መ/ቁ 179287    

ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- አቶ ዳንኤል አበጀ ተካልኝ ጠበቃ ብሩክ ደረጀ፡ ቀረቡ

ተከሳሾች፡- 1ኛ) አቶ አዳነ ደርብ ማሙዬ፡- አልቀረቡም

          2ኛ) ኤም ኤ ፕሪንቲንግ እና አድቨርታይዚንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፡- ም/ስራ አስኪያጅ መልካሙ በላቸዉ ፡- ቀረቡ

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ሕዳር 12 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽ የመኪና አስመጪነት ስራ ላይ የተሰማራ መሆኑን የ2ኛ ተከሳሽ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ መኪና እንዲመጣለት ባዘዘዉ መሰረት በሰሌዳ ቁጥር 2ኤ96731 የሚታወቀዉን እና በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተመዘገበዉን ቶዮታ ያሪስ ተሽከርካሪ ያስመጡላቸዉ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽም ቀሪ ክፍያ መክፈያ እንዲሆን በ2ኛ ተከሳሽ ስም የተመዘገበ ብር 175,000.00( አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ) የያዘ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚመነዘር ቼክ የሰጧዋቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ቼኩን ለክፍያ ለባንኩ ባቀረቡ ጊዜ የ2ኛ ተከሳሽ ሂሳብ በቂ ስንቅ የለዉም በሚል ቼኩ ተመላሽ የተደረገላቸዉ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሾች ብር 175,000.00(አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ) በእንድነት እና በነጠላ እንዲከፈላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮች ቆጥሯል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤታታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሾች ድርሶ የበኩላቸዉን መከላከያ እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ 1ኛ ተከሳሽ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ የደረሳቸዉ ቢሆንም ያቀረቡት የመከላከያ ማስፈቀጃ ባለመኖሩ ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት የመከላከል መብታቸዉን ፍርድ ቤቱ ያለፈ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ በበኩላቸዉ በቀን 25/4/2011 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ ማስፈቀጃ አቅርበዉ ፍርድ ቤቱም የቀረበባቸዉን ክስ እንዲከላከሉ ፈቅዶ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልሳቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም 1ኛ ተከሳሽ ለብቻዉ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ኃላፊነት የሚያስከትል ተግባራትን ለማከናወን ስልጣን ያልተሰጠዉ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ስልጣን እንደሌለዉ እያወቀ እንዲሁም ከሳሽ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቼክ የ2ኛ ተከሳሽ መሆኑን እያወቀ ቼኩን መቀበሉ በገዛ ፈቃዱ ሃላፊነት የወሰዱ መሆኑን የሚያስረዳ መሆኑን በከሳሽ እና በ1ኛ ተከሳሽ መካከል ያለዉ ግኑኘነት የመኪና ሽያጭ ውል መሆኑን የመኪናዉ ሽያጭ ውልም በመካከላቸዉ የተቋቋመ በመሆኑ 2ኛ ተከሳሽንም ወደዚህ ያስገቡት ሆን ብሎ ሃላፊነትን ለማሰከተል ስለሆነ ከሳሽ የመኪና ሽያጭ ዉሉን መሰረት አድርገዉ 1ኛ ተከሳሽ ከሚጠይቁ በቀር ቼኩን መሰረት አድርገዉ ዳኝነት ሊጠይቁ የማይገባ መሆኑን በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ  እና መመሰረቻ ጽሁፍ መሰረት የ2ኛ ተከሳሽ ስራ ሊከናወን የሚችለዉ በ1ኛ ተከሳሽ እና በ2ኛ ተከሳሽ ምክትል ስራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ መልካሙ በላቸዉ ጣምራ ዉሳኔ መሆኑ እየታወቀ 1ኛ ተከሳሽ ለብቻቸዉ ከስልጠናቸዉ ወጭ ለሰጡት ቼክ 2ኛ ተከሳሽ ሃላፊነት የሌለባቸዉ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ቼኩን የሰጠዉ ባንክ አስፈላጊዉ ፎርማሊቲ ባይሟላ የ2ኛ ተከሳሽን ሂሳብ የማይከፍት መሆኑን የ2ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ ለብቻዉ መፈረም የሚችል መሆኑን ቀደም ሲል የነበረዉ መመስረቻ ጽሁፍ በቃለ ጉባኤ የተሻሻለ መሆኑን ከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የፈጸመዉ የመኪና ሽያጭ ውል በጽሁፍ የተደረገ ሳይሆን በቃል የተደረገ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ቀደም ሲል ክፍያ የፈጸመዉ በ2ኛ ተከሳሽ ቼክ መሆኑን  

1ኛ ተከሳሽ ውል የተዋዋለዉ በ2ኛ ተከሳሽ ስም መሆኑን ግምት ሊወስድ የሚገባ መሆኑን  1ኛ ተከሳሽ መኪናዉ ወደ ሀገር ዉስጥ ከገባ በኃላ ስመ ሀብቱን በስሙ ያዞረ መሆኑን ይሁን እንጂ ይህ የ1ኛ ተከሳሽ ተግባር የ2ኛ ተከሳሽ ሃላፊነትን የማያስቀር መሆኑን በመግለጽ ሲከራከሩ 2ኛ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር ስለመኪናዉ የሚያውቁት ነገር የሌለ መሆኑን ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቼክ በ2ኛ ተከሳሽ ሃላፊነት የሚያስከትል አለመሆኑን  ቼኩንም 1ኛ ተከሳሽ ለግል ጥቅሙ ያዋለዉ መሆኑን ለድርጅቱ ጥቅም ቢሆን 1ኛ ተከሳሽ በድርጅቱ ስም የሚዋዋል መሆኑን በመግለጽ ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡

የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመሰል ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች በእንደነት እና በነጠላ በክሱ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡

እንደመረመረዉም ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቼክ በ1ኛ ተከሳሽ የተፈረመ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ መሆኑን ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ የመኪና ሽያጭ ውል የፈጸሙ መሆኑን በመኪና ሽያጭ ዉሉም ላይ የተገለጸቺዉ ተሽከርካሪም በ1ኛ ተከሳሽ ስም ተመዝገባ የምትገኝ መሆኑ ከግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃዎች መረጋገጥ የተቻሉ ፍሬ ነገሮች ናቸዉ፡፡

1ኛ ተከሳሽ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ደረሶት ያቀረበዉ መከላከያ የለም፡፡በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 285(2) በመጥሪያዉ ላይ በተወሰነዉ ጊዜ ዉስጥ ተከሳሽ ቀርቦ መከላከያ ለማቅርብ እንዲፈቀድለት ለፍርድ በቱ ያላመለከተ እንደሆነ ከሳሽ የጠየቀዉ ገንዘብ ከነ ወለዱ እንዲከፍል ፍርድ ሊሰጥ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ሊከፍል ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡

2ኛ ተከሳሽን በተመለከተ በንግድ ህጉ አንቀጽ 35 እንደተመለከተዉ ከሶስተኛ ወገኖች ጋራ በሚያገናኙት ጉዳዮች ሁሉ ስልጣን ያለዉ ስራ አስኪያጅ ከነጋዴዉ ስራ ጋራ ነክነት ያላቸዉን ማናቸዉንም ግዴታዎች ለመፈረምና የሚተላላፉ የንግድ ሰነዶችን ጭምር ለመፈረም ሙሉ ስልጣን እንዳለዉ ሆኖ የሚቆጠር መሆኑ ተመልከተዋል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለዉ

የአንድ ማህበር ስራ አስኪያጅ በማህበር ህጋዊ ዉጤት ያለዉ ተግባር ለመፈጸም እና ማህበሩም በስራ አስኪያጁ ተግባር ሊገደድ የሚገባዉ ስራ አስኪያጁ ያከናወነዉ ተግባር ከማህበሩ የንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የፈጸመዉ ተግባር እንደሆነ መሆኑን እንዲሁም ከማህበሩ የንግድ እንቅሰቃሴ ጋር የማይገናኝ ከሆነ ስራ አስኪያጁ በማህበሩ ላይ ግዴታ ሊያስከትል የሚችል ተግባር ሊፈጽም እንደማይችል መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ከሳሽ በክስ አቤቱታዉ ላይ በግልጽ የማለከተዉ ከ1ኛ ተከሳሸ ጋር የመኪና ሽያጭ የፈጸመ መሆኑን በከፊል ከፍያም የፈጸመለት1ኛ ተከሳሽ መሆኑን የቀረበዉ ክስ ይዘት ያስረዳል ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ ከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የፈጸመዉ የመኪና ሽያጭ ውል ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የንግድ ስራ ጋር የሚገናኝ አይደለም በዚህ መልኩ ከሳሽ ያቀረበዉም ክርክር የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 35(1) መሰረት 2ኛ ተከሳሽን ሊያስገድድ የሚችል ህጋዊ ተግባር ያልፈጸመ መሆኑን መረዳት የሚቻል ከመሆኑም በላይ 1ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የመኪና ሽያጭ ዉሉን የፈጸመዉ ለግሉ ጥቅም መሆኑን ተሽከርካሪዉ በአሁኑ ጊዜም በ1ኛ ተከሳሽ ስም ተመዝገቦ የሚገኝ መሆኑ አስረጂ ነዉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8 መሰረት ቼክን የመሰሉ የሚተላላፉ ሰነዶች ለሶስተኛ ወገን ሊሰጡ የሚችሉት በ1ኛ ተከሳሽ እና በ2ኛ ተከሳሽ ምክትል ስራ አስኪጅ የጋራ ፊርማ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ ከተሰጠዉ ስልጣን በማለፍ ቼክ ፈርሞ ለከሳሽ መስጠቱ ጥፋት የፈጸመ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን ስራ አስኪያጅ ሙሉ ስልጣን ያለዉ እና በማህበሩ ላይ ህጋዊ ዉጤት ሊያሰከትል የሚችል ተግባር ሊፈጽም የሚችለዉ የማህበሩን አላማ ለማሳካት ብቻ እንጂ የግል ጥቅሙን በአሰቀደመ ጊዜ አለመሆኑን የንግድ ህጉ አንቀጽ 528 ያስረዳል፡፡

ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር 1ኛ ተከሳሽ የመኪና ሽያጭ ውል የፈጸመዉ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጥቅም ብሎም የማህበሩ ዓለማ ከግብ ለማድረስ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም የማህበር ስራ አስኪያጅ ከላይ ከተጠቀሱት ህጋዊ ተግባራት ወጪ ሌሎች ህገወጥ ተግባራትን የፈጸመ እንደሆነ ደግሞ በንግድ ህጉ አንቀጽ 530 መሰረት ሶስተኛ ወገኖች ላይ ለደረሰ ጉዳት ሃላፊነት

ያለባቸዉ መሆኑ የተመለከተ ስለሆነ በቼኩ ላይ ለተመለከተዉ የገንዘብ መጠን 1ኛ ተከሳሽ ሃላፊ ከሚባል በስተቀር 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት ሳይኖረዉ እና  ለክርክሩ መነሻ የሆነዉም ቼክ ለከሳሽ የተሰጠዉ ከእርሱ ጋር ባለ የንግድ ግኑኝነት ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ 2ኛ ተከሳሽ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቼክ ላይ የተገለጸዉን የገንዘብ መጠን የመክፈል ሃላፊነት የለበትም በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 ውሣኔ

  1. 1ኛ ተከሳሽ ብር 175,000.00(አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ) ከ9/1/2011 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ ተብሎ ተወስኗል፡፡
  2. 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈለዉን ብር 4,475፤ለቴምብር ቀረጥ የተከፈለዉን ብር 25 እንዲሁም ለጠበቃ አበል ብር 17,000 እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

ትዕዛዝ

ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ ፡፡

መዝገቡ ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡