በሀገራችን ህዝባዊ አመጽን ተከትሎ በሰኔ 2010 ዓ.ም ብትረ መንግሥቱን የሚዘውረው የብልጽግና ፓርቲ ለአመጹ ምክንያት የሆኑትን የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋም ግንባታ እና የህግ ለውጦችን እያደረገ ነው፡፡
በተጨማሪም ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ከኦሮሚያ እና አማራ ብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በቅርቡ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሕገ-መንግሥቱን በጋራ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚሰሩ ስለመሆኑ ተፈራርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲሚሻሻሉ በጋራ የተስማሙባቸው የሕገ-መንግሥት የአንቀጾች ዝርዝር ላይ ስምምነት ላይ አልደረሱም(ወይም ለህዝብ ሊገልጹት አልፈለጉም)፡፡ ነገር ግን በመግባቢያው ሰነድ ላይ ከፈረሙት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከጥቂት የሕገ-መንግሥት ምሁራን እንዲሻሻል ጥያቄ የሚቀርብበት አንዱ ድንጋጌ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ 62(1) የሆነውና “ሕገ-መንግሥትን የመተርጓም” እና በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን ከምክር ቤቱ ተወስዶ የሕገ-መንግሥት ጉዳይን የሚያይና የሚወስን የሕገ-መንግሥት ፍ/ቤት እንዲቋቋም በማለት ባህር አቋርጠው የምዕራቡንና የምስራቁም ልምድ በማስረጃነት በመጥቀስ በሀገራችንም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡