊሆን የሚችልበት አግባብ የሌለ መሆኑንአንዱ በሌላኛዉ ላይ የበላይነት አለዉ የሚባል ከሆነምመብቱን ቀድሞ ያገኘዉ ማን ነዉ የሚለዉ ነጥብ መተያት ያለበት መሆኑን ተከሳሽ የንግድ ስም የምስር ወረቀትያገኘዉ በ10/5/2009 ዓ/ም መሆኑን ከሳሽ በዚህ ጊዜ የንግድ ምልዕክቱንበጋዜጣ ማስታወቂያ አሳውጆ ተቃዋሚ የሚቀርብ ከሆነ ሲጠባበቅ የነበረ መሆኑን የምስከር ወረቀት ሊያገኝ የሚችለዉም ከዚህ ጊዜ በኃላ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልክት አስመዝገቢያለሁ በማለት የሚከራከሩ ቢሆንም በንግድ ስሙ የከፈተዉ ሆቴል ወይም የሚንቀሳቅሰዉ ንግድ የሌለ መሆኑን በአንጻሩ ደግሞ ተከሳሽ ባስመዘገበዉ የንግድ ስም በስራ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከሳሽ በንግድ ስሙ እንዳይጠቀም የሚከለከል ከሆነ ያገኘዉን መልካም ስም የሚያጣ መሆኑንበመገለጽ የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልዕክት ከሳሽ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ የሚሰጡት አገልግሎት ተመሳሳይ መሆኑን የእዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ ጽ/ቤት በሰጠዉ ማስረጃ ተከሳሽ የሚጠቀምበት የንግድ ምልክት የከሳሽ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን፤ sun land hotel የሚለዉ ቃል እና የከሳሽ የንግድ ምልክት በተከሳሽ ሆቴል ላይ በተሰጠቀለዉ ቦርድ ላይ ያለ መሆኑን የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀትም የተሰጣቸዉ መሆኑን ተከሳሽ የንግድ ምልዕክቱን የተጠቀሙት ያለፈቃዳቸዉ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር sun land hotel የሚል የንግድ ስም ለተከሳሽ መስጠቱ ህገወጥ መሆኑን በእዕምሮ ፈጣራ ዉጤት የተያዘን ስም በንግድ ስምንነት ለተከሳሽ መስጠቱ አግባብነት የሌለዉ መሆኑንተከሳሽ የቀደምነትነት መብት የሌላቸዉ መሆኑንየቅድምትንት መብት ያለዉ ከሳሽ መሆኑን ተከሳሽ የተጠቀመዉ የንግድ ምልዕክቱ ላይ ያለዉን ስም እና መስሉን ጭምር መሆኑን በመግለጽ ክርክራቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር የንግድ ምልዕክት ያስመዘገበ ሰዉ በመብቱ መስራት የሚችለዉ የምስክር ወረቀቱ በእጁ በገባ ጊዜ መሆኑን እዕምሮዊ ንብረት በተቀመጠ የምስክር ወረቀት መብት ሊቋቋም የማይችል መሆኑን የንግድ ምልክቱን በጋዜጣ ሊወጣ የሚገባ መሆኑን ክሱም መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር መሆኑንገልጸዉ የመከላካያ መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክሯል፡፡
የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡
ከሳሽ የሚከራከረዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት ስለተጠቀም እና ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን ከሳሽ ከሚሰጠዉ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መሳከርን የሚያስከትል ስለሆነ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀም ሊወሰንልን ይገባል በማለት ነዉ፡፡
ከከሳሽ ክርክር አንጻር ምላሽ ሊያገኝ የሚገባዉ ጉዳይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 501/2000 ያገኘዉን የብቸኝነት መብት(exclusive right) የሚጠስ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉ ሲሆን ይህ መልስ ከመስጠታችን በፊት የንግድ ስምን እና የንግድ ምልከት አገልግሎታቸዉ/ጥቅማቸዉ ምን እንደሆነ መለየቱ ተገቢ ነዉ፡፡
ከዚህ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 2(12) እንደተመለከተዉ የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰዉ ዕቃዎች ወይም አገለግሎቶቸ ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን የንግድ ምልክቱም ቃላቶችን፤ዲዛይኖችን፤ ፊደሎችን፤ቁጥሮችን፤ቀለሞችን ወይም ዕቃዎችን ወይም የመያዣቸዉን ቅርጾችወይም የነዚህን ቅንጅቶች ሊይዝ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
የንግድ ምልክትን ለመመዘገብም ስልጣን የተሰጠዉ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ስለመሆኑ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ዓ/ም አንቀጽ 2(10) እንደተደነገገዉ የንግድ ስም ማለት አንድ ነጋዴ ለንግድ ስራዉ የሚጠቀምበት እና በህብረተሰቡ ዘንድበግልጽ የሚታወቅበት ስም ነዉ በሚል ተደንግጓል፡፡ ማንኛዉም ነጋዴ የንግድ ስሙን በግለጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ እንዳለበትም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ዓ/ም አንቀጽ 18(1) ተድንግጓል፡፡
የንግድ ስም የመመዘገብ ስልጣንም የንግድ ሚኒስቴር እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ስር ተመልክቷል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለዉ የንግድ ምልክት የሚያገለግለዉ የአንድን ድርጅት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚሰጡት አገልግሎት/ከሚያቀርቡት ዕቃዎች ለመለየት ሲሆን የንግድ ስም ደግሞ አምራቹ ወይም አገልግሎት ሰጪዉ አገልግሎቱን ወይም ዕቃዎቹን ለህበረተሰቡ የሚያቀርብበት ስም መሆኑን እንዲሁም ነጋዴው በንግድ ቦታዉ የንግድ ስሙን በሚታይ ቦታ መለጠፍ በህግ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የከሳሽ የንግድ ምልክት በምዝገባ ቁጥር LTM/4386/2009 E.C የተመዘገበ መሆኑን፤ከሳሽምከ25/1/2009 ዓ/ም አስከ 25/1/2016 ዓ/ም ድረስ ለንግድ ምልክቱ ጥበቃ የተሰጠዉ መሆኑን የንግድ ምልከቱም ለሆቴል አገልግሎት በዓለም አቀፍ ምድብ 43 የተመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ሚያዚያ 15 ቀን 2011 ዓም ለፍርድ ቤቱ የላከዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ ይህም የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት በአዋጅ ቁጥር አንቀጽ 501/98 አንቀጽ 15 መሰረት የተሰጠ መሆኑን እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረበዉ የንግድ ምልክት ባለቤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የንግድ ምልከቱ የተመዘገበለት ሰዉ የንግድ ምልከቱን ከተመዘገበበት ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር አያይዞ የመጠቀም ወይም ሌላ ሰዉ እንዲጠቀምበት የመፈቀድ መብት የሚኖረዉ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(1) ስር ተመልክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ምልከት ባለቤት የሆነ ሰዉ ሌሎች ሰዎች የንግድ ምልክቱን ወይም ህዝብን ሊያሳስት የሚችል ማናቸዉንም የንግድ ምልከቱን የሚመስል መለያ የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበባቸዉ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ወይም ህዝብን ሊያሳስት በሚችል አኳን ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ እንዳይጠቀሙ፤የንግድ ምልከቱን ወይንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ ያለ በቂ ምክንያቶች ጥቅሙን በሚጎዳ አኳን እንዳይጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለማገድ የሚችል ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 26(2)(ሀ)(ለ)(ሐ) የሚደነግግ ሲሆን አንድ አይነት መለያ ለአንድ አይነት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ሲውል የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት መውስድ የሚቻል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 26(3) ስር ተመልክቷል፡፡
ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረቡት የንግድ ምልክትከላይ የተጠቀሱት የብቸኘነት መብት (exclusive right) ያላቸዉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተከሳሽ የሚጠቀመዉየንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ፤ተከሳሽ የተሰማራበት የስራ ዝርፍም የሆቴል አገልግሎት መሆኑን እንዲሁም ተከሳሽ በንግድ ምልክትነት ያስመዘገበዉን ስም እና መስል በሆቴሉ ላይ ሰቅሎ ሲጠቀም የነበረ መሆኑን በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች አስረድቷል እንዲሁም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃል በንግድ ምልክትነት ለሆቴል አገልግሎት ያስመዘገቡ መሆኑን የአዕምሮዊ ንብረት ለፖሊስ በቀን 25/12/2009 ዓ/ም የሰጠዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ ከዚህ አንጻር አማካኝ (average) የሆነ ተጠቃሚን ብንወስድ ተከሳሽ SunlandHotel የሚለዉን ቃል ከሳሽ በንግድ ምልክትነት ካስመዘገቡት መስል ጋር በሆቴሉ ላይ መጠቀሙ ተጠቃሚዉን ሊያሳስት የሚችል መሆኑን መረዳት የሚችል ከመሆኑም በላይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክትም ሆነ ስም በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(3) መሰረት የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት ሊያስወስድ የሚችል ነዉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ የሚጠቀሙበትን የንግድ ስም ያስመዘገቡት በቀን 10/5/2009 ዓ/ም መሆኑን በማስረጃነት ያቀረቡት የምስክር ወረቀት የሚያስረዳ ሲሆን ከሳሽ በበኩላቸዉ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት በ25/1/2009 ዓ/ም መሆኑን የእዕምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት የሰጠዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት መኖሩን ነዉ፡፡ይሁን እንጂበንግድ ምልከት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት በተፈጠረ ጊዜ እንዴት እንደሚፈተ ህጋችን ያስቀመጠዉ የህግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰዎች ድርጊቶችን በቀን ልቦና እንዲፈጽሙ የሚጠበቅ ሲሆን ከሳሽ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የንግድ ምልክት ያስመዘገቡት በቀን 21/1/2009 ዓ/ም መሆኑ እና የንግድ ምልክቱን የሚቃወም ካለም እንዲቀርብ በጋዜጣ ጥሪ የተደረገ መሆኑ ሲታይ በሌላ በኩል ተከሳሽ የንግድ ስሙን ያስመዘገቡት እና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ/ም መሆኑ ሲታይ ምንም እንኳን በአዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 17(1) የንግድ ስም በመዝገብ መግባት የንግድ ስሙን ለመጠቀም መብት የሚሰጥ ተቀዳሚ ማስረጃ መሆኑን የሚደነግግ ቢሆንም ተከሳሽ የንግድ ስሙን በማስመዘገብ ከቅን ልቦና ውጪ ሊጠቀሙት አይችሉም ቀን ልቦና አላቸዉ ሊባልም አይችልም፡፡በመሆኑም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃል ከሚሰጡት የሆቴል አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለመጠቀም የቀዳሚነት መብት አላቸዉ ተብሏል፡፡
ሲጠቃለልም ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት/ስም አማካይ የሆነ ተጠቃሚን ሊያሳስት የሚችል በመሆኑ፤ከሳሽ እና ተከሳሽ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን የሚያሳክር በመሆኑ፤ከሳሽ የንግድ ምልክታቸዉን ያስመዘገቡት ለሆቴል አገልግሎት በመሆኑ ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘም የንግድ ምልክቱን ቃልም ሆነ መስል መጠቀም የብቸኝነት መብት ያላቸዉበመሆኑ ተከሳሽ ይህ ዉሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ የከሳሽን የንግድ ምልክት እንዳይጠቀሙ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት የፈጸሙ ስለሆነ የከሳሽን የንግድ ምልከት እንዳይጠቀሙ የሰቀሉትንም የከሳሽ የንግድ ምልክት ከሆቴላቸዉ ላይ እንዲያነሱ ተወስኗል፡፡
- ተከሳሽ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈለዉን ብር 90፤የጠበቃ አበል ብር 16,000 እና ለሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች ብር 200 ለከሳሽ ይክፈል፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡