ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት አስር አመታት ስትጠቀምበት የነበረውን የንግድ ሕግ በማሻሻል በአዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ተክታለች፡፡ ለቀድሞ ንግድ ህግ መሻሻል የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም በሌላው ዓለም የተለመዱ እና ለንግዱ ማህበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ የንግድ ማህበራትን ማካተት አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ በቀድሞ የንግድ ህግ አንድ ነጋዴ ሊመሠርት የሚችለው የንግድ ማህበር ወይም ድርጅት ስድስት ዓይነት ሲሆን እነዚህም ተራ የሽርክና ማህበር (ordinary partnership)፣ የህብረት ሽርክና ማህበር (general partnership)፣ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር (limited Partnership)፣ የእሽሙር ሽርክና ማህበር (joint venture) ፣ የአክሲዮን ማህበር (share company) እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል (private limited company) ማህበር ናቸው፡፡   

በአዲሱ የንግድ ሕግ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One person private limited Company) እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር (Limited Liability Partnership) አዲስ የተጨመሩ ማህበራት ሲሆኑ ተራ የሽርክና ማህበር ደግሞ ከአማራጭ ማህበርነት ተቀንሷል፡፡ የዚህ አጭር ፅሁፍ ዓላማ አዳዲስ የተጨመሩትን እንግዳ የንግድ ማህበራት በመመርመር ማስተዋወቅ ነው፡፡

ይህ ፅሁፍ የህግ አስተያየትን እንዲተካ በማሰብ የተዘጋጀ ባለመሆኑ በዚህ ፅሁፍ የሠፈሩትን ሃሳቦች መሠረት በማድረግ ውሳኔ ለመስጠት የህግ አስተያየት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

2. ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One person private limited Company)፣

 2.1 ስለ ማህበሩ ባህሪያት እና አመሠራረት

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማለት አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ (Unilateral Declaration) መሠረት የተቋቋመ የንግድ ማህበር ነው:: ማህበሩ ከአባላት የተለየና የተነጠለ የራሱ የህግ ሰውነት ወይም corporate existence አለው፡፡ ይህን ማህበር ለማቋቋም የሚያስፈልገው አነስተኛ ካፒታል መጠን ብር 15,000 (አስራ አምስት ሺህ) ነው፡፡

ይህ የንግድ ማህበር በአገራችን ከተለመዱት የንግድ ማህበራት የተለየ ሲሆን በአዲሱ የንግድ ህግ የተካተተበት ምክንያት አንድ ማህበር (ኩባንያ) ለመመስረት በቂ ካፒታል የያዘ ባለሃብት የግድ ምናባዊ (fictitious) ማህበርተኛ መፈለግ እንዳይገደድ ፤ የተለያየ ካፒታል በመመደብ ለሥራ የሚውለውን ገንዘብ ነጥለው ሥራ መስራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች እድል ማመቻቸት፤ በሌሎች ሃገራት የተለመዱ የንግድ ማህበራት ወደ ሃገራች ማካተት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመሠረተው አባሉ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት በመቅረብ በሚሠጠው መግለጫ መሰረት ነው፡፡ ይህን መግለጫ መመስረቻ ፅሁፍን የተካ ነው፡፡ መግለጫው ማህበሩ ከተለመዱት ዝርዝሮች በተጨማሪ አንድ አባል ብቻ ያለው መሆኑን፣አባሉ የሞተ፣ የጠፋ ወይም በፍርድ የተከለከለ እንደሆነ ስለ ወራሾች ወይም ስለአባሉ ሆኖ ሕጋዊ ተግባራትን እዲፈፅም የታጨው የንብረት ጠባቂ ሰው ስም እና ዕጩ ንብረት ጠባቂው ፍቃደኛ ሆኖ ኃላፊነቱን የተቀበለ መሆኑ ሊያካትት ይገባል፡፡

ዕጩ ንብረት ጠባቂ መሰየም የምስረታ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ዕጩ ንብረት ጠባቂው ዕጩነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት ቀርቦ ካላረጋገጠ ማህበሩ ሊመሰረት አይችልም፡፡ አንድ ንብረት ጠባቂ በአንድ ጊዜ ለተለያዩ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለሆኑ ማህበራት ንብረት ጠባቂ ሆኖ ሊሾም አይችልም፡፡

አንድ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሌላ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሊያቋቋም አይችልም ይህን ተላላፎ የተቋቋም ማህበር ያገባኛል በሚል ሰው ጠያቂነት ሊፈር እንዲሁም በምስረታው ምክንያት እና በኋላ ለሶስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት አባሉና ማህበሩ በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ ይሆናሉ፡፡

አንድ ግለሰብ ነጋዴ (Sole proprietor) ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማህበር መለወጥ የሚችል ሲሆን ግለሰቡ ማህበሩን ከመመስረቱ በፊት ለገባበት ዕዳ ሁሉ ከማህበሩ ጋር በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ ይሆናል፡፡

 

2.2 ስለ ማህበሩ ሥራ አመራር እና ኃላፊነት ወሰን፣

 

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንደ ማንኛውም ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊኖረው ግዴታ ሲሆን ፤ አባሉ ራሱ ወይም ሌላ ሰው የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ በህግ የተሠጠው ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

አባሉ በንግድ ሕጉ ለአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠቅላላ ጉባዬ የተሠጠው ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ አባሉ በጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣኑ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ቃለጉባዔ ስበሰባው በተደረገ ከሦስት ሣምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፅሁፍ ተዘጋጅተው የማህበር ማህደሩ ውስጥ ሊቀመጡ እንዲሁም ውሳኔዎቹ የማህበሩን ማቋቋሚያ መግለጫ የሚለውጡ ከሆነ ውሳኔው ከተሠጠበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይህን ቅድመ ሁኔታ ባይሟላ እንኳን ውሳኔዎቹ በሕግ የሚፀኑ ቢሆንም ጉድለቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አባሉና ማህበሩ በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂዎች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የአባሉ ኃላፊነት የተወሰነ (Limited Liability) ቢሆንም አባሉ ወይም በማህበሩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ያለው ሌላ ሰው ማህበሩን፣ ወይም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ጉዳት ላይ የሚጥል ሕገ ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ ከፈፀመ፤ የማህበሩን ንብረትን ከራሱ ንብረት ጋር ከቀላቀለ፤ የማህበሩን እና የራሱን ማንነት ካልነጣጠለ፤ ስለማህበሩ የፋይናንስ አቋም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ካወጣ፤ ያለ ተመጣጣኝ ክፍያ የማህበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሦስተኛ ወገኖች የግል ጥቅም ካዋለ፤ በሕግ ሊከፈል ከሚችለው በላይ የትርፍ ክፍያ ከፈፀመ ወይም ተመሳሳይ ተግባራት ከፈፀመ ከማህበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናል ወይም በሌላ አገላለፅ የኩባንያን ጭምብል መግለጥ መርህ ወይም piercing the corporate veil principle ተግባራዊ ይሆናል፡፡

 

2.3 ስለማህበሩ መፍረስ፣

 

ስለ ማህበራት መፍረስ ከተጠቀሱት ጠቅላላ ድንጋጌዎች በተጨማሪ አባሉ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሂሳቡ ሳይጣራ እንዲፈርስ ከፈለገ ሂሳብ ሳይጣራ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ማህበሩ ሂሳቡ ሳይጣራ የፈረሰ እንደሆነ የማህበሩ ሃብት በጠቅላላው ለአባሉ ይተላለፋል፡፡ በማናቸውም ምክንያት ማህበሩ ከፈረሰ በኋላ ገንዘብ ጠያቂዎች የቀረቡ እንደሆነ አባሉ በግሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ማህበሩ ከፈረሰ በኃላ የሚቀርብ ገንዘብ ጠያቂ የሚያቀርበው ጥያቄ ማህበሩ መፍረሱን ካወቀ በአምስት ዓመት ወይም የማህበሩ ሀብት ለአባሉ ከተከፋፈለ በምንም ዓይነት ከአስር ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡

ከላይ በዝርዝር ከተመለከትናቸው ነጥቦች ውጪ ስለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተደነገጉት ህጎች ለባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም የሚያገለግሉ በመሆኑ ክፍተቶችን ለመሙላት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡

  

3. ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር (Limited Liability Partnership)፣

3.1 ስለ ማህበሩ ባህሪያት እና አመሠራረት

ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሙያና ለሙያው ደጋፊ የሆነ አገልግሎት (professional and complementary service) ለመስጠት የሚያቋቁሙት የማህበርተኞች ኃላፊነት በመዋጮዋቸው የተወሰነ የንግድ ማህበር ነው፡፡ ይህን ማህበር ሊያቋቁሙ የሚችሉት ሥልጣን ባለው መስሪያ ቤት የሙያ ፈቃድ ወይም ለሙያ ደጋፊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉ ለምሳሌ እንደ ህግ ባለሙያ፣ ጤና ባለሙያ ፣ የሂሣብ ባለሙያ አይነት የተፈጥሮ ሰዎች አሊያም ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበራት ናቸው፡፡

ይህ ማህበር ከአባላቱ የተለየ የህግ ሰውነት ያለው ፤ እንደ መክሰስ መከሰስእና በራሱ ስም ውል መዋዋል የመሳሰሉ ህጋዊ ድርጊቶች በራሱ ስም መፈፀም የሚችል ሲሆን የሽሪኮቹ መሞት ፣ መክሰር፣ ከማህበሩ መውጣት ወይም በሽርኮቹ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ለውጥ በማህበሩ ሕልውና፣ መብት ወይም ግዴታ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ ማህበሩ ስም ለማውጣት የተቀመጡት ማለትም ለሞራል ተቃራኒ አለመሆን ፣ የሌሎች ነጋዴዎችን መብት አለመጋፋት ወዘተ… የመሳሰሉ የህግ መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆነው የመረጠውን ሥም (Assumed Name) መጠቀም የሚችል ሲሆን ከስሙ በስተመጨረሻ ግን "ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር" የሚል ሐረግ መጨመር አለበት፡፡

በአዲሱ የንግድ ሕግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን ጨምሮ ከባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውጪ ያሉት ማህበራት በሙሉ የሚቋቋሙት በመመስረቻ ፅሁፍ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቀድሞ ሕግ የነበረው መተዳደሪያ ደንብ በአዲሱ ሕግ ቀሪ ተደርጓል፡፡ የዚህን ዓይነት ማህበር መመስረት የሚችሉት የሙያ ፈቃድ ያላቸው የተፈጥሮ ሰዎች ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበራት ናቸው፡፡

 

3.2 ሥለ ማህበሩ ሥራ አመራር እና ኃላፊነት ወሰን

ማህበሩ ምንም እንኳን ከተፈጥሮ ሰው በተጨማሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን በአባልነት መያዝ የሚችል ቢሆንም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ መሾም የሚችለው የተፈጥሮ ሰው የሆነ እና ማህበሩ አገልግሎት በሚሰጥበት ሞያ ፈቃድ ያለው ሸሪክ ብቻ ነው፡፡ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ የማህበሩን ዓላማ ለማሳካት በማህበሩ ስም ማንኛውንም ሕጋዊ ተግባር ለማከናወን የሚችል ሲሆን ይህን ሥልጣን የሚገድቡ ስምምነቶች ሶስተኛ ወገኖችን መቃወሚያ የሚሆኑት በንግድ መዝገብ የተመዘገቡ ወይም ሦስተኛ ወገኖች የሥራ ኃላፊነቱን የሚያውቁ መሆናቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው የማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ ሲሆን ይህም መመስረቻ ፅሁፍ ተቃራኒ ስምምነተ ከሌለ በአባላት ሁለት ሶስተኛ (2/3) ድምፅ በሚሰጥ ውሳኔ ሊሻሻል ይችላል፡፡ ሌላ ማንኛውም ውሳኔ በአብዛኛዎቹ አባላት የድምፅ ድጋፍ ማለትም (50+1) ሊፀድቅ ይችላል፡፡ የማህበሩ ዜግነት ወይም የሥራ መስክ ለመለወጥ የሚሰጥ ውሳኔ የሚፀናው በ3/4ኛ (ሶስት አራተኛ) ድጋፍ ድምፅ ነው፡፡

የማህበሩ እና የአባላት ኃላፊነት ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነጥብ ነው ፡፡ በመሠረቱ ህጋዊ ሰውነት እና የማህበሩ ኃላፊነት ውስንነት የማይነጣጠኑ ሀሳቦች ናቸው (corporate existence and limited liability are inseparable):: ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን የሚለው ስም በቁሙ ስንመለከተው ኃላፊነቱ የተወሰነው የሚመስለው የማህበሩ ነው ነገር ግን ዝርዝሩን ስንመለከት ኃላፊነቱ የተወሰነው የሽሪኮች ነው ምክንያቱም የሽሪኮች ኃላፊነት በመዋጮዋቸው የተወሰነ ነው፡፡ በእርግጥ የማህበሩ ኃላፊነትም ቢሆን በግልፅ አልተጠቀሰም እንጂ የኃላፊነቱ መጠን በማህበሩ ሀብት (Asset) ልክ ነው፡፡

ሥራ አስኪያጅ ወይም ሸሪክ ከመዋጮ ባለፈ ኃላፊ ሊሆን የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች የኩባንያውን ጭምብል መግለጥ ወይም (Pericing the corporate Veil) ይባላል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከሥልጣኑ በላይ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነቱ የማህበሩ ሳይሆን የሥራ አስኪያጁ ብቻ ነው፡፡ ሸሪኩ ወይም ሠራተኛው የማህበሩን ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ሆን ብሎ ወይም የማታለል ተግባር በመፈፀም ወይም በቸልተኝነት ለሚፈፅመው ጥፋት ወይም ለሚያደርሰው ጉዳት ጥፋቱን ካደረሰው ሸሪክ ወይም ሠራተኛ ጋር ማህበሩ በአንድነትና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ማህበሩ ጉዳት የደረሰበት አካል ጉዳት አድራሹ ሥልጣን ያልተሠጠው መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ ከኃላፊነት ነፃ ይወጣል፡፡ ማህበሩ ይህን መሠል ዕዳዎች ለመሸፈን የመድን ሽፋን እንዲኖረው በህግ ይገደዳል፡፡

 

3.3 አባል ከማህበሩ ስለሚወጣበት መንገድ እና ስለማህበሩ መፍረስ

አንድ አባል ከማህበሩ ሊወጣ የሚችለው የሶስት ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት (ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ) ፣ ሲሞት ወይም ህጋዊ ሰውነት ሲያጣ ፣ ድርሻው በገንዘብ ጠያቂዎች ሲወሰድ ፣ የሞያ ፈቃዱ ሲሰረዝ ወይም ለረጅም ጊዜ ሲታገድ፣ በሕመም ወይም አካል ጉድለት ወይም ሌሎች ምክንያቶች ግዴታውን ለመወጣት የማያስችለው ሲሆን ወይም ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ከማህበሩ እንዲወጣ ሲወስን ነው፡፡ አንድ ሸሪክ ከማህበሩ ከመውጣቱ በፊት ለሶስተኛ ወገኖች የነበረበት ዕዳ ኃላፊነት ከማህበሩ በመውጣቱ ቀሪ አይሆንም ፡፡

አንድ ሽሪክ ድርሻውን በሌሎች ማህበርተኞች ተቀባይነት ላገኘ ሌላ ማህበርተኛ ወይም ሶስተኛ ወገን ሳያስተላልፍ የወጣ እንደሆነ ህጋዊ መብት ያለው ወራሽ ወይም ባለመብት ድርሻው ተሰልቶ እንዲሰጠው ከመጠየቅ ውጪ አባል ለመሆን የሚያቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡

በንግድ ሕግ ቁጥር 181 ንግድ ማህበራት ከሚፈርሱበት ሁኔታ በተጨማሪ የማህበሩ አባላት ቁጥር ወደ አንድ ዝቅ ያለ እንደሆነ እና በስድስት ወራት አሊያም ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ሁለት ከፍ ካላለ ማህበሩ ሊፈርስ ይገባል። 

Download this article with full citation