- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4649
የኮ/መ/ቁ - 168817 - ወ/ሮ መሪም ኡመር አህመድ እና ወ/ሮ ሲቲ ኡመር
የኮ/መ/ቁ 168817
ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- ወ/ሮ መሪም ኡመር አህመድ፡-ከጠበቃ ፈቃዱ ዳመነ ጋር ቀረቡ
ተከሳሽ፡- ወ/ሮ ሲቲ ኡመር፡- ጠበቃ ደረጄ ታደሰ፡-ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ በቀን 14/07/2010 ዓ/ም አሻሽለዉ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽና ተከሳሽ በሽርክና ለመስራት ተስማምተዉ የአሽሙር የሽርክና ማህበር ያቋቋሙ መሆኑን ይህ ማህበር የተከሳሽ ባለቤት በሆነዉ በአቶ አለበል ቢልልኝ ስም የንግድ ፈቃድ ወጥቶ ኤሮሼክ ጭማቂ ቤት በሚል ስም ከሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ማህበሩ የንግድ ስራ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ይህም የማህበሩ የንግድ ስራ የሚሰራዉ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በቤት ቁጥር 884(ሐ) በተከሳሽ ባለቤት በአቶ አለበል ቢልልኝ ስም በብር 30,000(ሰላሳ ሺህ) በተከራየዉ የንግድ ቤት ዉስጥ መሆኑን እንዲሁም ለማህበሩ የንግድ ስራ የሚሆኑ አታክልቶች በከሳሽ ባለቤት በአቶ አህመድ አደም ስም በአራዳ ክፍል ከተማ ወረዳ 9 በቤት ቁጥር 04/02 የሚታወቀዉን ከባሻ ወልዴ ችሎት የጋራ ህንጻ ባለቤቶች ኃ/የተ/የግል ማህበር የተከራዩ መሆኑን ይህን የኪራይ ቤትም በወር 8,500(ስምንት ሺህ) የተከራዩ መሆኑን ማህበሩን ሲመሰረቱን ከሳሽና ተከሳሽ እያንዳንዳቸዉ ብር 250,000(ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ) ያወጡ መሆኑን ማህበሩ ለስራ የተከራያቸዉን ቤቶች የቤት ኪራይ ግራ ቀኙ እኩል ያዋጡ መሆኑን አስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ/ም ያለዉን የማህበሩን ወጪና ትርፍ እኩል ሲከፋፈሉ የነበረ መሆኑን ማህበሩም በጣምራ ስራ አስኪያጆች እንዲመራ ስምምነት አድርገዉ የነበረ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ይህን ስምምነት ወደ ጎን በማድረግ ከሳሽን በማግለል ማህበሩን ለብቻቸዉ ሲያንቀሳቀሱ የነበረ መሆኑን ከሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮም ተከሳሽ ስለ ማህበሩ ዕቅድ፤ የስራ ክንዉን፤ የፋይናንስ አቋምና ሌሎች የማህበሩን እንቅስቃሴዎች ለከሳሽ ሪፖርት አድርገዉ የማያውቁ መሆኑን የትርፍ ገንዘቡን ለከሳሽ ገቢ ማድረግ ያቆሙ መሆኑን በዚህም ሳቢያ በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ የተፈጠረ መሆኑን አብሮ የመስራት ፍላጎታቸዉ የጠፋ መሆኑን ገልጸዉ በከሳሽና በተከሳሽ የተመሰረተዉ የሽርክና ማህበር እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸዉ የማህበሩን ሂሳብ አጣርቶ የሚያቀርብ የሂሳብ ባለሙያ እንዲሾምላቸዉ፤ ከሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ ያልተከፈላቸዉን የትርፍ ክፍያ ከሰዉ የመጠየቅ መብታቸዉ እንዲጠበቅላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርበዋል የሰዉ ምስክርም ቆጥረዋል፡፡
ከሳሽ ያቀረቡት የተሻሻለ ክስ ለተከሳሽ ደርሶ ተከሳሽ መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡ ከሳሽ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ መጋቢት 5 ቀን 2010 ዓ/ም በተሰጠ ብይንና ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት በተሰጠ ትዕዛዝ ወድቅ ያደረገዉ በመሆኑና ዝርዝሩም ከመዝገቡ ሰፍሮ የሚገኝ በመሆኑ ከዚህ ማስፈር ሳያስፍልግ ታልፏል፡፡
ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት የመከላከያ መልስ ከከሳሽ ለጋራ በተሰጣቸዉ ውክልና ከሚያስተዳድሩት የዉርስ ሀብት በቀር በከሳሽ ክስ ላይ የተጠቀሱትን ቤቶች ተከራይተዉ የአሽሙር የሽርክና ማህበር አቋቁመዉ የንግድ ስራ ሰርተዉ የማያውቁ መሆኑን የአሽሙር የሽርክና ማህበር የንግድ ስራ የሚሰራዉ በአንደኛዉ ተሻራኪ ስም በሚወጣ ንግድ ፈቃድ መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ በእርሳቸዉም ሆነ በተከሳሽ ስም የንግድ ፈቃድ ወጥቶ እና ቤት ተከራይተዉ የንግድ ስራዉ ሲሰራ የነበረ መሆኑን የሚያስረዳ ማስራጃ ያላቀረቡ መሆኑን እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ/ም ድርስ ትርፍ ሰንከፋፈል ነበር በማለት ከሳሽ የገለጹት ሃሰት መሆኑን፤ የንግድ ስራዉ የሚሰራበትን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በቤት ቁጥር 884(ሐ) የሚታወቀዉን ቤት የተከራየዉ አቶ አለበል ቢልልኝ መሆኑን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በቤት ቁጥር 04/02 የሚታወቀዉን ቤት የተከራየዉ አቶ አህመድ አደም መሆኑን አነዚህን ቤቶች ከሳሽና ተከሳሽ በስማችን የተከራየን ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን፤ ከሳሽ በተከሳሽ ስም ወይም በከሳሽ በእራሳቸዉ ስም የንግድ ስራዉ ሲሰራ የነበረ መሆኑን፤ ከሳሽ ስራዉ ተሰርቷል በማለት ለገለጹት ጊዜያት ግብር በከሳሽ ወይም በተከሳሽ ስለመከፈሉ የሚያስረዳ ማስረጃ ያላቀረቡ መሆኑን ሂሳብ ይጣራልኝ ብለዉ የጠየቁትም በሌለ ማህበር መሆኑን ከከሳሽ በጋራ የዉርስ ሀብት የሚያስተዳድሩ በመሆኑ የጋራ ሂሳቦች የነበራቸዉ መሆኑን ከሳሽም ከተከሳሽ ጋር ያላቸዉን የጋራ ሂሳብ በመጥቅስ የአሽሙር የሽርክና ማህበር አቋቁመናል በማለት ያቀረቡት ክስ አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዉ የከሳሽ ክስ ከበቂ ወጪና ኪሳራ ጋር ውድቅ እንዲደረግላቸዉ ጠይቋል፡፡
ተከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፤ የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ/ም ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡ የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ጭብጥ ከለየ በኃላ የግራ ቀኙን ምስክሮች ሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ከሳሽና ተከሳሽ በሽርክና አብረዉ ለመስራት በ2007 ዓ/ም ስምምነተ ያደረጉ መሆኑን በዚህ ስምምነት መነሻነትም ከሳሽ በአራት ኪሎ በተለምዶ ብርሃንና ስላም ተብሎ በሚታወቀዉ አከባቢ የንግድ ስራዉ የሚሰራበትን የንግድ ቤት በደላላ አፈላልገዉ ያገኙ መሆኑን የኪራይ ውልም የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ በተባሉት በአቶ አለበል ቢልልኝ ሰም ከአልጆ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህር የተፈጸመ መሆኑን፤ ከሳሽና ተከሳሽ በዚህ የንግድ ቤት ኤሮሼክ በሚል ስያሜ የጁስ ጭማቂ ንግድ በጋራ ሲሰሩ የነበረ መሆኑን፤ ይህንንም ስራ ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰሩ የነበረ መሆኑን፤ ስራዉን ለሁለት አመታት በሰላም ሲሰሩ የነበረ መሆኑን፤ በወቅቱ ለንግድ ስራዉ የከሳሽ ባለቤት እና የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል የሚያስፈልጉትን ግባዓቶች ሲያቀርቡ የነበረ መሆኑን፤ ከሳሽና ተከሳሽ የሚሰሩት ስራ ከዉርስ ሀብት ጋር ግንኙነት የሌለዉ መሆኑን ከሳሽና ተከሳሽ በየወሩ ሂሳብ እየተሳሰቡ ከንግድ ስራዉ የሚገኘዉን ትርፍ ሲከፋፈሉ የነበረ መሆኑን፤ ተከሳሽም ከሳሽ ቤት ከምትቀመጥ አብረን ልንሰራ ነዉ ብለዉ የነገሯቸዉ መሆኑን፤ ከሳሽም ተከሳሽም አብረዉ እየሰሩ የነበረ መሆኑን የነገሯቸዉ መሆኑን፤ ከሳሽ በንግድ ቤቱ ስራ ቦታ ላይ እየተገኙ ጁስ ሲፈጩ የነበር መሆኑን፤ የዚህ ንግድ ቤት ንግድ ፈቃድ የወጣዉ የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ በተባሉት በአቶ አለበል ቢሊልኝ ስም መሆኑን፤ ይህም ሊደረግ የቻለዉ ከሳሽ በስማቸዉ የመጋዘን የንግድ ፈቃድ ስለነበራቸዉ፤ ተከሳሽም በስማቸዉ ሌላ ንግድ ፈቃድ ስለነበራቸዉ፤ የከሳሽ ባለቤት የዘይት ንግድ ፈቃድ ስለነበራቸዉ በወቅቱ ሌላ አማራጭ ያልነበረ በመሆኑና በንግድ ፈቃድ ላይ ንግድ ፈቃድ መደረብ ባለመፈለጋቸዉ እና የተከሳሽ ባለቤት ተመሳሳይ የንግድ ስራ ሲሰራ ስለነበረ ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ የከሳሽ ባለቤት እና የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል ቢሊልኝ ተነጋግረዉ የንግድ ፈቃዱ በተከሳሽ ባለቤት ስም እንዲወጣ የተደረገ መሆኑን፤ ኤሮሼክ በተባለዉ ጁስ ቤት ላይ የከሳሽና የተከሳሽ ስልክ ቁጥሮች በማስታወቂያዉ ላይ ተለጥፎ የነበረ መሆኑን ከዚያም በከሳሽና በተከሳሽ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል የከሳሽን ስልክ ቁጥር ከንግድ ቤቱ ላይ ያነሱት መሆኑን፤ ለዚህ የጁስ ቤት ንግድ ስራ የሚያስፈልጉ ግባዓቶች ማከማቻ የሚሆን ሰቶር ከባሻ ወልዴ ችሎት የጋራ ህንጻ ባለቤቶች ኃ/የተ/የህ/ስራ ማህበር በከሳሽ ባለቤት ስም የተከራዩ መሆኑን፤ የከሳሽ ባለቤት ለጁስ ቤት የንግድ ስራዉ የሚያስፈልጉትን አታክልቶች ሲያቀርብ የነበረ መሆኑን፤ ከሳሽና ተከሳሽ ከንግድ ስራዉ የሚገኘዉን ገንዘብ በጋራ በቡና ባንክ በከፈቱት አካዉንት ገቢ ሲደረግ የነበረ መሆኑን፤ ለሰራተኞች እና ግብር የሚከፈለዉ ክፍያ በተከሳሽ ባለቤት የሚከፈል ቢሆንም ገንዘቡ የሚከፈለዉ ከከሳሽና ተከሳሽ የጋራ አካዉንት ዉስጥ ወጪ ተደርጎ መሆኑን ከሳሽና ተከሳሽ የንግድ ስራዉን ለመስራት እያንዳንዳቸዉ ብር 250,000 ያዋጡ መሆኑን በከሳሽና በተከሳሽ መካከል አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት ተሞክሮ ተከሳሽ በወቅቱ በእጇ ብር 120,000 የሚገኝ መሆኑን መግለፅዋን፤ የአመቱ ግብር ከተከፈለ በኃላ እንነጋገራለን ዞሮዞሮ የንግድ ፈቃዱ የተመዘገበዉ በባለቤቴ ስም ስለሆነ ከተከፈለ በኋላ እንጨርሰላን ብለዉ ከንግድ ስራዉ የተገኘዉን ትርፍ ለማካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ መሆኑን፤ ከዚያ ተከሳሽ ንግድ ፈቃዱ በባለቤቴ ስም ነዉ ያለዉ ብለዉ ከሳሽን ከንግድ ስራዉ ያሰናበቱ መሆኑን፤ ተከሳሽና አቶ አለበል ከ2004/5 ዓ/ም ጀምሮ አብረዉ ሲኖሩ የነበረ መሆኑን፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ሁለት ልጆች አፍርተዋል፤ አንዱ ልጅ የሁለት አመት አንዱ ደግሞ የስድስት ወር መሆኑን፤ ተከሳሽና አቶ አለበል ይህ የንግድ ስራ መሰራት ሲጀምርም አብረዉ ሲኖሩ የነበር፤ የንግድ ስራዉ የሚሰራበትን ፍሪጅ፣ ጄኔረተር በተከሳሽ ባለቤት ስም የገዙ መሆኑን፤ የከሳሽ ባለቤት ለጁስ ቤቱ ስራ ሰራተኞች ሲቀጥሩ የነበረ መሆኑን የንግድ ስራዉን ሲሰሩ ነበር የከሳሽ ባለቤት እና የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል ከሳሽና ተከሳሽ እንዳይጣሉ በሚል በእናት ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ የጋራ አካዉንት የከፈቱ መሆኑን በዚህ የባንክ አካዉንትም ገንዘብ ገቢ ሲደረግ የነበረ መሆኑን መስክረዋል፡፡
በተከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች በበኩላቸዉ በሰጡት የምስክርነት ቃል በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በቤት ቁጥር 884(ሐ) በሚታወቀዉ የንግድ ቤት ዉስጥ የንግድ ስራ የሚሰራዉ የተከሳሽ ባለቤት ነዉ የተባለዉ አቶ አለበል መሆኑን፤ ይህንንም የንግድ ቤት አቶ አለበል የከፈተዉ ከአቶ ይታያል ጌትነት ብር 200,000 ተብድሮ መሆኑን፤ ከአባዳሪዉ ጋርም በጹሁፍ የተደረገ የብድር ውል የሌላቸዉ መሆኑን፤ የኪራይ ውሉን አቶ አለበል ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ/ም ከአልጆ ቢዘነስ ሴንተር ጋር የፈጸሙ መሆኑን፤ ቤቱን ለሁለት አመት ከዘጠኝ ወር የተከራየ መሆኑን፤ አቶ አለበል ይህን የንግድ ቤት ሲያገኙ ተከሳሽን ጠርተዉ ተከሳሽ ምስክር የነበሩ መሆኑን፤ ቤቱን ከተከራዩ በኋላ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ገዝተዉ ሰራተኛ ቀጥረዉ ቤቱን ያሳደሱ መሆኑን የቤቱን ንግድ ፈቃድም በአቶ አለበል ቢልልኝ ስም የወጣ መሆኑን፤ ይህ ንግድ ፈቃድም አቶ አለበል ቦሌ ከሚገኘዉ የንግድ ቤቱ ፈቃድ ጋር ያጣመረዉ መሆኑን የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል በቦሌ ክፍል ከተማ ጃክሮስ ጋር የጁስ ቤት ያላቸዉ መሆኑን፤ ከዚህኛዉ ጁስ ቤት የእርሳቸዉ ሰራተኞች እየመጡ ሲሰሩ ነበር፤ እዚያ የነበሩትን ዋና ዋና እቃዎች አዲስ ወደ ተከፈተዉ አራት ኪሎ ወደ ሚገኘዉ ኤሮሼክ ጁስ ቤት ያመጡ መሆኑን፤ የቤቱ ዕድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ አለበል ጥቅምት 2008 ዓ/ም ካሽ ሬጅስተር በስማቸዉ አውጥተዉ ስራ የጀመሩ መሆኑን፤ የእራሳቸዉ የሂሳብ ሰራተኛ ነበራቸዉ፣ የስራ ልምድም ስለነበራቸዉ ከማንም እርዳታ ያልጠየቁ መሆኑን ሰራተኛ ሲቀጥሩ የነበሩት አቶ አለበል ናቸዉ፤ አቶ አለበል ተከሳሽ አርግዛ ለመዉለድ ሁለት ወር ሲቀራት በ2009 ዓ/ም ከተከሳሽ ጋር አብረዉ መኖር የጀመሩ መሆኑን፤ ክርክር የተነሳበት የንግድ ቤት ተከሳሽን የማይመለከት መሆኑን በዚህ ንግድ ቤት ላይም ስራ የማይሰሩ መሆኑን፤ በስራ ቦታ ላይም ከአቶ አለበል ውጭ ማንም ሰዉ ያላዩ መሆኑን፤ የንግድ ቤቱ የኪራይ ውል በአቶ አለበል ስም መሆኑን፤ በንግድ ቤቱ ማሰታወቂያ ላይ የተለጠፉትን ስልኮች ለአቶ አለበል የሰጡት ተከሳሽ መሆናቸዉን አቶ አለበልም በነዚህ ስልኮች ሲደውሉ ተከሳሽን ያገኙ የነበረ መሆኑን፤ ለንግድ ቤቱ አትክልቶች ደውለዉ ሲያሰቀርቡ የነበረ መሆኑን፤ አስፈላጊ በሆነ ጊዜም አቶ አለበል እራሳቸዉ አትክልት ተራ ሄደዉ የሚገዙ መሆኑን፤ የአታክልት ማስቀመጫ ስቶር ተቸግረዉ ተከሳሽ እህቴ የተከራየችዉ ንግድ ፈቃድ ሊወጣበት የማይችል ኮንዶሚኒዬም ቤት አለ ከፈለክ እሱን ተጠቀምበት በማለቷ አቶ አለበል እሺ ብለዉ የከሳሽ ባለቤት የተከራዩትን የኮንዶሚኒዬም ቤት ለአታክልት ማከማቻና ለሰራተኛ ማደሪያ ሲጠቀሙበት የነበረ መሆኑን የከሳሽ ባለቤት የከፈሉትንም የሁለት ወር ብር 17,000 የኪራይ ገንዘብ ተመላሽ ያደረጉ መሆኑን፤ ከንግድ ቤቱ ላይ የሚፈለጉት ክፍያዎች አቶ አለበል ከእራሳቸዉ ገንዘብ ሲከፍሉ እንደነበር የንግድ ስራዉን ለማስራት አቶ አለበል ከማንም ሰዉ ጋር የሽርክና ውል ያልፈጸሙ መሆኑን፤ ተከሳሽ አቶ አለበል የንግድ ቤቱን ሲከራይ ለቤቱ ኪራይ ክፍያ እንዲሆን ቼክ የሰጧቸዉ መሆኑን መስክረዋል፡፡
የግራ ቀኙ ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል በአጭሩ ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል እኛም በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የተቋቋመ የአሽሙር የሽርክና ማህበር አለ ወይስ የለም? አለ ከተባለስ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባ? የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ ይገባል ወይስ አይገባም? እንዲሁም ከሳሽ ከሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ አልተከፈለኝም የሚሉትን የትርፍ ክፍያ ከሰዉ የመጠየቅ መብታቸዉ ሊጠበቅ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ነጥቦች ምላሽ የሚሹ ነጥቦች ናቸዉ:: ፍርድ ቤቱም ከዚህ እንደሚከተለዉ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ለመጀመሪያዉ ነጥብ ምላሽ ለመስጠት የአሽሙር የሽርክና ማህበር ባህሪያትን መመለከት ጠቃሚ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር የአሽሙር ማህበር ለመመስረት ማህበርተኞቹ የንግድ ስራን ለመሰራት ሰምምነት ማድረግ ያለባቸዉ መሆኑን፤ ማህበረተኞቹ ስምምነታቸዉን በጽሁፍ ወይም በቃል ሊያደረጉት አንደሚችሉ፤ ይህ ስምምነትም በግልጽ የተደረገ (express) ወይም ከተግባርና ከድርጊት ሊገለጥ የሚችል (implied) መሆኑን፤ ይህን አይነት የንግድ ማህብር ለማቋቋም በህግ ተለይቶ የተቀመጠ ፎርም (formality) የማያሰፈልግ መሆኑን፤ የማህበሩ አባላትም ከንግድ ስራዉ የሚገኘዉን ትርፍና ኪሳራ የሚከፋፈሉት በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት መሆኑን፤ ማህበረቶቹ በማህበሩ አመራር እና ቁጥጥር ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ መሆኑን፤ ይህ አይነት ማህበር የራሱ ህጋዊ ሰዉነት የሌለዉ መሆኑን ማህበሩም ሚስጥራዊ (secrecy nature of joint venture) መሆኑ፤ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ብቻ ለሶሰተኛ ወገኖች ሊታወቅ የሚችል መሆኑና አባላቱ የማይታወቁ መሆኑን ማህበርተኞቹ ለማህበሩ በአይነቱ፤ በጉልበት፤ በሙያ እና በገንዘብ መዋጮ ሊያደርጉ እንዲሚችሉ እንዲሁም እያንዳንዱ የማህበሩ አባል ከ3ኛ ወገኖች ጋር በሚያደርገዉ ግንኙነት/ግብይት በእራሱ ስም ማድረግ አለበት፡፡ ከላይ የተገለጹትን የአሽሙር የሽርክና ማህበር ባህሪያት በንግድ ህጉ ስለ ንግድ ማህበራት የተደነገጉት አግባብነት ያላቸዉ ጠቅላላ ድንጋጌዎች እንዲሁም በንግድ ህጉ ከአንቀጽ 271-279 በተደነገጉት ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቷል፡፡
ከላይ ከተገለጹት የአሽሙር የሽርክና ማህበር ባህሪያት አንፃር የተያዘዉን ጉዳይ ስንመለከተ ከሳሽ ከተከሳሽ ጋር ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ኢሮሼክ ጁስ ቤት በመክፈት በጋራ ሲሰሩ የነበረ መሆኑን፤ ከሳሽ በዚህ የጁስ ቤት ዉስጥ መዋጮ አዋጥተዉ በጉልበትም ጭምር ማህበሩን ሲያግዙ የነበረ መሆኑን፤ የከሳሽ ባለቤት በማህበሩ ዉስጥ ሲሰሩ የነበረ መሆኑን፤ ለማህበሩም ስራ አታክልት ሲያቀርቡ የነበረ መሆኑን፤ የንግድ ቤቱ ንግድ ፈቃድ በአቶ አለበል ስም እንዲወጣ የተደረገዉ ከሳሽ፤ ተከሳሽ፤ የከሳሽ ባለቤትና አቶ አለበል ባደረጉት ስምምነተ መሰረት መሆኑ መመስከሩ ሲታይ ይህም የምስክርነት ቃልም የተሰጠዉ ለከሳሽና ተከሳሽ በእኩል ደረጃ ዝምድና ያላቸዉ ምስክሮች መሆናቸዉ ሲታይ በጁስ ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የከሳሽና የተከሳሽ ስልክ ቁጥር የነበረ መሆኑ፤ ለማህበሩ የሚያሰፈልጉት አታክልቶች የከሳሽ ባለቤት በስሙ በተከራይዉ ኮንዶሚኒዬም ቤት ዉስጥ ሲቀመጥ የነበረ መሆኑ፤ ከሳሽና ተከሳሽ በቡና ኢንትርናሽናል ባንክ በሂሳብ ቁጥር 1019501009436 የሚታወቀዉን ሂሳብ በጋራ የከፈቱ መሆኑና ይህ የሂሳብ ቁጥር የተከፈተዉ ለሌላ አላማ መሆኑ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩ ሲታይ፤ በዚህ አካዉንትም ከንግድ ስራዉ የተገኘዉ ገንዘብ ገቢ ሲደረግበት የነበረ መሆኑና የአትክልት ማከማቸዉ የኪራይ ውል የተፈጸመዉ በከሳሽ ባለቤት ስም መሆኑ ሲታይና አቶ አለበል በዚህ የአታክልት ማከማቻ ቤት ዉስጥ ሲጠቀሙ የነበረ መሆኑ እንዲሁም የከሳሽ ባለቤትና የተከሳሽ ባለቤት ናቸዉ የተባሉት አቶ አለበል በእናት ባንክ በሂሳብ ቁጥር 0031105814013001 የሚታወቅ የጋራ ሂሳብ ቁጥር መክፈታቸዉ፤ ይህ የሂሳብ ቁጥር የተከፈተበት ዓላማ ለክርክሩ መነሻ ከሆነዉ የጁስ ቤት ጋር የማይገናኝ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩ እንዲሁም ተከሳሽ ከአቶ አለበል ጋር ከ2004/5 ዓ/ም ጀምሮ አብረዉ መኖራቸዉ ሲታይ በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የአሽመር የሽርክና ማህብር የተመሰረተ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡
በተከሳሽ በኩል የቀረቡት 1ኛ ምስክር አቶ አለበል በሰጡት የምስክርነት ቃል ለክርክር መነሻ የሆነዉ የንግድ ቤት የኔ ነዉ በማለት የምስክርነት ቃላቸዉን ሰጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምስክሩ ክርክር የተነሳበት የንግድ ቤት የእርሱ ስለመሆኑ ክርክሩ መኖሩን አያወቀ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበዉ አቤቱታ የለም፡፡ ምስክሩ ከተከሳሽ ጋር መቼ የፍቅር ግንኙነት እንደጀመረ ተጠይቆ አላስታውስም በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን የከሳሽን ስልክ ቁጥር ለምን በጁስ ቤቱ እንደለጠፈ ሲጠየቅ ተከሳሽ ቁጥሮቹን ሰጥታዉ ጁስ ቤቱ ላይ የለጠፈ መሆኑን፤ ቁጥሩንም የማያውቀዉ መሆኑን በመሰቀልኛ ጥያቄ ወቅት መመስከሩ ሲታይ አንድ ሰዉ የንግድ ስራዉ ቤት ላይ የማያወቀዉን ስልክ ይለጥፋል ተብሎ የሚገመት ባለመሆኑ ምስክርነቱ እምነት የሚጣልበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ የንግድ ቤት ኪራይ ውል በአቶ አለበል ስም የተፈጸመና በውሉ ላይም ክፍያዉን የከፈለችዉ ተከሳሽ በቼክ መሆኑን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ ቀርቦ ሳለ ለንግድ ቤቱ ኪራይ የከፈልኩት ከ2ኛ ምስክር በተበደርኩት ገንዘብ ነዉ በማለት መመስከሩ ሲታይ፤ የከሳሽ ባለቤት የተከራየዉን የኮንዶሚኒዬም ቤት ለአታክልት ማከማቻነት መጠቀሙን መስክሮ እያለ ከመቼ ጀምሮ ሲጠቀም እንደነበረ ሲጠየቅ አላስታውስም ማለቱ ሲታይ፤ ከከሳሽ ባለቤት ጋር በእናት ባንክ በጋራ የከፈቱት አካዉንት መኖሩን የሚያስረዳ ማስረጃ ቀርቦ እያለ ምስክሩ የከሳሽ ባልነዉ አካዉንቱን ከፍቶ የሰጠኝ ማለቱ ሲታይ እንዲሁም ከከሳሽ ጋር የተዋወቅነዉ አንድ ፍርድ ቤት ተገናኝተን ነዉ በማለት ከመሰከረ በኃላ በአናት ባንክ በሁለቱ ስም የተከፈተዉ አካዉንት ከጁስ ቤቱ ጋር የማይገናኝ ሌላ ስራ ለመስራት ነዉ አካዉንቱን የከፈትነዉ ማለቱ ሲታይ የሰጠዉ የምስክርነት ቃል እምነት የሚጣልበት የምስክርነት ቃል ሆኖ ፍርድ ቤቱ አላገኘዉም፡፡
2ኛ የተከሳሽ ምስክርም በዋና ጥያቄ ሲጠይቅ የሚሰራዉ የኮምፒዩትተር አክሰሰሪ ሽያጭ መሆኑን ሲመሰክር ፍርድ ቤቱ ባቀረበዉ የማጣሪያ ጥያቄ ደግሞ በኢሜል የኮንስልቲንግ አግልግሎት የሚሰጥ መሆኑን፤ ንግድ ፈቃድ እንደሌለዉ ግብር የማይከፍል መሆኑን፤ መስክረዋል፡፡ ይሁ ምስክር በሌላ ቀን ከመዝገቡ ጋር የተከሳሽን የማጠቃላያ ሃሳብ ለማያያዝ የጠበቃዉ ረዳት ነኝ በማለት መቅረቡ ሲታይ ምስክሩ የሰጠዉ ቃል እርስ በራሱ የሚምታታ መሆኑን ለአቶ አለበልም ብር 200,000 ለማበደር በሚያስችል ቁመና ላይ የማይገኝ መሆኑን እንዲሁም ምስክሩ ክርክር የተነሳበትን የንግድ መደብር ሙሉን አድራሻ ለችሎቱ ሲገልጽ እስራበታለሁ በማለት ለችሎቱ የገለጸዉን የንግድ ቤት አድራሻ ሲጠየቅ የማያውቁ መሆኑን መስክረዋል፡፡ ይህ የምስክርነነት ቃል ሲታይ ምስክሩ በጥናት ላይ ተመስርቶ የምስክርነት ቃሉን የሰጠ መሆኑን እና እምነት ሊጣልበት የሚችል የምስክርነት ቃል ያልሰጠ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ቀሪዎቹ የተከሳሽ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት አቶ አለበል ቀጥሮ በንግድ ቤቱ ሲያሰራቸዉ የነበረ መሆኑን እንዲሁም በከሳሽና በተከሳሽ መካከል የሽርክና ውል ይኑር አይኑር የማያውቁ መሆኑን መስክረዋል፡፡ የነዚህ ምስክሮችም ቃል ሲታይ አነነዚህ ምስክሮች በአሁኑ ሰዓትም በአቶ አለበል ቀጣሪነት የሚተዳደሩ መሆኑ ገልልተኛ ምስክርነት ለመስጠት ጫና ያለባቸዉ መሆኑ፤ ማህበሩ ህጋዊ ሰዉነት የሌለዉ መሆኑ፤ ማህበሩ ለሶስተኛ ወገኖች ሚሰጥር መሆኑ እና አባላቱም ለሶሰተኛ ወገኖች መታወቅ የሌለባቸዉ መሆኑ ሲታይ እነዚህ ምስክሮች የቀጠሩትና ደመዉዝ የተከፈላቸዉ በአቶ አለበል መሆኑ የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም፡፡ በከሳሽ ምስክሮች መኖሩ የተረጋገጠዉን የአሽሙር የሽርክና ማህበርም የለም ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ አይደለም፡፡
ተከሳሽ የሚከራከሩት በተከሳሽ ስም የወጣ ንግድ ፈቃድ የለም፤ የአሽመር የሽርክና ማህብር አለ ለማለት የንግድ ስራዉ የግድ ከተሻራኪዎቹ በአንዱ ስም ሊሰራ ይገባል፤ ክርክር የቀረበበት የጁስ ቤት ንግድ ፈቃድ በተከሳሽ ስም የተመዘገበ አይደለም የንግድ ፈቃዱ የወጣዉ በአቶ አለበል ቢልልኝ ስም ነዉ፤ ግብርም የሰራተኛ ደመዉዝም ሲከፍል የነበረዉ በአቶ አለበል ስም ነዉ በማለት ክርክር አቅርበዋል፡፡ ለዚህም በዋቢነት የጠቀሱት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 76394 የሰጣዉን የህግ ትርጉም በመጥቀስ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ የአሽሙር የሽርክና ማህበር በባህሪው ሚስጥራዊ በመሆኑ አባላቱም ለሶስተኛ ወገኖች መታወቅ የሌለባቸዉ በመሆኑና በዚህ አይነት ማህበር ዉስጥ ተሳትፎ የሚያደረጉ ማህበርተኞች በተለያዩ ምክንያቶች በስማቸዉ የንግድ ፈቃድ ማውጣት የማይፈልጉ በመሆኑ ማህበሩ የንግድ ስራዉን የሚሰራበት ንግድ ፈቃድ የግድ በተሻራኪዎቹ ስም እንዲወጣ የሚያስገድድ ህግ የለም፡፡ በንግድ ህጉም በዚህ መልኩ የተቀመጠ ድንጋጌ የለም፡፡ አስፈላጊዉ ጉዳይ ማህበርተኞቹ በቃል ወይንም በጽሁፍ ባደረጉት ስምምነት የንግድ ፈቃዱ በተከሳሽ ባለቤት በአቶ አለበል ስም እንዲወጣ መስማማታቸዉ እና በስምምነታቸዉ መሰረት ተገቢዉን መዋጮ አድርገዉ ስራዉን በትብብር መስራታቸዉ ነዉ፡፡ ግራ ቀኙ ይህን ስለማደረጋቸዉም በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች አስረድቷል፡፡
ተከሳሽ የጠቀሱት የሰበር ችሎቱ ዉሳኔ ሲታይ ዉሳኔ የተሰጠዉ ማህበርተኞቹ የሽርክና ውል አድርገዉ ከሁለት ማህበርተኞች መካከል በአንዱ ማህበርተኛ ስም የንግድ ፈቃድ በማዉጣት ሲሰሩ የቆዩ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ በሁለቱ ማህበርተኞች መካከል የተመሰረተ የአሽሙር የሽርክና ማህብር የለም ተብሎ በመወሰኑ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ሰበር ችሎቱም በአንዱ ተሻራኪ ስም የንግድ ፈቃድ ወጥቶ በጋራ መስራታቸዉ በመረጋገጡ የአሽሙር ሽርክና ማህብር አለ በማለት ወሰኗል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዉሳኔ ላይ አሽሙር የሽርክና ማህበር የሚሰራበት ንግድ ፈቃድ ሁሌም ቢሆንም ከአባላቱ በአንዱ ስም የንግድ ፈቃድ ሊወጣ ይገባል በሚል ድምዳሜ የተሰጠበት አይደለም ፡፡ ተጠቃሹ የሰበር ዉሳኔም አስገዳጅነት የሚኖረዉ በተመሳሳይ የፍሬ ነገር እና የህግ ክርክር ሲቀርብ በመሆኑ እና በዚህ መዝገብ የቀረበዉ ፍሬ ነገር በተጠቃሹ የሰበር ዉሳኔ ላይ ከተገለጸዉ ፍሬ ነገር የተለየ ስለሆነ በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) መሰረት አስገዳጅነት የለዉም፡፡ በተመሳሳይ ከሳሽ የጠቀሱት የሰበር መዝገብ ቁጥር 46358 ለተያዘዉ ጉዳይ አግባብነት የለዉም፡፡
በንግድ ቤቱም ግብርና ደመዉዝ ሲከፈሉ የነበሩት አቶ አለበል ነው፡፡ እንዲሁም ሰራተኞች ሲቀጥር የነበረዉ እርሱ ነዉ በመሆኑም የንግድ ስራዉ የተከሳሽና የከሳሽ አይደለም የአቶ አለበል ነዉ በሚል የቀረበዉን ክርክርም በተመለከተ አቶ አለበል በዚህ መዝገብ ክርከሩ መኖሩን እያወቁ ድርጅቱ የእኔ ነዉ በሚል መብታቸዉን ለማስከበር ያቀረቡት አቤቱታ የለም የቀረቡትም ለተከሳሽ በምስክርነት ነዉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአሽሙር የሽርክና ማህበር ህጋዊ ሰዉነት የሌለዉ እንደመሆኑ መጠን በራሱ ውል ሊዋውል አይችልም ይህ ከሆነ ደግሞ ማህበሩ ህጋዊ ዉጤት ያላቸዉን ተግባራት (juridical act) በራሱ ስም መከወን አይችልም፡፡ ስራዉን በአብዛኛዉ የሚያከናውነዉም ለሶሰተኛ ወገኖች ግልጽ በሆኑ የንግድ ፈቃዱ በስሙ በተመዘገበዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር አቶ አለበል ሰራተኛ መቅጠራቸዉ፤ ደመዉዝና ግብር በራሳቸዉ ስም መክፈላቸዉ ክርክር ያስነሳዉ ድርጅት የእርሳቸዉ ነዉ የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ አይደለም ይልቁንም ማህበሩ ለሶሰተኛ ወገኖች መኖሩ የማይታወቅ በመሆኑ እና ህጋዊ ሰዉነት የሌለዉ ማህበር መሆኑ ሲታይ አቶ አለበል ቢልልኝ ለማህበሩ ሰራተኞች የሚከፍሉት ደመውዝ እና የግብር ወጪ በታክስ ክፍያ ወቅት በወጪነት እንዲያዝ ታስቦ ነዉ ከሚባል በቀር በከሳሽና ተከሳሽ መካከል የተመሰረተ የአሽሙር የሽርክና ማህበር የለም የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም በከሳሽና በተከሳሽ መካከል የአሽሙር የሽርክና ማህብር ተመስርቷል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ በግራ ቀኙ መካከል ያለዉ ግኑነት የሻከረ መሆኑን ተከሳሽ ክዶ ያቀረበዉ ክርክር የለም ግራ ቀኙ ያቋቋሙት ማህበር የአሽሙር ማህበር ከመሆኑ አኳያም ሲታይ ስለ ሽርክና ማኅበሮች በወጣው ህግ ጠቅላላ መሰረታዊ ሃሳቦች የሚመራ መሆኑ በንግድ ህግ ቁጥር 271 ላይ ስለተመለከተና የሽርክና ማኅበሮች የሚቋቋሙት በማህበርተኞቹ ማንነት ላይ በመመስረት ስራውን ለመስራት ስለሆነ በሽርክና ተዋዋዮች መሃል ያለው ግንኙነት መሻከሩ በሚታይበትና ሁኔታ ማህበሩ እንዲቀጥል ማድረጉ ተገቢነት ስለሌለው ማህበሩን ለማፍረስ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው ምክንያት በቂ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ከሳሽና ተከሳሽ የተቋቋመው የአሽሙር ማህበር በንግድ ህጉ ቁጥር 278(1) እንዲሁም 218(1) እና (2) መሰረት እንዲፈርስ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
3ኛዉን ነጥብ በተመለከተ በከሳሽና በተከሳሽ የተመሰረተዉ የአሽሙር ማህበር እንዲፈርስ ከላይ ዉሳኔ የተሰጠ ስለሆነ እንዲህ አይነት ዉሳኔ ሲሰጥ የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራ አብሮ መወሰን ያለበት መሆኑን የፍ/ሥ/ሥ/ቁ/ 188 እና 189 የሚያስረዱ ስለሆነ የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
4ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ የጠየቁት ከሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ ያልተከፈላቸዉን የትርፍ ክፍያ ክስ አቅርበዉ የመጠየቅ መብታቸዉ እንዲጠበቅ ሲሆን ከሳሽ የማህበሩ ሂሳብ ሳይጣራ የሚገባቸዉን ትርፍ ማወቅ የማይችሉ መሆኑ ገልጽ ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የከሳሽን ክስ የማቅርብ መብት ለመጠበቅ ሂሳቡ አለመጣራቱ በቂ ምክንያት ስለሆነ ከሳሽ ያልተከፈላቸዉን ትርፍ በተመለከተ ክስ የማቅርብ መብታቸዉ ተጠብቋል፡፡
ውሳኔ
- በከሳሽና ተከሳሽ መሃል የተቋቋመው የአሽሙር ማህበር እንዲፈርስ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
- ሬጅስትራር ሂሳብ አጣሪ እንዲመድብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ አጣሪው ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ አጣርተው ሪፖርት ለፍርድ ቤት ያቅርቡ፡፡ ትዕዛዙ ይድረሳቸው፡፡
- በዚህ መዝገብ 2ኛ የተከሳሽ ምስክር ሆነዉ የተሰሙት አቶ ይታያል ጌትነት በችሎት ቀርበዉ የምስክርነት ቃላቸዉን ሲሰጡ ስራቸዉ የኮምፒዩተር አክሰሰሪ ሽያጭና ኮንሰልቲንግ ሰርቪስ መሆኑን ገልጸዉ የምስክርነት ቃላቸዉን ሰጥተዉ በቀን 5/4/2011 ዓ/ም ደግሞ ቀርበዉ የተከሳሽ ጠበቃ ረዳት ነኝ በማለት የማጠቃላያ ሀሳብ ከመዝገቡ ጋር ለማያያዝ በችሎት ቀርቧል፡፡ ይህም በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ምስክሩ የሰጡት የምስክርነት ቃል የሀሰት ምስክርነት ሊሆን እንደሚችል የገመተ ስለሆነ በወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸዉ እንደሚገባ ችሎቱ አምኗል፡፡ በመሆኑም የአራዳ ክፍል ከተማ ፖሊስ መመሪያ በምስክሩ ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲያካሂድ ታዟል፡፡ በፍርድ ቤቱ ፖስተኛ በኩል ይህ ትዕዛዝ ይላክ፡፡
- ከሳሽ ከሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ ያልተከፈላቸዉ የትርፍ ክፍያ ካለ ክስ አቅርበዉ የመጠየቅ መብታቸዉ ተጠብቋል፡፡
- ከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡ መዝገቡ አልባት ስላገኘ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡