ከሰሞኑ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍቺን በተመለከተ ለየት ያለ ውሳኔ ተሰጥቷል፡: ይህን ውሳኔ ለሕዝብ ይፋ ቢደረግ ጠቃሚ ሃሳብ እንዲሸራሸር ሊረዳ የሚችል ከመሆኑም በላይ ሕጉንም ለመፈተሸ ይረዳል በሚል አስተያየት ለአንባብያን ለማድረስ እሞክራለሁ፡፡ ጉዳዩ ይፋ ቢሆንም ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል በመሆኑ ለጊዜው የግለሰቦችን ስም ተቀይሯል፡፡ የጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታውም ከዚህ በታች ባለው መልኩ ተቀምጧል፡፡

አቶ ሀ እና ወ/ሮ ለ 42 ዓመታት በትዳር ቆይተዋል፡፡ ትዳራቸውም የተደላደለ ነበር፡፡ በዚህ ትዳራቸው ጊዜ ውስጥ ልጅ ያልወለዱ ሲሆን አቶ ሀ ግን ከሌላ የወለዱት  አንድ ወንድ ልጅ አላቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቶ ሀ በእድሜ መግፋት (እድሜያቸው 90 ይሆናል) ምክንያት አእምሮአቸው ላይ ከፍተኛ ችግር የተከሰተ በመሆኑ የሚሰሩትን አያውቁም፡፡ የአእምሮ ችግሩን መሰረት በማድረግም የአቶ ሀ ልጅ ወላጅ አባቴ በአእምሮ ችግር የተነሳ የሚሰሩትን አያውቁም በማለት በፍርድ ይከልከሉ፤ የሞግዚትነት ስልጣንም ይሰጠኝ ሲል ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመለከቱ፡፡ ፍርድ ቤቱም የግለሰቡን የጤና ሁኔታ የሚያሳይ የሕክምና ማስረጃ እንዲቀርብ እና ግለሰቡም በችሎት ቀርበው ሁኔታቸው እንዲታይ በማድረግ ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ በራሳቸው ራሳቸውንና ንብረታቸውን ለመቆጣጠር የማይችሉ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡ ይህን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ አቶ ሀ ላይ የክልከላ (Judicial Interdiction) ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም የአቶ ሀ ልጅ አሳዳሪና ሞግዚት አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

የአቶ ሀ ልጅም ሞግዚትና አሳዳሪ የሚለውን ሹመት ካገኘ በኋላም ይህንን ሥልጣን መሰረት በማድረግ፣ ሞግዚት አድራጊዬ በእድሜ መግፋት ምክንያት በአእምሮአቸው ላይ የጤና መታወክ የተከሰተ ቢሆንም ተጠሪ ሊንከባከቧቸው አልቻሉም፤ ተለያይተው መኖር ከጀመሩም ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል፡፡ ስለዚህ የሞግዚት አድራጊዬና የተጠሪ ጋብቻ እንዲፈርስ ይወሰንልኝ በማለት ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመልክተዋል፡፡ ወ/ሮ ለ ሞግዚቱ የፍቺ ጥያቄ ይወሰንልኝ ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር አይችሉም፣ ለፍቺ የሚያበቃም ምክንያት የለም ሲሉ መቃወሚያና መልስ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤትም፣ ሞግዚቱ ጋብቻ እንዲፈርስ ለመጠየቅ ስልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም? የግራ ቀኙ ጋብቻ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚል ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምሮታል፡፡ አንደኛውን ጭብጥ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሲተነትን

“… በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 370(1) መሰረት ሞግዚት አድራጊ ጋብቻ እንዲፈርስ ለመጠየቅ የሚችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ የአቶ ሀ ሞግዚት የሆኑት ልጃቸው ጋብቻው እንዲፈርስ ለመጠየቅ በሕግ ሥልጣን አላቻው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በወ/ሮ ለ የቀረበውን ሞግዚት አድራጊው ጋብቻ እንዲፈርስ ለመጠየቅ አይችሉም የሚል ክርክርን አልተቀበለውም፡፡” 

ይላል፡፡

ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፣ ጋብቻው ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጭብጥ ፍርድ ቤቱ ሲመረምር፣

“….በጭብጡ ላይ ለመወሰን እንዲረዳውም አቶ ሀ በተደጋጋሚ ችሎት አስቀርቦ ተመልክቷል፡፡ እንደተመከታቸውም ፣ ግለሰቡ መናገርና ራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ነገሮችንም የማያስተውሉ እንዲሁም ነገሮች ያለበትን ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡ ከዚህም ፍርድ ቤቱ የአቶ ሀ እና ወ/ሮ ለ ትዳር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 መርሆች መሰረት በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ፣ በመደጋገፍና በመረዳዳት የተደገፈ አለመሆኑን ለመረዳት ችሏል፡፡  ስለሆነም ጋብቻው ጋብቻው በፍቺ ፈርሷል ሲል ወስኗል፡፡”

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከዚህ በላይ እንደቀረበው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡ ይኸውም የሞግዚትና አሳዳሪ ሥልጣን እስከምን ድረስ ይደርሳል የሚለውን እና ፍቺ ለመወሰን ታሳቢ የሚሆኑ ጉዳዮች የሚለውን ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ከላይ የተመለከተውን የፍርድ ቤት ውሳኔ ከሕገ መንግስቱ፣ ከፍትሐብሔር ሕግ እና ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በማገናዘብ ለመነሻ የሚሆን ጽሑፍ ለማቅረብና ለአስተያየት ማቅረብ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 34 (3)፣ ቤተሰብ የኅብረተሰብ የተፈጥሮ መሠረታዊ መነሻ ነው፡፡ ከኅብረተሰብና ከመንግስት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው ሲል ደንግጓል፡፡ ይህን ተከትሎም ጥበቃ የሚገለጽበት መንገድም የቤተሰብ ግንኙነትን በሕግ መደንገግና መግዛት በመሆኑ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ወጥቷል፡፡ ይህ ሕግም ጋብቻ ለሚለው ቀጥተኛ ትርጉም ያልሰጠ ቢሆንም አንድን ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት የሚገባቸውን አስፈላጊ ሁኔታዎች፣ ጋብቻው እንዴት እንደሚመራና የመምራት ኃላፊነቱ ምን ድረስ እንደሆነ፣ የንብረት ሁኔታ፣ ስለ ልጆች፣ ስለ አባትነትና እናትነት፣ ስለ ጉዲፈቻ፣ ስለ ቀለብ መስጠት፣ ስለ ፍቺ፣ የፍቺ ውጤት፣ ስለ ሞግዚትና አሳዳሪነትና መሰል ጉዳዮች በዝርዝር ደንግጎ አናገኛለን፡፡ በዚህ ሕግ ቀደም ሲል በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የነበሩ በተለይም በፍቺ ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ አድርጓል፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ አንድ ጋብቻን ለመመስረት አስፈላጊ ሲል ከዘረዘራቸው ውስጥ ፈቃድ (ነጻና ሙሉ ፈቃድ፤ በኃይል ወይም በስህተት ያልተገኘ)፣ ዕድሜ፣ ዝምድና (የስጋ እና የጋብቻ)፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመሰሉ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከሁሉ በላይ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕጉ ላይ ሰፊ ቦታ የተሰጠው ግን ፈቃድ ነው፡፡ በሕጉ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ፈቃድ የተሰጠው በኃይልም ሆነ በስህተት ከሆነ ጋብቻው ሊጸና እንደማይችል በግልጽ ያመለክታል፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ የቤተሰብ ሕጉ ጋብቻ ሊፈጸም የሚችለው ሁለቱ ተጋቢዎች በግንባር ተገኝተው ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ ነው በማለት በአስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም በከባድ ምክንያት ካለ እና በእንደራሴ አማካኝነት ጋብቻውን ለመፈጸም የሚፈልገው ተጋቢ ፈቃድ በማያሻማ ሁኔታ የገለጸ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ሲያረጋግጥ ጋብቻው በእንደራሴ ሊፈጸም የሚችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህም ሕጉ ለተጋቢዎች ፈቃድ የሰጠው ስፍራ ከፍተኛ መሆኑን ያመላክተናል፡፡

የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በፍርድ የተከለከለ ሰው ጋብቻ ስለሚፈጽምበት ስርዓት አስቀጧል፡፡ በዚህም መሰረት አንድ በፍርድ የተከለከለ ሰው ፍርድ ቤት ካልፈቀደለት በስተቀር ጋብቻ መፈጸም አይችልም፡፡ ጥያቄው ግን ራሱ የተከለከለው ሰው ወይም አሳዳሪው ሊያቀርበው ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ከፍርድ ቤት ፈቃድ ውጭ አንድ የተከለከለ ሰው ጋብቻውን የፈጸመ እንደሆን ጋብቻው እንዲፈርስ እራሱ ወይም አሳዳሪው ለመጠየቅ የሚችል መሆኑን ደንግጓል፡፡

ከዚህ በላይ በጨረፍታም ቢሆን ለማሳየት እንደተሞከረው የቤተሰብ ሕጉ ጋብቻ ከምስረታው አንስቶ እስከ ፍጻሜው ስላለው ሥነ ሥርዐት በዝርዝር ይደነግጋል፡፡ ከነዚህ ድንጋጌዎች መካከል ጋብቻው በተጋቢዎቹ ግላዊ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ውጤት አንዱ ነው፡፡ በባህልም ሆነ ሃይማኖት ተጋቢዎች ጋብቻውን ሲመሰርቱ ተደጋግፈው እንደሚኖሩ ችግርና ሕመም ቢፈጠር እንደማይከዳዱ ጭምር መሐላ ይፈጽማሉ፡፡ ይህም በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተጠብቆ የቆየ ነው፡፡ ሕጉም የዚሁ እውነታ ነጸብራቅ እንደመሆኑ መጠን የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግም ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ እንደሚኖርባቸው አመልክቷል፡፡ ቤተሰቡንም የማስተዳደር ኃላፊነታቸውም ቢሆን የጋራ ነው፡፡ ሆኖም ከባልና ሚስት አንደኛው ችሎታ ያጣ፣ የጠፋ፣ ወይም ቤተሰቡን ጥሎ የሔደ ወይም ከመኖሪያ ስፍራው በመራቅም ሆነ በማናቸውም ምክንያት ፈቃዱን ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ በሚገኝበት ጊዜ የቤተሰቡን አመራር አንደኛው ተጋቢ ብቻ ይፈጽማል ሲል ይደነግጋል፡፡ ችሎታ ከሚታጣበት ምክንያት አንደኛው ደግሞ በፍርድ መከልከል ሲሆን የአንደኛው ተጋቢ በፍርድ መከልከል ምክንያት ችሎታ ማጣት ውጤቱ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት በአንደኛው ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ነው፡፡

ጋብቻ የእድሜ ልክ ሆኖ ቢቆይ መልካም ነው፡፡ ይሁንና በተለያየ ምክንያት ጋብቻው መቀጠል የማይችልበት ሁኔታ ቢኖር ሊፈርስ ይችላል፡፡ ቤተሰብ በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት የሕብረተሰብ መሰረት እንደመሆኑ መጠን የፍቺው ስርዓትም ቢሆን ተጋቢዎቹ እንደፈለጉ እንዲያፈርሱት አልተፈቀደም፡፡ ፍርድ ቤቶች ጋብቻውን ከመፍረስ ሊታደጉ የሚችሉበት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል፣ ባልና ሚስቱን በተናጥልም ሆነ በአንድነት የመፍታት ሃሳባቸውን እንዲለውጡ የመጠየቅ፣ ጉዳያቸውን በመረጧቸው ሽማግሌዎች በእርቅ እንዲጨርሱ ማድረግ፣ የማሰላሰያ ጊዜ መስጠት ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ ይህም የቤተሰብ ጉዳይ የተለየ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ያመለክታል፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሰረት ጋብቻ እንዲፈርስ አና የፍቺ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ መቅረብ የሚገባው ከሁለት በአንዱ መንገድ ነው፤ በስምምነት እና አንደኛው ወይም ሁለቱ ተጋቢዎች በአንድነት ጋብቻው በፍቺ እንዲፈርስ ጥያቄ ሲያቀርቡ፡፡ ሁለቱም የፍቺ ስርዓቶች ዝርዝር ሁኔታ የተቀመጠላቸው ሲሆን ለፍቺ ያበቃቸው ምክንያት የመግለጽ ግዴታ ግን የለባቸውም፡፡ የፍቺ ውጤትም እንዲሁ በዝርዝር ተመላክቷል፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግን ምንም እንኳ የፍቺ ውጤት የሚገለጽ ባይሆንም ሊያስገኝ የሚችለው ውጤት እንዳለ ግን መገመት ይቻላል፡፡

የቀለብ መስጠትን ግዴታ በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ሁኔታ በባልና ሚስት መካከል ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለ ወይ የሚለው ነው፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198፣ በአንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ  የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚኖረው በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች ወይም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ነው በማለት ግዴታው በእነማን ላይ እንደሚጸና ያመለክታል፡፡ በዚህም አንቀጽ በመመራት አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 1 ስንመለከት ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ አለባቸው የሚል ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ሁሉ ቀለብ ለመጠየቅ አስፈላጊ የሆኑት ሁኔታዎች እስከተሟሉ ድረስ (ቀለብ ጠያቂው ሠርቶ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነ ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለውና በችግር ላይ የወደቀ መሆን) በባልና ሚስት መካከል ቀለብ የመስጠት ግዴታ መኖሩን መደምደም ይቻላል፡፡ የአንደኛው ጤና መታወክ ወይም በችግር ላይ መውደቅ ጋብቻውን አደጋ ላይ አይጥልም፤ ይልቁንም ሌላኛው ተጋቢ አንደኛውን እንዲንከባከብ ግዴታ ይጥላል እንጂ፡፡

ከዚህ በላይ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ጉዳዮች ተመልክተናል፡፡ የጉዳዩ መነሻ በፍርድ የተከለከለ ሰው የሥልጣን ልክን የሚመለከት እንደመሆኑ መጠን

የሚለውን በአጭሩ መመልከቱ በፍርድ ቤቱ ለተሰጠው ውሳኔ ላይ ውሃ የሚቋጥር ትችት ለማቅረብ ይረዳል፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 351 እና ተከታዮቹ በፍርድ ስለ መከልከል በዝርዝር ደንግገው እናገኛለን፡፡ በዚህም መሰረት፣ ለእብድ ሰው መከልከሉ ለጤናውና ለጥቅሙ ወይም ለወራሾቹ ጥቅም የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ ዳኞች ይህ ሰው እንዲከለከል ፍርድ ለመስጠት ይችላሉ፡፡ በሌላም በኩል ከእብድነት ውጭ በፍትብሔር ሕግ አንቀጽ 340 በተመለከቱት ምክንያቶች ራሳቸውን ለማስተዳደር ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች ወይም ንብረታቸውን ለማስተዳደር ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች ላይም እንዲሁ በፍርድ የመከልከል ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የመከልከሉን ጥያቄ ራሱ የሚከለከለው ሰው፣ ባለቤቱ/ቷ፣ በስጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ባላቸው ሰዎች ወይም በዐቃቤ ሕግ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄው እንደቀረበለት የሚከለከለው ሰው ቀርቦ በመመልከት ወይም ተወካይ ወይም ባለሙያ በመላክ ካጣራ በኋላ ሊወስን ይችላል፡፡ ለተከለከለ ሰው ሞግዚትና አሳዳሪ የሚሾመው ፍርድ ቤት ሲሆን የሚደረግለትም ጥበቃ (በፍርድ መከልከል በሚለው ክፍል ከተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ) አካለ መጠን ስላላደረሰው ልጅ ሰውነትና ንብረቶች አጠባበቅ በተሰጠው ደንብ ነው፡፡ በፍርድ የተከለከለ ሰው ሞግዚትና አሳዳሪ ሥልጣን ፍርድ ቤቶች ሊወስኑት ይችላሉ፡፡ አንድ የተከለከለ ሰው የሚፈጽማቸው ተግባሮች ውጤትም እንዲሁ ተመልክቷል፡፡ የተከለከለ ሰው ሞግዚትና አሳዳሪ የተከለከለውን ሰው ገቢ ለተከለከለው ሰው ጥቅም ብቻ ማዋል እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ዋናውና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ፣ በፍርድ የተከለከለው ሰው ከመከልከሉ በፊት የነበረውን ጋብቻ እንዴት ሊያፈርስ ይችላል የሚለው ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 370(1)፣

“ፍቺ ወይም ከሕግ ውጭ የሚደረገው የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የተከለከለው ሰው ፍቃድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳደሪው ፈቃድ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ “

 

በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ሕግ የእንግሊዘኛው ቅጂ ከዚህ በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል፣  

“The personal consent of the interdicted person as well as that of his guardian shall be required for requesting a divorce or putting an end to an irregular union.”

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በፍርድ የተከለከለ ሰው ጋብቻ መመስረት የሚችልበት ሁኔታ ሆነ ይህን ሁኔታ ባልተሟላ ጊዜ ጋብቻው እንዴት ሊፈርስ እንደሚገባም እንዲሁ ተደንግጓል፡፡ ተመሳሳይ ድንጋጌ በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ ተቀምጦ እናገኛለን፡፡ ሆኖም ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ሁኔታ አንደኛው ተጋቢ በፍርድ ሊከለከል የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር እና ጋብቻው እንዲፈርስ ለመጠየቅ ቢፈለግ መሟላት የሚገባው ሁኔታ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 370 (1) ላይ የተመለከተው መሟላት አለበት፡፡ ከዚህ በላይ ለማመልከት እንደተሞከረው ጋብቻ በስምምነት ወይም በአንደኛው አመልካችነት ጋብቻው እንዲፈርስ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በፍርድ የተከለከለው ሰው ጋብቻውን ለማፍረስ በስመምነት የፍቺ ጥያቄ ለማቅረብ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ቢነሳ ችሎታ ያጣ ሰው አስቀድሞውኑ ወደ ስምምነት ሊገባ አይገባም፤ ቢገባም ፈራሽ ነው የሚል መቃወሚያ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በተመሳሳይ በአንደኛው አመላካችነት ጋብቻው እንዲፈርስ ጥያቄ በቀረበ ጊዜም እንዲሁ ከፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌ ስንመለከት የተከለከለ ሰው ሞግዚት ወይም አሳዳሪ የፍቺ ጥያቄ ለማቅረብ አይችልም የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ ይቻላል፡፡ አብይ ምክንያቱም የፍትሐብሔር ሕጉ የፍቺ ጥያቄ የሚያቀርበው ማን እንደሆነ አይደነግግም፡፡ ይልቁንም የፍትሐብሔር ሕጉ የፍቺ ጥያቄ እንዲቀር የተከለከለው ሰው ፈቃድ አስፈላጊ እንደሆነ የሞግዚቱም ፈቃድ መገኘት አለበት የሚል ነው፡፡ ማን ያቀረበውን የፍቺ ጥያቄ ነው እንዲቀር ጥያቄ የሚቀርበው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያሻዋል፡፡ ለዚህ ምላሽ ለማግኘት አማራጭ የሚሆነው የእንግሊዘኛውን ቅጂ መመልከት ብቻ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው ቅጂ ጋብቻ ወይም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር እንዲቀር የተከለከለው ሰውም ሆነ የሞግዚቱ ይሁንታ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ ይህ ቅድመ ሁኔታ አስፈላጊነቱ የተቀመጠው በአስገዳጅ ሁኔታ ነው፡፡ የተከለከለው ሰው ይሁንታ መገኘት ያለበት የፍቺ ጥያቄው ገና ሲቀርብ ነው ወይስ የፍቺው ሂደት ከተጀመረ በኋላ ነው? በእብደቱ ምክንያት በፍርድ የተከለከለ ሰው ፈቃዱን እንዴት ሊሰጥ ይችላል? ፈቃዱን መስጠት ያልቻለ የተከለከለ ሰው ጋብቻውን ለማፍረስ አይችልም ማለት ነው? የአማርኛ ቅጂ ፍትሐብሔር ሕጉን ስንመለከት ደግሞ የፍቺ ጥያቄ እንዲቀር የተከለከለው ሰው ፈቃድ አስፈላጊ ከሆነ የሚለው አገላለጽ የተከለከለው ሰው ፈቃድ አስፈላጊ ላይሆን የሚችልበትን ሁኔታ ለምሳሌ የተከለከለው ሰው እብድ መሆንን ታሳቢ ያደረገ ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች የሚያስነሳና ሰፊ ምርምር የሚጠይቅ ነው፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ሞግዚት የተከለከለውን ሰው ገቢ ለተከለከለው ሰው ቀለብ የማዋል እና የኪራይ ውል መፈጸም የሚመለከት ግልጽ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ፍቺን በተመለከተ ግን ጋብቻ በሕግ የተለየ ጥበቃ የሚደረግለት እንደመሆኑ መጠን የፍትሐብሔር ሕጉ ፍቺው የሚደረገው ለተከለከለው ሰው ጥቅም ስለሆነ የተከለከለው ሰው ፈቃድ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሞግዚትና አሳዳሪው በተናጥል የፍቺ ማመልከቻ ለማቅረብ አይችልም፡፡ ጋብቻ  በመርህ ደረጃ በእንደራሴ ለመፈጸም እንደማይችል ሁሉ በተመሳሳይም ፍቺውንም በሞግዚቱ የተናጠል ጥያቄ ለማስተናገድ አይቻልም፡፡ ሕጉ ይህን በተለየ ሁኔታ የደነገገው ጋብቻ የራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው፤ ሰፊ ቦታም ለፈቃድ የተሰጠውም ለዚሁ ነው፡፡ የጋብቻን መፍረስ ሁኔታ በሞግዚቱና አሳዳሪው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይገባም ከሚል መነሻም ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉን መሰረት በማድረግ በፍርድ የተከለከለ ሰው ጋብቻ ሊፈርስ የሚችለው የተከለከለው ሰው እና ሞግዚቱ ፈቃዳቸውን የሰጡ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን በፍርድ የተከለከሉት ሰው ጋብቻው እንዲፈርስ ፈቃዳቸውን አልሰጡም፤ ፈቃዳቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ በሞግዚቱ የግል ጠያቂነት ብቻ ጋብቻው ሊፈርስ አይችልም፡፡  ስለሆነም በሞግዚቱ የግል አመልካችነት ብቻ ጋብቻው እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል ተብሎ የተወሰነው ውሳኔ ተገቢነት ያለው መስሎ አይታይም፤ የፍትሐብሔር ሕጉንም ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ነው፡፡

በሌላም በኩል የአንደኛው ተጋቢ የአእምሮ መታወክ በቤተሰብ ሕጉ ላይ የተቀመጠውን የመተጋገዝና መደጋገፍ ግዴታን ከሚያጠነክር በስተቀር ፍርድ ቤቱ በተሳሳተ መልኩ እንዳብራራው ለጋብቻው መኖር ምክንያት ቀሪ መሆንን አያመለክትም፤ የሕጉ መንፈስም ይህ አይደለም፡፡ ይልቁንም የፍርድ ቤት ውሳኔ የጋብቻን ዓላማ በተሳሳተ መልክ ከማስቀመጡም በላይ ጋብቻ የሚጸናው ሁለቱም ተጋቢዎች ጤናማ የሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሳል፡፡ ይህ ደግሞ የሕጉ ዓላማ ካለመሆኑም በላይ በሕብረተሰቡ ዘንድ የቆየውን ልማድ የሚንድ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው የፍቺ ውሳኔ ችሎታ በሌለው ሰው የቀረበ በመሆኑ ምክንያት ሊሻር ይገባዋል፡፡  

ከዚህ በላይ የቀረበው ለመነሻ እንደመሆኑ መጠን አንባቢያን በዚሁ ዙሪያ ያላችሁን አስተያየት እንድትሰጡ እንጠየቃለን፡፡