የኮ/መ/ቁ 171664 - እንደራስ ናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና እንደራስ የንብረት አስተዳደር ኃ/የተ/የግል/ማህበር

የኮ/መ/ቁ 171664

የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- እንደራስ ናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ፡- ጠበቃ ጀሚላ ክብረት ቀረቡ

ተከሳሽ፡- እንደራስ የንብረት አስተዳደር ኃ/የተ/የግል/ማህበር ፡- ጠበቃ ከበደ ደራራ ቀረቡ

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ የካቲት 20 ቀን 2011 ዓ/ም  በተጻፈ ያቀረበዉ የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽ እንደራስ ናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር በሚል የንግድ ስም በ17/02/1998 ዓ/ም የተቋቋመ መሆኑን ይህ የከሳሽ ማህበርም የሪል እስቴትና ሌሎች ንብረቶችን የማስተዳደር፤ የንግድ እንደራሴነት ስራ፤ የሪልስቴት ልማት ስራዎች፤ የንብረት አቻ ግምት ስራዎች የሚሰራ መሆኑን፤ ከሳሽ የሚሰጣቸዉን አገልግሎቶች ከሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ለመለየት እንደራስ ናሽናልስ አሴት ማኔጅመንት የሚል ቃል እና ምስል ያለበት የንግድ ምልክት በአለም አቀፍ ምድብ 36 እንዲመዘገብለት ለኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት አመልክቶ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱ እንዳይመዘገብ ተቃውሞ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የተከሳሽ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጎ የንግድ ምልክቱ በምዝገባ ቁጥር LTM/3042/2009 ተመዝግቦ የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ሳለ ከሳሽ ባስመዘገበዉ የንግድ ምልክት የተካተተዉን ቃል እና ምስል በንግድ ስምነት የሚጠቀም መሆኑን እንዲሁም ከከሳሽ ጋር አንድ አይነት የሆነ የንግድ ስም የሚጠቀም መሆኑን እንዲሁም አሳሳች የንግድ ምልክት የሚጠቀም መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት በንግድ ስም ስያሜነት እና የንግድ ምልክትነት መጠቀሙን እንዲያቆም እንዲወሰንላቸዉ፤ በአዋጅ ቁጥር 40 መሰረት ካሳ ብር 400,000 እንዲከፈለላቸዉ፤ የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክርም ቆጥሯል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ደርሶ ተከሳሽ ሚያዚያ 1 ቀን 2010 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክትም ሆነ የንግድ ስም  ያልተጠቀመ መሆኑን፤ እንደራስ ከሚለዉ ቃል ውጪ የከሳሽ እና የተከሳሽ የንግድ ስም የማይመሳሰል መሆኑን ተከሳሽ የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች ከሳሽ ከሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች የተለዩ መሆናቸዉን፤ የተከሳሽ የንግድ ምልክት እንደራስ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎት ኃ.የተ.የግል ማህበር በሚለዉ የንግድ ስም እና የጣት አሻራ ምስል በቅንጅት የተፈጠረ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ተከሳሽ የከሳሽ የንግድ ምልክት እንዳይመዘገብ ያቀረበዉን ተቃውሞ ውድቅ አድርጎ የከሳሽን የንግድ ምልክት መመዝገቡ የከሳሽ እና የተከሳሽ  የንግድ ምልክቶች ተመሳሳይ ናቸዉ የሚል መደምደሚያ ላይ የማያደርስ መሆኑን፤ ከሳሽ የደረሰበትን ጉዳት ያላስረዳ መሆኑን፤ ከሳሽ እንዲከፈለዉ የጠየቀዉ ካሳ ከደረሰበት ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚገባ መሆኑን እንዲሁም የሮያሊቲ ክፍያ ለጉዳዩ አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዉ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸዉ ጠይቋል፡፡

ተከሳሽ እንድ መከላከያ መልሳችን ያስረዱልኛል ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡   

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም? ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የጉዳት ካሳ ሊከፍል ይገባል ወይስ አይገባም? እንዲሁም ተከሳሽ የሞራል ካሳ ሊከፍል ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ነጥቦች  እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡

የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ የሚከራከረዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት በንግድ ስምነት ስለተጠቀመ እና ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን ከሳሽ ከሚሰጠዉ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መሳከርን የሚያስከትል ስለሆነ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀም ሊወሰንልን ይገባል በማለት  ነዉ፡፡

ከከሳሽ ክርክር አንጻር ምላሽ ሊያገኝ የሚገባዉ ጉዳይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ስም እና የንግድ ምልክት ከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 501/2000 ያገኘዉን የብቸኝነት መብት (exclusive right) የሚጥስ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉ ሲሆን ይህ መልስ ከመስጠታችን በፊት የንግድ ስምን እና የንግድ ምልከት አገልግሎታቸዉ/ጥቅማቸዉ ምን እንደሆነ መለየቱ ተገቢ ነዉ፡፡

ከዚህ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 2(12) እንደተመለከተዉ የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰዉ ዕቃዎች ወይም አገለግሎቶቸ ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን የንግድ ምልክቱም ቃላቶችን፤ ዲዛይኖችን፤ ፊደሎችን፤ ቁጥሮችን፤ ቀለሞችን ወይም ዕቃዎችን ወይም የመያዣቸዉን ቅርጾች ወይም የነዚህን ቅንጅቶች ሊይዝ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

የንግድ ምልክትን ለመመዝገብም ስልጣን የተሰጠዉ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ስለመሆኑ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በአዋጅ  ቁጥር 980/2008 ዓ/ም አንቀጽ 2(10) እንደተደነገገዉ የንግድ ስም ማለት  አንድ ነጋዴ ለንግድ ስራዉ የሚጠቀምበት እና በህብረተሰቡ ዘንድ በግልጽ የሚታወቅበት ስም ነዉ በሚል ተደንግጓል፡፡ ማንኛዉም ነጋዴ የንግድ ስሙን በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ እንዳለበትም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ዓ/ም አንቀጽ 18(1) ተደንግጓል፡፡

የንግድ ስም የመመዝገብ ስልጣንም የንግድ ሚኒስቴር እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ስር ተመልክቷል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለዉ የንግድ ምልክት የሚያገለግለዉ የአንድን ድርጅት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚሰጡት አገልግሎት/ከሚያቀርቡት ዕቃዎች ለመለየት ሲሆን የንግድ ስም ደግሞ አምራቹ ወይም አገልግሎት ሰጪዉ አገልግሎቱን ወይም ዕቃዎቹን ለህበረተሰቡ የሚያቀርብበት ስም መሆኑን እንዲሁም ነጋዴው በንግድ ቦታዉ የንግድ ስሙን በሚታይ ቦታ መለጠፍ በህግ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከሳሽ በማስረጃነት ያቀረበዉ የንግድ ምልክት በምዝገባ ቁጥር LTM/3042/2009 E.C በኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት የተመዘገበ መሆኑን፤ ከሳሽም ከ22/9/2015 ዓ/ም አስከ 30/5/2023 እ.ኤ.አ ድረስ ለንግድ ምልክቱ ጥበቃ የተሰጠዉ መሆኑን የንግድ ምልከቱም ለንብረት አቻ ግምት ስራዎች ምድብ 36 የተመዘገበ መሆኑን የቀረበዉ የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት ያስረዳል፡፡ ይህም የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት በአዋጅ ቁጥር አንቀጽ 501/98 አንቀጽ 15 መሰረት የተሰጠ መሆኑን እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረበዉ የንግድ ምልክት ባለቤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የንግድ ምልክቱ የተመዘገበለት ሰዉ የንግድ ምልክቱን ከተመዘገበበት ዕቃ ወይም አገልግሎት  ጋር አያይዞ የመጠቀም ወይም ሌላ ሰዉ እንዲጠቀምበት የመፍቀድ መብት የሚኖረዉ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(1) ስር ተመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ምልከት ባለቤት የሆነ ሰዉ ሌሎች ሰዎች የንግድ ምልክቱን ወይም ህዝብን ሊያሳስት የሚችል ማናቸዉንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበባቸዉ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ወይም ህዝብን ሊያሳስት በሚችል አኳን ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ እንዳይጠቀሙ፤ የንግድ ምልክቱን ወይንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ ያለበቂ ምክንያቶች ጥቅሙን በሚጎዳ አኳኋን እንዳይጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለማገድ የሚችል ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 26(2)(ሀ)(ለ)(ሐ) የሚደነግግ ሲሆን አንድ አይነት መለያ ለአንድ አይነት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ሲውል የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት መውስድ የሚቻል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 26(3) ስር ተመልክቷል፡፡

ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረቡት የንግድ ምልክት ከላይ የተጠቀሱት የብቸኝነት መብት (exclusive right) ያላቸዉ መሆኑን መረዳት የሚቻል ሲሆን ከሳሽ የሚከራከሩት ተከሳሽ የንግድ ምልክቴን በንግድ ስምነት እየተጠቀሙ ነዉ እንዲሁም አሳሳች የሆነ የንግድ ምልክት እየተጠቀሙ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት እየፈጸሙ ይገኛሉ በማለት ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሽ የሚጠቀሙት የንግድ ምልክት አማካይ (average) የሆነ ተጠቃሚን ብንወስድ ተከሳሽ የሚጠቀምበት የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ሲነጻጸር በይዘትም፤ በቅርጽም እንዲሁም በአቀማመጡ ተመሳሳይ ነዉ ሊባል አይችልም እንዲሁም ተጠቃሚዉን ሊያሳስት የሚችል የንግድ ምልክት ነዉ ሊባል አይችልም፤ ከሳሽ ተከሳሽ በማስረጃነት ካቀረበዉ ውጭ ሌላ ከከሳሽ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ የንግድ ምልክት የሚጠቀም ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክትም ሆነ ስም በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(3) መሰረት ሊወሰድ የሚችለዉንም ግምት ሊያስወስድ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሽ አሳሳች የንግድ ምልክት ተጠቅሟል የሚለዉ ክርክር የከሳሽ የንግድ ምልክት እና የተከሳሽ የንግድ ምልክትን በማነጻጸር ከታየ መሳከርን ይፈጥራል ሊባል የሚችል ካለመሆኑም በላይ ከሳሽ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት ለንብረት አቻ ግምት ስራዎች ሲሆን የንግድ ምልክቱንም በብቸኝነት መጠቅም የሚችሉት ከዚሁ የንግድ ምልክቱን ካስመዘገቡበት አገልግሎት አንጻር እንጂ የከሳሽ ማህበር መመስረቻ ጽሁፍ ላይ ለተመለከቱት አላማዎች በሙሉ አይደለም፤ ተከሳሽ የሚሰራዉ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎት ሲሆን ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት ከዚህ አገልግሎት ጋር አልተጠቀሙም እንጂ ተጠቅሟል ቢባል እንኳን ከሳሽ ለዚህ አይነት አግልግሎት የንግድ ምልክቱን ባላስመዘገቡበት ሁኔታ ይህን መሰል ተግባር ሊከለከሉ የሚችሉበት የህግ አግባብ የለም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ በንግድ ምልክታቸዉ ላይ የሚጠቀሙት ስም እንደራስ የንብረት አስተዳደር አገልግሎት የሚል ሲሆን ለዚህም ተከሳሽ በቀን 25/12/2008 ዓ/ም የንግድ ስያሜዉን ያስመዘገቡ መሆኑን የቀረበዉ የንግድ ስም የምስክር ወረቀት ያስረዳል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት የለም እንጂ አለ እንኳን ቢባል ህጋችን የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም ግጭት በተፈጠረ ጊዜ እንዴት እንደሚፈታ ያስቀመጠዉ የህግ ማዕቀፍ ባይኖርም ተከሳሽ ይህን የንግድ ስም ያስመዘገቡት በቀን 25/12/2008 ዓ/ም መሆኑ ሲታይ በሌላ በኩል ከሳሽ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት እና የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ/ም ከመሆኑ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 17(1) የንግድ ስም በመዝገብ መግባት የንግድ ስሙን ለመጠቀም መብት የሚሰጥ ተቀዳሚ ማስረጃ ስለመሆኑ የሚያመለክት በመሆኑ እንዲሁም ተከሳሽ የንግድ ስማቸዉን በሚታይ ቦታ መለጠፍ ግዴታ ያለባቸዉ ከመሆኑ አንጻር ተከሳሽ እንድራስ የንብረት አስተዳደር አገልግሎት የሚለዉን ቃል የሚጠቀሙት ከቅን ልቦና  ውጪ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ እንዲሁም ከሳሽ ተከሳሽ የንግድ ስማቸዉን የተጠቀመ ስለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጃ የለም ናሽናል አሴት ማኔጅመንት በሚለዉ ቃል ላይም የብቸኝነት መብት የላቸዉም፡፡ እንደራስ የሚለዉን ቃል ላይም የብቸኝነት መብት ያላቸዉ ንግድ ምልክቱን ካስመዘገቡበት የንብረት አቻ ግምት ስራዎች ጋር በተያያዘ  ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር  ሌሎች ሰዎች እንደራስ የሚለዉን ቃል ከንብረት አቻ ግምት ስራዎች ውጭ ላሉ አገልግሎቶች እንዳይጠቀሙ የመከልከል እና የማስከልከል በህግ ጥበቃ የተሰጣቸዉ መብት የለም፡፡

ከሳሽ አጥብቀዉ የሚከራከሩት የንግድ ምልክቱ ሲመዘገብ ተከሳሽ ተቃውሞ አቅርቦ ወድቅ ተደርጎበታል፡፡ በመሆኑም በንግድ ምልክቱ መጠቀሙ የብቸኝነት መብቴን የሚጥስ ስለሆነ አግባብነት የለዉም በማለት ነዉ፡፡ እዚህ ጋር መታየት ያለበት ነጥብ ተከሳሽ ከሳሽ የንግድ ምልክቱ እንዲመዘገብላቸዉ ለአእምሮዊ ንብረት ባመለከቱ ጊዜ የንግድ ምልክቱ እንዳይመዘገብ ተቃውሞ አቅርበዉ የነበረ ቢሆንም ያቀረቡትን መቃወሚያ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት በጽ/ቤት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ ማለት ከሳሽ የንግድ ስሙን መጠቅም አይችልም ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የንግድ ስሙን የመዘገበዉ በአዋጅ ስልጣን ያለዉ አካል የንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ እና የንግድ ምልክቱ ስለተመዘገበ የንግድ ስሙ ላይ የበላይነት (priority clause) ሊኖረዉ እንደሚችል የሚያስቀምጥ የህግ ማዕቀፍ የሌለ በመሆኑ ነዉ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያዊ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት በአዋጅ በተሰጣቸዉ ስልጣን መሰረት ላከናወኑት ተግባር አንዱ በሌላኛዉ ላይ የበላይ የሚሆንበትም አግባብ የለም፡፡

ከሳሽ ያቀረባቸዉ ማስረጃዎች ማለትም የአገልግሎት ክፍያ የተከፈለባቸዉ ደረሰኞች፤ የከሳሽ ማህበር መመሰረቻ ጽሁፍ፤መተዳደሪያ ደንብ፤ ከሳሽ አግልግሎታቸዉን በጋዜጣ ያስተዋዋቀባቸዉ ጋዜጦች፤ ለማስተዋቂያ ስራ የተደረገ ስምምነት፤ ተከሳሽ የከሳሽ የንግድ ምልክት እንዳይመዘገብ ያቀረቡትን አቤቱታ፤ ከሳሽ ግብር የከፈሉ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎች የቀረቡ ቢሆንም እነዚህ ማስረጃዎች የከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥስት የተፈጸመ መሆኑን አያስረዱም ለተያዘዉ ጉዳይም አስረጂነት የላቸዉም፡፡ 

ሲጠቃለልም ከሳሽ ተከሳሽ የንግድ ስሙን የተጠቀመ ስለመሆኑ በማስረጃ ያላረጋገጠ በመሆኑ፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይነት የሌለዉ በመሆኑ፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት አማካይ የሆነ ተጠቃሚን ሊያሳስት የሚችል ባለመሆኑ፤ ከሳሽ እና ተከሳሽ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን የማያሳክር በመሆኑ፤ ከሳሽ የንግድ ምልክታቸዉን ያስመዘገቡት ለንብረት ግምት አቻ ስራዎች ስለሆነ በንግድ ምልክቱ ላይ ያላቸዉም የብቸኝነት መብት ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በመሆኑ፤ ከሳሽ እንዳራስ የሚለዉን ቃል በብቸነት ሊጠቀሙ የሚችሉት የንግድ ምልክቱን ካሰመዘገቡበት የንብረት ግምት አቻ ስራዎች ጋር በተያያዘ ብቻ በመሆኑ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች እንደራስ የሚለዉን ቃል ለሌሎች አገልግሎቶች መጠቀም እንዳይችሉ ለመከልከል የሚያስችል መብት በህግ ስላልተጠበቀላቸዉ ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ስምም ሆነ የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት አልፈጸምም በማለት ፍርድ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

2ኛ እና 3ኛዉን ነጥቦችን በተመለከተ ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ስም እና የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት ያልፈጸሙ መሆኑ ስለተረጋገጠ መመርመር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡

ዉሳኔ

  • ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም ላይ ጥሰት አልፈጸመም ተብሏል፡፡
  • ተከሳሽ በከሳሽ ላይ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅርብ መብቱ ተጠብቋል፡፡

ትዕዛዝ

              ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡

              መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት

 

 

Leave a comment