የኮ/መ/ቁ 275909

ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም

በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት

የልደታ ምድብ 6ኛ ፍ/ብሔር ንግድ ችሎት

                   ዳኛ፡- ዮሓንስ አፈወርቅ

አመልካች፡- ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር - ጠበቃ ስንታየሁ ዘለቀ - ቀረቡ

ተጠሪ፡- ዛሚ ፐብሊክ ኮኒክሽን ኃላ/የተ/የግ/ማህበር - ጠበቃ ደረሰ በዛወርቅ - ቀረቡ

        መዝገቡ ተመርምሮ ቀጥሎ የተመለከተው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

      አመልካች ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ የክስ አቤቱታ አመልካች እና ተጠሪ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረጉት የሽያጭ ውል ሥምምነት አመልካች ከተጠሪ ላይ 90.7 የዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ ደርጅትን ለመግዛት የውል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዚህ የሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት አመልካች ለተጠሪ ከሽያጭ ክፍያው ላይ የመጀመሪያውን ከፍያ ብር 5,000,000.00 (አምስት ሚሊዮን ብር) በጨየክ እና በጥሬ ውሉ በሚፈረምበት ቀን ለተጠሪ ከፍሏል፡፡ አመልካች በገባው ውል መሰረት ግዴታውን የተወጣ ቢሆንም ተጠሪ በውሉ አንቀጽ 5፤ 6፤ እና 8 መሰረት መፈጸም ያለበትን ግዴታ አልፈጸመም፡፡ ተጠሪ በገባው የውል ግዴታ መሰረት እንዲፈጽም በተደጋጋሚ በቃልና በጽሑፍ ቢጠየቅም ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ የተጠሪ ባለ አክስዮኖች በውሉ አንቀጽ 5(2) መሰረት ቃለ ጉባኤ በመያዝ አመልካችን ወይም የአመልካችን ተወካይ የራዲዮ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አድርገው መሽም ሲገባቸው ይህን አላደረጉም፡፡ የሚፈለገውን የግብር ዕዳ በመክፈል ክሊራንስ ለማውጣት እና የስም ዝውውሩን ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲኖርባቸው ድርጅቱ ኦዲት እንዲደረግ ማድረግ ሲገባው ይህን አላደረገም፡፡ ስለሆነም ተጠሪ ከአመልካች ጋር በገባው የውል ስምምነት መሰረት ባለመፈጸሙ ምክንያት በመካከላችን አለመግባባት የተፈጠረ በመሆኑ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወስን በውሉ አንቀጽ 10(2) መሰረት አመልካች አና ተጠሪ የየበኩላቸውን ገላጋይ ዳኛ እንዲመርጡ ፤ተጠሪ የበኩሉን ገላጋይ ዳኛ ካልመረጠ በፍ/ቤት በኩል ገላጋይ ዳኛው እንዲሾም እንዲሁም በግራ ቀኙ በኩል የሚመረጡት ገላጋይ ዳኞች በስምምነት ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛውን መምረጥ ካልቻሉ በፍ/ቤቱ በኩል ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛ ተመርጦ የግልግል ዳኝነት ጉባኤ አንዲቋቋም እንዲሁም ተጠሪ በገባው ግዴታ መሰረት ባለመፈጸሙ ምክንያት ክስ ያቀረብን በመሆኑ በዚህ ክስ ምክንያት ያወጣነውን የዳኝነት ክፍያ ፤ የጠበቃ አበል እና ሌሎች ወጭዎችን እንዲተኩ እንዲወሰንልን በማለት አመልክተዋል፡፡

     በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዘው የምስክሮችን ሥም ጠቅሰው አቅርበዋል፡፡

      ተጠሪ በበኩሉ ሰኔ 10 ቀን 2011ዓ.ም. ዓ.ም ባቀረበው መልስ አመልካች ያቀረበው ክስ የግልግል ዳኝነት ስርአት ሊከተለው የሚገባውን ልምድ እና አሰራር ሳይከተል ያቀረበው ነው፡፡ አመልካች በራሱ በኩል የግልግል ዳኛ ሳይመርጥ የመረጠውን ዳኛ ለተከሳሽ ሳያሳውቅ ተከሳሽ እንቢተኛ ባልሆነበት ሁኔታ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ በሌላ በኩል አለመግባባት  የተከሰተ እንደሆነ የግልግል ሥርዓቱ በአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፍ ማህበራት የግልግል ተቋም ደንቦች መሰረት እንዲሁም ተዋዋዮች የተቋሙን የግልግል ደንቦች የመረጡት ከዳኞች አመራረጥ ጀምሮ ያለው ሂደት ያለመደበኛ ፍ/ቤት ጣልቃገብነት እንዲከናወን በመሆኑ አመልካች የውል ድንጋገየ እና የታወቀ አሰራር ሳይከተል ያቀረበው አቤቱታ አጋባብነት ስለሌለው ውድቅ እንዲደረግ ፤ አመልካች በመጀመሪያ የራሱን ገላጋይ ዳኛ መርጦ እንዲያሳውቅ ፤ የዳኛ ይሾምልን ጥያቄውን ለአዲሰ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ማቅረብ ይችላል ተብሎ አንዲወሰን፡፡ በአንዳች ምክንያት ጥያቄያችን ተቀባይነት ያላገኘ እንደሆነ በተጠሪ በኩል አቶ ገብረአምላክ ገብረጊዮርጊስን ገላጋይ ዳኛ አድርገን መርጠናል በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

      በመዝገቡ ላይ የቀረበው ክርክር ከላይ በአጭሩ የተመለከተውን ሲመስል ፍ/ቤቱም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወስን የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊቋቋም ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ መስርቶ ግራ ቀኙ ወገኖች ያቀረቡትን ክርክር እና ማስረጃ ከሕጉ አንጻር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምሯል፡፡

      አመልካች በዚህ መዝገብ ላይ ባቀረበው ክስ የሚጠይቀው ዳኝነት አመልካች እና ተጠሪ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረጉት የሽያጭ ውል ሥምምነት አመልካች ከተጠሪ ላይ 90.7 የዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ ደርጅትን ለመግዛት የውል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዚህ የሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት  ቃለ ጉባኤ በመያዝ አመልካችን ወይም የአመልካችን ተወካይ የራዲዮ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አድርገው መሾም ሲገባቸው አልሾሙም ፤ የሚፈለገውን የግብር ዕዳ በመክፈል ክሊራንስ ለማውጣት እና የስም ዝውውሩን ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲኖርባቸው ድርጅቱ ኦዲት እንዲደረግ ማድረግ ሲገባው ይህንንም አላደረጉም  ስለሆነም ተጠሪ ከአመልካች ጋር በገባው የውል ስምምነት መሰረት ባለመፈጸሙ ምክንያት በመካከላችን የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወስን የግልግል ዳኝነት ጉባኤ አንዲቋቋም ይወሰንልኝ በማለት ነው፡፡ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ታህሣሥ 26 ቀን 2011ዓ.ም. የተደረገ የዛሚ ሬድዮ ጣቢያ የሽያጭ ውል ስምምነት መኖሩ የታመነ ጉዳይ ነው፡፡ ማስረጃም ቀርቦበታል፡፡

     በመሰረቱ በሕግ አግባብ የተደረጉ ውሎች ማለትም በህግ ፊት የሚፀና ህጋዊ ውጤትን የሚያስከትል ውል ለመዋዋል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1678 ስር መሟላት አለባቸው ተብለው የተቀመጡትን መሥፈርቶች /Requirements/ በሙሉ ባሟላ መልኩ የተደረጉ ውሎች በተዋዋይ ወገኖች ላይ ሕግ ስለመሆኑ በፍ/ሕ/ቁ 1731/1/ ሥር ተመልክቷል፡፡ ተዋዋይ ወገኖችም በገቡት የውል ስምምነት  መሠረት ለመገዛት በየበኩላቸው መፈፀም ያለባቸውን ተግባራት የመፈፀም ግዴታ ያለባቸው ሲሆን አንደኛው ተዋዋይ ወገን በውሉ መሠረት መፈፀም ያለበትን ተግባር ሳይፈጽም ከቀረ ወይም ውሉን ካላከበረ ወይም ከጣሰ ሌላኛው ተዋዋይ ወገን ውሉን መሠረት በማድረግ ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በህግ የተቀመጠውን ወሠን ሳያልፍ ውሉን በመሠላቸው መዋዋል የሚችሉ ሲሆን ተዋዋይ ወገኖች በፍ/ብ/ህ/ቁ 3131 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ስር የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ በውሉ ላይ አስቀድመው ውሉን ተከትሎ በመካከላቸው አለመግባባት ቢፈጠር ይህ አለመግባባት በምን መልኩ ታይቶ መፈታት እና መወሠን እንዳለበት ካስቀመጡት በኃላ በመካከላቸው አለመግባባት ከተፈጠረ ይህ አለመግባባትና መፈታት ያለበት በውሉ ላይ በተቀመጠው የሙግት ወይም አለመግባባት መፈቻ መንገድ ሊሆን ይገባል፡፡

        ይሕ በእንዲህ እንዳለ በሰዎች /የተፈጥሮ ወይም በህግ የሰውነት መብት ያገኙ ድርጅቶች የንግድ ማህበሮች የመንግስት ተቋማት ወዘተ…/ መካከል የሚፈጠሩ ሙግቶች ወይም አለመግባባቶች በፍ/ቤት ወይም በሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን በተሠጠው አካል ወይም በአማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች ታይተው ሊወሠኑ ዋይም ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ተዋዋይ ወገኖች ባደረጉት ውል ላይ ውሉን ተከትሎ በመካከላቸው ወደፊት አለመግባባት ቢፈጠር ይህ አለመግባባት በአማራጭ የሙግት መፍቻ መንገድ ታይቶ መፈታት ወይም መወሠን እንዳለበት በመስማማት ካስቀመጡ በኃላ አለመግባባቱ ቢፈጠር ይህ አለመግባባት መታየት አና መፈታት ያለበት በውሉ ላይ በተቀመጠው አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገድ በመሆኑ አንደኛው ተዋዋይ ወገን አለመግባባት ተፈጥሯል የሚል ከሆነ ይህን ጥያቄ ማቅረብ ያለበት ውሉን መሠረት በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ በውሉ ላይ አለመግባባቱ ከአማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች አንዱ በሆነው በግልግል ዳኝነት ታይቶ መወሰን እንዳለበት ከተቀመጠ አለመግባባቱ በግልግል ዳኝነት ታይቶ መወሰን አለበት፡፡ በውሉ ላይ ገላጋይ ዳኛው ተመርጦ በግልጽ ካልተቀመጠ እና አንደኛው ተዋዋይ ወገን አለመግባባቱ በውሉ መሠረት በግልግል ዳኝነት ታይቶ እንዲወሠን ለማድረግ የበኩሉን የግልግል ዳኛ ካልመረጠ ሌላኛው ተዋዋይ ወገን የግልግል ዳኞች ጉባኤ እንዲሠየም ለፍ/ቤቱ ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል፡፡

      በዚሁ መሰረት አመልካች በግራቀኙ መካከል ታህሣሥ 26 ቀን 2011ዓ.ም. የተደረገውን ውል  ተከትሎ ተጠሪ በገባው የውል ግዴታ መሰረት መፈጸም ያለበትን ተግባር ባለመፈጸሙ ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን ገልጿል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ ክሱ የግልግል ዳኝነት ሥርዓት ሊከተለው የሚገባውን ልምድ እና አሰራር ሳይከተል የቀረበ ክስ ነው፡፡አለመግባባት  የተከሰተ እንደሆነ የግልግል ሥርዓቱ በአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፍ ማህበራት የግልግል ተቋም ደንቦች መሰረት እንዲሁም ተዋዋዮች የተቋሙን የግልግል ደንቦች የመረጡት ከዳኞች አመራረጥ ጀምሮ ያለው ሂደት ያለመደበኛ ፍ/ቤት ጣልቃገብነት እንዲከናወን ነው፡፡  ይሁን እንጂ በአንዳች ምክንያት ጥያቄያችን ተቀባይነት ያላገኘ እንደሆነ በተጠሪ በኩል አቶ ገብረአምላክ ገብረጊዮርጊስን ገላጋይ ዳኛ አድርገን መርጠናል የሚል ነው፡፡ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ታህሣሥ 26 ቀን 2011ዓ.ም. በተደረገው የዛሚ ሬድዮ ጣቢያ ድርጅት የሽያጭ ውል አንቀጽ 10 መሰረት አለመግባባት የተፈጠረ እንደሆነ በግልግል ዳኝነት ለመፍታት መስማማታቸውን እና በዚህ ስምምነት መሠረት የግልግል ጉባኤው በተዋዋይ ወገኖች በሚመረጥ አንድ አንድ ገላጋይ ዳኛ እና በሁለቱ ገላጋይ ዳኞች በሚመረጥ አንድ ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛ የሚሰይሙ ስለመሆኑ በግልጽ ተደንግጎ ሳለ ተጠሪ የግልግል ሥርዓቱ በአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፍ ማህበራት የግልግል ተቋም ደንቦች መሰረት እንዲሁም ተዋዋዮች የተቋሙን የግልግል ደንቦች የመረጡት ከዳኞች አመራረጥ ጀምሮ ያለው ሂደት ያለመደበኛ ፍ/ቤት ጣልቃገብነት እንዲከናወን በመሆኑ አመልካች የውል ድንጋገየ እና የታወቀ አሰራር ሳይከተል ያቀረበው አቤቱታ አጋባብነት ስለሌለው ውድቅ ይደረግልን በማለት ያቀረቡት ክርክር በግራ ቀኙ መካከል የተደረገውን ሥምምነት መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሚፈጠር አለመግባባት ደግሞ በገላጋይ ዳኞች ሊታይ እንደሚገባ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑ ካልተካደ አለመግባባቱን የሚፈታ የገላጋይ ዳኞች ጉባኤ እንዲቋቋም የማይደረግበት ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ታህሣሥ 26 ቀን 2011ዓ.ም. በተደረገው የዛሚ ሬድዮ ጣቢያ ድርጅት የሽያጭ ውልን ተከትሎ አለመግባባት የተፈጠረ እንደሆነ  የተፈጠረውን አለመግባባት የሚፈታ የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊሠየም ይገባል ተብሏል፡፡ በዚህ ረገድ በአመልካች በኩል አቶ ደሳለኝ በርሔን እንዲሁም በተጠሪ በኩል አቶ ገብረአምላክ ገብረጊዮርጊስን ገላጋይ ዳኛ አድርገው መርጠዋል፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ውሳኔ

  1. በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ታህሣሥ 26 ቀን 2011ዓ.ም. በተደረገው የዛሚ ሬድዮ ጣቢያ ድርጅት የሽያጭ ውል ስምምነትን ተከትሎ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወሰን የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊሰየም ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
  2. አመልካች እና ተጠሪ የየበኩላቸውን የግልግል ዳኛ የመረጡ በመሆኑ በአመልካች በኩል አቶ ደሳለኝ በርሔ እንዲሁም በተጠሪ በኩል አቶ ገብረአምላክ ገብረጊዮርጊስ ገላጋይ ዳኛ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
  3. በግራቀኙ በኩል የተመረጡት /የተሾሙት/ ገላጋይ ዳኞች በስምምነት ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛ ይምረጡ ተብሏል፡፡ ሆኖም ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛውን በስምምነት መምረጥ ካልቻሉ በአንደኛው ወገን አመልካችነት ሰብሳቢ ገላጋይ ዳኛ በፍ/ቤቱ ሬጅስትራር በኩል እንዲሾም ተብሏል፡፡
  4. በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት የወጣ ወጪና የደረሰ ኪሣራን ግራቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻቻሉ ተብሏል፡፡

 

ትዕዛዝ

  • የፍርዱ ቅጂ በማስረጃነት ይሰጥ ፡፡
  • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

                                                          የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡