የመጽሐፍ ማየስ (Book Review) - Blog
Font size: +
6 minutes reading time (1107 words)

የመጽሐፍ ማየስ (Book Review)

በካሴ መልካም (የውርስ ሕግ፣ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች እና የሌሎች 6 መፅሐፍ ደረሲ)
 
የመፅሐፉ ርዕስ፡ የአእምሯዊ ንብረት ሕግ
የሕትመት ዘመን፡ 2018 ዓ.ም
የመፅሐፉ ደራሲ፡ ዳዊት በዛብህ
ዘውግ፡ የሙያ መፅሐፍ (የሕግ)
 
ይህ መፅሐፍ ከማውጫው እስከ ምንጮች በ281 ገፅ የተከተበ ነው፡፡ መፅሑፍ ለሕግ ባለሙያዎች ሆነ ለሌሎች ሰዎች በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ምክንያት ተፈላጊ ያደርገዋል፡፡


 
የመጀመሪያው የአንድ መፅሐፍ አስፈላጊነት አንዱ መለኪያ ዘመኑን የዋጀ መሆን ነው፡፡ የታሪክ መፅሐፍ ሲጻፍ እንኳን ከወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር አዛምዶ እና አዋዶ ከተጻፍ የአንባቢውን ቀልብ ይስባል፤ አዕምሮውንም ሰቅዞ ይይዛል፡፡
 
የዚህ መፅሐፉ በርዕሱ ላይ እንደተገለፀው የአእምሯዊ ንብረት ሕግን የሚመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም መፅሐፉ ከወቅቱ የዲጅታል ጊዜ በተለይ ከAI ጋር በማዛመድ በጥልቀት በዓለም ላይ የተነሱ ውዝግቦችን (ለምሳሌ DABUS) በማነሳት (በገፅ 239) የጉዳዩን አሰሳቢነት ይተርካል፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን በኢትዮጵያ በAI የተፈጠረ አዲስ ግኝት የአእምሯዊ ንብረት ነው ተብሎ ጥበቃ እንዲደረግለት የሕግ ማሻሻል የግድ አስፈላጊ ለመሆኑ ይነግረናል፡፡
 
ሁለተኛው የአንድ መፅሐፍ አስፈላጊነት ሌላኛው መስፈሪያ አካታችነት ነው፡፡ ዳዊት በዚህ መፅሐፉ የአዕምሯዊ ንብረት የሚባሉት የፈጠራ፣ የቅጅና ተዛማጅ፣ የንግድ ምልክትና ሚስጠርን ከአለም አቀፍ እስከ አገር ውስጥ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን ዳሷል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ማንሳትና መተንተን ብቻ ሳይሆን ከእውቀት ፍልስፋና፣ ከሥነ-ውበት፣ ከማህበራዊ ፍትህና ከሀገራት የኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር ያላቸውን ትስስር ተንትኗል፡፡
መፅሐፉ በዚህም ሳይገታ እነዚህ አእምሯዊ ንብረቶች ከማህበረሱ የባህል ጥበቃ እና በመልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ መሬቱ በሚይዘው ማዕድን ከሚገኝ የአእምሯዊ ንብረት መብት (የሲዳማ፣ የይርጋ ጨፌ እና የሀረር ቡናን በምሳሌነት በገፅ 206 ላይ እያነሳ) አዛምዶ ከትቧል፤ የዚህን የሕግ ዘረፍ የመፍሰሻ መንገዱን በማሳየት ይመራናል፡፡
 
ሶስተኛ መፅሐፉን ተነቦ አይረሴ የሚያደረግው በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ክስተቶችን በምሳሌነት በማካተቱ ነው፡፡ በመፅሐፉ የአውሮፓውን፣ የኤሲያውን፣ የአፍሪካውን… የአዕምሯዊ ንብረትን ጉዳይ ይዳስሳል፡፡ በሀገራት ውስጥ የተነሱ እና ፍርድ የተሰጠባቸው ከኮሪያ እስከ አሜሪካ፣ ከአፕል እስከ ጎግል፣ ከፔፕሲ እስከ ኮካ ኮላ ያሉ የአእምሯዊ ንብረቶችን ክርክሮችን በምሳሌት ያስቀመጣል፡፡
 
ዳዊት በዚህ መፅሐፉ ወደ እናት ሀገሩ የሕግ ማጀትም ገብቶ በሰፊው ያንጎዳጉዳል፡፡ የአእምሯዊ ንብረት መብቶችን የሚመለከቱትን አዋጆችና ደንብ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰበሩም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ጎራ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱም በወንጀል እና በፍትሐብሔር ጉዳዮች የተሰጡ አስተማሪ እና አይረሴ የሆኑ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞችንም (ለምሳሌ የDURA CELL እና DURA SUN “ን” ጉዳይን በገፅ 187-189 ላይ አንስቶ) የመፅሐፉ ጣራ እና ግድግዳን አዋህዶ እና አዋዶ ሰርቶባቸዋል፡፡
 
መፅሐፉ ለእነ ማን?
 
አንድ ደራሲ መፅሐፍ ሲከትብ ተስፈኛ አንባቢ (potential readers) ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ እኔ “የኢትዮጵያ መሰረታዊ የውርስ ሕግ” እና “በፍትሐብሔር የሥነ-ሥርዓት ሕግ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን” መፅሐፍ ሳዘጋጅ በዋናነት ለዳኞች፣ ለጠበቆች፣ ለዐቃቢያን-ሕጎች፣ ለነገረ-ፈጆች እና ለሌሎችም የሕግ ባለሙያዎች ነው፡፡ በሌላ በኩል “የችሎት ወግ” እና “እሳቷ ጠበቃ” የሚሉትን መፅሐፎቼን ስከትባቸው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍልን ታሳቢ በማደረግ ነው፡፡ (ከዚህ ላይ የራሴን መፅሐፍት በምሳሌነት ማንሳቴ የሌሎችን ፀሐፍት intention ማወቅ የማይቻል በመሆኑ ነው)፡፡
 
የዳዊት መፅሐፍ ርዕሱ “የአእምሯዊ ንብረት ሕግ” ስለሚል የሕግ ባለሙያዎችን ብቻ ታሳቢ የሚያደረግ ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም የአእምሯዊ ንብረቶች ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች፣ ለድርጅት ሰራተኞች፣ ለነጋዲዎች፣ የቴለቪዥን እና ራዲዮ ባለቤቶችና መሪዎች፣ ለንግድ ሥራ አስኪያጆች፣ ለimporters and exporters ወዘተ አስፈላጊም ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ፡፡ ምክንያቱም፡-
 
እነዚህ ሰዎች በአእምሯዊ ንብረት ሊኖራ የሚችለውን የመብት አድማስ፣ የንግድ ደርጅት ሲያቋቁሙ ሊሰጡት እና ሊጠቀሙት የሚችለውን የንግድ ምልከት፣ የንግድ ሚስጥራቸውን የሚጠብቁበትን ዘዴ፣ ከወጭ በሚያስገቧቸው ዕቃዎች ሊኖራቸው የሚችል የብቸኛ መብት፣ መብታቸው ተጥሶ የሞራል ሆነ የገንዘብ ኪሳራ እንዳይገጥማቸው ቅድመ-ጥንቃቄ ለማደረግ፤ ከተጣሰም መብትን በማስከበር እንደ ጎግል 245 ሚሊዮን ዶላር ካሳ (ገፅ 223-240) ለማስከፈል የሚችሉበትን መረጃችን ይሰጣል፡፡
 
የድርጅት ሰራተኞችም ቢሆን የኮካ-ኮላ ሰራተኛ እንደሆነችው ጆይያ 8 ዓመት ፅኑ እስራት ከመቀጣት ይታደጋቸዋል፡፡ ለድርጅት ሥራ አስኪያጆችም ቢሆን እንደ ፔፒሲ የንግድ ሚስጥር ሲደርሰው አልፈልግም፤ ስርቆት አልተባበርም በማለት ለሚመለከተው አካል ወንጀሉን በማመልከት ከስም መጥፋት እና ካሳ ከመክፈል ያድናቸዋል (ገፅ 224)፡፡
ዳዊት በሕግ ፍልስፈና ላይ ከዓለም አቀፍ እስከ ሀገረ-ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ምርምር አድርጓል (የእኔ ሳይሆን ከመፅሐፉ ጀርባ የተከተበ ነው)፡፡ መመራመር ብቻ ሳይሆን የሕግ ፍልስፍና እና ኢትዮጵያዊ ሥነ-ሕግ በሚሉት መፅሐፍት ላይ የማስረዳት ሸክም የሚል መፅሐፍ ሰልሶበታል፤ መፅሐፍቶቹንም ለህትምት አብቅቶ አስነብቦናል፡፡ ይህ የአእምሮ ንብረት ሕግ የሚለው መፅሐፈም ከሕግ ፍልስፍና እና ከሥነ-ሕግ ተሸካሚነት አላመለጠም (ለአብነት ያከል ከገፅ 32-40 እና ከገፅ 82-90 ይመልከቱ)፡፡
 
ሆኖም በዚህ መፅሐፍም የተካተቱት የሕግ ፍልስፍና እና ሥነ-ሕግ ከአእምሮ ንብረት ጋር የሚገናኙ እና የአእምሮ ንብረትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም “ውሃን ከጥሩ፣ ነገረን ከሥሩ” እንዲሉ በዚህ መፅሐፍም የተካተቱት የሕግ ፍልስፍና እና ሥነ-ሕግ ለመፅሐፉ ውብት ሁነውታል፤ የንባብ ጉዞን አያደናቅፉም፤ የንባብ ተመሰጦንም አያናጥቡም፡፡  ይልቁንም ኦ! እንዲዝህም አለ እንዴ? በማስባል ግርምትን ያጭራሉ፡፡ አለያም በዚም በኩል ለካ ማስብ አለብኝ አስብለው ከንባብ ገታ አስደረገው ወደ ፍልስፍና ጉባኤ ወሰድ ያደረጋሉ፡፡
 
ዳዊት ለረጀም ጊዜ በዳኝነት ሙያ ሀገሩንና ሕዝቡን ያገለገል፤ በማገልገል ላይ ያለ የፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ነው፡፡ ዳኛ ደግሞ ከፍልስፍና ይልቅ እጅ ከፍንጅ ለሚገጥሙ ክርክሮች ሕጋዊ መፍትሔ (Legal Remedy) የሚሰጥ ባለሙያ ነው፡፡ (ለዳኛ ፍልስፍና አይፈቀድም አላልኩም) ፡፡
ዳዊት በመፅሐፉ በሀገር ውስጥ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከሰጣቸው የሁለት እጅ ጣት ያክል የማይሞሉ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞችን ብቻ አካቷል፡፡ ሆኖም የአእምሮ ንብረትን በተመለከተ አከራክሮ ውሳኔ ከሚሰጠው የአስተዳደር አካል እና በይግባኝ ስልጣን ባለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም በፌዴራል የፌዴራሽን ምክር ቤት ከዚህ የአእምሮ ንብረትን የሚመለከቱ ክርክሮች የተሰጡ ውሳኔዎች በስፋት እና በጥልቀት ቢካተቱበት መፅሐፉን ይበልጥ ሙሉ ያደርገዋል፡፡
 
ይህ ክታብ የሕግ ሙያ መፅሐፍ ነው፡፡ በሕግ ሙያ ደግሞ ሙግት ሲነሳ በተለምዶ ‘WH questions’ ለሚሉት መልስ መስጠት አለበት፡፡ እነዚህም ክሱ መቼ መቅረብ አለበት (በዋናነት ይርጋ ይመለታል)፤ ክስ ማን በእነ ማን ላይ ያቀርባል (መብትና ጥቅምን የሚመለከት ጉዳይ ነው)፤ ክሱ እንዴት መቅረብ አለበት (የክስ አመጣጥና ዝርዝርን መለከታል)፤ የክሱ መሰረት ምንድን ነው (በዋናነት የክስ ምክንያትን ይመለከታል)፤ ክሱ የት ይቀርባል (ጉዳዩን አከራክሮ የመወስን ስልጣን ያለውን አካል የሚመለከት ነው) …የሚሉት የሚነሱ እና የሚያከራክሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡
 
አንድ መፅሐፍ ሲጻፍ በተለይ ደግሞ የአእምሮ ንብረት ሕግ እና መሰል ሕጎችን በተመለከተ ለአንባቢያን መልስ መስጠት ያለበት በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የአእምሯዊ ንብረትን በተመለከተ አከራክሮ የመወስን ስልጣን ያለው አካልን በሚመለከት ነው፡፡ ምክንያቱም በፅሐፉ ውስጥም ከዚያም ከዚህም በተበታተነ መልኩ እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የአእምሯዊ ንብረትን በተመለከተ አከራክሮ የመወስን ስልጣን የማን ነው? የሚለው እስከ ሰበር ደርሶ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ይህንን ነጥብ በተመለከተ ራሱን አስችሎ አንድ ምዕራፍ ተሰጥቶት በጥልቀት ቢዳሰስ የመፅሐፉን ሙሉዕነት ይበልጥ ይጨምረዋል፡፡
 
የመፅሐፉ ውስጥ ገፅ የምንጭ አጠቃቀስ በሕግ የተለመደው foot note አይደለም፡፡ በብዛት በማህበራዊ ሳይንስ ጥናት የተለመደው in text የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ይህም የመፅሐፉን ምንጮች በቀላሉ ለማየት እና ለማግኘት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ የፍርድ ቤት ክርክሮች በስም ብቻ ከሚጠቀሱ በስተቀር ሙሉ ምንጫቸው አልተጠቀሱም፡፡ ይህንን የምንጭ አጠቃቀስ በተመለከተ በተለመደው የሕግ ምንጭ አጠቃቀስ በመፅሐፉ ግርጌ በማደረግ ሙሉ ምንጩን ቢያስቀምጠው መፅሐፉን ይበልጥ ታማኝነቱን ያሳድገዋል፡፡
 
  
መውጫ
 
የዳዊት መፅሐፍ የመጣው በዚህ የአዕምሮ ንብረት በአንድ ስልክ በቀላሉ በደቂቃ ባህረ-ማዶ ድረስ ያለ ባለመብቱ ፍቃድ በወንበዴዎች (ራሱ ዳዊት በፅሐፉ እንደሚለው) በሚደራሰበት ዘመን ነው፡፡ ይህም የአእምሮ ንብረት ፊጣሪውን የገንዘብ ሆነ የሕሊና መብትን በአንደ ጊዜ አፈር-ደሜ የሚያበላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም ጨምር ሌሎችን የዘመኑ ትልልቅ የሆነ አገብጋቢ ጉዳዮችን በማንሳት ዘመኑን በአማዕከለ ሁኔታ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በቀላሉ ተነቦ እንዲረዳው በማደረግ የተዘጋጀ መፅሐፍ በመሆኑ ዳዊት መፅሐፉን እንኳን ጀባ አልከን ያስብለዋል፡፡
 
መፅሐፉ በኢትዮጵያ በአእምሮ ንብረትን በተመለከተ በችሎት ሆነ በሚመለከተው የአስተዳደር አካል ለሚነሱ ክርክሮችን በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው በቂ ስንቅ ያለው ነው ወይስ ደረቅ ቼክ? ለሚለው መልሱ ከተደራሲያን የሚገኝ ነው፡፡ በተለይ  በኢትዮጵያ በአእምሮ ንብረትን በተመለከተ ፍትሕ ሰጭ በሆነ ችሎት እና በሚመለከተው የአስተዳደር አካል የሚነሱ ክርክሮችን አከራክራቹህ ፍርድ የሰጣቹህ እና የምትሰጡ ባለሙያዎች የእናንተ ምላሽ አጥጋቢ በመሆኑ ወዲህ በሉት፡፡
 
ለእኔ መፅሐፉ በተለያዩ ሀገራት ያለውን የአእምሮ ንብረት ክርክር፤ ውዝግብ፣ ፍርድን እና ምሳሌዎች ጭምር የያዘ መፅሐፍ በመሆኑ ሊነበብ የሚገባ ነው፡፡ ለነገሩ እንኳን ይህ ዘመኑን የዋጀ መፅሐፉ ቀርቶ ሌላ መፅሐፍ ማንበብ ትርፍ እንጂ ኪሳራ ስሌለው ብታነቡት መልካም ነው፡፡

ቀሪ ጊዜያቹህ የተባረከ ይሁን!!!
ካሴ መልካም

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Can Courts Invoke an Arbitration Agreement on thei...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 20 July 2026