ልደትና ሞት ጋብቻና ፍቺ የሰው ልጅ ሕይወት የሚጀመርባቸውና የሚጠናቀቅባቸው እንዲሁም የሚያልፍባቸው የሕይወት ኩነቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ ወሣኝ ኩነት በመባል የሚታወቁት የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ክስተቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ክስተቶች ወሣኝ ኩነቶች የተባሉበት ዋናው ምክንያት በየአገሮች ሕገ-መንግሥትና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የታወቁ የሰብዓዊ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ መብቶችን ተፈጻሚ ለማድረግና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆኑ ሕጋዊ የግለሰብ ማንነት መረጃዎች ምንጭ በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ኩነቶቹ የአንድን አገር ሕዝብ ብዛትና ዕድገትን በትክክል ስለሚያሳዩ፣ ለኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለሚዘጋጁ ዕቅዶች ዝግጅትና አፈጻጸም እስከ ዝቅተኛው አስተዳደር ክፍል አልፎም በግለሰቦች ደረጃ ተፈላጊና ወሳኝ መረጃዎች በመሆናቸው ወሳኝ ኩነት ተብለዋል፡፡