የመድህን እና የማጓጓዣ ሕግ ይርጋ
ይህ ጽሑፍ በቀጥታ የተወሰደው በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ከሚለው ተሻሽሎ ከታተመው መጽሐፍ ላይ ነው። ሆኖም ለዚህ የበየነ-መረብ ጽሑፍ ለንባብ እንዲመች በግርጌ ተቀምጠው የነበሩት ማጣቀሻዎች በፅሑፉ ውስጥ እንዲከተቱ ተደርጓል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 166/1952 ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገለ ቢሆንም በከፊል በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 የተሸሻለ/የተተካ/ ቢሆንም የድሮው የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 166/1952 ውስጥ መጽሐፍ 3 (ሦስት) ማለትም ከአንቀጽ 561 እስከ 714 እና መጽሐፍ 4 (አራት) ማለትም ከአንቀጽ 715 እስከ 967 ያሉ ድንጋገጌዎች ያልተሻሩ ለመሆኑ በአዲሱ የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 በመግቢያው አንቀጽ 3(3) ላይ በግልፅ ተደንግጓል። ስለዚህ የንግድ ሕግ ይርጋዎች በአዲሱ ሕግ እና በድሮው ሕግ ያልተሻሩ ድንጋጌዎችን ከሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ጋር በመጽሐፉ በጥልቀት ተዳሷል።
በመጽሐፉ የንግድ ሕግ ይርጋዎች ማለትም የንግድ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚቀርቡ የይርጋ መቃዎሚያዎች ማለትም፡-
1. በዳይሬክተሮች ቦርድ ላይ የሚቀርብ ክስ ይርጋ
2. የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ (የሐዋላ ወረቀት እና የቼክ) 3 ዓይነት ይርጋዎች
3. በባለአክሲዮኖች ጉባዔ የተሰጠ ውሳኔን የማሰረዣ ክስ የማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ
4. በአክሲዮን ማህበር አደራጆች ላይ የሚቀርብ ክስ ይርጋ
5. የንግድ ማህበራት የሀብትና ዕዳ መግለጫን የመቃወሚያ ክስ ማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ
6. በዓይነት መዋጮ በተጋነነ ግምት ለደረሰ ጉዳት ክስን ለማቅረብ የይርጋ ጊዜ
7. ሀሰተኛ የትርፍ ክፍያን ለማስመለስ የሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜ
ከሕጉ እና ከሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንጻር ተዳሰዋል። የእነዚህ ጉዳዮች የይርጋ ጊዜ ሰፊ ትንታኔ ከፈለጉ መጽሐፉን እንዲያነቡ እነሆ ጀባ ብለናል።
በዚህ ጽሑፍ የቀረበው ግን የመድህን እና የማጓጓዣ ሙግትን በሚመለከት የሚነሱ እና ከዚህ ቀደምም እስከ ሰበር ክርክር ተደርጎባቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸው ናቸው።
1. የመድን ሕግ ይርጋዎች
የመድን ውል ማለት በመድህን ሰጭና መድህን ገቢው መካከል የሚደረግ ሆኖ መድን ሰጭው ከመድን ገቢው የመግቢያ ዋጋ (premium) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ መድን ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ለመሆኑ በድሮው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 166/1952 በን/ህ/ቁ.654 (1) ላይ ተደንግጓል። የመድን ውል ዓይነቶች በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት፣ ለ3ኛ ወገን ሃላፊነት እና የሕይወት መድህን ማለትም ለአካል ጉዳት፣ ለሞትና ለህመም ሊሆን ይችላል።
1.1.መደበኛው የመድን ሕግ ይርጋ
መድህን ውል ስለሆነ ከተዋዋይ ወገኖች አንዱ ግዴታውን ካልተወጣ መብታቸውን በፍ/ቤት በክስ ያስከብራሉ። ይህም ማለት መድህን ገቢው የመድን ውል ገብቶ ያልከፈለው ቀሪ ገንዘብ ካለበት እንዲከፍል፤ መድህን ሰጭው ለመድህን ገቢው ለደረሰበት አደጋ በህጉ መሠረት መክፈል ሲገባው ካልከፈለው አንዲከፍለው በፍ/ቤት ለማስመለስ መብት ያለው በመሆኑ የመድህን ሰጭ ሆነ ገቢው የሚያቀርቡት የይርጋ ጊዜ ስንት ነው? ለሚለው በድሮው የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 166/1952 በን/ህ/ቁ.674 (2) ላይ እንደተደነገገው ጉዳቱ ከደረሰበት ወይም በጉዳቱ ጥቅም ያላቸው ሰዎች ጉዳቱን ካወቁበት ቀን ጀምሮ በ2 (በሁለት) ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው በማለት ይደነግጋል። ነገር ግን የተሸሸገ ወይም የሀሰት ቃል የቀረበ ጉዳይ ያጋጠመ ሲሆን የይርጋ ዘመን የሚታሰበው መድህን ሰጭው ይህንን ነገር ካወቀበት ቀን ጀምሮ ነው። ይህ ሁለት ዓመት የይርጋ ጊዜ በውል ማሳጠር አይቻልም።
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎቱም መድህን ሰጭ ድርጅቶች ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በሁለት ዓመት ውስጥ ካልጠየቀ በይርጋ ይታገዳል በማለት በቅፅ 10 በሰ/መ/ቁ.46778 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። የተሸሸገው ወይም በሀሰት ቃል የቀረበ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ይህ የሀሰት ቃል መኖሩን ወይም የተሸሸገ ነገር መኖሩን ካወቁ ከሁለት ዓመት በኋላ ክስ ካቀረቡ በሁለት ዓመት ይርጋ ይታገዳል ነው በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 674 መሠረት ሰጥቷል። እንዲሁም ሰበር የይርጋው ማቋረጫ ምክንያቱ ከተከሰተ ከሁለት ዓመት በኋላ መድህን ገቢው ከሶ (ከመድህን ሰጭው ጠይቆ) ጉዳዩ በይርጋ የሚታገድ ለመሆኑ በን/ህ/ቁ.674 (1) መሠረት ውሳኔ በቅፅ 6 በሰ/መ/ቁ.31185 ሰጥቷል። ይህ የመድህን ውል ይርጋ በፍ/ቤቶች በተግባር አከራካሪ ሆኖ እየቀረበ ተፈጻሚ መሆኑን ለማሳየት ነው።
በመሆኑም ከሕጉ እና ከሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት የሚቻለው በመድህን ውል መሰረት ተዋዋዮች መካከል የሚጠየቅ ዳኝነት ይህ የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ ተፈጻሚነት አለው። ማለትም መድን ገቢ ያልከፈለው የአርቦን ክፍያ ካለ መድን ሰጭ ኩባንያ ከመድን ገቢው ላይ ለመጠየቅ የሚችሉት በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲሆን መድን ገቢው በመድን የገባለት ነገር ጉዳት ከደረሰበት ካሳ መጠየቅ ከኢንሹራንስ ድርጅት ለመጠየቅ ያለብት በ2 ዓመት ጊዜ ነው። በመሆኑም የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ ለአርቦን ክፍያ እና የካሳ ጥያቄ ለሁለቱም ተፈጻሚነት አለው።
1.2. የመድን ሰጭ በመዳረግ የሚያቀርበው ክስ የይርጋ ጊዜ
መድን ሰጭ ድርጅቶች ባለባቸው የሕግ እና የውል ግዴታ ለደረሰው ጉዳት በመጀመሪያ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳውን ከከፈሉ በኋላ ገንዘባቸውን በጉዳት አድራሹ አካል ክስ አቅረበው ጉዳት ለደረሰበት ሰው የከፈሉት ካሳ እንዲተካላቸው ለመጠየቅ የሚችሉበት ሁኔታዎች ያሉ ለመሆኑ ከንግድ ሕ አንቀጽ 683፣ ከአዋጅ ቁጥር 799/2005 አንቀጽ 6(2) እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.194880 እና 177907 ላይ ከሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ለመረዳት ይቻላል። ከእነዚህ የሕግ ድንጋጌዎች እና የሰበር ውሳኔዎች ለመረዳት የሚቻለው የመድን ሰጭ ኩባንያዎች የከፈሉትን ካሳ ለማስመለስ ክስ የሚያቀርብባቸው ጉዳት አድራሾች ከመድን ሰጭ ደርጅት ጋር ግንኙነት የሌለው 3ኛ ወገን ወይም በመድን ገቢ ሊሆን ይችላል።
የመድን ሰጭ ኩባንያዎች የከፈሉትን ካሳ ለማስመለስ ክስ የሚያቀርብባቸው ጉዳት አድራሾች ከመድን ሰጭ ደርጅት ጋር ግንኙነት የሌለው 3ኛ ወገን እና በመድን ገቢ ላይ ሲሆን ይርጋው ከመቼ ጀምሮ መቆጠር እንደሚችል እና የትኛው ሕግ ተፈጻሚነት አለው የሚለውን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.194880 እና 177907 ላይ ከሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እና ከሕጎቹ አንጻር በሚከተለው ሁኔታ ለየብቻ ማየቱ ይበልጥ ገልፅ ለማድረግ ይበጃል።
የመድን ሰጭ ድርጅቶች የከፈሉትን ካሳ ሳያስመልሱ የሚቀሩበት ሁኔታ ጉዳቱ የደረሰው በመድን ገቢ ጥፋት ሆኖ ነገር ግን በመድን ገቢው በመድን ሕጉ፣ በአዋጅ ቁጥር 799/2005 እና በመድን ውሉ መሰረት የሚጠበቅበትን ሁሉ አሟልቶ ከተገኘ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን የመድን ድርጅቶች በሕግ ሆነ በውሉ መሰረት የከፈሉትን ካሳ ከጉዳት አድራሽ የሚያስመልሱ በመሆኑ የከፈሉትን ካሳ የሚከስሩበት ሁኔታ የለም።
ሀ.መድን ሰጭ ድርጅት መድን ገቢን በመዳረግ በ3ኛ ወገን ጉዳት አድራሽ ላይ የከፈለውን ካሳ ለማስመለስ የሚያቀርበው የመዳረግ ክስ የይርጋ ጊዜ
መድን ሰጭ ኩባንያዎች በደንበኞቻቸው (መድህን ገቢዎች) ላይ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳውን ቀድመው ለደንበኞቻቸው ከከፈሉ በኋላ ጥፋቱ የጉዳት አድራሽ 3ኛው ወገን ከሆን የመድን ሰጭ በደንበኞቻቸው እግር ገብተው የከፈሉትን ካሳ ከጉዳት አድራሹ ላይ በ1952 ዓ.ም በወጣው የንግድ ሕግ አንቀጽ 683 መሰረት የመዳረግ ክስ በማቅረብ የማስመለስ መብት አላቸው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.194880 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መድን ሰጪ መድን በተገባለት ንብረት ላይ የደረሰዉን ጉዳት በማስጠገን ያወጣዉን ወጪ (ለመድን ገቢዉ የከፈለውን) በመድን ገቢዉ ምትክ ሆኖ ለማስመለስ በጉዳት አድራሹ ተሸከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪዉ ላይ ለሚያቀርበዉ ክስ ተፈጻሚነት የሚኖረዉ የይርጋ ሕግ ድንጋጌ ከውል ውጭ ሃላፊነት ሕግ ለመሆኑ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡-
አመልካች(መድን ሰጭ ድርጅት) ክሱን ያቀረበው በኢንሹራንስ ገቢው መብት በመዳረግ ወይም በምትክነት ነው። አመልካች ለክሱ መሠረት ያደረገው የመድን ገቢው ጋር ያደረገው የዕቃዎች/ንብረት ኢንሹራንስ ሲሆን በንግድ ሕጉ አንቀጽ 683 መሠረት ኢንሹራንስ ሰጪው በከፈለው ካሣ መጠን ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ ሦስተኛ ወገኖች ላይ ክስ ለማቅረብ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው በተከፈለው ገንዝብ መጠን፣ ባለት መብቶችና ክሶች ኢንሹራንስ ሰጪው ምትክ ሆኖ እንደሚገባ ተመልክቷል። ይህም የመዳረግ መብቱ ከውል ሳይሆን ከሕግ የመነጨ መሆኑን ያስገነዝባል። የመዳረግ መብትን ተመስርቶ የሚቀርብ ክስ ይርጋ አቆጣጠርን ስንመለከት በአንድ በኩል የመዳረግ መብቱ ኢንሹራንስ ገቢው መብት ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ መሆኑ እና በሌላ በኩል መዳረግ በሕግ የተፈቀደበት ሕግ አውጪው ሊያሳካው የፈለገው ዓላማ ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው። መድን ገቢውና ተጠሪ ያላቸው ግንኙነት የተመሠረተው ከውል ውጭ በመሆኑ አመልካች በመድን ገቢው እግር ተተክቶ የሚያቀርበው ክስም ከውል ውጭ ማዕቀፍ የሚታይ ነው።
ሰበሩ በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.194880 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የመድን ሰጭ ድርጅት የመዳረግ የተሰጠበት ሁለት ምክንያቶች መሆናቸውን ከገለፀ በኋላ የመጀመሪያውን እንደሚከተለው ያብራራዋል፡-
የመጀመሪያው ማሕበራዊ ምክንያት ነው።ይኸዉም መድን ገቢው ካሣውን ከኢንሹራንስ ሰጪው ከተቀበለ ጥፋት ከፈጸመው ሰው ላይ ክስ ለማቅረብ ፍላጎት ስለማይኖረውና ክስ ቢያቀርብ እንኳን ለደረሰው ጉዳት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090/1 እና 2091 መሠረት ከካሣ ተመዛዛኝነት መርሕ አኳያ ድጋሚ የሚካስበት ዕድል አይኖርም። ይሕም ጥፊቱን ያደረሰው ሰው ለጥፊቱ ተገቢው ተጠያቂነት ሳይከተለበት እንዲቀር ያደርጋል። ስለሆነም ኢንሹራንስ ሰጪው የመዳረግ መብት እንዲኖረው ማድረግ ለጉዳቱ ምክንያት የሆነው ጥፊት ፈጻሚው ሰው ለጥፊቱ ኃላፊነት እንዲወሰድና በሂደትም ጥፊት መፈጸምን በመቀነስ ወይም በመተው በሕብረተሰቡ ዘንድ አዎንታዊ የባሕሪ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ዓላማ ያደረገ ነው።
ሰበሩ 2ኛውን ምክንያት በዚህ መዝገብ ላይ እንደሚከተለው ይተነትናል፡-
ሁለተኛው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነው። የመዳረግ መብት መኖሩ ኢንሹራንስ ሰጪው ለመድን ገቢው የከፈለውን ገንዘብ እንዲተካለት ጉዳት አድራሹ ወይም የእሱ መድህን እንዲተካ በማድረግ የኢንሹራንስ ሥራ ትርፍ ማግኘት ከመሆኑ አኳያ ትርፋማ ድርጅት እንዲሆን ማድረግ ነዉ። ይሕም የአረቦን ክፍያ መጠን ሊይ ቅናሽ እንዲያረግና ሕብረተሱቡ የኢንሹራንስ ኢንደስትሪውን በተሻለ እንዲጠቀም ሊያበረታታ የሚችል ነው። ኢንሹራንስ ሰጪ ድርጅቶች ጤናማ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚኖራቸው ከሆነ በኢኮኖሚው ላይም አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ይሆናል።
ሰበር በዚህ መዝገብ ላይ ይርጋው መተርጎም ያለበት ከፍ ብሎ ከተገለፅ የመዳረግ ዓላማዎች የሆኑትን የማህራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ምክነያቶችን ለማሳካት በሚያችል አግባብ ለመሆኑ እና ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው መድን ሰጭ ካሳ ከከፈለበት እንጅ ጉዳቱ ከደረሰበት ላለመሆኑ እንደሚከተለው ያብራራል፡-
ስለሆነም ሕጉ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በሕጉ ለማሳካት የተፈለውን ዓላማ በማገናዘብ አመልካች በሕግ የተሰጠውን የመዳረግ መብቱን እንዲሰራበት በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል። ከላይ እንደተመለከተዉ አመልካች በሕግ የመዳረግ መብት ማግኘት የሚችለው ለመድን ገቢው ካሣውን ሲከፍል እንደመሆኑ ክስ ሊያቀርብ የሚችለው ጉዳቱ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን የመዳረግ መብቱን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ይህም በካሣው አከፋፈል ሂደት በሕጉ የተመለከተው የሁለት ዓመት ጊዜ ሊያልፍ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር ያስገነዝባል። በመሆኑም የፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2143/1 የተመለከተው የይርጋ ጊዜና አቆጣጠር በፍትሐብሔር ሕጋችን ስለ ይርጋ በጠቅላላዉ በሚደነግገዉ ክፍል በአንቀጽ 1846 “የይርጋው መነሻ ጊዜ” በሚል ርእስ ሥር ;የይርጋው ቀን መቆጠር የሚጀምረው ግዴታዉን ለመጠየቅ ተገቢ ከሆነዉ ወይም ዉል የሚሰጠዉ መብት ከተሰራበት ቀን ጀምሮ ነዉ“ በማለት ከተደነገገው ጋር ተገናዝቦ ሊመረመር ይገባል። በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2143 እና በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1846 ድንጋጌዎች ስር የተደነገገዉን ይዘት፣ መንፈስና ዓላማ መሠረት በማድረግ…በመድን ሰጪዉ ላይ ለክሱ ምክንያት የሆነ ጉዳት ደረሰበት ማለት የሚቻለዉ (the occurrence giving rise to the claim) እና በመብቱ መሥራት የሚችለው ለደንበኛዉ የካሳ ክፍያ ከፈጸመበት ቀን ጀምሮ ነዉ። በመሆኑም የይርጋ ጊዜዉም መቆጠር የሚጀምረዉ አመልካች(መድን ሰጭ) ለደንበኛዉ ካሳ ወይም የተሽከርካሪ ማስጠገኛ ክፍያ ከፈጸመበት ቀን ቀጥሎ ካለዉ ቀን ጀምሮ እንጂ በአመልካች ደንበኛ ተሽከርካሪ ላይ አዳጋዉ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ አይደለም።
ለ.መድን ሰጭ ድርጅት በደንበኛው በመድን ገቢ ለደረሰ ጉዳት ተጎጅ ለሆነው ለ3ኛ ወገን የከፈለውን ካሳ ከጉዳት አድራሽ ደንበኛው ላይ ለማስመለስ የሚያቀርበው ክስ የይርጋ ጊዜ
መድን ሰጭ ጉዳት አድራሽ ከሆነው ከደንበኛው ላይ በሕግ ወይም በመድን ውላቸው መሰረት ጉዳት ለደረሰበት 3ኛ ወገን የከፈለውን ሲጠይቅ የሚነሳው አከራካሪ ነጥብ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ሕግ የንግድ ህጉ አንቀጽ 674 ነው? ወይስ የፍ//ብ/ህ/ቁ.2143 ነው? የሚለው ሲሆን ይህንን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.177907 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የመድን ገቢውን የሃላፊነት ምንጭ ውል መሆኑን መሰረት በማድረግ እንደሚከተለው ያብራራል፡-
በተሽከርካሪ አዳጋ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርስ ጉዳት የሚሰጥ የመድን ሽፋን የሚመነጨዉ በመድን ሰጭዉና በመድን ገቢዉ መካከል በሚረግ የመድን ዉል ፖሊሲ መነሻ ቢሆንም በተሽከርካሪ አዳጋ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚደርሰው አዳጋ የመድን ሽፋን ለመስጠት በወጣ አዋጅ ቁጥር 799/2005 በተዘረጋዉ ስርዓት መሰረት በመድን ዉለ ተዋዋይ ወገን ያልሆኑ አዳጋ የደረሰባቸዉ ሦስተኛ ወገኖች በሽፋኑ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ግንኙነት መፍጠሩን መገንዘብ የሚቻል ነዉ። በዚህ አግባብ ምንም እንኳን ግራ ቀኝ የመድን ዉለ ተዋዋዮች ቢሆኑም ከዉለ ተጠቃሚዎች ሦስተኛ ወገኖች ጭምር በመሆናቸዉ የመድን ዉል ፖሊሲዉ እና አዋጅ ቁጥር 799/2005 የሦስትዮሽ ግንኙነትን እንደተቋቋመ መረዳት ያስፈልጋል። አመልካች በተጠሪ ላይ ክሱን የመሰረተዉ የመድን ዉለን እና በአዋጅ ቁጥር 799/2005 መሰረት በማድረግ በመሆኑ ግንኙነታቸዉ በመድን ዉል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት የሚኖረዉ የይርጋ ድንጋጌ ይህንን በዉል ላይ የተመሰረተዉን ግንኙነት መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል። ግንኙነቱም የመድን ዉልን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለዉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 674 ላይ የተመለከተዉ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች በዉሳኔያቸዉ ይህን ድንጋጌ መጥቀሳቸዉ በመሠረቱ የሚነቀፍ አይደለም። በመሆኑም ከውል ዉጭ የሆነ ኃላፊነት መነሻ በማድረግ ካሳ ለማስከፈል ለሚቀርብ ክስ ተፈጻሚነት እንዲኖረዉ በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2143/2 ስር የተደነገገዉ የይርጋ ድንጋጌ ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት የለውም።
ሰበሩ በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.177907 በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው ጉዳቱ ከደረሰበት (ጉዳዩ ከተፈፀመበት) ሳይሆን የመድን ሰጭው ካሳውን ከከፈለበት ጊዜ ጀምሮ ለመሆኑ ከመድን ሕግ በ1952 ከወጣው የንግድ ሕግ አንቀጽ 674(1) እና ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1845-1856 ያሉትን ድንጋጌዎች መነሻ በማድረግ ወስኗል።
2. የማጓጓዣ ሕግ ይርጋ
2.1. የመልቲ-ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ የይርጋ ጊዜ
መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን የፍርድ ቤት ስልጣን በመልቲ-ሞዳል ትራንስፖርት በሚለው በምዕራፍ ሁለት ትርጉሙን የተመለከትን በመሆኑ በዚህ ምዕራፍ በድጋሜ ማብራራት ተገቢነት የለውም። የመልቲ-ሞዳል ትራንስፖርት የይርጋ ጊዜ በተመለከተ ከአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40 እና ሰበር ከሰጣቸው የተለያዩ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች መረዳት የሚቻለው ይህንን ይርጋን በተመለከተ በፍርድ ቤት አከራካሪ በመሆን የሚቀርቡት ነጥቦች ይርጋው 6 ወር ወይስ 2 ዓመት ነው የሚለው እና ሌሎች ነጥቦች ናቸው።
የመልቲ ሞዳል የይርጋ ጊዜ 2 ዓመት እና 6 ወር በምን አግባብ ተለያይተው እና እንዴታ ሊፈፀሙ ይቻላሉ የሚለውን በተመለከተ በዚሁ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(1) እና (2) አጣምሮ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ 5ኛ ባንክና ኢንሹራንስ ችሎት፣ ከሳሽ አባይ ኢንሹራንስ አ.ማ እና ተከሳሽ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግት ድርጅት፣ የኮ/መ/ቁ 14294፣ ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም በሆነ መዝገብ ላይ በሰጠው ውሳኔ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል፡-
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 40(1) መሰረት ከመልቲ ሞዳል ትርንስፖርት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚቀርብ ክስ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ካላቀረበ በይርጋ ቀሪ ይሆናል ሆኖም በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ (2) መሰረት ርክክብ ከተፈጸመ ርክክብ ከተፈጸመበት ቀን በኋላ፣ ርክክብ ካልተደረገ የእቀው ርክክብ መደረግ ከነበረበት ቀን ቀጥሎ ባሉት 6 ወራት ውስጥ የክሱን ይዘትና ዋና ዋና ዝርዝሮች የሚገልጽ የጽሑፍ ማስታወቂያ ካልተሰጠ ይህ ጊዜ ካበቃበት ቀን ቀጥሎ ባለው ቀን ክስ ካልቀረበ ክሱ በይርጋ የሚቋረጥ ይሆናል። ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻለውም ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ውል ጋር በተያያዘ ክስ የሚያቀርብ ወገን የ2 ዓመት ይርጋው ተፈጸሚ የሚደረግለት ርክክብ ከተፈጸመ ርክክብ ከተደረረገበት፤ ርክክብ ሳይደርግ ከቀረ ደግሞ ርክክብ መደረግ ከነበረበት ቀን ቀጥሎ ባለው ቀን ጀምሮ ባለው 6 ወር ጊዜ ውስጥ በህጉ የተመለተውን ዝርዝር ይዘት የያዘ ማስጠንቀቂያ ለመልቲሞዳል ትርንስፖርት አጓጓዡ ከተሰጠ ነው። ይህ ካልሆነ ከሳሽ ርክክብ ከተፈጸመ ወይም ርክክብ መፈጸም ከነበረበት ቀን ቀጥሎ ካለው ቀን ጀምሮ በሚቆጠር 6 ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ካላቀረበ መብቱን በይርጋ እንደሚያጣ ነው።
በዚህ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(2) ላይ ክስ የሚያቀርበው ሰው በመልቲሞዳል ትርንስፖርት አጓጓዡ ሰው ላይ ክስ ለማቀርብ ለመልቲሞዳል ትርንስፖርት አጓጓዡ የክሱን ይዘትና ዋና ዋና ዝርዝሮች የሚገልጽ የጽሑፍ ማስታወቂያ መስጠት አለበት በማለት በደነገገው ሕግ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ በሰበር አመልካች አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና በሰበር ተጠሪ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ጽ/ቤት፣ የሰ/መ/ቁ.152341፣ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም በሆነ መዝገብ ላይ የክሱን አጠቃላይ ይዘት ማሳወቅ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በሚከተለው አግባብ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያብራራል፡-
አጠቃላይ የክስ ይዘትና ዝርዝር ገልፆ ማስታዎቅ…ንብረቱ ስለመጎዳቱ ማሳዎቅ ብቻ ሳይሆን ከጉዳት አድራሹ የሚፈልገውን ዳኝነት ጨምር የሚመለከትና ጉዳዩን ፍርድ ቤት ከመድረሱ በፊት ጉዳት አድራሹ ለችግሩ የሚወስደው የመፍትሔ እርምጃ ካለ እንዲወስድ ለማስቻል የሚሰጥ ነው። …ይህንን ሳያደርግ ክስ ወደ ፍርድ ቤት ይዞ መቅረብን የአዋጁ አንቀጽ 40(2) በይርጋ ቀሪ ያደርገዋል።
ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40 እና ከዚህ የሰበር ውሳኔ ለመረዳት የሚቻለው ከሳሹ ወደ ፊት ክስ በዕቃ አጓጓዡ ላይ ክስ የሚያቀርብ ለመሆኑ በጽሑፍ አጠቃላይ የክስ ይዘትና ዝርዝር ገልፆ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ የከሳሽ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 መሰረት ያደረገው ክስ የይርጋ ጊዜ 2 ዓመት ሲሆን ሆኖም ከሳሹ በጽሑፍ አጠቃላይ የክስ ይዘትና ዝርዝር ገልፆ ማስጠንቀቂያ ካልሰጠ እና የክሱ መሰረት የሆነው የሕግ ማዕቀፍ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 ከሆነ የከሳሽ ክስ በ6 ወር የይርጋ ጊዜ የሚታገድ ይሆናል ማለት ነው።
የ2 ዓመቱ ሆነ የ6 ወር የይርጋው ጊዜ ከመቼ አንሰቶ መቆጥር ይጀምራል የሚለውን በተመለከተ አከራካሪ እየሆነ አስከ ሰበር ችሎቱ የደረሱ ክርክሮች አሉ። ምክንያቱም መድን ድጅቶች ሆነ በሌሎች ከሳሾች እና ተከሳሾች ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው የሚጓጓዘው ዕቃ ጉዳት የደረሰበት ለመሆኑ ከታወቀበት ወይም ክፍያ ከተፈፀመበት ወይም ርክክብ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ሊሆን ይገባል የሚሉ አማራች መከራካሪያ ነጥቦች ስለሚቀርቡ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ በሰበር አመልካች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ድርጅት እና ማርቪልደን ካንፓኒ ሊሚትድ፣ የሰ/መ/ቁ.204288 መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም በሆነ መዝገብ ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በዚሁ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40 (2) (1) ላይ የተቀመጠውን መሰረት በማድረግ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ውል ጋር በተያያዘ ክስ የሚያቀርብ ወገን የይርጋው ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው የሚጓጓዘው ዕቃው ርክክብ ከተፈጸመ ርክክብ ከተደረረገበት ቀን ጀምሮ፤ ርክክብ ሳይደርግ ከቀረ ደግሞ ርክክብ መደረግ ከነበረበት ቀን ቀጥሎ ባለው ቀን ጀምሮ ነው በማለት ወስኗል።
በዚህ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 መሰረት ከሚቀርብ የይርጋ ክርክር ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ነጥብ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 40(5) ላይ የተቀመጠው “አግባብ ባለው ሕግ መሰረት ሃላፊ የተባለው ሰው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፻ (አንድ) ላይ የተመለከተው የይርጋ ጊዜ ቢያልፍም በበኩሉ ለመጠየቅ የሚችለው የካሳ ጥያቄ ካሳውን ለጠየቀው ሰው የካሳ ክፍያ ከፈፀመበት ቀን ወይም ካሳ የቀረበበት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ከደረሰበት በኋላ ባሉት ፺ (ዘጠና) ቀናት ውስጥ ክሱን ከመሰረተ ነው” የሚለው የ90 ቀን የይርጋ ጊዜ ነው።
ከዚህ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ድንጋጌ አንድም አግባብ ባለው ሕግ መሰረት ሃላፊ የተባለው ሰው የካሳ ጥያቄ ካሳውን ለጠየቀው ሰው የካሳ ክፍያ የፈፀመበት እና ካሳውን የከፈለውም የ2 ዓመት የይርጋው ጊዜ ካለፈ በኋላ ከሆነ ወይም የካሳ ክስ የቀረበበት የ2 ዓመት የይርጋው ጊዜ ካለፈ በኋላ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ የደረሰው ከሆነ ይህ ከዕቃ አጓጓዥ እና ከዕቃ አስጫኝ ውጭ የሆነ 3ኛ ወገን በዚህ ሕግ መሰረት ካሳውን በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(1) የተቀመጠው የ2 ዓመቱ የይርጋ ጊዜ ቢያልፍም ካሳውን ከከፈለበት ወይም ደግሞ ክሱ ከቀረበበት ጀምሮ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ አይታገደም የሚል ነው።
ከዚህ ላይ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በደንበኞቻቸው እግር በመተካት በንግድ ሕጉ አንቀጽ 683 መሰረት የሚያቀርቡት የመዳረግ (subrogation) ክስ ሲሆን ለዕቃ አስጫኙ መድን የሰጠ ኢንሹራንስ ኩባንያ በመጀመሪያ ለአስጫኙ ካሳውን ከከፈለ በኋላ በደንበኛው እግር በመግባት ለደንበኛው የከፈለውን ካሳ ለማስመለስ በዕቃ አጓጓዡ ላይ ክስ ሲያቀረብ የይርጋ መቃዎሚያ በተከሳሹ በኢንሹራን ኩባንያው ላይ ካቀረበ የይረጋ ክርክሩ እልባት መሰጠት ያለበት በዚህ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ድንጋጌ መሰረት ይሆናል ማለት ነው።
በዚህ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ድንጋጌ መሰረት የመዳረግ (subrogation) ክስ ሲዳኝ የሚነሳው አከራካሪ ነጥብ የመድን ድርጅቱ ለደንበኛው ክፍያውን የፈፀመው የዕቃ አስጫኙ ከዕቃ አጓጓዡ ላይ ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ ከታገደ በኋላ ሆኖ ነገር ግን የመድን ድርጅቱ ክፍያ በፈፀመ በ3 ወር ጊዜ ከጠየቅ እና ተከሳሹ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ካሳ ለደንበኛው (ለዕቃ አስጫኙ) የከፈለው ከእኔ ላይ ክስ ለማቅረብ መብቱ በይርጋ ቀሪ ከሆነ በኋላ በመሆኑ እኔ ልጠየቅ አይገባም የሚል መከራከሪያ ካነሳ ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም የሚለው ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ ገልፅ ለማድረግ በምሳሌ እንመለከተው።
ምሳሌ1፡- የዕቃ አስጫኙ እቃውን ከዕቃ አጓጓዡ ከተረከበው እና መጋዝን ካስቀመጠው ከ6 ወር በኋላ በዕቃው ላይ ሲጓጓዝ ጉዳት የደረሰበት ለመሆኑ በባለሙያ ያረጋገጠ በመሆኑ እና ዕቃውን ከተረከበ በኋላ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የክስ እና ሌሎች ዝርዝር ነገሮችን ገልፆ ማስጠንቀቂያ ያልሰጠ በመሆኑ የዕቃ አጓጓዡን በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 መሰረት ክስ በፍርድ ቤት በማቅረብ እንዳይጠይቀው መብቱ በይርጋ የታገደ ለመሆኑ ስለተረዳ የዕቃ አስጫኙ ካሳ ከመድን ሰጭ ድርጅቱ ሲጠይቀው ኢንሹራንስ ድርጅቱ በገቡት የመድን ውል መሰረት የመድን ገቢ ከኢንሹራንሱ ጋር ያለው የይርጋ ጊዜ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 674 መሰረት 2 ዓመት በመሆኑ መደን ሰጭ የይርጋ ጊዜ በመድን ገቢ ላይ ማንሳት የማይችል በመሆኑ ለዚህ ጉዳት ካሳ ለዕቃ አስጫኙ ከፍሎታል እንበል። ይህ የካሳ ገንዘቡን ለዕቃ አስጫኙ የከፈለው ኢንሹራን የእቃ አጓጓዡን ደንበኛውን በመዳረግ ከ2 ወር በኋላ ከ3 ወር በፊት በሚመለከተው ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክስ ሲያቀርብ ተከሳሹ ባቀረበው የይርጋ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ከሳሽ ለደበኛው ካሳ የከፈለው ከሳሹ በእኔ ላይ ካሳ የመጠየቅ መብቱ በይርጋ ከታገደ በኋላ በመሆኑ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 683 (2) መሰረት ሃላፊነቱ ቀሪ ሆኖ እያለ በመሆኑ ክፍያውን በችሮታ የከፈለው በመሆኑ ከሳሹ እኔን ተከሳሽን ሊጠይቀኝ አይገባም በማለት መቃዎሚያ አቀረበ እንበል። ከሳሹ ኢንሹራንስ በበኩሉ በተከሳሽ ለቀረበበት የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ በቃል ክርክር የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ድንጋጌ ለእኔ የመዳረግ (subrogation) ክስ ካሳ ከከፈልኩበት ቀን ጀምሮ እስከ 3 ወር ድርስ ክስ እንዳቀርብ የሚፈቅድ በመሆኑ መብቴ በይርጋ አይታገድም የሚል ክርክር አቀረበ እንበል።
በዚህ ምሳሌ ላይ ተቀባይነት ያለው ክርክር ካሳ የከፈለው የኢንሹራንሱ ወይስ ደግሞ የዕቃ አጓጓዡ የሚለው ነጥብ ምላሽ ማግኘት ያለበት ነው። እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ የመጀመሪያውን ሁኔታ በተመለከተ ኢንሹራንስ ድርጅቱ ለዕቃ አስጫኙ ክፍያውን ከመፈፀሙ በፊት የመዳረግ መብቱን ያሳጣው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ እያለበት ሳያረጋግጥ የከፈለው በመሆኑ ይህም ኢንሹራንስ ድርጅቱ ከፈለገ የከፈለውን ገንዘብ ከደንበኛው ከራሱ ከዕቃ አስጫኙ እንዲመልስለት ክስ ማቅረብ እንጅ በዕቃ አስጫኙ ላይ ክስ የማቀረብ መብቱን በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) አጥቷል።
ምሳሌ 2፡- ከላይ በምሳሌ አንድ ላይ በተገለጠው ኢንሹራንስ ድርጅቱ ለዕቃ አስጫኙ ካሳውን የከፈለው የዕቃ ርክክብ በተደረገ በ5ኛ ወር ካሳውን ቢከፍል እና ክሱን ግን ካሳውን ከከፈለ ከ2 ወር በኋላ የዕቃው ርክክብ ከተደረገ ከ7 ወር በኋላ ሆኖ ዕቃ አስጫኙ ሆነ የዕቃ አስጫኙ የኢንሹራንስ ድርጅቱ የክሱን ይዘት እና ሌሎች መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለዕቃ አጓጓዥ ሳያሳውቁ ቢሆን እና ተከሳሹ ከሳሽ ኢንሹራንስ ሆነ ዕቃ አስጫኙ የክሱን ይዘት እና ሌሎች መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ማሳወቅ እየጫሉ ያላሳወቁኝ በመሆኑ የከሳሽ መብት በይርጋ የሚል መቃዎሚያ አቀረበ እንበል። ከሳሹ ሊዚህ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ በቃል ክርክር የከሳሽ የመዳረግ መብት የሚጀምረው ክፍያ ከፈፀምኩበት ቀን ጀምሮ በመሆኑ እና ክፍያም የከፈልኩት የደንበኛዬ ክስ የማቅርብ መብቱ የይርጋ ጊዜ ሳያልፍ በመሆኑ እና ክፍያ ከፈፀምኩበት ቀን ጀምሮ እስከ 3 ወር ጊዜ ክስ የማቀርብ መብቴ በይርጋ የማይታገድ ለመሆኑ ሕጉ የደነገገ ስለሆኑ መብቴ በይርጋ አይተገደም የሚል ክርክር አቀረበ እንበል።
በዚህ ሁኔታ የከሳሹ ክስ በይታገዳል ወይስ አይታገደም የሚለውም ምላሽ ማግኘት ያለበት ነጥብ ነው።
2ኛውን ሁኔታ በተመለከተ አከራካሪ የሚሆነው ጉዳይ ከሳሹ ካሳው በኢንሹራንሱ የተከፈለው በመሆኑ ለዕቃ አጓጓዡ የክሱን ይዘት እና ሌሎች መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ መብቱ በይርጋ እንዳይታገድ የማሳወቅ ግዴታ ያለበት ቢሆንም ለማሳወቅ የሚያነሳሳው ምክንያት አይኖርም። በሌላ በኩል የኢንሹራንስ ድርጅቱ ዕቃ አስጫኙን ተክቶ የመዳረግ ክስ የሚያቀርብ በመሆኑ ዕቃ አስጫኙ የክሱን ይዘት እና ሌሎች መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ካላሳወቀ ራሱ ኢንሹራንሱ ለዕቃ አጓጓዡ የማሳወቅ ግዴታ ያለበት ለመሆኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር አመልካች አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና በሰበር ተጠሪ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ጽ/ቤት የሰ/መ/ቁ.152341 መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት የሚቻል ነው።
እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ሰበር በሰ/መ/ቁ.152341 መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አስገዳጅነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 መሰረት ተደርገው የሚቀርቡ የመዳረግ (subrogation) ክሶችን በተመለከተ በእቃ አጓጓዡ ላይ የመዳረግ ክስ የሚያቀርበው ሰው የካሳ ክፍያውን የከፈለው በዕቃ አስጫኙ በኩል የመዳረግ መብቱን ሳያሳጣው ከሆነ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40 (5) ካሳ ከከፈለበት ቀን ጀምሮ እስከ 3 ወር መብት ያለው በመሆኑ የከሳሽ መብት በሚከተሉት ሦስት ምክንያቶች በይርጋ አይታገድም።
የመጀመሪያው ምክንያት የሚያያዘው ከይርጋ የትርጉም ምርህ አንጻር ነው። በዚህ መጽሐፍ በዚህ ምዕራፍ ከላይ ከፍ ብሎ በሰፊው እንደተብራራው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰጠው አስገዳጅ የሕገ ትርጉም መሰረት አከራካሪ የይርጋ ጉዳይ በአጋጠ ጊዜ እና ሕጉን የግድ መተርጎም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ አከራካሪው ሕግ መተርጎም ያለበት የሕግ ትረጉሙ ውጤት መብቱን በይርጋ ሊያጣ የሚችል ተከራከሪን መብት በአስከበረ መልኩ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለፀው ሁነት በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40 ላይ አከራካሪ የሆነ የይርጋ ጉዳይ አለው። በከሳሽ ኢንሹራንስ በኩል የደንበኛው ካሳ የመጠየቅ መብቱ በይርጋ ሳይታገድ በመድን ውሉ መሰረት ገንዘቡን ከከፈልኩኝ ይህንን የካሳ ክፍያ የክሱን ይዘት እና ሌሎች መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለተከሳሽ ባላሳወቅም በደንበኛዬ እግር ተተክቼ ካሳውን ከከፈልኩብ ቀን ጀምሮ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ለማቅረብ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ላይ መብት ይሰጠኛል የሚለው መከራካሪያ በከሳሽ በኩል የሚቀርበው ሚዛን የሚደፋ ነው። ምክንያቱም በዚህ መልኩ ከተረጎምነው የከሳሽ ገንዘቡን የማስመለስ መብቱ በይርጋ ምክንያት የማያጣ በመሆኑ ከይርጋ ሕግ የአተረጓጎም መርህ ጋር የሚስማማ ነው።
2ኛው ምክንያት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.194880 እና 177907 ላይ በሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እና በጠቅላላ የኢንሹራንስ ሕጎቹ መሰረት የኢንሹራን ድርጅት የመዳረግ ክስ ለማቅረብ መብቱ የሚመነጨው ገንዘቡን ከከፈለበት ቀን ጀምሮ በመሆኑ ይርጋ መቆጠር የሚጀምረው ዕቃውን ርክክብ ካደረጉት ሳይሆን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ከእነዚህ የሰበር ውሳኔዎች ጋር ትርጉሙ የተስማማ ያደርገዋል። ከዚህ ላይ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 ልዩ ሕግ ነው የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል ግን የግድ ትርጉም ሲያስፈልግ ትርጉሙ ከሌሎች ለሌሎች መሰል ክርክሮች ትርጉም ለመስጠት መሰረት የሚሆኑ ምክንየቶችን ወስዶ መጠቀሙ የሕግ ተርጓሚ አካል የሆነውን የፍርድ ቤት ሥራ ተገማች እና ምክንያታዊ የመኪያደርገው በመሆኑ ልዩ ሕግ ነው የሚለውን ተቀብለን ምክንያቱን መውሰዱ ሚዛን የሚደፋ በመሆኑ ነው።
3ኛው ምክንያት በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ መሰረት የመዳረግ ክስ ለሚያቀርቡ አካላት ራሱ አዋጅ ቁጥር 548/1999 በአንቀጽ 40(5) ላይ የይርጋ ጊዜ በልዩ ሁኔታ ሲያስቀምጥ የመዳረግ ክስ በሚያርበው ሰው ላይ ለተከሳሹ የክሱን ይዘት እና ሌሎች ልዩ ልዩ መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አይጥልበትም። በመሆኑም ሕግ ሰውጫው ያልጣለውን ግዴታ የሕግ ተርጓሚው በከሳሽ ላይ ይህንን ግዴታ በመጣል ከሳሽ መብቱን እንዲያጣ ማድረግ ሕግ ተርጓሚው የሕግ አውጭው ሚና በመተካት ከሳሽን መብቱን እንዲያጣ ሊያደርገው አይገባም።
በሰ/መ/ቁ.152341 ላይ የቀረበ አስተያየት
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት የመጨራሻ ነጥብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር አመልካች አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና በሰበር ተጠሪ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ጽ/ቤት የሰ/መ/ቁ.152341 መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ የሰበር አመልካቹ በደንበኛው እግር ተተክቶ የሚያቀርበው የመዳረግ ክስ የኢንሹራንስ ድርጅት ሆኖ እያለ ይህ የኢንሹራንስ ኩባንያ ክፍያውን ለደንበኛው መቼ እንደከፈለ በፍርዱ ላይ ያልተገለፀ እና ክርክርም ያልተነሳበት ለመሆኑ ፍርዱ የሚያሳይ በመሆኑ ከሳሽ ኢንሹራንስ ክፍያ የፈፀመው ደንበኛው ክስ የማቅረብ መብቱ ከማለፉ በፊት ወይስ በኋላ የሚለው በፍርዱ ላይ አልተገለፀም። እንዲዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ሰበሩ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ ኢንሹራንስ ክፍያ የፈፀመው የደንበኛው ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ ከመታገዱ በፊት ወይስ በኋላ የሚለውን ነጥብ በፍሬ ነገር ደረጃ እንዲያጣራ አድርጎ ከሳሽ ኢንሹራንስ ክፍያ የፈፀመው የደንበኛው ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ ከመታገዱ በፊት ከሆኑ ሰበሩ ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) አንጻር ይርጋው ታይቶ እንዲወስን ማድረግ ነበረበት።
በእርግጥ ከዚህ ላይ አመልካች ኢንሹራንስ ክርክር ያላቀረበበትን ከይርጋ ጋር የሚገናኝን የፍሬ ነገር ጉዳይ ፍርድ ቤቱ በራሱ አንስቶ እንዲከራከሩበት እና በማስረጃ እንዲነጥር ማድረግ ፍርድ ቤቱ ባልተሰጠው ስልጣን በራሱ የስረ-ነገር ሕግን ይርጋ አንስቷል ያስብለዋል የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ምልከታ ግን በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 በአንቀጽ 40(5) ላይ የተመለከተውን የመልቶ ሞዳል ትራንስቶርትን ይርጋ ልዩ ሁኔታ አከራክሮ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት በመሆኑ እና በዚህ ድንጋጌ ላይ የመዳርግ ክስ የሚያቀርብ ሰው የ2 ዓመቱ የይርጋው ጊዜ ቢያልፍም ክፍያ ከፈፀመበት ጀምሮ እስከ 3 ወር መብቱ በይርጋ አይታገድም የሚል በመሆኑ በፍርድ ቤቶች ላይ ከሳሽ ኢንሹራንስ መቼ ክፍያ ፈፀመ የሚለውን ከይርጋ አቆጣጠር መርህ አንጻር እንዲያነሱ ሕጉ በራሱ ግዴታ የጣለባቸውን ሃላፊነት መዋጣት እንጅ ፍርድ ቤቱ ባልተሰጠው ስልጣን በራሱ የስረ-ነገር ሕግን ይርጋ አንስቷል ሊያስብለው የሚችል አይደልም። የይርጋ ጉዳይን በትክክል ለመወሰን ከሕጉ ጋር የሚገናኙ ፍሬ ነገሮች ሳይጣሩ ከተወሰነ ፍትሕ ከሚያዛባ ውሳኔ ላይ የሚያደርስ ይሆናል። በመሆኑም ሰበሩ ጉዳዩ በይርጋ ታግዷል በማለት ውሳኔ የሰጠው እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ከሆነ መጣራት ያለበት ፍሬ ነገር ተጣርቶ ሳያልቅ ነው የሚል የዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ አቋም ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር አመልካች አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና በሰበር ተጠሪ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ጽ/ቤት የሰ/መ/ቁ.152341 መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ የሰበር አመልካቹ የኢንሹራንስ ድርጅት በደንበኛው እግር ተተክቶ በሚያቀርበው የመዳረግ ክስ ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀጽ 40(5) ጋር በማገናኘት እና በማዛመድ የመዳረግ ክስ የሚያቀርብ ሰው ኢንሹራንስን ጨምሮ ሌሎች ከሳሾች የክስ ይዘትን እና ሌሎች ልዩ ልዩ ነገርሮችን በጽሑፍ ለተከሳሹ የማሳወቅ ግዴታ በድፍኑ ያለባቸው ለመሆኑ ከመወስን ይልቅ ሰፊት ትንታኔ በመስጠት ግዴታቸውን በትንታኔ ማሳየት ነበርበት። ምክንያቱም እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ከሆኑ ከላይ እንደገለፅኩት የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሕግ መሰረት የመዳረግ ክስ ለሚያቀርቡ አካላት ራሱ አዋጅ ቁጥር 548/1999 በአንቀጽ 40(5) ላይ የይርጋ ጊዜ በልዩ ሁኔታ ሲያስቀምጥ የመዳረግ ክስ በሚያቀርበው ሰው ላይ ለተከሳሹ የክሱን ይዘት እና ሌሎች ልዩ ልዩ መግለጫዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አይጥልበትም።
2.2.የባሕር ሕግ ይርጋዎች
ከመጓጓዣ ዘዴዎች መካከል አንዱ የባህር ላይ መጓጓዣ ነው። በባህር ላይ በሚረግ የዕቃ ማጓጓዣ መሰረት አድርጎ ለደረሰ ጉዳትን ካሳ እና በባህር የዕቃ ማቅርብን መሰረት አድርጎ የሚገኝ የገንዘብ ክፍያን ለመጠየቅ በመርህ ደረጃ የይርጋ ጊዜው ከሳሹ ዕቃውን ከተረከበበት ወይም ዕቃውን ካልተረከበ ደግሞ ዕቃው መረከብ ከነበረበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ለመሆኑ የ1952ቱ የኢትዮጵያ የባህር ሕግ በአንቀጽ 16(1) እና 203(1) ላይ በግልፅ ደንግጓል። በተግባርም ቢሆን በፍርድ ቤት በቀረበ ክርክር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 14 በሰ/መ/ቁ.80642 ታህሳስ 2 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ከዚህ የባህር ሕግ አንቀጽ 203 (1) ላይ በመነሳት የይርጋው ጊዜ አንድ ዓመት ለመሆኑ ወስኗል።
2.3. በአየር ለተጫኑ ዕቃ ካሳ ይርጋ
አሁን ባለው ዘመን የአየር ጉዞ እጅግ ዘመናዊ እና ውድ ከሚባሉት አንዱ ሲሆን ሰዎች ሆነ ዕቃዎች በፍጥነት በአየር እተጓጓዙበት ይገኛል። ይህ የአየር ላይ መጓጓዣ ምንም እንኳን ፈጣንና ምቹ ቢሆንም አዳጋዎች፤ እናቅፋቶች እና አለመግባባቶች አልፎ አልፎም ቢሆን የሚከሰቱ በመሆኑ ልክ እንደ ሌላው መጓጓዣ ዘዴ የክርክር መንስኤ ከመሆኑ አልዳነም።
አሁን ላይ የአየር ጉዞን በተመለከተ የሚፈጠር አለመግባባትን በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ዕልባት ለመስጠት የሕግ መሰረቱ የሞንትሪያል ኮንቬንሽን ሲሆን ይህ ስምምነትን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት የሚገዛባቸውን ደንቦች ለማዋሃድ የወጣው የሞንትሪያል ኮንቬንሽን በአዋጅ ቁጥር 820/2006 ተብሎ በሚጠቀሰው አፅድቃው የሀገሪቱ የሕግ አካል ሁኗል። ይህንንም የሞንትሪያል ኮንቬንሽንን መሰረት በማደረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.171352 ላይ አንድ ዕቃ በአየር መንግድ ተጭኖ ሲጓጓዝ ባለዕቃው ሲያስረክብ በዕቃው ያለውን ልዩ ጥቅም በመግለፅ ተገቢውን ተጫማሪ ዋጋ መክፈሉን ካላስረዳ በቀር ዕቃው ተጓጉዞ ርክክብ እስከሚፈፀም ድረስ ባለው ጊዜ ቢጠፋ ወይም ጉዳት ቢደርስበት የሞንትሪያል ቃል ኪዲን (Montreal Convention of 1999) አንቀጽ 22 (3) እና በአዋጅ ቁጥር 820/2006 መሰረት ካሳ ሊከፈል የሚገባው በጣፈው ዕቃ ወይም ጉዳት በደረሰበት ዕቃ በአንድ ኪሎ ግራም 17 ስፔሻል ድሮዊንግ ራይት በመክፍል ነው በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጎም ሰጥቷል።
ከዚህ ላይ በየብስ ዕቃ ማጓጓዣ ስራን ለመደንገግ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 2(11) ላይ እንደተቀመጠው ስፔሻል ድሮዊንግ ራይት (Special drawing rights) ማለት በጥቅል ወይም በኪሎ ግራም የተጠቀሰው የአጓጓዡ የሃላፊነት መጠን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ አሰራርን መሰረት በማድረግ ገንዘቡ ከሚከፈልበት ሀገር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ምንዛሬ ተመን ማለት ነው። በኢትዮጵያ የእቃውን ዋጋ ሂሳብ ለመስራት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመጀመሪያ የአንድ የአሜሪካን ዶላር ስንት ስፔሻል ድሮዊንግ ራይት እንደሆነ እና በዚያን ቀን አንድ የአሜሪካን ዶላር ስንት የኢትዮጵያ ብር እንደሆነ አስልቶ እንዲልክ ሲታዘዝ ከበየነ-መርብ ቋቱ ላይ የየቀኑ በየዓመተ-ምህረቱ የተቀመጠ በመሆኑ ለፍርድ ቤት አስልቶ ይልካል።
አንድ የዕቃ አስጫን አንድን ዕቃ በአየር መንግድ አስጭኖ እና የአየር መንገዱ በአግባቡ ተረክቦ ሲያጓጉዝ ዕቃው ተጓጉዞ ርክክብ እስከሚፈፀም ድረስ ባለው ጊዜ ቢጠፋ ወይም ጉዳት ቢደርስበት ዕቃ አስጫኙ የሞንትሪያል ቃል ኪዲን (Montreal Convention of 1999) እና በአዋጅ ቁጥር 820/2006 መሰረት ካሳ ካሳ መጠየቅ የሚችለው አውሮፕላኑ ከዕቃ ማራገፊያው ከደረሰበት ወይም መድረስ ከነበረበት ወይም ካቆመበት ቀን ጀምሮ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመሆኑ በሞንትሪያል ቃል ኪዳን አንቀጽ 35 ላይ በግልፅ ተቀምጧል። በመሆኑም በአየር ሲጓጓዝ በዕቃ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ የይርጋ ጊዜው 2 ዓመት ነው።
2.4.በየብስ ለተጫነ ዕቃ የካሳ ጥያቄ ሕግ ይርጋዎች
ዕቃዎች ከባህርና ከአየር መጓጓዝ በተጨማሪ በየብስ ብቻ ሊጓጓዙ ይችላሉ። እንዳውም እንደኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ዕቃ የሚጓጓዘው በየብስ ነው። በየብስ ዕቃዎች ሲጓጓዙ የመኪና መገልበጥ ጉዳት በመድረሱ ዕቃውን አጓጓዥ ለአስጫኙ ሳያደረስ ይቀራል፤ እቃው መኪና ላይ እንደተጫነ የሰረቃል፤ ይዘረፋል፤ ይቃጠላል። በእነዚህ ምክንያት አጓጓዥ ዕቃውን በውሉ መሰረት ለዕቃ አስጫኙ ሳያስረክብ ሲቀር ዕቃ አስጫኝ በደረሰበት ጉዳት መጠን ከአጓጓዡ ላይ ካሳ ይጠይቃል።
የእቃ አስጫኝ አጓጓዡ ላይ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ በየብስ ዕቃ ማጓጓዣ ስራን ለመደንገግ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 35 መሰረት የይርጋው ጊዜ 2 ዓመት ነው። የይርጋው ጊዜ የሚጀምርብት ቀን ግን እንደ ነገር ሁኔታው የሚለያይ ሲሆን ዕቃው የጠፋው ወይም የተጎዳው ወይም ከማስረከቢያው ጊዜ የዘገየው በከፊል ከሆነ ከማስረኪቢያው ቀን ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 35(1) (ሀ) መሰረት ይርጋው ይቆጠራል።
ዕቃው የጠፋው ወይም የተጎዳው ወይም ከማስረከቢያው ጊዜ የዘገየው በሙሉ ከሆነ እና የማስረከቢያ ጊዜ በውሉ ላይ ካለ ይህ ጊዜ ካለቀ ጀምሮ በ60 ቀናት ውስጥ፤ የማስረከቢያ ጊዜ በውሉ ላይ ከሌለ ይህ ዕቃው ከተጫነበት ቀን ጀምሮ በ60 ቀናት ካለፈ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 35(1) (ለ) መሰረት ይርጋው መቆጠር የሚጀምር ይሆናል። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 35(1) (ሐ) መሰረት በሌሎች ሁነቶች የማጓጓዣ ውሉ የተደረገበት ካለቀ ከ3 ወር በኋላ ይርጋው መቆጠር የሚጀምር ይሆናል።
እነዚህ የይርጋ ጊዜ የእቃ አስጫኙ ለአጓጓዡ ጉዳት የደረሰባቸውን ወይም ሳይረከብ የዘገዩ ዕቃዎችን በተመለከተ ካሳውን እንዲከፍለው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እነዚህ ዕቃዎች ከሚመለከቱ ከተገቢው የሰነድ ማስረጃ ጋር ከላከለት ይህ አጓጓዥ ለዕቃ አስጫኙ ወይም ለዕቃ ተረካቢው በጽሑፍ መልስ እስከሚሰጥ ድረስ የይርጋ ጊዜው በአዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 35(2) መሰረት ይራዘማል። ይህም ማለት የዕቃ አስጫኙ ለዕቃ አጓጓዥ ለሰጠው ማስጠኝቀቂያ በጽሑፍ መልስ እስከሚሰጥ ድረስ የይርጋ ጊዜው መቆጠር አይጀምርም ማለት ነው።
በዚህ የይርጋ መራዘም ተጠቃሚ ነኝ የሚለው የዕቃ አስጫኝ ለአጓጓዡ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የሰጠው እና የደረሰ ለመሆኑ ማስረዳት ያለበት ሲሆን ዕቃ አስጫኝ ይህንን አስረድቶ አጓጓዥ ማስጠንቀቂያ አልደረሰኝም የሚል ከሆነ አዋጅ ቁጥር 457/1999 አንቀጽ 35(3) መሰረት አለመድረሱን የማስረዳት ግዴታ አለበት። በሌላ አነጋገር ከሳሹ ማስጠንቀቂያ ለመስጠቱ እና ለመደረሱ ካስረዳ ተከሳሽ ማስጠንቂያ ያልተሰጠው እና ያልደረሰው ለመሆኑ የማስተባበል ግዴታ አለበት።
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments