Font size: +
8 minutes reading time (1637 words)

በቂ ምክንያት ሳይኖር ዳኛ ከችሎት ይነሳልኝ በሚል የሚቀርብ ማመልከቻ ላይ ስለተቀመጠው ቅጣት

ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝ ከታች እንደተገለጸው አንድ ተከራካሪ ወገን በፍ/ቤት ክርክር በሚያቀርብበት ወቅት ሊያጋጥሙት ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ከችሎት ይነሳልኝ (ችሎት ይቀየርልኝ) በሚል የሚቀርብ አቤቱታ ሲሆን ዳኞች ከችሎት የሚነሱባቸውን ምክንያቶችና ባለጉዳዮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 25/88 ከአንቀጽ 27 እስከ 30 ባሉት ድንጋጌዎች የተመለከተ ሲሆን የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አላማ እነዚህን ምክንያቶች ማብራራት ሳይሆን ማመልከቻው ውድቅ ቢደረግ አመልካቹ (ተከራካሪው) ሊቀጣ የሚችለውን አዋጁ በአንቀጽ 30 ላይ ያስቀመጠውን የገንዘብ መቀጫ አግባብነትና ፍትሃዊነት ላይ ሃሳብ ለመስጠት ነው፡፡

አንቀጽ 30 - በቂ ምክንያት ሳይኖር የሚቀርብ ማመልከቻ ስለሚያስከትለው ቅጣት

“ከተከራካሪዎቹ አንድኛው ወገን ዳኛው ከችሎት እንዲነሳለት ያቀረበው ማመልከቻ በቂ ምክንያት ሳይኖረው የቀረ እንደሆነ ፍ/ቤቱ ማመልከቻውን ውድቅ አድርጎ በአመልካቹ ላይ እስከ አምስ መቶ (፭፻) ብር መቀጫ ሊጥልበት ይችላል፡፡”

በማለት ቅጣት ያስቀመጠበትን አግባብ ለመመዘን ሲሆን ምንም እንኳን ህግ አውጪው እና ህጉን በማርቀቅና በማዘጋጀት ከተሳተፉት አካላት እና ግለሰቦች አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል እውቀት ባይኖረኝም ባለኝ የህግ እውቀትና ግንዛቤ የተሰማኝንና ያመንኩበትን ሀሳብ በማንሳት ህጉ (አ/ቁ. 25/88) ሲሻሻልም ይሁን በሌላ አዋጅ ሲተካ ሊነሳ የሚችል ነጥብን ለማመላከትና ህግ ተርጓሚው አካል ህጉን በሚተረጉምበት ወቅት በቀጥታ እንደወረደ ተግባራዊ ከማድረግ በፊት በህጉ ላይ የሚታዩ ስህተቶች /ግድፈቶች ካሉ እንዲታዩ ሀሳብ ለማቅረብ ሲሆን በሌላም በኩል የተለየ አመለካከት ያለው ካለም የተሻለውን ሃሳብ ለማግኘትና ለውይይት በር ለመክፈት ያክልና ለመማርም ጭምር የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው፡፡  

እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ከችሎት ይነሳልኝ ጥያቄን በተመለከተ የሚቀርቡ ሁሉም ማመልከቻዎች እውነትነት አላቸው ወይም የሚጠቀሱት ምክንያቶች አሳማኝና በቂ ናቸው ብሎ ጸሃፊው እንደማያምንና በዚህ አጋጣሚ ተከራካሪዎች የሃሰት ቅሬታ በማቅረብ ለሚፈልጉት ዳኛ (ችሎት) እንዲቀርብላቸው የሚያደርጉበት ሁኔታና አጋጣሚ ያለ መሆኑንም ጪምር ጸሃፊው ባሳለፈው የዳኝነት ቆይታም ይሁን ዳኝነትን ከለቀቀ ቡሃላ ባሉት የስራ አጋጣሚዎች ያረጋገጠ መሆኑን ከወዲሁ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ እንዲሁም አንድ ማመልከቻን በህግ አግባብ መዝኖ ውድቅ የማድረግን ስልጣንና የሙያ ሃላፊነትና ብቃትን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባትም አይደለም ፤ ዳኛ የመሰለውንና ያመነበትን ሊወስን ሙሉ ነፃነት ያለው መሆኑንና ለዳኝነት ነፃነት መጎልበትም ከሚታገሉ ባለሙያዎችም አንዱነኝ በማለት  በድፍረት መናገርም እችላለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ቅጣት የተቀመጠበት አግባብ ህግን የተከተለ አይደለም

መብት በመሆኑ

አንድ ተሟጋች በመረጠው ዳኛ መዳኘት ባይባልም ነገር ግን በህግ አግባብ የተሾመ ዳኛ ጉዳዩን ለሙያውና ለስራው ታማኝና እውነተኛ በሆነ ዳኛ ጉዳዩ እንዲታይለትና ዳኝነት እንዲያገኝ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ለዚያም ነው አ/ቁ. 25/88 እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 31 እንዲሁም ለማነፃጸሪያነት ይረዳን ዘንድ የአብክመ ዝክረ ህግ አ/ቁ. 223/2007 አንቀጽ 24 እና 25 ላይ በግልጽ ከችሎት ለማስነሳ (ችሎት ለማስቀየር) ማመልከት እንደሚቻልና ችሎት ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችና ምክንያችን ዘርዝረው ያስቀመጡት፡፡ችግሩ አለ በዚህ ችሎት እነዚህ ምክንያቶች ባሉበት ሁኔታ ትክክለኛ ፍትህ አላገኝም በማለት ማመልከት እንዲችል ህጉ መብት ሰጥቶታል፡፡ መብቱን በአግባቡ ካልተጠቀመ ደግሞ ማመልከቻን ውድቅ በማድረግና ኪሳራ በማስከፈል መቅጣት እየተቻለ ተጨማሪ የገንዘብ መቀጮ ማስቀመጡ አግባብነት የሌለው ነው፡፡

ሁለትና ከዚያ በላይ ቅጣት የሚጣልበት በመሆኑ

ችሎት ይቀየርልኝ ወይም ይነሳልኝ በማለት የቀረበውን ማመልከቻ በቂ ምክንያተ ስላልቀረበበት አልተቀበልኩትም (አልተቀበልነውም) በማለት ችሎቱ ማመልከቻውን ውድቅ ማድረጉ በራሱ እንደ ቅጣት ሊወሰድ ይገባል፡፡ ግለሰቡ ያቀረበው ማመልከቻ ወደ ሚፈልገው ችሎት (ዳኛ) እንዲሄድለት በማሰብ ወይም የዚህ አይነት ሃሳብ ባይኖረውም የፍርድ ስርአቱን በማየት በመስጋት ወይም በፍራቻና በጥርጣሬ ይፈረድብኛል ፣ ትክክለኛ ፍትህ አላገኝም በሚል ስጋት አንድ ምክንያት ፈጥሮ ያቀረበው ማመልከቻም ይሁን በርግጥ አዋጁ የገለፃቸው ምክንያቶች አጋጥመውት (ተከስተው) አዋጁ ስለሚፈቅድ በሚያቀርበው ማመልከቻ ጥያቄው ውድቅ ከመደረጉም በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል ማለት ነው፡፡

ሌላኛው በአዋጁ ውስጥ የተካተተው የቅጣት አይነት ፍታብሄራዊ ይዘት ያለው ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 29 ላይ የተቀመጠው ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ላይ እንደተቀመጠው ማመልከቻው ውድቅ የተደረገበት ተከራካሪ ማመልከቻው በመቅረቡ ላስከተለው ኪሳራ ወዲያውኑ እንዲከፍል ፍ/ቤቱ መወሰን ይችላል፡፡ ማመልከቻውን ያቀረበው ተከራካሪ ወገን ምክንያቱ በቂ ሳይሆን ሲቀር የሚከተለው ውጤት 1ኛ. ማመልከቻው ውድቅ ይደረግበታል 2ተኛ. ኪሳራ እንዲከፍል ይደረጋል ወይም ሊከፍል ይችላል 3ተኛ. የገንዘብ መቀጫ ሊቀጣ ይችላል ፡፡ በአንድ  ድርጊት ሁለትና ከሁለት በላይ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ በአንድ በተመሳሳይ ጉዳይ ከአንድ ግዜ በላይ አንድ አጥፊ ሊቀጣ አይገባም የሚለውን የወንጀል መርህ የሚጥስ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ድንጋጌ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ያላቸውን ቅሬታና የመብት ጥያቄ እንዳያቀርቡ የሚያደርግ ክልከላ የሚያደርግ ድንጋጌ ነው፡፡

የወንጀል ባህሪ ስለሌለው

ድርጊቱ ወንጀል አይደለም የምለበትን መሰረታዊ ምክንያቶች ከማብራራቴ በፊት ምናልባት በአንባቢዎች ሊከሰት የሚችልን ጥያቄ ላንሳና መልስ መስጠት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ እሱም ከወንጀል ህግ ጋር ምን አገናኘው ? ፍ/ቤት መቅጣት ካለበት የሚቀጣው እንጂ የወንጀል ህግና አስተሳሰብ ወይም አስተምሮ ወደዚህ ሊመጣ አይአችልም የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም  አንድ ድርጊት በፍ/ቤት ወይም በህግ ስልጣን በተሰጠው አካል እንዲቀጣ ከተባለና ቅጣት ከተላለፈበት ድርጊቱ ወንጀል ነው ወይም የወንጀል ባህሪ አለው ማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ ችሎት መድፈር በፍ/ቤት በገንዘብ መቀጫ ወይም በእስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ድርጊቱም ወንጀል በመሆኑ በወንጀል ህጉ አንጽ 449 ፍርድ ቤትን መድፈር በሚል ተደንግጎ ይገኛል ሌሎችንም በተመሳሳይ መጥቀስ ይቻላል፡፡ችሎት መድፈር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.448 ላይ የሚያስቀጣ መሆኑም ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ የችሎት መድፈር ወይም ፍ/ቤትን መድፈር ወንጀል በመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህጉ ቅጣት ከማስቀመጡም በተጨማሪ የወንጀል ህጉም አካቶታል፡፡ ሌላው ቅጣት መቀመጡ ወንጀል መሆኑ ታሳቢ በማድረግ ነው የምልበት ምክንያት አዋጁ አንቀጽ 29 ላይ ያስቀመጠው የወጪና ኪሳራ ድንጋጌ ነው፡፡ ማመልከቻው በመቅረቡ ያስከተለውን ኪሳራ በተመለከተ ፍ/ቤቱ ማመልከቻውን ያቀረበውን አካል እንደሚያስከፍለው ደንግጓል፡፡ ኪሳራውን እንዲሸፍን የተደረገው ፍታብሄራዊ ሲሆን የሚካሰው ደግሞ ሌላኛው ማመልከቻውን ያላቀረበው ተከራካሪ ወገን እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ አንቀጽ 30 ላይ የተጠቀሰው ቅጣት የወንጀል ድንጋጌ ባይሆን ኑሮ አንቀጽ 29 ላይ የተቀመጠውን ወጪና ኪሳራ እንዲከፍል ባልተደረገ ነበር፡፡ አንዱ ድንጋጌ ፍታብሄራዊ ሃላፊነት እንዲያስከትልበት የተቀመጠ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በወንጀል ሃላፊነት ለመቅጣት የተቀመጠ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንቀጽ 30 ላይ የተቀመጠው ቅጣት የወንጀል ባህሪ ስላለው በወንጀል ህግ ያሉትን መስፈርቶች ያሟላል አያሟላም የሚለው መመዘን ያለበት መሆኑን በማመን ካለው የወንጀል ህግና አስተምሮ አንፃር የተሰማኝን እና ያመንኩበትን አስቀምጫለሁ፡፡  

የወጀል ህጋችን አንቀጽ  23(2) ላይ አንድ ድርጊት በጥፋተኝነት በፍ/ቤት ሊያስቀጣ የሚችለው ድርጊቱ ሶስት ነገሮችን ሲያሟላ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህም ማለት አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት እነዚህን ነገሮች ካላሟላ ወንጀል ባለመሆኑ የጥፋተኝነት እና ቅጣት ውሳኔ ሊተላለፍበት አይገባም ማለት ነው፡፡ ሶስቱ መስፈርቶችም ህጋዊ ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ናቸው፡፡ የተያዘውን ነጥብ በነዚህ መስፍርቶች በተከታይ በመመዘን በአዋጁ አንቀጽ 30 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ አግባብነት የሌለው መሆኑን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

 ሀ. ህጋዊ መስፈርትን ያሟላ አይደለም (የወንጀል ህግ አን. 2(2) እና 23(1))

በአዋጁ አንቀጽ 30 ላይ የተቀመጠው ቅጣት ህጋዊ መስፈርትን ማሟላቱን የሚያሳይ ነው የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል ነገር ገን እንደ እኔ አረዳድ አንቀጽ 30 እንደ ወንጀል ድንጋጌ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የችሎት ይነሳልኝ ማመልከቻ ማቅረብ እንደ ድርጊት ከቆጠርነው ሊያስቀጣ የሚገባው ማመልከቻ አለማቅረብ እንጂ ማመልከቻ ማቅረብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አዋጁ እራሱ የተጠቀሱት ምክንያቶች ካጋጠሙ ማመልከት እንደሚቻል ስለፈቀደና የቀረቡት ምክንያች አሳማኝ ወይም በቂ ከሆኑ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንዲሁም ችሎቱ ሊቀየር ወይም ዳኛው ሊነሳ እንደሚገባ የሚደነግግ በመሆኑ ነው፡፡ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚችል ተደንግጎ የቀረበው ምክንያት በቂ ካልሆነ ማመልከቻውን ውድቅ የማድረግ ውጤት የሚኖረው እንጂ ድርጊቱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚያስቀጣ መሆን አልነበረበትም፡፡ ድርጊቱ ማመልከቻን ውድቅ ከማድረግና ካለማድረግ ወይም ምክንያቱን ከመቀበልና ካለመቀበል ጋር የተያያዘ ሲሆን የምክንያቱ በቂ (አሳማኝ) አለመሆን በሌላ አካላ (ግለሰብ) ላይ ያደረሰው ጉዳትም ይሁን የመብት ጥሰት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔት የለም፡፡ በተለይ በወንጀል ህግ እንዳይደረግ የተከለከለን ድርጊት በማድረግ የመብት ወይም የጥቀም ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ 

ለ. ግዙፋዊ መስፈርትን ያሟላ አይደለም

ግዙፋዊ መስፈርት ማለት አድርግ ተብሎ አለማድረግ ወይም አታድርግ የሚለውን የወንጀል ድንጋጌ በመተላለፍ ያደረገ ከሆነ የሚያስቀጣና በድርጊቱ ወይም ባለማድረጉ የተጎዳ ፣ የጠፋ ወይም የታጣ መብት እና ጥቅም ማለት ነው ፡፡ በተነሳው ጉዳይ አንድ ባለጉዳይ ህጉ በፈቀደለት አግባብ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ምክንያቶችን በመጥቀስ ማመልከቻ ማስገባቱ አድርግም ወይም አታድርግ የሚለውን መስፈርት የሚያሟላ አይደለም፡፡ አዋጁ ቅጣት ያስቀመጠው ማመልከቻ በማቅረቡ ቢሆን አታድርግ የሚለውን መስፈርት ተላልፏል ማለት ይቻል ነበር ነገር ግን ቅጣቱ የተጣለው ማመልከቻው በመቅረቡ ሳይሆን በማመልከቻው ላይ የተገለጹት ምክንያቶች በቂ ባለመሆናቸው ነው፡፡ የቀረቡት ምክንያቶች በቂ አለመሆናቸው አድርግም አታድርግም ማለት አይደለም፡፡ በተጨማሪም ምክንያቶቹ በቂ አለመሆናቸው በሌላ አካል ላይ የመብት ጥሰትም ይሁን ጉዳት የሚያስከትሉ አይደሉም፡፡ ይህ ማለት በቂ አለመሆናቸው ጥያቄውን ውድቅ በመደረጉ የተጎዳም ይሁን የታጣ ወይም የጠፋ መብት ወይም ጥቅም የለም ፡፡ እንዳውም አመልካቹ እራሱ ጥያቄው ውድቅ በመደረጉ የሚጎዳ ከመሆኑ በስተቀረ፡፡

ሐ. ሞራላዊ መስፈርትን ያሟላ አይደለም (የወንጀል ህግ አን. 57(1)፣ 58)

ሞራላዊ መስፈርት ስንል የአድራጊውን የሃሳባ ክፍል የሚመለከት ሲሆን ድርጊቱን ለማድረግ ሃሳብ ነበረው አልነበረውም ፡ ድርጊቱን የፈጸመው በማወቅ ነው አይደለም የሚሉትን የሚመለከት ነው፡፡ ወደ ያዝነው ጉዳይ ስንመለስ አንድ ባለጉዳይ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ምክንያቶች ሲያጋጥሙት እነዚህን ምክንያች በመጥቀስ ችሎት እንዲቀየርለት መጠየቅ እንደሚችል መብት ተሰጥቶታል፡፡ እንዲጠይቅ መብት በተሰጠው ነገር ላይ ማመልከቱ ሆን ብሎ እያወቀ ወይም በቸልተኝነት የሚያደርገው ድርጊት ጥፋት ወይም ወንጀል ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት የህግ አውጪው እሳቤ በሃሰተኛ ምክንያትና ማስረጃ ዳኞች እንዳይወነጀሉ እንዲሁም ባለጉዳዮች ለሚፈልጉት ዳኛ ወይም ችሎት እንዲቀርብላቸው በማሰብ በፈጠራ ማመልከቻ እንዳያቀርቡ ለመከላከል የተቀመጠ ድንጋጌ ነው ሊባል ይችል ይሆናል ግን መሰረታዊ የሆኑ ከላይ የገለጽናቸውን መብቶችና ሁኔታዎች እየተጣሰ ሳይሆን አዋጁ በራሱ ከቅጣቱ ውጪ ባስቀመጣቸው ማመልከቻውን ውድቅ በማድረግና ኪሳራ እንዲከፍል በማድረግ መከላከል የሚቻል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ባይነኝ፡፡

ከህጉ አላማና ያስገኛል ከተባለው ጥቅም አኳያ ሲታይ

አዋጅ ቁጥር 25/88 እንደሌሎቹ ህጎችና አዋጆች ሰፊ የሆነ የህጉን አስፈላጊነትና አላማ እንዲሁም ህጉ በመውጣቱ ሊገኝና ሊጠበቅ ወይም ሊረጋገጥ የታሰበውን ጥቅምና መብት እንዲሁም ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፍትሃዊ  በሚያስረዳ መልኩ ፕሪአምብል የለውም፡፡ በመግቢያው ላይ የተገለጸው የዳኝነት ስልጣን በክልልና በፌደራላ መንግስቱ መካከል የተከፋፈለ ስለሆነና የፌደራል ፍ/ቤቶችን ስልጣን መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ የታወጀ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አጪርና ሰፊ ማብራሪያ ካልተሰጠው ፕሪያምብል ተነስተን የህጉ አስፈላጊነት የፌደራል ፍ/ቤቶችን ስልጣን ለመወሰን የወጣ ስለሆነ የዳኞችን ከችሎት መነሳትና የችሎት ይዛወርልኝ ወይም ይነሳልኝ አቤቱታ በአዋጁ መካተት የለበትም በማለት ክርክር ሊነሳ ይችል ይሆናል ምክንያቱም የችሎት ይነሳልኝ ጥያቄ ከዳኞች ስነ-ምግባር ጋር የተያያዘ ስለሆነ መካተት ያለበት የዳኞችን ስነ-ምግባር በተመለከተ በሚደነግገው አዋጅ ወይም ደንብ / ኮድ ኦፍ ኮንታክት / ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ክርክር እንደተጠበቀ ሁኖ በአዋጁ የተካተተበት ሁኔታ ስላለና መካተቱም የሚያመጣው ችግር ስለሌለ በዚህ ባለበት ሁኔታ መቀመጡ የስነ-ምግባር ኮዱ እስኪዘጋጅ ግዜ ስለሚወስድ የተፋጠነ ፍትህ ከመስጠት አኳያ በማየት በአዋጁ መካተቱ ላይ ትችትም ይሁን የተለየ አሰተሳሰብ የለኝም፡፡

ወደ ተነሳው ነጥብ ስመለስ አንድ ህግ ሲወጣ ለማህበረሰቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፍትህዊ ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ነው፡፡ በዋናነት የወንጀል ጥፋቶችንና ቅጣቶችን ይዞ የወጣው የወንጀ ህግ እንኳን የሚያስቀምጠው ቅጣትና የቅጣት አፈፃጸሙ ሊተረጎምና ሊተገበር የሚገባው በአስተማሪነቱ እንጂ ቅጣትን አላማው በማድረግ አይደለም መሆንም የለበትም፡፡ አ/ቁ. 25/88 አንቀጽ 30 ድንጋጌ የተቀመጠው ቅጣት ይህን የማስተማር አላማ ይዞ የተነሳ አይደለም፡፡ ከአስተማሪነቱና ለማህበረሰቡ በተለይ የፍ/ቤት ተገልጋይ በሆነው የማህበረሰብ ክፍል ማህበራዊና ፍትሃዊ ተግዳሮቶችን ከመቅረፍ ይልቅ ቅጣት ይተላለፍብኛል በሚል እሳቤን በማስረጽ ተገልጋዩ በዳኝነት ተቋሙ ላይ ሊያነሳ የሚችለውን የፍትህና የመብ ጥያቄ ከወዲሁ እንዲተወው የሚያደርግ ውጤት አለው፡፡ ከችሎት እንዲነሳ የሚያስችሉ የስነ-ምግባር ግድፈቶች መኖራቸውን እያወቀ የማመልከቻውን ውድቅ መሆን ተከትሎ የሚመጣውን ቅጣት በመፍራት የተጓደለ ፍትህ እና ሚዛናዊ ያልሆነ ውሳኔ እንዲሰጠው አሜን ብሎ እንዲቀበል የሚያስገድድ ድንጋጌ ነው፡፡ ስለዚህ ድንጋጌው በመውጣቱ የህብረተሰቡን ጥቅምና መብት ከማስጠበቅ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ነው፡፡

ማጠቃለያ

ከጽሑፉ አርእስት ላይ እንደተገለጸው የአ/ቁ. 25/88 አንቀጽ 30 ድንጋጌ ያስቀመጠው ቅጣት ከላይ ባስቀመጥኩት ማብራሪያና ምክንያቶች “ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ” የሚለውን አባባል የሚያጠናክርና በእጅ አዙር የሚያስፈጽም ነው፡፡ ማህበረሰባችን ለፍ/ቤት ያለው የገዘፈ አመለካከትና ፍራቻ ላይ የዚህ አይነት ድንጋጌ መቀመጡ ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ እንደመጨመር የሚታይ ነው፡፡ ሥለዚህ ከችሎት ይነሳልኝ ማመልከቻን ተከትሎ ማመልከቻው ውድቅ ከተደረገ ቅጣት የሚከተል መሆኑ መቀመጡ ኢ-ፍትሃዊ ነው ባይነኝ፡፡ ህግ ሲተረጎምም ይሁን ሲፈጸም መታሰብ ያለበት ህጉ የወጣውና የተቀመጠው ማህበረሰቡን ለማገልገልና ለመጠበቅ እንዲሁም የማህበረሰቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠበቅ በሚያስችለው መልኩ ስለሆነ ህጉ ቁረጥ፣ ፍለጥ ስላለ ብቻ የምንቆርጥና የምንፈልጥ ከሆነ የራሳችንን ህብረተሰብ ህግን መሳሪያ በማድረግ የምንጎዳ በመሆኑ ከህጉ ማህበረሰቡ የሚጠቀምበትንና የማይጎዳበትን ዘዴ መከተልና መጠቀም ያለብን መሆኑን አምናለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡  

 

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Contemporary Violations of Human Rights in Ethiopi...
Effect of Irregularities in Public Contract Awardi...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024