- መግቢያ
ሰዎች ንብረታቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ አንድን ግዴታ ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል ስምምነት ሲፈፅሙ ውል እንዳደረጉ ከኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ህግ ቁጥር 1675 መረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ውል ከተደረገ በኋላ በአንደኛው ወይም በሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች ላይ ግዴታን ይጥላል፡፡ ይህንን ግዴታ በተባለው ጊዜ አለመፈፀም ወይም ጊዜ ካልተቀመጠ ደግሞ ማዘግየት የሚያስከትለውን ኪሳራ በተመለከተ ተዋዋይ ወገኖች ገደብ ወይም ቅጣት ወይም አንድ የተወሰነ ወለድ ግዴታውን ያልፈፀመ ተዋዋይ ወገን ውሉን ላከበረው ወገን እንዲከፍል ሲዋዋሉ መመልከት ወይም በፍርድ ቤቶች ሲወሰን ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወለድና የወለድ ወለድ (Interest on interest or compound interest) አስተሳሰብ ደንቦችን በተመለከተ እና ተያያዥ ጉዳዮችን የኢትዩጵያ ህጎች ላይ ተመስርተን በጨረፍታ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡
- ትርጓሜ
ወለድ የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ስንመለከተው አንድ ገንዘብ ያበደረ ሰው ተበዳሪው ብድሩን በመጠቀሙ ላበዳሪው ወገን በበኩሉ የሚከፍለው ወይም አንድ የባንክ ደንበኛ ያለውን ገንዘብ በአንድ ባንክ ገንዘብ ተቀማጭ ሲያደርግ በመቶኛ የሚታሰብ ገንዘብን የሚመለከት ወይም ተበዳሪ የወሰደውን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፈል የገንዘብ ካሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወለድ ለገንዘብ ብድር ብቻ የሚከፈል ሳይሆን አንድ ግዴታን ባለመፈፀም ወይም በማዘግየት እና ይሄ ፍሬ ነገር ሲረጋገጥ የሚከፈል ጭምር ነው፡፡ በተጨማሪም ወለድ በስምምነት ወይም ያለስምምነት ማለትም በህግ አግባብ ሲወሰን ሊከፈል የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ዓላማ ሲባል በመቶኛ የሚታሰበውን ገንዘብን በሚመለከት ብቻ ያለውን እናያለን፡፡
የወለድ ወለድ ማለት በሚከፈል ወለድ ላይ በስምምነቱ ወይም በህግ መሰረት ወለዱን በወቅቱ ያልከፈለ ወገን በወለዱ ላይ የሚከፍለው ተጨማሪ የወለድ ወለድ እንደመቀጫ ያለ ገንዘብ ማለት ነው፡፡