ሕገ መንግሥት በባሕርይው ጠቅላላ ድንጋጌዎችን የሚይዝ በመሆኑ፤ ሕገ መንግሥትን ከተለዋወጭ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር ለመጣጣም እና ዘላቂነት ኖሮት ገዚ ሆኖ እንዲኖር ያስችል ዘንድ ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሲባል የተፃፉ ሕገ-መንግሥት ያላቸው ሀገራት በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ማሻሻያ ሥርዓቶችን ወይም ማስተካከያ የሚደረግበት ሂደት የሚደነግጉ አንቀጾችን አካተው ይይዛሉ፡፡ በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥትም እንዴት እንደሚሻሻል የማሻሻያ ሥርዓቶቹን በአንቀጽ 104 እና 105 ስር ተደነግጎ ቢገኝም እስካሁን ድረስ ሥርዓቶቹን ተከትሎ ማሻሻያ ሳይደረግበት ቆይቷል።  

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴን ታህሳስ 9 2014 ዓ.ም ለቱርኩ አናዶል ኤጀንሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲያጨቃጭቁ የቆዩ ጉዳዪች ላይ ምክክር ማድረግና ለሕዝበ ውሳኔ በማቅረብ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልን ጨምሮ ሁሉን አካታች ሀገራዊ የምምክር መድረክ ለማካሄድ መታቀዱን ተናግረዋል።  በተመሳሳይ መልኩ የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድም የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ምክክር እንደሚደረግ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሰረትም አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ የታመነበት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክር ኮሚሽን መቋቋሚ አዋጅ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ነግር ግን የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓቶች እጅግ ውስብስና ጥብቅ (very stringent and rigid) ስለመሆናቸው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል የገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጉዳይ መዳሰስ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በገለፀው መሠረት የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥትን እጅግ ውስብስና ጥብቅ የሆነውን ማሻሻያ ሥርዓትን በመከተል ለማሻሻል ይቻላል ወይ? የሚለውን ጥያቄ በማጤን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105ን ሥር የተቀመጡትን እጅግ ውስብስና ጥብቅ የሆነውን ሂደቶች በመከተል ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የማይቻል መሆኑን በበቂ ምክንያት በማሳየት፤ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(4፣ሐ) መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት አንቀጽ 104 እና 105 የሚገደቡ ድንጋጌዎች ስለሆኑ በመጀመርያ ሕገ-መንግሥት ስለሚሻሻልበት የሚደነግገውን አንቀጽ (አንቀጽ 104 እና 105ን) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገድቦ በማሻሻል ቀላል የማሻሻያ ሥርዓትን በመደንገግ፣ ከዚያ በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ስምምነት ላይ የሚደረስባቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ማሻሻል  ሕገ መንግሥቱን በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ለማሻሻል የሚያስችል ብቸኛው መንገድ ስለመሆኑ የሚያመለክት የመፍትሄ ሐሳብ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ነው፡፡

2. የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓቶች በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ መንግሥት

የኢፌድሪ ሕግ መንግሥት በአንቀጽ 104 እና 105 ሥር ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል የሚችልበትን ሥርዓቶች ደንግጓል፡፡ አንቀጽ 104 የማሻሻያ ሀሳብ ስለሚመነጭበት ሥርዓት የያዘ ሲሆን አንቀጽ 105 ደግሞ ማሻሻያው የሚያልፍባቸውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቶችን ዘርዝሮ ይዟል።

2.1 የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ ስለማመንጨት

ሕገ መንግሥቱ የማሻሻያ ሀሳብን ማመንጨትን በሚመለከት አንቀጽ 104 ሲገልፅ “አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ የደገፈው፣ የፌድሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ የደገፈው ወይም ከፌድሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሶስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፈት ከሆነ ለወይይትና ለሕዝበ ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕግ መንግሥቱ ማሻሻያ ለሚመለከተው ክፍሎች ይቀርባል” በማለት ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብን ለምክር ቤቶቹ የሚያቀርበው ማን እንደሆነ በግልጽ በድንጋጌው ያልተቀመጠ ሲሆን፣ የማሻሻያ ሀሳቡ በፌደራል ደረጃ (በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በፌድሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲደገፍ) ወይም በክልል ደረጃ (ካሉት 11 ክልሎች ቢያንስ የ4 ክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ) ሲፀድቅ ወደ ሚቀጥለው ሂደት ሊገባ ይችላል፡፡

 

2.2 ማሻሻያውን ለወይይት እና ለሕዝበ ለውሳኔ ለመላው ሕዝብ ማቅረብ

የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ሀሳብ በፌደራል ደረጃ ወይም በክልል ደረጃ ቀርቦ ከጸደቀ የሚቀጥለው ስነ-ሥርዓት ማሻሻያው ለወይይት እና ለሕዝበ ለውሳኔ (referendum) ለመላው ሕዝብ እንደሚቀርብ በአንቀጽ 104 ሥር ተቀምጧል፡፡ “ወይይት” ምን ማለት እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚመራ፣ በማን እና በማን መሀላ ውይይት እንደሚደረግ፣ የወይይቱ ውጤት ምን እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያልተመላከተ ሲሆን፣ “ሕዝበ ውሳኔ” በተመለከተ ግን በአዋጅ ቁ.1162/2012 መሠረት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያዘጋጀው የሕዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት ምርጫ የሚመራ ይሆናል፡፡

“ሕዝበ ውሳኔ” ማለት በኢ.ፌ.ደ.ሪ. ሕገ መንግሥት ወይም አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት ሲወሰን የህዝብ ፍላጎትን ለመለካት ወይም የህዝብን ውሳኔ ለማወቅ የሚደረግ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ነው፡፡ (አዋጅ 1162/2012 አንቀጽ 2(10)

በዚሁ መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ምርጫ ቦርድ በሚያከናውነው የሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ከጸደቀ እና “ወይይት” ከተደረገበት ቡሃላ የማሻሻያ ሀሳቡ በአንቀጽ 104 መሠረት ተቀባይነት አግኝቷል ተብሎ ወደ ማሻሻያ ሂደት ይታለፋል፡፡ ቢሆንም በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት መሻሻያ ሀሳቡ በሚመለከተው አካል ሳይጸድቅ ማሻሻያ ሀሳቡ ላይ “ወይይት” ማድረጉን ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም፡፡ በመሠረቱ ውይይት (discussion or deliberation) ሕገ መንግሥት የሚረቅበት ወይም የሚሻሻልበት ሂደት ሲሆን ሂደቱም የማሻሻያ ሀሳብ ማመንጨት(initiation) ቀጥሎ የሚመጣ ሥርዓት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ሕዝቡ ወይም ፖለቲካ ሊሂቃኖች ስለማሻሻያ ቀድመው ተወያይተው ከተስማሙ ወደ ማሻሻያ ሀሳብ ማቅረብ የሚገቡበት ወይም ወደ ማሻሻያ ሂደት ሊገባ የሚችልበትን ሥርዓትን አላስቀመጠም፡፡ በዚህ መሠረት በብሄራዊ ምክክር አዋጁ በጸደቀው ኮሚሽን አማካኝነት ሊካሄድ የታሰበው ምክክር ወይም ውይይት ስለ ሀገ መንግሥታዊ ማሻሻያው አስፈላጊነት መግባባት ላይ ለመድረስ ወይም አዲስ ሕገ-መንግሥት ለማዘጋጀት ካልሆነ በቀር እንደ ማሻሻያ ሂደት ሊወሰድ የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ስነ-ሥርዓት የለም፡፡ ካለም “ከፈረሱ ጋሪው” መቅደሙን ያሳያል፡፡

 

2.3 የሚሻሻልበት ሂደቶች ወይም ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል

መሻሻያው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ማሻሽያ ሂደት በሚገባበት ወቅት በአንቀጽ 105 መሠረት የሚሻሻሉት ድንጋጌ አይነቶችን ላይ በመመርኮዝ ሁለት አይነት መስፈርቶች ተቀምጧል፡፡ ይህም በአንቀጽ 105 ንዑስ ቁጥር አንድ መሠረት በሕገ መንግሥቱ ምህራፍ ሶስት ሥር የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፣ እና የሕገ ምንግስቱን ማሻሻያ የሚመለከቱ ድጋጌዎች (አንቀጽ 104 እና 105) ሊሻሻሉ የሚችሉት ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ማሻሻያውን በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት እና የፌደራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው እንዲሁም የፌድሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ብቻ ነው፡፡

በአንቀጽ 105(2) መሠረት ደግሞ ከሰባዊ መብት ድንጋጌዎች እና ከአንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ሌሎቹ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌድሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁትና ከፌድሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሶስተኛው አባል ክልል ምክር ቤቶች (ማለትም ከአስራ አንዱ ክልሎች ውስጥ ከሰባት ክልሎች ባላይ) በድምፅ ብልጫ ሲያጸድቁት ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

3. ሕገ መንግሥቱን በአንቀጽ 104 እና 105 ሥር የተቀመጠው ሥነ-ሥርዓቶችን ተከትሎ ማሻሻል ይቻላል?

በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ምንም መሻሻያ ሳይደረግበት 27 አመታትን ያስቆጠር ሲሆን፣ በአንጻሩ የአሜሪካን ሕገ-መንግሥት በ1788 የተፈረመውን የመጀመሪያውን ሰነድ ባለፉት ዓመታት ከ 11,623 ጊዜ በላይ ማሻሻያዎች ላይ በሴኔቱ ለውይይት ቀርቦ ለማሻሻል እርምጃ ለመውሰድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ለ 27 ጊዜ ተሻሸሏል፡፡ (ሮበርት ሊንሊ፡ የአሜሪካንን ሕገ-መንግሥት ማሻሻል) በሀገራችን በርካታ መሠረታዊ በሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን የሚሹ ጉዳዮች፡- ከሰንደቅ አላማ እስከ የስራ ቋንቋ፣ ከመሬት ፖሊሲ እስከ የምርጫ ሥርዕቱ፣ ከአገር መንግሥት ግንባት ሂደቱ እስከ የመንግሥት አወቃቀር ቅርጽ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እስከ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እና መሰል ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች እና አለመግባባቶች ያሉ ስለመሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ በነዚህ እና በሌሎች ሕገ መነግስታዊ ማሻሻያ የሚሹ ጉዳዮች ላይ በተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክር ኮሚሽን በኩል ሀገር አቀፍ ምክክር እና ወይይት እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ በሚደረገው ብሄራዊ የምክክር መግባባት ላይ ቢደረስ እንኳን በተጨባጭ ባለው ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 ሥር በተቀመጠውን ስነ-ሥርዓት ተከትሎ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የሚችል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም፡-

 

1ኛ. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 መሠረት የማሻሻያ ሃሳቡ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ለመላው ሕዝብ ለማቅረብ የማያስችል ሁኔታ የሌለ ስለመሆኑ፡-

በአንቀጽ 104 መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ሀሳብ በፌደራል ደረጃ ወይም በክልል ደረጃ ቀርቦ ከጸደቀ የሚቀጥለው ስነ-ሥርዓት ማሻሻያው ለወይይት እና ለሕዝበ ለውሳኔ (referendum) እንደሚቀርብ ተደንግጓል፡፡ ሕዝበ ውሳኔ በሁሉም ሐገሪቱ ክፍል ለመላው በአዋጅ ቁጥር 1162/2012 መሠረት በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ለምርጫ የሚቀርብ በመሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ ባለው የሰጥታ ችግር ምክንያት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንኳን የሕዝበ ውሳኔ ምርጫን በመላው ሀገሪቱ ክፍል ማድረግ ቀርቶ 6ኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫን በመላው ሀገሪቱ አከባቢ ማድረግ አልቻለም፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በቤንሻንጉል ክልል በከፊል ምርጫ አልተደረገም፡፡ ስለዚህ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል የሚለው መላምት እንደተጠበቀ ሆኖ፤  የማሻሻያ ሀሳቡ በሚመለከተው አካል ቢጸድቅ እንኳን ሕዝበ ውሳኔው በመላው የሀገሪቱ ክፍል ሳይደረግ እና በአብላጫ ድምጽ ሳይጸድቅ አንቀጽ 105 ሥር ወደ ተዘረዘረው ማሻሻያ ሂደት መግባት አይቻልም፡፡ በዚህ መሠረት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ክልል መካከል ባለው ጦርነት ምክንያት ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ውስጥ ምርጫ እንኳን ማከናወን ሳይችል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ማድረግ የሚችልበት እድል አለ ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫው በአስሩም ክልሎች ቢደረግ እንኳን በትግራይ ክልል ሳይደረግ ሊታለፍ እና ወደ ማሻሻያ ሂደት ሊገባ የሚችልበት ሕገ መንግታዊ አግባብ ስለማይኖር፣ ገና ከጅምሩ ወደ ማሻሻያ ሂደት ሳይገባ የማሻሻያ ሃሳቡ ላይ የማሻሻያው ተስፋ የሚደናቀፍ ይሆናል፡፡

2ኛ. በአገሪቱ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአንቀጽ 105 ሥር የተቀመጠውን ሂደት ተከትሎ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ስለመሆኑ፡-

አንቀጽ 104 መሠረት የመሻሻያ ሀሳቡ ቢጸድቅ እና ወደ ማሻሻያ ሂደቱ ቢገባ እንኳን በአንቀጽ 105 መሠረት ሕገ-መንግሥት ማሻሻያው በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢጸድቅ ከፌደሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንዱ ክልል ምክር ቤት ቢቃወመው አንቀጽ 104 እና 105 እንዲሁም ምዕራፍ ሶስት ሥር ያሉ ድንጋጌዎችን ማሻሻል አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ውስጥ  ቢያንስ ትግራይ ክልል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከተ ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ላይ ያለ ሲሆን፣ ክልሉ ከፌድራል መንግሥቱ ጋር ባለው የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ማሻሻያውን ቢያጸድቁት እንኳን የትግራይ ክልል ምክር ቤት ማሻሻያውን ሊቃወም የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ በመሆኑ፣ አንቀጽ 104 እና 105 እንዲሁም ምዕራፍ ሶስት ሥር ያሉ ድንጋጌዎች ማሻሻል ፈጽሞ አዳጋች ይመስላል፡፡ በሌሎች ክልሎችም ቢሆን ሀገሪቷ ውስጥ በሚታየው የተራራቀ ፍላጎትና አስተሳሰብ ምክንያት የሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ማሻሻያውን ባያጸድቁት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ መረዳት የሚቻው በተጨባጭ አንቀጽ 104 እና 105 ሥር በተቀመጠው የማሻሻያ ሂደት መሠረት ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ምሁራን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥትን ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ማሻሻል አይቻልም የሚሉት፡፡ ስለዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሺያውን ውስብስብ እና አስቸጋሪ እንዲሆን ያደረገውን አንቀጽ 104 እና 105 በቅድሚያ ማሻሻል አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የድንጋጌዎቹ መሻሻል የሁሉን ክልል ምክር ቤቶች ይሁንታን የሚፈልግ በመሆኑ፣ በመጀመሪያ አንቀጽ 104 እና 105ን እንዴት ማሻሻል ይቻላል የሚለው ነጥብ በሚከተለው ክፍል ውስት ለማየት እንሞክራለን፡፡

4. ብቻኛው መፍትሔ፡ በመጀመርያ ሕገ-መንግሥት ስለሚሻሻልበት የሚደነግገውን አንቀጽ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገድቦ ማሻሻል ከዛ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል

ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይችል ሲሆን የፌደራሉ መንግሥት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(1፣ሀ) ሥር ተደንግጓል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ እንቀፅ 93(4፣ሐ) መሠረት ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የሚያመጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39(1፣2) የመገደብ ሊሆኑ እንደማችሉ ተደንግጓል፡፡ ይህም ከአንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39(1፣2) ውጪ አንቀጽ 104 እና 105ን ጨምሮ ሎሎች ሰባአዊ፣ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲዊ መብቶችና ሌሎች የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊገደቡ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ አንቀጽ 104 እና 105 ሥር የተደነገገው የሕገ-መንግሥቱ ማሻሻያ መስፈርቶች ሊገደቡ ስለሚችሉ ድጋጌዎችን በማገድ አሻሻሎ ቀላል የማሻሻያ ሥርዓቶችን ለመደንገግ ያስችላሉ፡፡ 

የሚነስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ የታወጀው በሀገር ህልውና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 5/2014 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ የሚያወጣቸው መመሪያዎች፣ የሚወስናቸው ውሳኔዎች እና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(4፣ሐ) ሥር የተደገጉትን ሊታገዱ የሚችሉ ድንጋጌዎችና መብቶችን ማክበር እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ይህም ከአንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39(1፣2) ውጪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዙ ሎሎቹን የሕገ መንግሥት ድጋጌዎችን የመገደብ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሠረት ምንም እንኳን   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 5/2014 የያዝነውን ጉዳይ ለመፍታት ታልሞ ባይወጣም፣ አዋጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዙ አንቀጽ 104 እና 105 ለማገድ የሚያስችል መመሪያ ከማውጣት የሚያግደው አይደለም፡፡ ይህ ካልሆነም ሀገሪቷ ውስጥ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ያስገደደው ሥር የሰደደ ችግር “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚጥል ሁኔታ” በሚል ማዕቀፍ ውስጥ አዲስ የአስቸኳይ አዋጅን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በማውጣት አንቀጽ 104 እና 105ን መገደብ ይችላል፡፡

ስለዚህ በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ 104 እና 105 ለማገድ የሚያስችል መመሪያ በማውጣት ተፈጻሚነቱን ሊታገድ ይገባል፡፡ ሲቀጥል የሀገሪቱ ፖርላማ የአለም አቀፍ እና የሌሎች ሀገራት ተመኩሮ እንዱሁም የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታን ግምት ውስት በማስገባት ቀላል እና ምቹ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሺያ ሥርዓቶችን በመወሰን የአንቀጽ 104 እና 105ን ማሻሻያን የሚደነግግ አዋጅ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ በአንቀጽ 104 እና 105 ላይ በሚደረገው ማሻሻያም ለምሳሌ በሕዝብ ውሳኔ ማድረጉ ቀርቶ እንዲሁም የሁሉንም የክልል ምክር ቤቶችን ውሳኔ መጠበቅ ቀርቶ ሕገ-መንግሥት ማሻሻያው ላይ በአብላጫ ክልልች ውሳኔ ወይም በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ አንዲወሰን ማድረግ ወይም ሌላ ቀላል የሆነ ሥርዓትን መወሰን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛም በሚደረገው ሀገረ አቀፍ ምክክር ስምምነት ላይ የሚደረስባቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ድንጋጌዎች ማሻሻል ይቻላል፡፡ ይህ አማራጭ በተግባር በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ባለው መሠረት በብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኩል ሀገራዊ ምክክክር እና ውይይት ተደርጎበት ስምምነት ላይ ቢደረስ እንኳን በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ ጉንጭ ከማልፋት ወጪ ከንቱ ድካም ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ይህን ጽሑፍ እንደ ግብዓት በመጠቀም ቢተገብረው ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለው፡፡