የጉዳዩ መነሻ
ለዚህ አጭር ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 74950 የሰጠዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ጉዳዩ የገንዘብ ብድርን ይመለከታል፡፡ ተበዳሪ ከአበዳሪ በታሕሳስ 26 ቀን 1995 የተወሰደዉን ብር 237000.00 በጥር 30 ቀን 1995 ለመመለስ ቃል ገብቷል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን ሳይመልስ በመቅረቱ የአበዳሪ ወራሾች በተበዳሪ ላይ ሐምሌ 21 ቀን 2002 ባስገቡት ክስ ተበዳሪ ዋናዉን ገንዘብ እንዲመልስና ከየካቲት 01 ቀን 1995 መሰረት የሚታሰብ ወለድም እንዲከፍል ዳኝነት ይጠይቃሉ፡፡ ተበዳሪ በበኩሉ በዉላቸዉ ዉስጥ ወለድ ይከፍላል የሚል ቃል እንደሌለና ማስታወቂያ/ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጠዉ ወለዱን መክፈል እንደማይገደድ ይከራከራል፡፡ በዚህ ሙግት የተነሳዉና ይህ ጽሁፍ የሚዳስሰዉ ጥያቄም ይኸዉ ነዉ፤ ያልተመለሰ የገንዘብ ብድር ያለስምምነትና ያለማስታወቂያ/ያለማስጠንቀቂያ ወለድ ይቆጥራል?