ስለ ንብረት የዋጋ ግምት ጥቂት ነጥቦች

 

ለፍርድ ቤቶች በሚቀርቡ ክርክሮች ላይ የንብረትን ትክክለኛ የዋጋ ግምት ማወቅ የግድ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያቶች አሉ፡፡ ለመሆኑ የንብረት የዋጋ ግምት ማወቅ ለምን ያስፈልጋል? የንብረት የዋጋ ግምት ተገምቶ እንዲቀርብ የሚጠይቁ ሕጎች የትኞቹ ናቸው? የንብረት የዋጋ ግምት የመገመት ኃላፊነት በሕግ የተሰጠው ለማን ነው? በአሠራር ደረጃ የንብረት የዋጋ ግምት በማን እና እንዴት እየተገመተ ይገኛል? የንብረት ዋጋ ግምትን አስመልክቶ የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው? የንብረት የዋጋ ግምት ሲሰራ በመሠረታዊነት ሊካተቱ የሚገባቸው ነጥቦችስ ምንድን ናቸው? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች በዚህ ፅሁፍ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡        

 1. የንብረት የዋጋ ግምት ማወቅ ለምን ይጠቅማል?

የንብረት የዋጋ ግምት ማወቅ የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፡፡ እነዚህም፡ -

 • ፍትሐዊና ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት እንዲቻል፤
 • የፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣን ለመወሰን እንዲቻል፤
 • ለፍርድ ቤቶች ተገቢውን የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ለማከፈል፤
 • ጥፋተኛ ተብለው በወንጀል የሚፈረድባቸው ሠዎች ላይ ተመጣጣኝና የተገኘውን ልተገባ የጥቅም መጠን ወይም የደረሰውን የጉዳት መጠን መሠረት ያደረገ ቅጣት ለመወሰን ነው፡፡
 1. ተከራካሪ ወገኖች የንብረት ዋጋ ግምት መጠን እንዲጠቅሱ የሚጠይቁ ሕጎች የትኞቹ ናቸው?
 • ክስ የሚቀርበው አንድን ንብረት ለማስለቀቅ ወይም ከአንድ ንብረት ላይ ድርሻ ለመጠየቅ በሆነ ጊዜ ክስ የቀረበበትን ንብረት ወይም የንብረቱን ወይም ከንብረቱ ላይ የሚገኘውን የድርሻ የዋጋ ግምት በክስ አቤቱታ ላይ ሊጠቀስ እንደሚገባ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 222 /1/ /ቀ/ እና 226 /3/ /4/ ላይ ይጠይቃል፤
 • የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም በወጣው በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 11 /1/ እና 14 መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋጋ ግምታቸው ከብር 500,000.00/አምስት መቶ ሺሕ/ በላይ የሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን እንዲሁም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዋጋ ግምታቸው ከብር 500,000.00/አምስት መቶ ሺሕ/ በታች የሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን አከራክረው የመወሰን ሥልጣን ተሠጥቷቸዋል፡፡ ተከራካሪ ወገኖችም የሚያቀርቡትን የገንዘብ ወይም የንብረት ክርክር የዋጋ ግምት በክሳቸው ላይ መግለፃቸው የፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣን የሚወስን በመሆኑ በአዋጁና በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት በዳኝነት የሚጠይቁትን የገንዘብ መጠን ወይም የንብረት የዋጋ ግምት የመጥቀስ ግዴታ ተጥሏል፤
 • ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በወጣው የ1945 ዓ.ም. አስራ ሁለተኛ ዓመት ቁጥር 15 የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 177 መሠረት ከሳሽ የሆነ ወገን ዳኝነት በሚጠይቅበት ገንዘብ መጠን ልክ ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ሊከፍል እንደሚገባና ተመኑም ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም አንድን ንብረት አስመልክቶ የፍትሐብሔር ክስ የሚያቀረብ ሠው ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት የአገልገሎት ክፍያ አከፋፈል እንዲያመች የንብረቱን የዋጋ ግምት በክስ አቤቱታው ላይ የመግለፅ ግዴታ አለበት፡፡
 • የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የተሻሻለው የቅጣት አወሳስን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት በፍርድ ጥፋተኛ በተባሉ ሠዎች ላይ ቅጣትን ለመጣል በወንጀል ድርጊት የተገኘውን የንብረት ጥቅም ግምት ወይም የደረሰውን የንብረት ጉዳት ግምት ማወቅ አስፈላጊ ከመሆኑም ባለፈ የተጠቀሰው ሕግ የንብረት የዋጋ ግምት መጠን ላይ ክርክር ከተነሳበት የዋጋ ግምቱ ተለይቶ እንዲጠቀስና እንዲቀርብ ይጠይቃሉ፡፡    
 1. በሕጉ መሠረት የንብረት የዋጋ ግምት ላይ ክርክር ከቀረበ ግምቱን የሚገምተው ማን ነው? የግምት ሥራውስ እንዴትና በምን መመዘኛ ይሰራል?

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 250 መሠረት ከተከራካሪ ወገኖች መካከል አንደኛው የሚያቀርበውን የዋጋ ግምት ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በዋጋ ግምቱ ባለመስማማት ሊቃወም እንደሚችልና የግምት ክርክር ከተነሳ ደግሞ ፍርድ ቤቶች የሀብቱን ወይም የንብረቱን የዋጋ ግምት በመገመት ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቁ ምትክ ዳኞችን በመሾም ሊያስገምቱ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ 

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ የንብረት ዋጋ ግምት እንዲገምቱ የሚሾሙ ምትክ ዳኞችም የንብረት ዋጋ ግምቱን ምንን መሠረት በማድረግና እንዴት እንደሚከናወኑ የሚያመለክተው ነገር ባይኖርም ምትክ ዳኞቹ የግምት ሥራ ሲሰሩ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 132 እስከ 135 በተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችና የአሠራር ሥርዓት መሠረት የዋጋ ግምቱን ገምተው ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

Continue reading
  15621 Hits