- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 5295
የኮ/መ/ቁ 261663 - ወ/ሪት ኢለን ንጉስ እና አቶ ገ/ፃድቅ ካህሳይ
የመ/ቁ 261663
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ከሣሽ ፡- ወ/ሪት ኢለን ንጉስ
ተከሳሽ ፡- አቶ ገ/ፃድቅ ካህሳይ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡
ፍርድ
ከሣሽ በመጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ፅፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ተከሳሽ ለከሳሽ የቼክ ቁጥሩ 61206575 የሆነ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ያዘዘ ቼክ ፈርመው የሠጡኝ ቢሆንም ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ ሳቀርብ ባንኩ ሂሳቡ በቂ ስንቅ የለውም በማለት ቼኩ ሣይከፈልበት ተመልሷል፤ በመሆኑም ተከሣሽ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰብኝን ወጪና ኪሣራም እንዲተኩ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ተከሣሽ የመከላከያ ማስፈቀጃ አቅርበው ክሱን እንዲከላከሉ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት በጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ከሳሽ በተከሳሽ የተሰጠኝ ነዉ ያሉት ሰነድ ክፈል በሚለዉ ሁለት መስመሮች ቦታ የተፃፈዉ ካሽ የሚል እና በዚሁ መስመር ላይ በድጋሚ አራት መቶ ሺ ብር የሚል ተፅፏል ፡፡ በዚህ ክፍት ቦታ የሚፃፈዉ የተከፋይ ስም እንደሆነ ከቼኩ ማንም ሰዉ መረዳት ይችላል፡፡ ከዚህ ዉጪ የብር መጠን በአኃዝ የሚፃፍበት ቦታ ምንም ነገር አልተፃፈም፡፡ የብር መጠን የሚፃፍበት ሁለት መስመሮች ላይ የብሩን መጠን በአኃዝ የሚገልፅ ወይም በዚህ ሰነድ ላይ በተከሳሽ መፃፍ በነበረበት ቦታ የተፃፈ የብር መጠኑን የሚያሳይ ምንም ነገር ያልተፃፈበት ሰነድ ነዉ፡፡ በመሆኑም ይህ ሰነድ በንግድ ህጉ የተዘረዘሩትን አንድ ቼክ መያዝ የሚገባዉን መስፈርቶች ያልያዘ ሰነድ በመሆኑ እንደ ቼክ ሊቆጠር ስለማይገዉ የከሳሽ ክስ ተቀባይነት የለዉም፡፡
ተከሳሽ ይህንን ቼክ ያዘጋጀሁት አቶ ዳንኤል ገ/ሕይወት ከተባሉት ግለሰብ ላይ ለተበደርኩት ገንዘብ ክፍያ ለመፈፀም ነዉ፡ ይህንን ቼክ አዘጋጅቼ ለአቶ ዳንኤል ገ/ሕይወት ስሰጣቸዉ በዚህ ቼክ ላይ በፊደል የተፃፈዉ ገንዘብ መጠን ብር በሚለዉ ቦታ መፃፍ ሲገባኝ በስህተት የተከፋይ ስም በሚፃፍበት ቦታ መፃፌንና የገንዘብ መጠኑ በፊደል መፃፍ በሚገባዉ ቦታ ደግሞ ባዶ መሆኑን አቶ ዳኒኤል ገ/ሕይወት ቼኩን ተቀብለዉኝ ካዩ በኋላ ሲነግሩኝ ቼኩ የፎርም አሞላል ችግር ያለበት ስለሆነ ክፍያ በዚህ ሰነድ ስለማይፈፀምልኝ ቀይርልኝ በማለት ሲጠይቁኝ፤ እኔም የአሁን ተከሳሽ ይህ ሰነድ የፎርም አሞላል ችግር ያለበት መሆኑን ተገንዝቤ በዚሁ ሰነድ ክፍያ ሊፈፀምበት አይችልም የሚል ከቅንነት የመነጨ እምነት አድሮብኝ ሰጥቻቸዉ የነበረዉን ሰነድ ተቀብያቸዉ የመኪናዬ ኪስ ዉስጥ በማስቀመጥ በምትኩ ብር 400,000.00 / አራት መቶ ሺ/ የተፃፈበትን ቁጥር 61206576 የሆነ ሌላ ቼክ ቀይሬ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ተከሳሽ ለከሳሽ በዚህ ቼክ ላይ የተፃፈዉን የገንዘብ መጠን ፅፎ ለመስጠት የሚያበቃ ሕጋዊ ግዴታ ወይም ግብይት (transaction) የሌለን ሲሆን ከሳሽ የሴት ጓደኛዬ የነበሩ በመሆኑ ብዙ ጊዜ በእኔ በተከሳሽ ተሽከርካሪ አብረን ስንጓዝ የነበረ በመሆኑ አጋጣሚዉን በመጠቀም ከቅን ልቦና ውጪ ለክሱ ምክንያት የሆነዉን ቼክ ከተሸከርካሪዬ ኪስ ዉስጥ የወሰዱ መሆኑን ተከሳሽ ያወኩት ከሳሽ በቂ ስንቅ የለዉም በማለት ማስመታታቸዉን ካወኩ በኋላ ነዉ፡፡
በመሆኑም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን የገንዘብ መጠን ለመፃፍ የሚያበቃ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግዴታ ግብይት (transaction ) በመካከላችን ሳይኖር ያለአግባብ ለመበልፀግ በማሰብ ያቀረቡት ክስ በመሆኑ ወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብቴ ተጠብቆ ክሱ ዉድቅ እንዲደረግላቸው በመጠየቅ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት እለት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ቼኩ የፎርም ችግር የሌለበት መሆኑ በከፋዩ ባንክ ተረጋግጧል፤ ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡበት ምክንያት ለመኪና ሽያጭ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ከከሳሽ ወስደው የመኪናው ስም እስኪዛወር ለዋስትና እንዲሆን ታስቦ የተሰጠ ነው ተከሳሽም ቼኩ ከተመታ በኋላ የባንኩ ስራ አስኪያጁ ዘንድ ቀርበው እከፍላለሁ ብለው ድርድር ሲያደርጉ ነበር በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸው ባንኩ የፎርም ችግር እያለበት መሆኑን እያወቀ ይህንን አለመግለፁ ቼኩን ህጋዊ አያደርገውም፤ ከከሳሽ ጋር ግብይት የለንም ፤ የመኪና ሽያጭን በተመለከተም በክሱ ላይ ያልተገለፀ ነው በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡
ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሽ ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡
በያዝነው ጉዳይ ከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት ለመኪና ሽያጭ ሲሆን ተከሳሽ በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ከከሳሽ ወስደው የመኪናው ስም እስኪዛወር ለዋስትና እንዲሆን ታስቦ የተሰጠ መሆኑን ገልፀው የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ደግሞ ቼኩን ለከሳሽ ለመስጠት የሚያስችል ግንኙነት የሌላቸውና ቼኩ የፎርም ችግር ያለበት መሆኑን ከሳሽ ቼኩን ያገኙት ከቅን ልቦና ውጪ መሆኑን በመግለፅ የተከራከሩ ናቸው፡፡
ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ለመስራት ይችል ዘንድ የግራ ቀኙ ምስክሮችን አስቀርቦ የሰማ ሲሆን 1ኛየከሳሽ ምስክር ከሳሽ ራሳቸው ሲሆኑ በሰጡት የምስክርነት ቃል ተከሳሽ የልብስና ሽቶ ደንበኛዬ ናቸው ስራ ቦታ መጥተው መኪናዬን ልሸጣት ስለሆነ አንቺ በብር 600ሺህ ግዢኝ አሉኝ ተከሳሽም በጥር 9 ቀን 2010 ዓ/ም ፒክ አፕ የሆነች መኪና ይዘው መጥተው አሳዩኝ ሊብሬው የታለ ስላቸው አመጣለሁ ቤት ረስቼው ነው አሉኝ በእለቱም በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ ሰጠኋቸው መኪናው መጥቷል ያሉኝ በመሆኑ ሊብረውን ረስቼዋለሁ ያሉ በመሆኑ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ሰጥተውኝ በ20ቀን ውስጥ ስሙን አዞርልሻለሁ አሉኝ ውል እንዋዋል ስላቸው ችግር የለም መኪናው ገብቷል ዛሬ ነገ እያሉ ቆዩ ብሩን መልሱልኝ ስላቸው እሰጥሻለሁ እያሉ የቆዩ በመሆኑ ቼኩን አስመታሁ ብር 200ሺህ ስም ሲዞር ለመጨመር ነበር የተነጋገርነው ፤ ብሩን ለተከሳሽ ስሰጥም አቶ ይበቃል ገ/እግዚአብሔር የተባለ ግለሰብ ነበር ሲሉ መስክረዋል፡፡ 2ኛየከሳሽ ምስክር የባንኩ ሰራተኛ ሲሆኑ ቼኩ በቂ ስንቅ የለውም በማለት የመታሁት እኔ ነኝ የባንኩ ኦፊሰሮች ቼኩን በተመለከተ ደውለው ተነጋግረው ነበር ምን እንደተነጋገሩ ግን አላወኩም ብለዋል፡፡ 3ኛየከሳሽ ምስክርም የባንኩ ሰራተኛ ሲሆኑ ከሳሽ ይዘው የመጡት ቼክ በሂሳቡ ገንዘብ አልነበረውም በዚህም ምክንያት ለተከሳሽ ደወልኩ ተከሳሽም ጠብቀኝ ብለው ስልኩ ተዘጋ ተከሳሽ ባንኩ ዘንድ መጥተውም ቼኩን ተሰርቄ ነው ለፖሊስ አመለክታለሁ ሲሉ ነበር በማለት መስክረዋል፡፡
1ኛ የተከሳሽ ምስክር ተከሳሽ ሲሆኑ በሰጡት የምስክርነት ቃል ቼኩን ለአቶ ዳንኤል የፃፍኩት ነበር በመንደር ውል ብር 400ሺህ አበድረውኝ የነበረ በመሆኑ አቶ ዳንኤል ቼኩን ከወሰዱ ከ1 ሰአት በኋላ ደውለው ቼኩ በስም ቦታ ብር የተፃፈበት በመሆኑ ችግር አለበት ና አሉኝ እኔም ሄጄ ቼኩን በመቀበል ቀየርኩላቸው የተቀበልኩትን ቼክም መኪና ውስጥ አደረኩት ከሁለት ወር በኋላ በ18/07/2010 ዓ/ም ከባንክ ሲደወል ነው ቼኩ የጠፋ መሆኑን ያወኩት በእለቱም ከከሳሽ ጋር ነበርን ለባንኩም የጠፋ ቼክ ነው እንዳትከፍሉ አልኳቸው ከባንክ እንደተነገረኝም ለፖሊስ አመለከትኩ ከዚህ በኋላ ነው ከሳሽ በ19/07/2010 ዓ/ም ሄደው ያስመቱት ከሳሽ የሴት ጓደኛ እጮኛዬ በመሆናቸው መኪና ውስጥ አብረን እንሄድ ነበር የንግድ ግንኙነት የለንም ብለዋል፡፡ 2ኛየተከሳሽ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል ለተከሳሽ በታህሳስ 27 ቀን በተደረገ የብድር ውል ብር 400ሺህ ሰጥቻቸው ተከሳሽ ቼክ ሰጡኝ ከተከሳሽ ጋር ከተለያየን በኋላ ቼኩን ሳየው ክፈል በሚለው ላይ ካሽ ከታች ደግሞ በፊደል ብር 400ሺህ ይላል ብር በሚለው ላይ አልተፃፈም ነበር ወጋገን ባንክ ሄደን ስጠይቅ መስተካከል አለበት ስላሉን ለተከሳሽ ደውዬላቸው የሰጡኝን ቼክ መልሼላቸው ሌላ ቼክ ሰጡኝ ያሉ ሲሆን 3ኛየተከሳሽ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል ከ2ኛየተከሳሽ ምስክር ጋር በእለቱ የነበሩ መሆኑን በመግለፅ 2ኛየተከሳሽ ምስክር ከሰጡት የምስክርነት ቃል ተመሳሳይ የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል፡፡ 4ኛየተከሳሽ ምስክር በበኩላቸው ከሳሽ የተከሳሽ ሴት ጓደኛ ናቸው ብዙ ጊዜ ሶስታችንም አብረን ምግብ እንበላ ነበር ተከሳሽም ከሳሽን በመኪና ይሸኟቸው ነበር ሲሉ መስክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም መዝገቡን እንደመረመረው ተከሳሽ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ ለከሳሽ ያልሰጡና የግል ግንኙኘት ሳይኖራቸው ከሳሽ ከቅን ልቦና ውጪ ያገኙት መሆኑን የማስረዳት ሸክም ያለባቸው ሲሆን በተከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ይህ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ ተከሳሽ ለነበረባቸው እዳ ለመክፈል አዘጋጅተውት የነበረ መሆኑንና ስህተት ያለበት በመሆኑም ተከሳሽ ቼኩን እንዲቀይሩላቸው ጠይቀዋቸው ሰጥተዋቸው ከነበረው ግለሰብ (2ኛየተከሳሽ ምስክር) ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ የተቀበሉ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ተከሳሽ ቼኩን ለ2ኛምስክራቸው የሰጠሁት የነበረ ነው ባሉበት በታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ/ም ም ከ2ኛምስክራቸው ጋር የብር 400ሺህ የብድር ውል ያደረጉ መሆኑን የሚያስረዳ የብድር ውል ስምምነት ያቀረቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ ቼኩን በተመለከተ የጠፋባቸው መሆኑን በመግለፅ በመጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ/ም ለፖሊስ ያመለከቱ ስለመሆኑ ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ ያረዳል፡፡
ከላይ ከተመለከትናቸው የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም ከቀረቡት ምስክሮች ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ክስ የቀረበበትን ቼክ ለመስጠት የሚያስችል ግንኙነት እንደሌላቸው ቼኩም ለ2ኛየተከሳሽ ምስክር ተሰጥቶ የነበረ መሆኑን ፍ/ቤቱ ለመገንዘብ የቻለ ሲሆን ከሳሽ ራሳቸው ቀርበው በሰጡት የምስክርነት ቃል ከተከሳሽ በብር 600ሺህ ለመግዛት ለተስማሙት ተሽከርካሪ ክፍያ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ የከፈሉና ለዋስትናም ይህንን ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሽ እንደሰጧቸው ተሽከርካሪውንም ተከሳሽ በስምምነቱ መሰረት ያላስረከቧቸው በመሆኑ ለተከሳሽ የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ክሱን ያቀረቡ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ሆኖም ከሳሽ ይህንን የሰጡትን የምስክርነት ቃል በሌላ ገለልተኛ በሆነ ምስክርም ሆነ የመኪና ሽያጭ ውል ከተከሳሽ ጋር አድርገው የነበረ መሆኑን በሰነድ ማስረጃ ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ገንዘቡን ለተከሳሽ ሰጠሁ ባሉበት ቀን ነበሩ በማለት የጠቀሷቸውን አቶ ይበቃል ገ/እግዚአብሔር የተባሉትን ግለሰብ እንኳን በማስረጃ ዝርዝር መግለጫቸው ላይ ያልጠቀሷቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ ቼኩ ከተመታ በኋላ ተከሳሽ የባንኩ ስራ አስኪያጁ ዘንድ ቀርበው እከፍላለሁ ብለው ድርድር ሲያደርጉ ነበር በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ከባንኩ ዘንድ የቀረቡት ምስክሮች በዚህ አግባብ ተከሳሽ ለመክፈል የተደራደሩ መሆኑን ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ይልቁንም 3ኛየከሳሽ ምስክር ተከሳሽ ባንኩ ዘንድ መጥተው ቼኩን ተሰርቄ ነው ለፖሊስ አመለክታለሁ ሲሉ እንደነበር የሰሙ መሆኑን ያስረዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ ከተከሳሽ ሊገዙት ያሉትን ተሽከርካሪ ተከሳሽ ይዘው መጥተው ያዩት መሆኑን እየገለፁ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሽን ውል እንዋዋል ስላቸው ችግር የለም መኪናው ገብቷል በማለት መኪናው ገና አገር ውስጥ ሳይገባና መኪናውን ሳያዩ ገንዘብ እንደከፈሉ በሚያስረዳ መልኩ የምስክርነት ቃል በስጠታቸው ሲታይም የሰጡት የምስክርነት ቃል እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ በዚህም ይህ በሆነበት አግባብ ከሳሽ ከተከሳሽ ለመግዛት ለተስማሙት ተሽከርካሪ ክፍያ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ የሰጡ በመሆኑ የተሰጣቸው ቼክ መሆኑን በመግለፅ ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚህም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ በተመለከተ ከተከሳሽ ጋር ባላቸው ግንኙነት የተሰጣቸው መሆኑን ከተከሳሽ በተሻለ ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ይህ ከሆነ ደግሞ በቼኩ የተመለከተው ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ሊጠይቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ በመስጠት ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ውሳኔ
- ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም፡፡
- ወጪና ኪሣራን በተመለከተ ከሳሽ ለተከሳሽ የጠበቃ አበል ብር 40,000 ፣ የቴምብር ቀረጥ ብር 10 ፣ ልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 1,000 ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡