- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 5623
የኮ/መ/ቁ 273280 - አቶ መስፍን ሽፈራው ዘለቀ እና አባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር
የኮ/መ/ቁ 273280
ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም
ዳኛ፡- አበበ ሰለሞን
ከሣሽ፡----- አቶ መስፍን ሽፈራው ዘለቀ
ተከሣሽ፡---- አባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ጉዳዩ ቃለ ጉባኤ እንዲሠረዝ የቀረበ ክስን የሚመለከት ሲሆን ከሣሽ በየካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረቡት የክስ መመስረቻ ጽሑፍ ከሣሽየተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ባለአክሲዮን ስሆን በሕዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ለአክሲዮን ማህበሩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በተፃፈደብዳቤ አክሲዮን ማህበሩ በመስራቾች ከተቋቋመ በኋላ አክሲዮን ለሕዝብ ሲሸጥ በንግድ ሕጉ መሠረት የተዘጋጀ መግለጫ ካለ፣ ከአክሲዮን ማህበሩ መመስረቻ ፅሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ጋር እንዲሰጠኝ፤የ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ የሚካሄደው የባለአክሲዮኖች መደበኛ እና ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የአክሲዮን ማህበሩ ዋና መስሪያ ቤት ከሚገኝበት አዲስ አበባ ከተማ ውጭ የሚደረግበት ምክንያት ስለሌለ ጉባኤዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲካሄዱ፣ ከሣሽም በጉባኤዎቹ ላይ ተገኝተውና የዳይሬክተሮችን ሪፖርት አዳምጠው ለመከራከርና ድምጽ ለመስጠት እንዲችሉ በንግድ ሕግ ቁጥር 417 መሰረት የጉባኤው አጀንዳዎች የዳይሬክተሮችና ተቆጣጣሪዎች ሪፖርት፣ የሂሳብ ሚዛን፣ የኪሣራና የትርፍ ሒሳብ፤ ጉባኤዎቹ ከሚካሄዱበት 15 ቀናት በፊት እንዲሰጠኝ እንዲሁም የሚካሄዱት የጉባኤዎቹ ቃለጉባኤዎች ረቂቅ ጉባዔዎቹ ከተካሄዱ በኋላ ሳይዘገይ እንዲሰጠኝጠይቄ የነበረ ቢሆንም አክሲዮን ማህበሩ ግን ከሣሽ እንዲሰጠኝ የጠየቅኳቸውን ሰነዶች ሊሰጠኝ ፍቃደኛ አልሆነም፡፡
የአክሲዮን ማህበሩ "ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ" በማለት ሕዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ምአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ አውጥቶ የአክሲዮን ማህበሩ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በብሉናይል ሆቴል እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም 8ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እና 9ኛ የባለአክሲዮኖች ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በባህር ዳር ከተማ በብሉናይል ሪዞርት ሆቴል ያካሄደ መሆኑን እና ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤው የማህበሩ ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሠረት እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ውሣኔ ያሣለፈ መሆኑን እና ከሣሽም በዚሁ ቀመር አንፃር በአክሲዮን ማህበር ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ ምክንያት በበጀት ዓመቱ በሚደርሳቸው የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ አክሲዮን እንድገዙ እና አክሲዮን ማህበሩ ያዘጋጀውን የአክሲዮን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ማሳወቂያ ፎርም እንዲፈርሙ አዲስ አበባ በሚገኘው የተከሣሽ ዋና መ/ቤት ነግረውኛል፡፡
የተከሣሽ ማህበር ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ያሳለፈው ውሣኔ የንግድ ሕጉን አስገዳጅ ድንጋጌዎች እና የማህበሩን መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ያላከበረ በመሆኑ ይኸው ውሣኔ እንዲሰረዝና መሰረዙም በ10 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ለከሣሽ በፅሑፍ እንዲገለፅላቸውከሣሽ በጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም ለተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም ተከሣሽ ሕጉን አክብሮ ውሳኔውን አልሰረዘም፡፡
ተከሣሽካፒታል አሳደግሁ ያለው በንግድ ሕግ ቁጥር 464(1) ሥር እንደተመለከተው አዲስ አክሲዮን በማውጣትና በንግድ ሕግ ቁጥር 464(2)(ሀ) ሥር እንደተመለከተው አዲሶቹ አክሲዮኖች በጥሬ ገንዘብ እንዲከፈሉ ወስኛለሁ በማለት ሲሆንተከሣሽ ተጨማሪው አክሲዮን እንዴት መሸጥ እንዳለበት የንግድ ሕጋችን የዘረጋውን ሥርዓት በመጣስ ሽያጭ አከናውኗል፡፡ ተከሣሽበንግድ ሕግ ቁጥር 470 መሠረት ተጨማሪ አዲስ አክሲዮኖች በሙሉ አክሲዮን ለመግዛት በሕግ የቀደምትነት መብት ላላቸው ባለአክሲዮኖች የመሸጥ ግዴታ ያለበት ሲሆንተከሣሽ እነዚህን አዲስ አክሲዮኖች መሸጥ ያለበትም ለነባር ባለአክሲዮኖች አክሲዮን በመግዛት የመፃፍ መብታቸውን እንዲሠሩበት የተፈቀደው ጊዜ አንስቶ ከ30 ቀናት በማያንስ የአክሲዮን መሸጫ ጊዜ ውስጥ መሆን እንደአለበት የንግድ ሕግ ቁጥር 476 ሥር ተደንግÙል፡፡
ተከሣሽበንግድ ሕግ ቁጥር 477(1) መሠረት አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀመርበትን ቀን በንግድ ኦፊሴል ጋዜጣ ውስጥ አስቀድሞ ከ10 ቀናት በማያንስ ጊዜ ማስታወቂያ በማውጣት እንዲሁም ሕጋዊ የሆኑትን ማስታወቂያዎች ለመቀበል የተፈቀደለት የባንኩ ዋና መ/ቤት በሚገኝበት ቦታ ባለና የቀደምትነት መብታቸውን አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀምርበትንና የሚያልቅበትን ቀን እንዲሁም አክሲዮኖቹ የሚወጡበትን ዋጋና ከዋጋቸውም ላይ የሚከፈለውን ልክ በሚገልጽ ጋዜጣ ባለአክሲዮኖች እንዲያውቁት ማድረግ ያለበት ወይም አክሲዮኖች ሁሉ በስም የተመዘገቡ ስለሆነ ተከሣሽ አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ ከሚጀምርበት ቀን በፊት ከ10 ቀናት በማያንስ ጊዜ አክሲዮን ለመግዛት የመፃፍ ማስታወቂያ በሪኮማንዴ ደብዳቤ ለባለአክሲዮኖች ሁሉ መላክ የሚችል በንግድ ሕግ ቁጥር 477(2) ሥር በግልጽ ተደንግጓል፡፡
ተከሣሽ አክሲዮን ለመሸጥ ከወሰነ ሽያጩ ከሚጀምርበት 10 ቀናት አስቀድሞ የሽያጭ ማስታወቂያ በጋዜጣ ማውጣት ወይም በደብዳቤ ለእያንዳንዱ ባለአክሲዮን ማስታወቅ፤አክሲዮን ለመግዛት የሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን ለመግዛት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች ሁሉ አክሲዮኖቹን ለመግዛት በተወሰነው በተከሣሽ ዋና መ/ቤት በሚገኙት መጠየቂያ ፎርሞችሞልተው ለተከሣሽ መስጠት ያለበት ሲሆን አክሲዮን ለመግዛት ጥያቄ ያቀረቡ ነባር ባለአክሲዮኖች መግለጫውንና የተጠቀሰውን ልዩ ሪፖርት ያለ እንደሆነ መመልከታቸውን መግለጽ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በቀደምትነት ስም መብት ያላቸውን አክሲዮኖች ለመግዛት ያልፃፉ እንደሆነ ከሚተርፉት ከእነዚህ አክሲዮኖች ውስጥ ምን ያህል አክሲዮን መግዛት እንደሚፈልጉም መግለጥ የሚችሉበት ቦታ ተከሣሽ የሚያዘጋጀው ፎርም ላይ ሊኖር ይገባል፡፡ አንዳንድ ነባር ባለአክሲዮኖች ተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን ከተጨማሪው አክሲዮን ውስጥ ድርሻቸውን ያልገዙና የተውት እንደሆነ ይህ ያልተሸጠ አክሲዮን በተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ባላቸው አክሲዮን ድርሻ መጠን ተመጣጣኝ አክሲዮን የገዙና ከድርሻቸው መጠን በላይ ለመግዛት ለጠየቁ ነባር ባለአክሲዮኖች በንግድ ሕግ ቁጥር 471 መሠረት ከዋናው የተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ገንዘብ ውስጥ ባላቸው ድርሻ መጠንና ባደረጉት ጥያቄ ወሰን መሠረት እነዚህን የቀሩትን አክሲዮኖች ተከሣሽ ሊደለድልላቸው ይገባል፡፡ በንግድ ሕግ ቁጥር 470 እና 471 ድንጋጌ መሠረት ያልተሸጡ አክሲዮኖች ቢኖሩ ያለመሸጣቸው ከተረጋገጠ በ`ላ ያልተሸጡት ወይም የቀሩት አክሲዮኖች የተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በሚወስነው መሠረት የሚደለደል መሆኑ የንግድ ሕግ ቁጥር 472 ሥር ተመልክል፡፡
ካፒታል ስለሚያድግት ሁኔታ ከላይ በተመለከቱ ድንጋጌዎች ላይ ተቀምጦ እያለ ከሣሽ በህጉ ላይ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በመጣስ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለባለአክሲዮኖች፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ባለአክሲዮን ላልሆኑ ሰዎች እንዲሸጥ የተላለፈው ውሳኔ ሕግን ያልተከተለ ነው፡፡ በንግድ ሕግ ቁጥር 470 መሠረት ያልተሸጠ አክሲዮን በንግድ ሕግ ቁጥር 471 መሠረት ለነባር ባለአክሲዮኖች እንዲሸጥ ይደረጋል እንጂ ለአዲስ ባለአክሲዮኖች እንዲሸጥ ተብሎ ውሳኔ አይተላለፍም፡፡
በንግድ ሕግ ቁጥር 471 መሠረት ለነባር ባለአክሲዮኖች ባላቸው ድርሻ መጠንና በጠየቁት ወሰን መሠረት ያልተሸጠ አክሲዮን ካለ እንኳን ይህን ያልተሸጠውን አክሲዮን በተመለከተ ለጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ እንደገና ተመልሶ ይቀርባል እንጂ ለአዲስ ባለአክሲዮን ይሸጣል ሲል የንግድ ሕግ ቁጥር 472 ያልተመለከተ ስለሆነ ተከሣሽ በዚህም ረገድ ከፍተኛ የህግ ግድፈት ፈፅሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከሣሽ አክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮኖች 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ካፒታል ዕድገትን በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔ ሊሻር የሚገባው ነው፡፡
ስለሆነም ተከሳሽ ማህበር ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ሲል በአክሲዮን ማህበሩ 9ኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ የንግድ ሕጉን አስገዳጅ ድንጋጌዎች እና የማህበሩን መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ያላከበረ ስለሆነውሳኔውእንዲሰረዝ እና የከሣሽን ወጪና ኪሳራ የመጠየቅ መብት እንዲጠበቅ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የሠነድ ማስረጃም አቅርበዋል፡፡
ተከሣሽ በመጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረበው የመከላከያ መልስተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011ዓ.ም ባካሄደው 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የአክሲዮን ማህበሩ ካፒታል በብር 50 ሚሊዮን እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን መሠረት እንዲሸጥላቸው ወይም እንዲደለደል፤ብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጪ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ካፒታል የማሳደግ እና አፈጻጸሙን የመወሰን ስልጣን ለጠቅላላ ጉባኤው በሕግ የተሰጠ ስልጣን ነው፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ካፒታሉን አዳዲስ አክሲዮኖችን በመሸጥ ማሳደግ የፈለገ እንደሆነ ነባር ባለአክሲዮኖች አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት እንዳላቸው የንግድ ሕግ አንቀጽ 470(1) በመርህ ደረጃ ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ የአክሲዮን ማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ይህንኑ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
በዚህም መሰረት ተከሳሽ ማህበር ካፒታሉን በብር 50 ሚሊዮን ለማሳደግ ሲወስን ከዚህ ውስጥ ብር 30 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው (እንዲደለደል) ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ እንዲህ ባለ አዳዲስ አክሲዮኖችን በመሸጥ በሚደረግ ካፒታል ማሳደግ እያንዳንዱ ነባር ባለአክሲዮን ባለው ይዞታ መጠን የመግዛት የቀደምትነት መብቱን መጠቀም ይችላል፡፡ ይህም መብት የተመሰረተው ባለአክሲዮኖች ሁሉ በአክሲዮኖቻቸው ገንዘብ መጠን ዋናው ገንዘብ እንዲጨምር ለማድረግ የወጡትን በገንዘብ የሆኑ አክሲዮኖችን ፈርመው እንዲገዙ የቀደምትነት መብት አላቸው በሚለው የንግድ ሕግ አንቀጽ 345(4) መሰረት ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው የተሰጠው ውሳኔም ይህንኑ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም የተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ረገድ ያሳለፈው ውሳኔ ከሳሽ እየጠየቁ ያሉትን የቀደምትነት መብት ተፈጻሚነት መሠረት ያደረገ በመሆኑ ውሳኔው የንግድ ሕጉን፣መመስረቻ እና መተዳደሪያ ደንቡን በመጣረስ የተሰጠ ውሳኔ ነው ሲሉ ውሳኔው እንዲሻርላቸው የጠየቁት ዳኝነት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር የትኛውን የመመስረቻ እና መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ እንደጣሰ እንኳ በክሳቸው አላስረዱም፡፡
በተጨማሪም ከሳሽ በተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ተጨማሪ አክሲዮኖች ለመግዛት የሚፈልጉ ከሆነ በተሰጣቸው ፎርም ላይ ሞልተው ለማህበሩ እንዲሰጡ በተገለጸላቸው መሰረት ፎርሙን የወሰዱ ቢሆንም ሞልተው አልመለሱም፡፡ ይልቁንም የወሰዱትን ፎርም በዚህ ክስ በማሳረጃነት ያቀረቡት መሆኑን ተከሳሽ ተመልክተናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሳሽ ተጨማሪ አክሲዮን ለመግዛት አለመፈለጋቸውን ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከሳሽ ባቀረቡት ክስ የግል ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ እና የማንን መብት ወይም ጥቅም ወክለው እንደሚከራከሩ ግልጽ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ በዚህ ረገድ ያቀረቡት ክስ የክስ ምክንያት የለውም ተብሎ ክሱን ውድቅ እንዲያደርግልን የተከበረውን ፍ/ቤት ዳኝነት እንጠይቃለን፡፡
የከሳሽ ክስ መሰረት ያደረገው በጉባኤው የተሰጠው ውሳኔ ይሻርልኝ የሚል ሆኖ ሳለ ከሳሽ እንዲሻርላቸው ዳኝነት የጠየቁበትን ውሳኔ በማስረጃነት አስደግፈው ሳያቀርቡ ወይም በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርብላቸው ሳይጠይቁ ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት የለውም በመሆኑ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡ከሳሽ ጉባኤው ብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ወደ ውጪ ለሽያጭ እንዲቀርቡ ሲል በሰጠው ውሳኔ ከፍተኛ ስህተት ፈጽሟል ሲሉ ምክንያታቸውን ባቀረቡት ክስ ላይ የዘረዘሩ ሲሆንይኸውም በንግድ ሕግ አንቀጽ 470 መሰረት ነባር ባለአክሲዮኖች በቀደምትነት መብታቸው ተጠቅመው ተጨማሪ አክሲዮን ለመግዛት ያልፈለጉ(በድርሻቸው መጠን ያልገዙ ወይም የተዉ እንደሆነ) እነዚህን ያልተሸጡ አክሲዮኖች በንግድ ሕጉ አንቀጽ 471 መሰረት በማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን ተመጣጣኝ አክሲዮን የገዙና ከድርሻቸው መጠን በላይ ለመግዛት የጠየቁ ነባር ባለአክሲዮኖች ባላቸው ድርሻ መጠንና በጠየቁት ወሰን መሰረት የሚደለደልላቸው መሆኑን፤ ከዚህ ውጪ አሁንም ሳይሸጥ የቀረ(የተረፈ) አክሲዮን ቢኖር በንግድ ሕግ አንቀጽ 472 መሰረት ለጠቅላላ ጉባኤ ለውሳኔ ቀርቦ በጉባኤው ውሳኔ መሰረት የሚደለደል እንጂ ባለአክሲዮን ላልሆኑ ሰዎች የሚሸጡ አይደለም፤ ከዚሁ ጋር አያይዘውም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 471 መሰረት አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በቀደምትነት መብት የቀረበላቸውን አክሲዮኖች ለመግዛት ያልጻፉ እንደሆነ ከሚተርፉት ከእነዚህ አክሲዮኖች ውስጥ ምን ያህል አክሲዮን መግዛት እንደሚፈልጉ መግለጥ የሚችሉበት ቦታ በተከሳሽ በሚዘጋጀው ፎርም ላይ ሊኖር ይገባል ሲሉ በክሳቸው የገለጹ ቢሆንም ከሳሽ እራሳቸው በማስረጃ ዝርዝራቸው ተ.ቁ.5 ሰር ያያያዙት ፎርም ላይ በቁጥር 5 ስር ይህንኑ በሚመለከት በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ የተለየ መከራከሪያ አያስፈልገውም፡፡
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 470(1) የተመለከተው ቢኖርም በልዩ ሁኔታ የነባር ባለአክሲዮኖች የቀደምትነት መብት የካፒታሉን ማሳደግ ያፀደቀው ጉባኤ የቀደምትነት መብት እንዳይሰራ የወሰነ ከሆነ ይኸው መብት ቀሪ እንደሚሆን በንግድ ሕጉ አንቀጽ 473(1) በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው የነባር ባለአክሲዮኖች አዲስ አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት ያለ ገደብ የተተወ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ ነባር ባለአክሲዮኖቹ እራሳቸው ይህን በህግ የተሰጣቸውን የቀደምትነት መብት በመቀነስ ካፒታል ለማሳደጊያነት እንዲሸጡ ከታሰቡት አዳዲስ አክሲዮኖች መካከል ከፊሉን ወደ ውጪ አውጥተው እንዲሸጡ ማድረግ የማይከለክላቸው መሆኑን ጭምር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጉባኤው አዳዲስ አክሲዮኖችን የዳሬክተሮች ቦርድ ለሚፈልገው ሰው በግል እንዲሸጥ(Private Placement) ወይም ለሕዝብ ጥሪ በማድረግ (Public Subscription) እንዲሸጥ ለመወሰን እንደሚችል በህጉ ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም አዳዲስ አክሲዮኖች ወደ ውጪ ወጥተው እንዳይሸጡ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡
ከሳሽ የተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ወደ ውጪ ወጥተው እንዲሸጡ ውሳኔ የሰጠባቸው ብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ሽያጭ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 470- 472 ያሉትን ድንጋጌዎች የጣሰ ነው ይበሉ እንጂ እነዚህ የሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት በንግድ ሕጉ አዳዲስ አክሲዮኖች ለሽያጭ ሲቀርቡ በአንቀጽ 470 ስር ከተመለከተው የነባር ባለአክሲዮኖች አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በባለአክሲዮኖቹ መካከል ስላለው የአክሲዮን ድልድል በሚመለከት እንጂ አዳዲስ አክሲዮኖች ባለአክሲዮን ላልሆኑ ግለሰቦች ለሽያጭ ሲቀርቡ አይደለም፡፡ ስለሆነም የተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ጉባኤው ካፒታልን ለማሳደግ ወደ ውጪ እንዲሸጡ ውሳኔ የሰጠባቸውን የብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለመሸጥ በእነዚህ አናቅጽ የተመለከተውን የድልድል ተዋረድ ተፈጻሚ እንዲያደርግ አይጠበቅበትም፡፡ በመሆኑም ከሳሽ በእነዚህ ድንጋጌዎች የተመለከተውን በባለአክሲዮኖች መካከል ያለውን የአዳዲስ አክሲዮኖች የድልድል ተዋረድ በመጥቀስ በአንድ በኩል ይህ የአክሲዮን ድልድል ተዋረድ አዳዲስ አክሲዮኖች ወደ ውጪ ለሽያጭ ከመቅረባቸው በፊት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ ሲገባቸው በተከሳሽ ማህበር አልተደረጉም ሲሉ አግባብነት የሌላቸውን የንግድ ሕጉን ድንጋጌዎች በመቀላቀል ያቀረቡት ክስ፤ በሌላ በኩል አዳዲስ አክሲዮኖች ወደ ውጪ ወጥተው የሚሸጡበት አግባብ እንደሌለ በማስመሰል ያቀረቡት ክስ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች በተመሳሳይ በማህበሩ ውስጥ ባሉ ባለአክሲዮኖች መካከል ስለሚደረግ የአክሲዮን ክፍፍልን የሚመለከቱ እንጂ ወደ ውጪ እንዲወጡ ለተደረጉት አክሲዮኖች ሽያጭ በሚመለከት ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡
ባለአክሲዮኖቹ ለሽያጭ የቀረቡላቸውን አዳዲስ አክሲዮኖች ባላቸው አክሲዮን መጠን ልክ ለመግዛት የቀደምትነት መብት ቢኖራቸውም እንኳ በዚህ መብት ያለመጠቀም መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ሁሉ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 473 መሰረት ይህን የቀደምትነት መብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዳይሰራባቸው ማድረግ የሚችሉ ስለመሆኑ በግልጽ የተመለከተ ሲሆን የተከሳሽ አክሲዮን ማህበርም ብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ወደ ውጪ ወጥተው እንዲሸጡ ጠቅላላ ጉባኤው የሰጠው ውሳኔ ከመነሻው ይህን በቀደምትነት መብት ላይ የሚደረጉትን ልዩነቶች መሰረት ያደረገ በመሆኑ ውሳኔው የንግድ ሕጉን ያላከበረ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም ጉባኤው በዚህ ረገድ ያሳለፈው ውሳኔ ምንም ዓይነት ስህተት ያልተፈጸመበት እና በሕጉ አግባብ በመሆኑ ከሳሽ የጉባኤው ውሳኔው ይሻርልኝ ሲሉ የጠየቁትን ዳኝነት ውድቅ እንዲያደረግልን እና ይልቁንም ሕጉን፣የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፎች እና የመተዳደሪያ ደንብን በመከተል የተደረጉ የጉባኤ ውሳኔዎች በጉባኤው ያልተገኙትንም ወይም በሀሳብ ያልተስማሙትን ማህበረተኞች ሁሉ የሚያስገድድ ስለመሆኑ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 416(1) ስር በተመለከተ መሰረት ውሳኔው በሕግ ፊት የጸና ተብሎ ክሱ ውድቅ እንዲደረግልን እንጠይቃለን በማለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡ የሠነድ ማስረጃ እና ምስክርችንም ጠቅሶ አቅርቧል፡፡
ፍ/ቤቱ ለክርክሩ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች በተጠየቀው ዳኝነት መሠረት በትዕዛዝ እንዲቀርቡ ካደረገ በኋላ ግራቀኙን አስቀርቦ በቃል አከራክሯል፡፡ በቃል ክርክር ወቅት የከሣሽ ጠበቃ ተከሣሽ በመልሱ ላይ እንደገለፀው በንግድ ህግ ቁጥር 473 መሠረት ለውጪ ሰዎች አክሲዮን ሽያጭ ተደርጓል በማለት የጠቀሰው ክርክርተገቢነት የለውም፤ ውሣኔው በአብላጫ ድምፅ የሚፀድቅ አይደለም፤ ዋናው ገንዘብ የሚጨምርበት ምክንያት ካፒታል ለማሳደግ እና ስራ ለማስፋፋት ከማለት ባለፈሌላ ምክንያት ስላልተገለፀ የህጉን መስፈርት አላሟላም፡፡አክሲዮን ለሌሎች የሚሸጥበት ምክንያት አልተገለፀም፤ አክሲዮን ገዙ የተባሉ ሰዎች በስም መጠቀስ ያለባቸው ቢሆንም ቦርዱም ሆነ ተቆጣታሪዎች ይህን አላደረጉም፤የአክሲዮኖቹ ዋጋም አልተገለፀም፤ ትክክለኛነቱን የሚያረጋግጥ የተቆጣታሪ ሪፖርትም የለም፤ በን/ህ/ቁ 471 መሠረት የከሣሽ የቀደምትነት መብት ሊጠበቅ ይገባ ነበር፤ የቀደምትነት መብት ሊቀር የሚችለው ባለአክሲዮኖች ለኩባንያው መክፈል ሳይችሉ ሲቀሩ ነው፤አክሲዮን ሽያጩ በን/ህ/ቁ 473 መሠረት የተደረገ ነው ከተባለ አክሲዮኑለህዝብ የሚሸጥበት ሁኔታ የለም፤ የተሣሽን ፎርም ያልሞላነው ውሳኔውን በመቃወማችን ነው በማለት የተከራከሩ ሲሆን የተከሣሽ ነገረ ፈጅ በበኩላቸው የአክሲዮን ሽያጩ በመተዳደሪያ ደንቡ እና በንግድ ህጉ አግባብ የተደረገ ነው፤ ከሣሽ የትኛው ህግ እንደተጣሰ አልጠቀሱም፤በብር 30 ሚሊዮን ላይ ከሣሽ ምን ዳኝነት እንደጠየቁ አልተገለፀም፤ በቃለ ጉባኤው መሠረት የተጣሰ ህግ የለም፤ አዳዲስ አክሲዮን ወደ ውጪ ሲሸጥ ከን/ህ/ቁ 470- 474 ያሉ ድንጋጌዎችን የሚመለከት አይደለም፡፡ የቀደምትነት መብት ሊታፍ የማይችል እና በአስገዳችነት የተቀመጠ መብት አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ግራቀኙ በቃል ያስመዘገቡት ሙሉ ክርክር ከመዝገቡ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በመዝገቡ ላይ የቀረበው ክርክር ባጭሩ ከላይ ያስቀመጥነውን ሲመስል ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ካፒታልእንዲያድግ እናብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው እንዲሁም ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ያስተላለፈው ውሳኔ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በዋነኝነት በመያዝ መዝገቡን አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ግራቀኙን ክርክር ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች እና ከቀረቡ ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳን እንደሚከተለው መርምሯል፡፡
ከሣሽ ክስ ያቀረቡት እና ከፍ/ቤቱ ዳኝነት የጠየቁት ተከሣሽ ማህበር በ9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩን ካፒታል ማሳደግን እና አክሲዮን ማስተላለፍን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሣኔ እንዲሠረዝ እንዲወሰንልኝ በማለት ሲሆን ከሣሽ የተከሣሽ ማህበር ባለ አክሲዮን ስለመሆናቸው፤ ተከሣሽ ማህበርም በህግ አግባብ የተቋቋመ የንግድ ማህበር ስለመሆኑ፤ ተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ድንገተኛ ስብሰባ የካፒታል እድገትን እና አክሲዮን ሽያጭን አስመልክቶ ውሳኔ ያሳለፈ ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፤ ማስረጃም ቀርቦበታል፡፡ ከሣሽ ውሣኔው ሊሠረዝ ይገባል ያሉት ደግሞ ተከሣሽ ተጨማሪው አክሲዮን እንዴት መሸጥ እንዳለበት የንግድ ሕጉ የዘረጋውን ሥርዓት በመጣስ ሽያጭ አከናውኗል፤ ተከሣሽ ተጨማሪ አዲስ አክሲዮኖች በሙሉ አክሲዮን ለመግዛት በሕግ የቀደምትነት መብት ላላቸው ባለአክሲዮኖች የመሸጥ ግዴታ ያለበት ቢሆንም ተከሣሽ ይህን አላደረገም፤ ተከሣሽ አክሲዮን ለመሸጥ ከወሰነ ሽያጩ ከሚጀምርበት 10 ቀናት አስቀድሞ የሽያጭ ማስታወቂያ በጋዜጣ ማውጣት ወይም በደብዳቤ ለእያንዳንዱ ባለአክሲዮን ማስታወቅ፤ አክሲዮን ለመግዛት የሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን ለመግዛት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች ሁሉ አክሲዮኖቹን ለመግዛት በተወሰነው በተከሣሽ ዋና መ/ቤት በሚገኙት መጠየቂያ ፎርሞች ሞልተው ለተከሣሽ መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ሲገባው ይህን አላደረገም፤ ማህበሩ በሚያዘጋጀው ፎርም ላይ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች የቀደምትነት መብት ያላቸውን አክሲዮኖች ለመግዛት ያልፃፉ እንደሆነ ከሚተርፉት ከእነዚህ አክሲዮኖች ውስጥ ምን ያህል አክሲዮን መግዛት እንደሚፈልጉም መግለፅ የሚችሉበት ቦታ ተከሣሽ የሚያዘጋጀው ፎርም ላይ ሊኖር ሲገባ ይህ አልተደረገም፤ አንዳንድ ነባር ባለአክሲዮኖች ተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን ከተጨማሪው አክሲዮን ውስጥ ድርሻቸውን ያልገዙና የተውት እንደሆነ ይህ ያልተሸጠ አክሲዮን በተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ባላቸው አክሲዮን ድርሻ መጠን ተመጣጣኝ አክሲዮን የገዙና ከድርሻቸው መጠን በላይ ለመግዛት ለጠየቁ ነባር ባለአክሲዮኖች ከዋናው የተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ገንዘብ ውስጥ ባላቸው ድርሻ መጠንና ባደረጉት ጥያቄ ወሰን መሠረት እነዚህን የቀሩትን አክሲዮኖች ተከሣሽ ሊደለድልላቸው ሊደረግ ሲገባ ይህ አልተደረገም፤ ያልተሸጡ አክሲዮኖች ቢኖሩ ያለመሸጣቸው ከተረጋገጠ በ`ላ ያልተሸጡት ወይም የቀሩት አክሲዮኖች የተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በሚወስነው መሠረት የሚደለደል ቢሆንም ተከሣሽ ይህን አላደረገም፤ በንግድ ሕግ ቁጥር 470 መሠረት ያልተሸጠ አክሲዮን በንግድ ሕግ ቁጥር 471 መሠረት ለነባር ባለአክሲዮኖች እንዲሸጥ ይደረጋል እንጂ ለአዲስ ባለአክሲዮኖች እንዲሸጥ ተብሎ ውሳኔ ሊተላለፍ አይገባም፤ በንግድ ሕግ ቁጥር 471 መሠረት ለነባር ባለአክሲዮኖች ባላቸው ድርሻ መጠንና በጠየቁት ወሰን መሠረት ያልተሸጠ አክሲዮን ካለ እንኳን ይህን ያልተሸጠውን አክሲዮን በተመለከተ ለጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ እንደገና ተመልሶ ይቀርባል እንጂ ለአዲስ ባለአክሲዮን መሸጥ የለበትም በማለት ነው፡፡
ተከሣሽ በበኩሉ የማህበሩ አክሲዮን እንዲያድግ እና እንዲሸጥ የተደረገው በህግ አግባብ መሆኑን፤ ውሳኔው የተላለፈው ባለአክሲዮኖች ያላቸውን የቀደምትነት መብት ተፈጻሚ ባደረገ መሆኑን፤ ከሣሽ የትኛውን የመመስረቻ እና መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ እንደጣሰ በክሳቸው ያላስረዱ መሆኑን፤ ከሣሽ ፎርሙን የወሰዱ ቢሆንም ሞልተው ከመመለስ ይልቅ የወሰዱትን ፎርም ሳይመልሱ መቅረታቸውን፤ ከሣሽ በማስረጃነት አያይዘው ባቀረቡት ፎርም ላይ ላይ የጠየቋቸው እና አክሲዮን የሚተላለፍባቸው ሁኔታዎች በዝርዝር የተመለከቱ መሆናቸውን፤ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 470(1) የተመለከተው ቢኖርም በልዩ ሁኔታ የነባር ባለአክሲዮኖች የቀደምትነት መብት የካፒታሉን ማሳደግ ያፀደቀው ጉባኤ የቀደምትነት መብት እንዳይሰራ የወሰነ ከሆነ ይኸው መብት ቀሪ ሊሆን የሚችል መሆኑን፤ የነባር ባለአክሲዮኖች አዲስ አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት ያለ ገደብ የተተወ አለመሆኑን እና ነባር ባለአክሲዮኖቹ እራሳቸው ይህን በህግ የተሰጣቸውን የቀደምትነት መብት በመቀነስ ካፒታል ለማሳደጊያነት እንዲሸጡ ከታሰቡት አዳዲስ አክሲዮኖች መካከል ከፊሉን ወደ ውጪ አውጥተው እንዲሸጡ ማድረግ የማይከለክላቸው መሆኑን፤ ከሣሽ የጠቀሷቸው የሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት በንግድ ሕጉ አዳዲስ አክሲዮኖች ለሽያጭ ሲቀርቡ በአንቀጽ 470 ስር ከተመለከተው የነባር ባለአክሲዮኖች አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በባለአክሲዮኖቹ መካከል ስላለው የአክሲዮን ድልድል በሚመለከት እንጂ አዳዲስ አክሲዮኖች ባለአክሲዮን ላልሆኑ ግለሰቦች ለሽያጭ ሲቀርቡ አለመሆኑን፤ የተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ጉባኤው ካፒታልን ለማሳደግ ወደ ውጪ እንዲሸጡ ውሳኔ የሰጠባቸውን የብር 20 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለመሸጥ በእነዚህ አናቅጽ የተመለከተውን የድልድል ተዋረድ ተፈጻሚ እንዲያደርግ የማይጠበቅበት፤ ከሳሽ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች በተመሳሳይ በማህበሩ ውስጥ ባሉ ባለአክሲዮኖች መካከል ስለሚደረግ የአክሲዮን ክፍፍልን የሚመለከቱ እንጂ ወደ ውጪ እንዲወጡ ለተደረጉት አክሲዮኖች ሽያጭ በሚመለከት ተፈጻሚነት የሌላቸው መሆኑን፤ ባለአክሲዮኖቹ ለሽያጭ የቀረቡላቸውን አዳዲስ አክሲዮኖች ባላቸው አክሲዮን መጠን ልክ ለመግዛት የቀደምትነት መብት ቢኖራቸውም እንኳ በዚህ መብት ያለመጠቀም መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ሁሉ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 473 መሰረት ይህን የቀደምትነት መብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዳይሰራባቸው ማድረግ የሚችሉ ስለሆነ ውሣኔው የንግድ ሕጉን ያላከበረ ነው ሊባል የማይችል መሆኑን በመግለፅ ቃለ ጉባኤው ሊፃና ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡
ስለሆነም ተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈው ውሣኔ በህግ አግባ ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጭብጥ ላይ ምላሽ ለመስጠት በቅድሚያ በዚሁ ቀን በተደረገው ስብሰባ በጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነው ውሣኔ ህጉ በሚያዘው መልኩ የተላለፈ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ከህጉ እና ከቀረቡት ማስረጃዎች አኳያ መመርመሩ ተገቢ ነው፡፡
ከላይ እንደገለጽነው ተከሣሽ ማህበር በንግ ድህጉ መሠረት የተቋቋመ እና ህጋዊ ሠውነት ያለው ተቋም ሲሆን ተከሣሽ ማህበር የተቋቋመበትን ዓላማ በአግባቡ ማሳካት ይችል ዘንድ ማለትም በመተዳደሪያ ደንብ ላይ የዘረዘራቸውን ዓላማዎች በማሳካት አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የራሱን አዎንታዊ ውጤት ማበርከት ይችል ዘንድ ማህበሩ በህጉ መሠረት ሊመራ እና ሊተዳደር ይገባል፡፡ ስለሆነም ተከሣሽ ማህበር የቋቋመበትን ዓላማ በአግባቡ በማሳካት አባላቱን እና ሶስተኛ ወገኖችን እንዲሁም በአገሪቱ ኢኮኖሚ አውንታዊ ሚና ማድረግ ይችል ዘንድ በህጉ እና ህጉን መሠረት በማድረግ ባፀደቀው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሊመራ እና ሊተዳደር ይገባል፡፡
ተከሣሽ ማህበር የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ጉባኤዎችን ማድረግ እና በጉባኤዎች ላይ አጀንዳዎችን ይዞ በመምከር ውሣኔዎችን ማሳለፍ የሚችል ሲሆን ማህበሩ የሚያደርገው ጉባኤ ደግሞ መደበኛ /Regular/ ወይም አስቸኳይ /Extra ordinary/ ጉባኤ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ማህበሩ የሚያደርጋቸው ጉባኤዎች ህጋዊ ውጤትን ማስከተል እንዲሁም መብትና ግዴታን መፍጠር ይችሉ ዘንድ ጉባኤዎች መደረግ ያለባቸው ህጉ በሚያዘው መልኩ፣ ህጋዊ ውጤት ያለው ጉባኤ እና ውሣኔ ለማሳለፍ መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች ባሟላ መልኩ የተደረገ ከሆነ ነው፡፡ ተከሣሽ ጉባኤ ሲያደርግ በህግ አግባብ የማይመራ ከሆነ የሚጠበቅበትን ዓላማ የማያሳካ ከመሆኑም በላይ በአባላቱ፣ በሶስተኛ ወገኖች እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ውጤትን ያስከትላል፡፡ አንድ ጉባኤ በህግ ፊት የሚፀና፣ በአባላቱ በሶስተኛ ወገኖች መብትና ግዴታን የሚፈጥረው ወይም ህጋዊ ውጤትን የሚያስከትል ጉባኤ በህጉ እና በመ/ደንቡ ላይ መሟላት አለባቸው ተብለው የተቀመጡትን ሁኔታዎች ባሟላ መልኩ ካልተደረገ እና ህግን መተዳደሪያ ደንብን እንዲሁም የመመስረቻ ጽሑፍን በሚቃረን መልኩ ከተደረገ ማህበርተኛው ወይም ማንኛውም ጥቅም ያለው ሠው ውሣኔው እንዲሻርለት ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ክስ የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 416 /2/ ሥር ተመልክቷል፡፡
ከእነዚህ ሁኔታዎች አኳያ የያዝነውን ጉዳይ ስንመለከትከሣሽ ተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ድንገተኛ ስብሰባ የካፒታል እድገትን እና አክሲዮን ሽያጭን አስመልክቶ ያሳለፈው ውሣኔ እንዲሻርላቸው የጠየቁት የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ መወሰኑን ተከትሎ ለማህበሩ ባለአክሲዮን ላልሆኑ ሰዎች የአክሲዮን ሽያጭ እንዲከናወን የተላለፈው ውሣኔ ከህግ ውጪ ነው፤ ለነባር ባለ አክሲዮኖች የቀደምትነት መብት ሊሰጥ ሲገባ ይህ አልተደረገም በሚል በመሆኑ የአክሲዮን ማህበራት ካፒታል ሲያድግ አክሲዮኖች ለማህበሩ አባላት እና ለሶስተኛ ወገኖች የሚተላለፉበትን ሁኔታ ከንግድ ህጉ አኳያ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡
ተከሣሽ ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በአጀንዳ ተራ ቁጥር 5.4 ላይ የተመለከተው የኩባንያውን ካፒታል ማሳደግ እና አፈፃፀሙ ላይ ውሣኔ ማሳለፍ ሲሆን በዚሁ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤው በአጀንዳው ላይ ተወያይቶ የተከሣሽ ማህበር ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ውሣኔ አስተላልፏል፡፡
አንድ አክሲዮን ማህበር ዋና ገንዘቡን ከሚያሳድግባቸው ሁኔታዎች መካከል አንዱ አክሲዮኖችን በማውጣት ወይም ያሉትን አክሲዮኖች በማብዛት ስለመሆኑ በን/ሕ/ቁጥር 464(1) ሥር የተመለከተ ሲሆን ባለ አክሲዮኖች በጥሬ ገንዘብ የሚወጣውን አዲስ አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት ያላቸው ስለመሆኑም በን/ሕ/ቁ 470 ሥር ተመልክቷል፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በቀደምትነት ስም መብት ያላቸውን አክሲዮኖች ለመግዛት ያልፃፉ እንደሆነ በቀደምትነት ለመግዛት መፃፍ ከሚችሉት አክሲዮኖች በላይ ጠይቀው የነበሩ ሌሎች ባለ አክሲዮኖች ከዋናው ገንዘብ ውስጥ ባላቸው ድርሻ መጠን እና ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የቀሩት አክሲዮኖች የሚደለደልላቸው ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 471 ሥር የተመለከተ ሲሆን ያልተሸጡ አክሲዮኖች ደግሞ የአክሲዮን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በሚወስነው መሠረት የሚደለደል መሆኑ የን/ህ/ቁ 472 ሥር ተመልክቷል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤ ነባር ባለ አክሲዮኖች ያላቸው አዲስ አክሲዮን የመግዛት የቀደምትነት መብት እንዳይሰራ መወሰን የሚችል ስለመሆኑ እና ይህንንም መወሰን የሚችለው በቃለ ጉባኤው ላይ ዋናው ገንዘብ የሚጨምርበት ምክንያት፤ በቀደምትነት መብት የአክሲዮኖች መፃፈ የሚቀርበት ምክንያት፤ አዲሶቹን አክሲዮኖች ሚከፍሉትን ሰዎች እና ለእያንዳንዳቸው የሚደርሳቸውን አክሲዮኖች ልክ፤ አክሲዮኖቹ የሚወጡበትን ዋጋ እና ዋጋውንም ለመወሰን ተወሰደውን መሠረት የሚያመለክት የአስተዳዳሪዎች ሪፖርት እንዲሁም የአስተዳዳሪዎች ሪፖርት ትክክለኛነት የሚገምት የተቆጣጣሪዎች ሪፖርት ካመዛዘነ በኋላ ብቻ ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 473 /1/ (ሀ) እና (ለ) ስር የተመለከተ ሲሆን አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀመርበትን ቀን በንግድ ኦፊሴል ጋዜጣ ውስጥ አስቀድሞ ከ10 ቀናት በማያንስ ጊዜ ማስታወቂያ በማውጣት እንዲሁም ሕጋዊ የሆኑትን ማስታወቂያዎች ለመቀበል የተፈቀደለት የማህበሩ ዋና መ/ቤት በሚገኝበት ቦታ ባለና የቀደምትነት መብታቸውን አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀምርበትንና የሚያልቅበትን ቀን እንዲሁም አክሲዮኖቹ የሚወጡበትን ዋጋና ከዋጋቸውም ላይ የሚከፈለውን ልክ በሚገልጽ ጋዜጣ ባለአክሲዮኖች እንዲያውቁት ማድረግ ያለበት ወይም አክሲዮኖች ሁሉ በስም የተመዘገቡ ስለሆነ ተከሣሽ አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ ከሚጀምርበት ቀን በፊት ከ10 ቀናት በማያንስ ጊዜ አክሲዮን ለመግዛት የመፃፍ ማስታወቂያ በሪኮማንዴ ደብዳቤ ለባለአክሲዮኖች ሁሉ መላክ የሚችል ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 477 /1/ እና /2/ ሥር ተመልክቷል፡፡
አክሲዮን ለመግዛት የሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን ለመግዛት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች ሁሉ አክሲዮኖቹን ለመግዛት በተወሰነው በተከሣሽ ዋና መ/ቤት በሚገኙት መጠየቂያ ፎርሞች ሞልተው ለአክሲዮን ማህበሩ መስጠት ያለባቸው ስለመሆኑ እና አክሲዮን ለመግዛት ጥያቄ ያቀረቡ ነባር ባለአክሲዮኖች መግለጫውንና የተጠቀሰውን ልዩ ሪፖርት ያለ እንደሆነ መመልከታቸውን መግለጽ ያለባቸው ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 478(2) እና 319 ሥር ተመልክቷል፡፡
ከላይ ከተመለከትናቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ ተከሣሽ አክሲዮን ማህበር በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 9ኛ ድንገተኛ የባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩ ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ መወሰኑን ተከትሎ ከዚህ ውስጥ ዋጋቸው ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) የሆኑ አክሲዮኖችን ብቻ ለማህበሩ ባለ አክሲዮኖች እንዲሸጡ በመወሰን ዋጋቸው ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) የሆኑ አክሲዮኖች ከማህበሩ ውጪ ለሆኑ ሰዎች እንዲሸጡ መወሰኑ በህጉ ላይ ከተመለከተው አክሲዮኖችን በማብዛት የማህበሩን ዋና ገንዘብ ለማሳደግ ሲወሰን በህጉ እንዲተገበሩ ከተመለከቱ ሁኔታዎች እና ነባር ባለ አክሲዮኖች በህግ ከተሰጣቸው የቀደምትነት መብት አኳያ ያለውን አግባብነት መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ ላይ ተከሣሽ ማህበር ለክሱ መነሻ በሆነው ቃለ ጉባኤ አማካኝነት ካፒታል ያሳደገው አክሲዮኖችን በማመንጨት ወይም ያሉትን አክሲዮኖች በማባዛት በን/ህ/ቁ 464 /1/ ላይ በተመለከተው አግባብ ሲሆን በዚህ መልኩ ካፒታል ሲያድግ ደግሞ አዳዲሶቹ አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለ አክሲዮኖችም ሆነ ለሶስተኛ ወገኖች ለሽያጭ የሚቀርቡበትን ሁኔታ በተመለከተ ተፈፃሚነት የሚኖራቸው በዚሁ የንግድ ህጉ ልዩ ክፍል በተመለከቱት የን/ህ/ቁ 470 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሠረት ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህም መሠረት ተከሣሽ ማህበር በህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ካፒታሉን አሳድጎ አክሲዮኖች ለሽያጭ እንዲቀርቡ ያደረገበትን ዓይነት ሁኔታ ሲኖር ነባር ባለ አክሲዮኖች የቀደምትነት መብት ሊኖራቸው የሚገባ ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 470 ስር በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ለክሱ ምክንያት በሆነው ቃለ ጉባኤ ላይ አክሲዮን ሽያጭን አስመልክቶ የተላለፈውን ውሣኔ ስንመለከት ተከሣሽ ማህበር ካፒታሉን አሳድጎ አክሲዮኖችን ለሽያጭ እንዲቀርቡ ሲወስን ነባር አባላት በቀደምትነት መብታቸው እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማሟላት ያለበትን፤ ማለትም አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀመርበትን ቀን በንግድ ኦፊሴል ጋዜጣ ውስጥ አስቀድሞ ከ10 ቀናት በማያንስ ጊዜ ማስታወቂያ በማውጣት እንዲሁም ሕጋዊ የሆኑትን ማስታወቂያዎች ለመቀበል የተፈቀደለት የማህበሩ ዋና መ/ቤት በሚገኝበት ቦታ ባለና የቀደምትነት መብታቸውን አክሲዮን ለመግዛት መፃፍ የሚጀምርበትንና የሚያልቅበትን ቀን እንዲሁም አክሲዮኖቹ የሚወጡበትን ዋጋና ከዋጋቸውም ላይ የሚከፈለውን ልክ በሚገልጽ ጋዜጣ ባለአክሲዮኖች እንዲያውቁት ማድረግ ያለበት ቢሆንም አክሲዮኖች ለሶስተኛ ወገኖች እንዲሸጡ ከመወሰኑ በፊት አባላት በህግ በተቀመጠላቸው የቀደምትነት መብት እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ያሟላ ስለመሆኑ ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ ተከሣሽ ማህበር ለአባላት እና ለውጪ ሰዎች የሚሸጡ አክሲዮኖች በማለት በመጠን ከፋፍሎ ውሣኔ ከማሳለፉ ውጪ አባላት የቀደምትነት መብታቸውን እንዲጠቀሙ በሚያስችል መልኩ አክሲዮኖቹ ለውጪ ሰዎች እንዲተላለፉ ከመወሰኑ በፊት መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለአባላት ያሳወቀ ስለመሆኑ ወይም አባላት ይህን መብታቸውን ሳይጠቀሙበት ቀሩበትን ምክንያት ምን እንደሆነ በመግለፅ ያቀረበው ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ውሣኔውን ካሳለፈ በኋላ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ማስታወቂያ ፎርም ለአባላቱ /ለከሣሽ/ መስጠቱ ብቻውን አክሲዮኑ ሲያድግ ነባር ባለአክሲዮኖች በቀደምትነት መብታቸው እንዲጠቀሙ በሚያስችል መልኩ አክሲዮን ለመግዛት የሚያስችል ማስታወቂያ ለአባላት የሰጠና በህጉ ላይ የተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟላ መሆኑን አያሳይም፡፡ ከዚህ አንፃር ተከሣሽ ማህበር ስለ አክሲዮን ሽያጩ ዝርዝር የያዘውን ፎርም ለከሣሽ አስቀድሞ እንደሰጠ እና ከሣሽ በመብታቸው ሳይጠቀሙ እንደቀሩ በመግለፅ ያቀረበው ክርክር የህግ ድጋፍ ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ነባር አባላት በቀደምትነት መብታቸው ሳይጠቀሙ ቢቀሩና ያልተሸጡ አክሲዮኖች የአክሲዮን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በሚወስነው መሠረት የሚደለደል ሲሆን ከመነሻውም አባላት የቀደምትነት መብታቸውን መጠቀም የሚያስችላቸውን እድል ሳያገኙና እንዲያውቁ ሳይደረግ አባላት የቀደምትነት መብታቸውን መጠቀም እንዳልፈለጉ ወይም እንዳልቻሉ አልያም ይህ መብታቸው ቀሪ እንደሆነ በማስመሰል ተከሣሽ በቀጥታ አክሲዮኖችን ለሶስተኛ ወገኖች በሽያጭ እንዲተላለፍ መወሰኑ አግባብነት የሌለው ሆኖ እያለ የባለ አክሲዮኖቹን የቀደምትነት መብት መሠረት ባደረገ መልኩ የተከናወነ ሽያጭ መሆኑን በመግለፅ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡
የአክሲዮን ማህበር አባላት አዲስ አክሲዮኖችን በቀደምትነት መብታቸው መግዛት የሚችሉበት ሁኔታ በመርህ ደረጃ በህጉ የተቀመጠ ሲሆን አባላት ይህን መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ እስካልተፈጠረና በመብታቸው መጠቀም አለመፈለጋቸው ካልተረጋገጠ በስተቀር ተከሣሽ በፈለገው መንገድ የነባር አባላትን የቀደምትነት መብት እንደይጠቀሙ በሚያደርግ መልኩ ከህግ ውጪ የአክሲዮን ሽያጭ እንዲከናወን መወሰንም ሆነ ሽያጭ ማከናወን የሚችልበት የህግ አገባብ የለም፡፡ የአክሲዮን ማህበር ነባር አባላት የቀደምትነት መብታቸው እንዳይሰራ ለማድረግ በጠቅላላ ጉባኤ ሊወሰን የሚችል ስለመሆኑ በን/ህ/ቁ 473 /1/ (ሀ) እና (ለ) ሥር የተመለከተ ሲሆን ይህ የአባላት የቀደምትነት መብት ቀሪ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዲሁ ጠቅላላ ጉባኤው ስለፈለገ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በህጉ ላይ የተመለከቱ የቀደምትነት መብትን የሚያስቀሩ ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም ካፒታል ለማሳደግ እና አክሲዮኖችን ለመሸጥ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ዋናው ገንዘብ የሚጨምርበት ምክንያት ምን እንደሆነ፤ በቀደምትነት መብት የአክሲዮኖች መፃፈ የሚቀርበት ምክንያት፤ አዲሶቹን አክሲዮኖች የሚከፍሉትን ሰዎች እና ለእያንዳንዳቸው የሚደርሳቸውን አክሲዮኖች ልክ ምን ያህል እንደሆነ፤ አክሲዮኖቹ የሚወጡበትን ዋጋ እና ዋጋውንም ለመወሰን የተወሰደውን መሠረት የሚያመለክት የአስተዳዳሪዎች ሪፖርት እንዲሁም የአስተዳዳሪዎችን ሪፖርት ትክክለኛነት የሚገምት የተቆጣጣሪዎች ሪፖርት ካመዛዘነ በኋላ ብቻ ሲሆን ተከሣሽ ማህበር አክሲዮኖች ለውጪ ሰዎች ሲሸጡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የተሟሉ ስለመሆኑ የቀረበ ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ ተከሣሽ እነዚህን ሁኔታዎች መሟላታቸውን ባላረጋገጠበት ሁኔታ የቀደምትነት መብት በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ ቀሪ ሊሆን ስለሚችል ተከሣሽ አክሲዮን በቀጥታ ለውጪ ሰዎች እንዲሸጥ መወሰኑ በህጉ አግባብ ነው በማለት ያቀረበው መከራከሪያ የህግ ድጋፍ ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ተከሣሽ ማህበር አክሲዮኖችን ከማህበሩ ውጪ ለሆኑ ሰዎች እንዲሸጡ ሲወስን ነባር ባለ አክሲዮኖች በህግ የተቀመጠላቸውን የቀደምትነት መብት ያላከበረ እና የቀደምትነት መብታቸውን መጠቀም የሚያስችላቸውን በህጉ ላይ የተመለከቱ አዲስ አክሲዮኖች ሽያጭ የሚከናወንበትን አሰራር ያልተከተለ ሆኖ እያለ ተከሣሽ ማህበር ሽያጩ የተከናወነው የአባላቱን የቀደምትነት መብት ባከበረ መልኩ ነው እንዲሁም የቀደምትነት መብት በህጉ ላይ በአስገዳጅነት አልተቀመጠም በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ ድጋፍ ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሽ ማህበር የማህበሩ ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ሲል በአክሲዮን ማህበሩ 9ኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ያሳለፈው ውሣኔ በንግድ ህግ ቁጥር 470፤ 471፤ 472፤ 473፤ 477፤ 478 /2/ እና 319 በተመለከተው አግባብ አዳዲስ ተጨማሪ አክሲዮኖች እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው በንግድ ሕጉ የተመለከቱ ሁኔታዎችን በመጣስ የነባር ባለ አክሲዮኖችን የቀደምትነት መብት ያላከበረ በመሆኑ ውሣኔው ሊዘረዝ የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ስለሆነም የተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ማህበሩ 9ኛ ድንገተኛ ስብሰባየማህበሩን ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ሲል ያስተለለፈው ውሣኔ በን/ህ/ቁ 416 /2/ መሠረት ሊሠረዝ ይገባል ተብሎ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ውሣኔ
- ተከሣሽ አክሲዮን ማህበር ጠቅላላ በሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ማህበሩ 9ኛ ድንገተኛ ስብሰባ የማህበሩን ካፒታል በብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) እንዲያድግ እና ከዚህ ውስጥ ብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች በአክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻቸው መጠን መሰረት እንዲሸጥላቸው፣ ብር 20,000,000.00 (ሃያ ሚሊዮን ብር) ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ደግሞ ከአክሲዮን ማህበሩ ውጭ ላሉ ሰዎች እንዲሸጡ ሲል ያስተለለፈው ውሣኔ በን/ህ/ቁ 416 /2/ መሠረት ሊሠረዝ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
- ከሣሽ በዚህ ክስ ምክንያትየደረሰባቸው ወጪና ኪሣራ ካለ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተግልብጦ ይሰጠው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡