በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ትኩረት የሚሹ አወዛጋቢ ነጥቦችና መፍትሔዎቻቸው
ማስታዎሻ፡- ውደ አንባቢያን ይህ ጽሑፍ የተወሰደው በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች በሚል ከታተመው በ2017 ዓ.ም ተሻሻሎ በቀረበው መጽሐፌ ላይ ሲሆን የግርጌ ማስታዎሻዎቹ እና ማጣቀሻዎቹ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ለንባብ በሚመች አግባብ እንደገና ተቀናጅተው ተሰርተዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተካተቱት አብዛኛዎቹ ነጥቦች አወዛጋቢ ሆኖም በሕግ ባለሙያው ብዥታ እና ልዩነት የሚፈጥሩ ነጥቦች በመጽሐፉ የመጀመሪያ ዕትም ያልነበሩ አሁን ላይ በችሎት በሚገጥሙ ክርክሮች ሰበር ጭምር መፍትሔ የሰጣቸውን እና ሰበር መፍትሔ ያልሰጠባቸውን ደግሞ የመጽሐፉ አዘጋጅም የራሱን ምልከታ እና መፍትሔ የሚላቸውን ሃሳቦች ያሰቀመጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በዚህ በተሻሻለው ዕትም ከ400 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን የሚመለከቱ በ5 እና በ7 ዳኞች የተሰጠ የሰበር ችሎቱ አስገዳጅ የሕግ ትርጉ እና በርካታ የፌዴራሽን ምክር ቤቶች የተካተቱበት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያ ደረጃ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት በችሎት አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች እና ፍ/ቤቶቹ የሰጡት ፍርድን መነሻ በማድረግ መፍትሔ የሚሆኑ ነጥቦችን ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡
- በጽሑፍ ያልቀረበን የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን ከሳሹ በቃል ክርክር የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ
- በመቃወሚያ ላይ ማስረጃ የመስማት አስፈላጊነት
- በብዙ መቃወሚያዎች ላይ የውሳኔ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት
- በመቃወሚያዎች ላይ ከሳሽ በክሱ ያልዘረዘራቸውን ማስረጃዎች የማቅረብ መብት
- በተጣመሩ ተከሳሾች አንዱ በሌላኛው ላይ መቃዎሚያዎችን የሚያነሱበት አግባብ
- በመቃዎሚያዎች ላይ ይግባኝ የሚባልበት አግባብ
- በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የክስ መሻሻል ውጤት
- የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያና እሱን ለመወሰን መሰረት የሚሆነው ሕግ
- በፍርድ ቤት በራሱ እና በተከራከሪዎች ብቻ የሚነሱ መቃዎሚያዎችን
- በተከራካሪዎች ብቻ የሚነሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች
- ፍርድ ቤቱ በራሱ ሊያነሳቸው የሚችሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች
በጽሑፍ ያልቀረበን የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን ከሳሹ በቃል ክርክር የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ
በመርህ ደረጃ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.82 እና 241 ጣምራ ንባብ መረዳት የሚቻለው በክስ መስማት ቀን ግራ ቀኝ ተከራካሪዎች የሚያቀርቡት የቃል ክርክር በጽሑፍ በተነሳው ክርክር ላይ ግልጽ ያልሆነውን ለፍ/ቤት ማብራራት መሆኑን ነው፡፡ ይህ መርህ ሁል ጊዜም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ በሚደረገው የቃል ክርክር የሚሰራ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ከሳሽ በቀረቡበት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ክርክር የሚያቀርበው በቃሉ ብቻ በመሆኑ በተከሳሽ በቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥቦች መሰረት የመከራከር መብት ስላለው ነው፡፡ ይህንም በምሳሌ እንመልከተው፡፡
ምሳሌ፡- ከሳሽ ያቀረበው ክስ በውርስ ያገኘነውን ቤት ተከሳሹ ያካፍለኝ የሚል ነው፡፡ ተከሳሹ የከሳሽ መብት በይርጋ ታግዷል የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቧል፡፡ ከሳሽ ቤቱን ይዤ እየተጠቀምኩ በመሆኑ ወይም የሟችን የውርስ ሃብት በ3 ዓመት ውስጥ ያጣራሁ በመሆኑ በይርጋ ህግ መርህ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ መሰረት መብቴ በይርጋ አይታገድም በማለት ተከራክሯል፡፡
በዚህ ምሳሌ ላይ ከሳሹ የውርስ ሃብቱን ይዞ እየተጠቀመ ነው ወይስ አይደለም ወይም የውርስ ሃብቱ ሟች በሞተ በ3 ዓመት ውስጥ ተጣርቷል ወይስ አልተጣራም የሚሉት ነጥቦች በተከሳሽ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የጽሑፍ ክርክር ያልነበሩ ናቸው፡፡ ጉዳዮቹ ከሳሽ መብቱን በይርጋ ቀሪ አለመሆኑን ለማሳየት በቃል ክርክር ያቀረባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ናቸው፡፡ ከዚህ ምሳሌ መረዳት የሚቻለው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ የሚደረግ የቃል ክርክር ተከሳሹ ባነሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥቦች ወሰን ውስጥ መሆኑን፣ ፍ/ቤቱ የከሳሽን አዳዲስ የመከራከሪያ ነጥቦች ተቀብሎ የማከራከር ግዴታ ያለበት ለመሆኑን እና በቃል ክርክር ወቅት በጽሑፍ ክርክር ያልቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች በቃል ክርክር ሊቀርቡ አይቻሉም የሚለው መርህ ለመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የማይሰራ መሆኑን ነው፡፡
ከዚህ በላይ ከሳሽ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ በቃል ክርክር ጊዜ አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያነሳ ለመሆኑ አይተናል፡፡ አሁን ደግሞ ተከሳሽ በቃል ክርክር ጊዜ በጽሑፍ ያላነሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የማንሳት መብት ሊኖር የሚችልበትን የህግ መሰረት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-
ተከሳሽ በመርህ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የማንሳት መብት የተሰጠው በጽሑፍ መልስ ሲያቀርብ ለመሆኑ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 244 (1) እና 245 (3) መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ነገር ግን ተከሳሽ በጽሑፍ መልስ ላይ ሊያነሳቸው ይገባ የነበሩ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችን በመዘንጋትም ሆነ በእውቀት ማነስ ወይም በማስረጃ አለማግኘት ላያነሳ ይችላል፡፡ በዚህም በጽሑፍ መልስ ያላቀረባቸውን በክስ መሰማት ቀን በቃል ክርክር ጊዜ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን የለውም ወይም ጉዳዩ በውሳኔ ያለቀ ነው በማለት ለችሎቱ ቢያቀርብ ችሎቱ ሊቀበለው ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ነጥብ አከራካሪ ነጥብ ነው፡፡
ወደፊት በዝርዝር እንደምናየው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ለተከራካሪዎች ሊተው የሚቻሉ እና ሊተው የማይቻሉ ተብለው ይከፈላሉ፡፡ በተከሳሽ የሚተው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ተብሎ በምሳሌነት የሚጠቀሰው በዋናነት ይርጋ ነው፡፡ ይህን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ተከሳሽ በጽሑፍ መልሱ ዘርዝሮ ካላቀረበው ተከሳሹ በቃል ክርክር ጊዜ ቢያቀርበው ፍ/ቤቱ ይህን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የሚቀበልበት የህግ መሰረት ስለሌለው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.82፣ 241፣ 244 እና 245 እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1856 መሰረት ተከሳሹ ይርጋውን በመጀመሪያ በፅሁፍ መልሱ በመቃዎሚያነት ያላነሳው በመሆኑ ውድቅ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 25 በሰ/መ/ቁ.222297 ላይ ሰራተኛው በአሰሪው ላይ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 27(3) መሰረት የይርጋ መቃዎሚያ በክሱ ላይ ባይጠቅሰውም በቃል ክርክር ማንሳት የሚቻል ለመሆኑ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም በመርህ ደረጃ የይርጋ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን በተመለከተ መቃዎሚያን አንስቶ እንዲከራከር ሕጉ የፈቀደለት ሰው በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያነት የሚያገልግል መከራከሪያን በጽሑፍ መልሱ ካላቀረበ በቃል ክርክር አንስቶ የመከራክር መብት የሌለው በመሆኑ በጽሑፍ ያላነሳውን የይርጋ መቃዎሚያን በቃል አንስቶ መከራክር የማይችል በመሆኑ በቃል ክርክር በክስ መስማት ቀን ቢያነሳው ፍርድ ቤቱ አይቀበለውም፡፡ ሆኖም በልዩ ሁኔታ በተሻሻለው የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 27(3) መሰረት በማድረግ ሰራተኛው በአሰሪው ላይ የሚያነሳው የይርጋ መቃዎሚያ ግን ሰራተኛው በክሱ አንዱ የክርክር አካል አድርጎ ባያነሳውም በቃል ክርክር ካነሳው ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሹ በክስ መስማት ቀን ከሳሹ በቃል ክርክር በተሻሻለው የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 27(3) መሰረት ላነሳው የይርጋ መቃዎሚያ በበቂ ሁኔታ እንዲከራከር እድል ሊሰጠው እና ሊደመጥ ይገባል፡፡
ተከሳሽ በጽሑፍ መልስ ያላቀረባቸው ነገር ግን በቃል ክርክር ጊዜ ሊያቀርባቸው የሚችሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ትክክለኛ ፍትህ ከመስጠት የሚያግዱ እና በራሱ በፍ/ቤቱ መነሳት የነበረባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ፍ/ቤቱ የስረ ነገር ስልጣን የሌለው መሆኑ፣ ጉዳዩ በውሳኔ ያለቀ መሆኑ፣ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ለመክሰስም ሆነ ለመከሰስ ችሎታ የላቸውም የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን መቃዎሚያዎች ተከሳሹ በመጀመሪያ በፅሁፍ መልሱ ባያቀርባቸውም ፍ/ቤቱ ሊቀበል ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንደኛ እንደነዚህ አይነቶቹ መቃወሚያዎች መኖራቸውን ፍ/ቤቱ በራሱ ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ፣ የክርክር ሂደትና ደረጃ ከተረዳ በመቃዎሚያዎቹ ላይ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ በህግ ተጥሎበታል፡፡ ለምሳሌ ፍ/ቤቱ በማንኛውም ጊዜ የስረ ነገር ስልጣን የሌለው መሆኑን ከተረዳ በራሱ ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን የመዝጋት ግዴታ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ስልጣን ላለው ፍ/ቤት መዝገቡን እንዲላክ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 245(3) ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የማያሰናክሉ ካልሆነ በስተቀር በተቻለ መጠን በቶሎ ተጠቃለው ሁሉም መቅረብ አለባቸው በማለት ከተደነገገው ድንጋጌ የተቃርኖ ንባብ መረዳት የሚቻለው ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት መሰናከል የሚሆኑት የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚዎች ተከሳሹ በፅሁፍ ባያነሳቸውም በቃል ክርክር ማንሳት የሚችል ለመሆኑ ነው፡፡
ሲጠቃለል በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የክስ መስማት ቀን በቃል ክርክር ተከሳሹ በአነሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ወሰን ውስጥ በመሆን አዳዲስ ሀሳቦችን በማንሳት መከራከር የሚቻል ሲሆን ተከሳሹ ደግሞ በጽሑፍ መልሱ ላቀረባቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት ከሆነ በቃል ክርክር ጊዜ አንስቶ ቢከራክር ፍ/ቤቱ በራሱ ቀድሞውኑ መሰራት የነበረበትን በቸልተኛነት ወይም በዕውቀት ማነስ ወይም በመረጃ አለማግኘት ያልሰራውን ተከሳሹ እንዲሰራው እያስታወሰው በመሆኑ የተከሳሹን ክርክር የመቀበል ግዴታ አለበት ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው፡፡
በመቃወሚያ ላይ ማስረጃ የመስማት አስፈላጊነት
የቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የተካዱ ሆነው ማስረጃ ሳያስፈልግ ብይን የሚሰጥባቸው ከሆኑ ፍ/ቤቱ ማስረጃ ሳይሰማ ወይም ሌላ ማስረጃ መመልከት ወይም ማስቀረብ ሳያስፈለገው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ብይን ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ እልባት ለመስጠት ፍ/ቤት ማስረጃ መስማት እና መመርመር እንዲሁም ማስቀረብ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ማስረጃዎቹን አስቀርቦ ከሰማና ከመረመረ በኋላ ተገቢ ነው የሚለውን መስጠጥ ያለበት ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.244 እና 245 ድንጋጌዎች ጥምር ንባብ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ማስረጃ ማስቀረቡ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ማስረጃውን አስቀርቦ የመመርመር ስልጣን ያለው ለመሆኑ በቅፅ 18 በሰ/መ/ቁ.105869 ተከታዩን አስገዳጅ ይህ ትርጉም ሰጥቷል፡-
… ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ማስረጃ ተቀብሎ ከመመርመሩ ወይም ምስክሮችን ከመስማቱ አስቀድሞ በመጀመሪያ ደረጃ የመቃወሚያ ነጥቦች ላይ ውሳኔ መስጠት ያለበት ቢሆንም ለመቃወሚያ ክርክሩ አወሳሰን አግባብነት ያላቸው ምስክሮች ሳይሰሙ እና አግባብነት ያላቸው ሰነዶች ሳይቀርቡ በመቃወሚያ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የማይችል በሆነ ጊዜ ግን ፍርድ ቤቱ በመቃወሚያ ነጥቦች ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ተገቢ መስሎ የሚገመተው ማስረጃ እንዲከራከሩበት ትእዛዝ የሚሰጥ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.244/1/ እና 245/1/ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ የሰበር አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሆነ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 245 እና 244 መረዳት የሚቻለው ፍ/ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ማስረጃ መስማቱ የግድ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ምስክሮችን ሆነ የሰነድ ማስረጃ ወይም ሌሎች ለመቃወሚያ ክርክሩም ብይን ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን አስቀርቦ መስማቱ ተገቢ ለመሆኑ ነው፡፡
በብዙ መቃወሚያዎች ላይ የውሳኔ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት
በአንድ መዝገብ ላይ ብዙ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ፍ/ቤቱ ስልጣን የለውም፣ ጉዳዩ በይርጋ ይታገዳል፣ በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት ውሳኔ ተሠጥቶበታል፣ ከሳሽ ለመክሰስ መብትና ጥቅም የለውም ወ.ዘ.ተ. የሚሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንድ መዝገብ ላይ ብዙ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ሲቀርቡ አንዱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መዝገቡን የሚያዘጋው ከሆነ በሌሎቹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ እልባት መስጠት አስፈላጊ መሆን አለመሆኑ አከራካሪ ጉዳይ ሲሆን በተግባር በፍርድ ቤቶች ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ችሎቶች ምንም እንኳን አንዱ መቃዎሚያ መዝገቡን የሚዘጋው ቢሆኑም በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ እልባት ይሰጣሉ፡፡ ሌሎቹ ግን መዝገቡን አንዱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የሚዘጋው ከሆነ መዝገቡን በሚዘጋው መቃዎሚያ ላይ ብቻ እልባት ሰጥተው መዝገቡን ይዘጉታል፡፡ ስለሆነም ከችሎት አመራርና ከስነ-ስርዓት ህጉ አንጻር ትክክለኛው በሁሉም መቃዎሚያዎች ላይ ወይስ መዝገቡን በሚዘጋው መቃዎሚያ ላይ ብቻ ብይን መስጠት ለሚለው እንደቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የሚለያይ ነው፡፡
ለክርክር ከቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ውስጥ መዝገቡን የሚዘጋው ፍ/ቤቱ ስልጣን የለውም በሚል ከሆነ ፍ/ቤቱ በሌሎቹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ብይን መስጠት የሌለበት ለመሆኑ በሕንድ የፍትሐብሔር የስረነ-ሥርዓት ሕግ ላይ ጠብሰቅ ያለ መፅሐፍ የከተበው ፕሮፌሰር ጄይን (Professor M P Jain, The Code of Civil Procedure, (2007, Wadhwa and Company Nagpur Law puplisher, New Delhi)፣በገፅ 39) እንደሚከተለው ያብራሩታል፡-
A civil court having no jurisdiction over a subject matter of a suit, cannot decide any question on merits. It can simply decide questions of jurisdiction and order return of plaint for presentation to proper court if it comes to conclusion that it has no jurisdiction.
አንድ ፍ/ቤት ስልጣን የሌለው ከሆነ ስልጣን የለኝም ከማለት ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ውሳኔ መስጠት የለበትም፡፡ ምክንያቱም ፍ/ቤቱ ከጅምሩ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የሌለው በመሆኑ ነው፡፡
የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ ጉዳዩን በመጀመሪያ ሲመለከተው የነበረው ፍ/ቤት ላይ በተከሳሹ በቀረበው የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ምክንያት ከፍ/ቤት የስረ-ነገር ስልጣን በላይ ስለሆነ መዝገቡን የዘጋው በመሆኑ ሰበሩ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.17 (3) እና 19(2) በመነሳት አንድ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ የስረ-ነገር ስልጣን የሌለው መሆኑን በተከራካሪዎች አቤቱታ ሆነ በራሱ ከተገነዘበ ከስነ ስርዓት ሕጉ ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ ክርክሮች በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ እና በተፋጠነ ሁኔታ ተጠቃለው መፍትሔ እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፤ ይህም ትክክለኛ ፍትህ ላይ ለመድረስ አስፈላጊ ስለሆነ መዝገቡን የስረ-ነገር ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ሊያስተላልፉ ይገባል እንጅ መዝገቡን መዝጋቱ ተገቢነት የለውም በማለት በቅፅ 24 በሰ/መ/ቁ.173416 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.137043 በመሆነ መዝገብ ላይ በቀን 22/05/2010 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ክሱን የማቋረጥ ውጤት ያላቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ከቀረቡ አንዱ ብቻ ሳይሆን የቀረቡትን መቃዎሚያዎች ሁሉ አሟጦ ብይን መስጠቱ የባለጉዳዮች እና የፍርድ ቤቶች ጊዜ ጉልበት እና ወጭ የሚቆጥብ ተመራጭ ህጋዊ አካሄድ ነው፡፡ስለሆነም በአንደኛው መቃዎሚያ ላይ ብቻ ብይን ሰጥቶ በሌላው ላይ ምንም ሳይሉ ማለፍ ሥነ-ስርዓታዊ አይደለም በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ምክንያቱም የስር ፍ/ቤቱ መዝገቡን በሚዘጋው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብቻ እልባት ሰጥቶ በዚህም ላይ ይግባኝ ተብሎበት የሰጠው እልባት የሚሻር ከሆነ እንደገና በሌሎቹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች የሚያከራክር በመሆኑና እንደገና በሌሎች የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች በሰጠው እልባት ላይ ይግባኝ የሚጠይቁ ከሆነ አሁንም እንደገና ለመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ድጋሜ በይግባኝ የሚከራከሩ ይሆናል፡፡
ይህ ደግሞ ክርክር ወጭና ጉልበት ቆጣቢ መሆን አለበት የሚለውን የስነ-ስርዓት ዓላማ የሚጥስ ይሆናል፡፡ በመሆኑም እንደዚህ አይነቱን የክርክር አዙሪት ለመቀነስ/ለማስወገድ/ ፍ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ስልጣን ካለው በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ እልባት መስጠት ግዴታው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከዚህ ላይ መዝገቡን የሚዘጋው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ስልጣን የለውም የሚለ ከሆነ ፍ/ቤቱ ከጀምሩ ስልጣን ስሌለው በሌሎች መቃዎሚያዎች መመርመሩ ሕጋዊነት አለውን የሚለው አካራከሪ ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በመቃወሚያዎች ላይ ከሳሽ በክሱ ያልዘረዘራቸውን ማስረጃዎች የማቅረብ መብት
በመርህ ደረጃ ከሳሽ በክሱ ላይ ተከሳሽ በመልሱ ላይ ያላቸውን ማንኛውም የሰው፣ የሰነድ እና ሌሎች ማስረጃዎችን የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ከፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.223 እና 233 መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሰነድ ማስረጃዎችን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.137 መሰረት ከክስ መስማት በፊት ተከራካሪዎች የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ ተከራካሪዎች ከእጃቸው ላይ የማይገኙ የሰነድ ማስረጃዎችን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.223(1(ሀ)) እና 145 መሰረት በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲሁም የሰነድ የማስረጃዎችን መኖር ተከራካሪዎች ዘግይተው ከተረዱ እና ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ መቅረብ የማይችሉ ከሆነ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.256 መሰረት እንዲቀርቡላቸው ለፍ/ቤቱ አቤቱታ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡
የማስረጃ አቀራረብን አስመልክቶ በፍ/ቤቶች በተግባር አከራካሪ እየሆነ ያለው ነጥብ ተከራካሪዎቹ በክሱ እና በመልሳቸው ከዘረዘሯቸው ምስክሮች ውጭ ተጨማሪ ምስክሮችን እናቅርብ ወይም ጭብጡ ከተለየ በኋላ ምስክር እናቅርብ በማለት የሚያቀርቡት ነው፡፡ ይህን አከራከሪ ነጥብ በተመለከተ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎት በቅፅ 9 በሰ/መ/ቁ.45984 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ እንደሚከተለው አብራርቶታል፡-
በማስረጃ ዝርዝር ላይ የተቆጠሩ ምስክሮችን ማግኘት ባልተቻለ ጊዜ ምስክሮች የሚቀየሩበት የተለየ ሥነ-ሥርዓት በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ጊዜ በማስረጃ ዝርዝር ላይ የተጠቀሱ ምስክሮች በምንም ሁኔታ መለወጥ የማይቻል ስለመሆኑ የሥነ-ሥርዓት ህጉ ያስቀመጠው ገደብ የለም፡፡ በመሆኑም እንደየነገሩ ሁኔታ ፍ/ቤቶች ተለዋጭ ምስክሮች እንዲሰሙ ለመፍቀድ የሚከለክላቸው ህግ የለም፡፡ በተያዘው ጉዳይም ፍ/ቤቱ ተለዋጭ ምስክሮቹ በመከላከያ ማስረጃ ላይ ስላልተጠቀሱ አልሰማም ከማለት በቀር ምስክሮቹን እንዳይሰሙ የሚከለክል ህግ መኖሩን አልጠቀሰም፡፡ በእርግጥ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 223(2) እና 234 መሰረት የክሱ ማመልከቻና ከማመልከቻው ጋር ተያይዘው የቀረቡት የፅሁፍና ሌሎች ማስረጃዎች እንዱሁም የምስክሮች ዝርዝርና ማንኛውም ለፍ/ቤቱ የደረሱትን መግለጫዎች ትክክለኛ ግልባጮች ለተከሳሹ ሊደርሰው እንደሚገባ ሁሉ ተከሳሹም የሚያቀርበው መልስና የመከላከያ ማስረጃ፣ የምስክሮች ዝርዝር ለከሳሽ ሊደርሰው እና ሊከራከርበት ይገባል፡፡ ፍ/ቤቱም እንዲሰሙ በተጠየቁት አዲስ ምስክሮች ላይ ተጠሪው አስተያየት የመስጠት እድል ሊሰጠው ይገባል የሚል ከሆነ ይህንኑ እድል ከመስጠት ባለፈ አመልካች ማስረጃቸውን እንዲያሰሙ የሚከለክልበት ህጋዊ ምክንያት አልነበረም፡፡ ተጠሪም ቢሆን ምስክሮቹ ሲመሰክሩ መስቀለኛ ጥያቄ በመጠየቅ ዕውነቱ እንዲወጣ የማድረግ መብት ስላላቸው ምስክሮቹ እንዳይሰሙ የሚከለከልበት የህግ ምክንያት ይህ ችሎት አላገኘም፡፡
ከዚህ የሰበር ማብራሪያ መረዳት የሚቻለው ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ መጀመሪያ የዘረዘሯቸውን ምስክሮች ማግኘት አለመቻላቸውን በቃለ-መሃላ አረጋግጠው ሲያቀርቡ ለሌላኛው ተከራካሪ በቀረበው የምስክሮች ይቀየርልኝ አቤቱታ ላይ ክርክር ካለው አስተያየት እንዲሰጥ በማደረግ ፍ/ቤቱ በእርግጥም በክስ ወይም በመልሱ ላይ የተዘረዘሩት ምስክሮች ቦታ በመልቀቅና በመሞት አለመኖራቸው ወይም በጤና እክል ምክንያት መመስከር አለመቻላቸውን ከአረጋገጠ በአቤቱታው መሰረት ምስክሮች እንዲቀየሩ አድርጎ ለተቀየሩት ምስክሮች መጥሪያ እንዲጻፍ ትዕዛዝ በመስጠት ተለዋጭ ምስክሮችን ይሰማል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን በተመለከተ ከሳሹ ገና ለገና መቃዎሚያ ሊነሳብኝ ይችላል ብሎ በመገመት ወደፊት በተከሳሽ፣ በጣልቃ-ገብ፣ በ3ኛ ወገን እና በሌሎች ተከራካሪዎች ለሚቀርብበት መቃዎሚያ ማስረጃ ከክሱ ጋር ዘርዝሮ የማቅረብ እድል የሌለው ለመሆኑ ከመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች የክርክር መነሻ ተፈጥሯዊ ባህሪ ለመረዳት የሚቻል ነው፡፡ ከሳሹ ከጅምሩ በተከሳሽ፣በጣልቃ-ገብ፣በ3ኛ ወገን እና በሌሎች ተከራካሪዎች የሚቀርቡት መቃዎሚያዎች ሊያውቅ ይገባል የምንልበት የህግም ሆነ የአመክንዮ መሰረት የለም እንጅ አለ እንኳን ብለን ብንነሳ ወደፊት በዝርዝር እንደምናየው ከ10 በላይ ከሚሆኑት መቃዎሚያዎች ውስጥ የትኞቹ እንደሚነሱ ለመገመት የማይችል በመሆኑ ከሳሹ ገና መቃዎሚያዎች ይነሳሉ ብሎ ለመቃዎሚያዎች የሚያስረዱለትን ምስክሮች ዘርዝሮ ማቅረብ አለበት ማለት ከሰው ልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የወጣ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡
ከሳሹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን በተመለከተ ከክሱ ጋር ማስረጃ የሚያቀርብበት በህጉ የተፈቀደለት እድል ከሌለው እና የቀረቡበትን መቃዎሚያዎች ለመከላከል የግድ ከመልሱ ጋር ከዘረዘራቸው ውጭ ያሉ ማስረጃዎች ማቅረብ ካለበት ከሳሹ በምን አግባብ ማስረጃዎቹን ሊያቀርብ ይችላል? የሚለውን በተመለከተ አከራካሪ እና ምላሽ የሚፈልግ ነጥብ ነው፡፡ የሰነድ ማስረጃዎችን በተመለከተ ከሳሹ የተከሳሹ መልስ እንደደረሰው በክስ መስማት ቀንም ሆነ ከክስ መስማት ቀን በፊት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.137 መሰረት ዘርዝሮ ያለፍ/ቤት ፍቃድ የማቅረብ መብት አለው፡፡
ከሰነድ ማስረጃዎች ውጭ ያሉ ሌሎች ማስረጃዎችን በተመለከተ ግን ህጉ ግልጽ ምላሽ የሌለው በመሆኑ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 245(1) ላይ ፍ/ቤቱ ክስ ከሰማ በኋላ በመቃዎሚያዎች ላይ ተገቢ ሆኖ ካገኘው ማስረጃዎችን አስቀርቦ ይሰማል በማለት የደነገገ በመሆኑ ከዚህ ድንጋጌ በመነሳት ከሳሽ የቀረቡበትን መቃዎሚያዎች መከላከል የሚቻለው ምስክር በማቅረብ ብቻ ለመሆኑ ለችሎቱ ገልጾ ከተከራከረ ፍ/ቤቱ ከሳሽ በክሱ ላይ ያልዘረዘራቸውን ምስክሮች ከማሰማት የሚከለክልበት የህግ መሰረት የለም፡፡ ይህን ሃሳብ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ የሚከተለውን የቢሆን ክርክር (hypothetical case) እንመልከተው፡፡
ከሳሽ በወንድሙ ላይ አባታችን በህይወት በነበረበት ጊዜ ያለው አንድ ቤት ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን አባታችን አርፏል፡፡ የአባታችን ወራሾች እኔና ተከሳሹ ብቻ ነን፡፡ ስለዚህ የውርስ ሃብት የሆነውን የአባታችንን ቤት ተከሳሽ ለከሳሽ በድርሻዬ ያካፍለኝ በማለት ክስ መስርቷል፡፡ ክሱ የቀረበ ያለውርስ ማጣራት በቀጥታ የድርሻ ክፍፍል ክስ በማቅረብ ነው፡፡
ተከሳሽ ባቀረበው የጽሑፍ መልስ ከሳሹ ወንድሜ መሆኑን አልክድም፤ ነገር ግን ከሳሽ ክሱን ያቀረበው አባታችን ከሞተ ከ3 ዓመት በኋላ በ6ኛው ዓመት ነው፡፡ ውርሱም አልተጣራም፤ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከሳሽ አላወጣም፡፡ ስለዚህ ሰበሩ በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት በወራሾች መካከል የሚቀርብ ክስ በ3 ዓመት ይርጋ የሚታገድ በመሆኑ የከሳሹ መብት በይርጋ የታገደ በመሆኑ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት መቃዎሚያ አቀረበ፡፡
ፍ/ቤቱ ክስ ሲሰማ ከሳሽ አባታችን ከሞተ 6ኛ ዓመቱን የያዘ ቢሆንም እኔ ቤቱን በመያዝ እኖርኩበት በመሆኑ ሰበሩ የውርስ ሃብትን ይዞ የሚጠቀም ሰው በይርጋ አይታገድም በማለት በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት መብቴ በይርጋ ቀሪ ሊሆን አይችልም በማለት ተከራክሯል፡፡ ተከሳሹ በበኩሉ ከሳሹ ይህንን ቤት አባታችን ከሞተ ጀምሮ ይዞት አያውቅም በማለት ክዶ በቃል ክርክር አቅርቧል፡፡
በዚህ ክርክር ከሳሽ ቤቱን በመያዝ ለመጠቀሜ በክሴ ላይ ይህ መቃዎሚያ እንደሚነሳ ባለመገመቴ ለዚህ መቃዎሚያ ማስረጃ የሚሆኑትን የሰው ምስክሮች ዘርዝሬ አላቀረብኩም፡፡ አሁን ግን የምስክር ዝርዝር በጹሁፍ አቀርቢያለሁ፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤቱ የምስክር ዝርዝሬን ተቀብሎ ለምስክሮቼ መጥያ ይጻፍልኝ በማለት ከጠየቀ ፍ/ቤቱ የከሳሹን አቤቱታ ተቀብሎ ከሳሽ በክሱ ላይ ላልዘረዘራቸው ምስክሮች መጠሪያ ሊፅፍለት ይገባል፡፡
ከዚህ ላይ ከሳሹ በክሱ ላይ ያልዘረዘራቸውን ምስክሮች ፍ/ቤቱ ሊሰማ ይገባል ለማለት የሚያስችሉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.245 (1) ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ፍ/ቤቱ በመቃዎሚያው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ምስክር መስማት ተገቢ ሆኖ ካገኘው ምስክር ይሰማል ይላል፡፡ በዚህም ከላይ በተገለፀው የቢሆን ክርክር ላይ ከሳሹ ቤቱን ይዞ ይጠቀም ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ነጥብ አጣርቶ በቀረበው የይርጋ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የከሳሽን ምስክሮች መስማት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሹ ክሱን ሲያቀርብ መቃዎሚያ ገና ወደፊት ሊቀርብ ይችላል በማለት ገምቶ ቤቱን ይዞ ለመጠቀሙ የሚያውቁ ምስክሮቹን ዘርዝሮ የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቱ ይህን የከሳሽ ችግር በመረዳት እና የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.245 (1) ን ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት በሚያስችል አግባብ በመተርጎም ከሳሽ ምስክሮችን እንዲያሰማ ሊፈቅድለት ይገባል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.264(2) መሰረት ፍ/ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በግራ-ቀኙ የማስረጃ ዝርዝር ያልነበሩ ምስክሮችን አስቀርቦ ሊሰማ ይችላል በማለት ደንግጓል፡፡ ፍ/ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ ሲባል በማስረጃ ዝርዝር ላይ ያልነበሩ ምስክሮችን ሊሰማ የሚችልባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በመቃዎሚያዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት የግድ ምስክር መስማት አስፈላጊ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ይሁንና ከሳሹ በክሱ ላይ ምስክር ላይዘረዝር ይችላል፤ የዘረዘረ ቢሆንም በክሱ ላይ የተዘረዘሩት ምስክሮች በተከሳሽ የቀረቡትን መቃዎሚያዎች በተመለከተ የማያስረዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከሳሽ በማስረጃ ከተዘረዘሩት ምስክሮች ውጭ ከሳሹ የቀረበበትን መቃዎሚያ ለማስተባበል የሚችሉ ምስክሮች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ በዚህም ከሳሽ ምስክር እንዳለው ከተከራከረ ወይም አቤቱታ ካቀረበ ወይም ፍ/ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ ምስክር ያለው ለመሆኑ ከጠየቀው እና አለኝ ካለ ምስክሮቹ በ264 መሰረት መሰማት አለባቸው፡፡
በክሱ ላይ ከሳሽ ያልዘረዘራቸውን ማስረጃዎች ተከሳሽ መቃዎሚያ ሲያቀርብበት በአዲስ ዘርዝሮ የማቅረብ መብት ያለው ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.224265 በመሆነ መዝገብ በቀን 30/03/2015 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ከሳሹ ለመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች በክሱ ላይ ያልዘረዘራቸውን ማስረጃዎች የማቀረብ መብት ያለው ለመሆኑ ወስኗል፡፡ በመሆኑም ይህ 2ኛው አቋም የሕግ መሰረት ያለው በመሆኑ በተግባር በፍርድ ቤት በዚህ አግባብ የሚሰራበት ለመሆኑ ልብ ሊባይ ይገባል፡፡
በተጣመሩ ተከሳሾች አንዱ በሌላኛው ላይ መቃዎሚያዎችን የሚያነሱበት አግባብ
የፍትሐብሔር ሥነ-ሥረዓት ሕጉ በተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ እንዳስቀመጠው ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን በአንድ ላይ አጣምሮ ከሳሹ ብበዙ ተከሳሾች ክስ ሊያቀረብባቸው ይችላል፡፡ በተግባርም እጅግ ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ተከሳሾች ሁነው ተጣምረው በፍርድ ቤት ክስ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ተጣምረው የተከሰሱ ሰዎች ከሳሽ ባቀረበው ክስ ላይ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ ክርክር ማቅረብ የሚፈልግት ክስተት ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ በውርስ ጉዳይ ላይ የአንዱ ተከሳሽ መብት በይርጋ የታገደ በመሆኑ ይህንን የይርጋ ጉዳይ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ በማንሳት መከራከር ሊፈልግ ይችላል. በተግባርም የዚህ መፅሐፍ አዘጋጅ በአንድ የውርስ መዝገብ ላይ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ የይርጋ መቃዎሚያ ተነስቶ ተመልከቷል፡፡
አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ የቃል ሆነ የጽሑፍ ክርክር ማቅርብ የሚችሉ ወይም የማይችሉ ለመሆኑ በግልፅ የተቀመጠ ድንጋጌ የለም፡፡ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ሊያቀርብ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን በተመለከት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 244 (2) በግልጽ “ማናቸውም ተከራካሪ ወገን … መቃወሚያዎችን ያቀርባል” የሚል በመሆኑ ማቅርብ ይችላል ለማለት ይህ ድንጋጌ እንደ አንድ መከራከሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ7 ዳኞች በቅፅ 12 በሰ/መ/ቁ.49295 በሆነ መዝገብ ላይ መጋቢት 22 ቀን 2003 ዓ.ም በተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ ክርክር የማቅረብ መብት ያለው ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-
በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ክርክር ላይ በክርክር አመራር እና እውነትን በማውጣት ረገድ የፍርድ ቤት ሚና ሲታይ እጅጉን ከፍተኛ መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቀጥር 39፣ 40፣ 91፣ 136፣ 241፣ 246፣ 247 ፣ 248፣ 256፣ 265፣ 266፣ 272 እና ሌሎች በርካታ በዋቢነት የሚጠቀሱ ድንጋጌዎች ያለ በመሆኑ አንድ ተከሣሽ በሚያቀርበው ክርክር ላይ ሌላው ተከሣሽ መልስ /ክርክር/ እንዲያቀርብበት ማድረግ ሥርዓቱ የሚደግፈው አይድለምም ሊባል የሚችል አይሆንም፡፡ ዋናውና ቁልፍ ነገር የተከራከሪ ወገኖች የመከራከር መብት መጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ከሳሽ ተከሳሾችን አጣምሮ ክስ ባቀረበበት መዝገብ ላይ ተጣምረው የተከሰሱት ተከሳሾች አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ ክርክር ማቅረብ ይችላል፡፡
በዚህ የሰበር ችሎት ላይ በቀጥታ የቀረበው ጉዳይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን የሚመለከት ባይሆንም ሰበሩ ለዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መነሻ ካደረጋቸው የፍትሐብሔር የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች አንጻር አንድ ተከሣሽ በሚያቀርበው ክርክር ላይ ሌላው ተከሣሽ መልስ /ክርክር/ እንዲያቀርብበት ማድረግ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ የማይከለክል በመሆኑ የተከራከሪዎችን መብት ለማስከበር ሲባል ሊፈቀድ ይገባል የሚል ነው፡፡
በሌላ በችሎት የዚህ መፅሐፍ አዘጋጅ በተግባር በችሎት የገጠመውን በውርስ ጉዳይ ላይ የአንዱ ተከሳሽ መብት በይርጋ የታገደ በመሆኑ ይህንን የይርጋ ጉዳይ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ ማንሳትና መከራከር እንዲችል መፍቀድ ክርክሮችን በአንድ መዝገብ በተመሳሳይ ሰዓት እንዲቋጩ የሚያደርግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰበሩ በ7 ዳኞች “ዋናውና ቁልፍ ነገር የተከራከሪ ወገኖች የመከራከር መብት መጠበቅ ነው” በሚል የሰጠው ትርጉም የሚያሳየው አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃሚያዎችን ማቅረብ የሚችል ለመሆኑ ተቋሚ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከሙግት አመራር አንጻር ቀጠሮ ተሰጠው ተከሳሽ ከሳሽ ላቀረበው ክስ ለከሳሹ መልስ ለማቅረብ የተቀጠረ በመሆኑ መልስ ማቅረብ ያለበት ለከሳሽ ክስ እንጅ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ በድንጋት መቃዎሚያ ሊያቀርብ አይገባም በሚል መከራከር የሚቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ዓላማ ክርክሮችን ውጭ እና ጉልበት ቆጣቢ በሆነ አግባብ የተፋጠነ ፍትሕ መስጠት ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ የሚያነሳውን መቃዎሚያ አብሮ አከራክሮ ውሳኔ መስጠት ይህንን የሕጉን ዓላማ የሚያሳካ ከመሆኑም የመዛግብት መራባት(depulication of files) ለማስቀረት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ አንዱ ተከሳሽ በሌላኛው ተከሳሽ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ክርክር የማቅረብ መብት አለው መባሉ ሚዛን የሚደፋ ይሆናል፡፡
በመቃዎሚያዎች ላይ ይግባኝ የሚባልበት አግባብ
በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 320 (3) መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች በተሰጠ ብይን ላይ ይግባኝ ለማለት በስረ-ነገር ጉዳዩ ላይ ውሳኔ የተሰጠ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎት ይህንን ድንጋጌ በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ጋር በተያያዘ በሚሰጥ ብይን ላይ ፍ/ቤቱ በሥረ-ነገር ረገድ የመጨረሻ ውሣኔ ሣይሰጥ የይግባኝ ሆነ የሰበር አቤቱታ ለማቅረብ አይቻልም በማለት አስገዳጅ ውሳኔ በቅፅ 6 በሰ/መ/ቁ.19142 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ሰበር ይህንን ጉዳይ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.320 (1) (3) እና (4) ስር ከተመለከቱት በመነሳት በቅፅ 26 በሰ/መ/ቁ.200117 ላይ እንደሚከተለው እንደሚከተለው ያብራራዋል፡-
በመሠረቱ በህጉ በሌላ ሁኔታ እንዲፈፀም የሚያዝ ድንጋጌ ከሌለ በቀር ከሳሽ ወይም ተከሳሽ በተወሰነበት የመጨረሻ ፍርድ ላይ ይግባኝ ማለት የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ክርክሩን በሚሰማበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ ጊዜያዊ አገልግልት ያለው ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ በመጀመሪያ ደረጃ በሚቀርብ መቃወሚያ ላይ ተገቢ መስሎ የታየውን ብይን ሲሰጥና ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት በሚሰጠው በማናቸውም ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ለማለት ወይም የሰበር አቤቱታ ማቅረብ አይቻሉም፡፡
ይህም ማለት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች የሚሰጠው ብይን መዝገቡን የማያዘጋው የሆነ እንደሆነ ብቻ ለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
በሌላ በኩል የስር ፍ/ቤት ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን ዘግቶት በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ በፍሬ ጉዳዩ ላይ እንዲከራክር መዝገቡ ከተመለሰለት በሌላ መቃዎሚያ መሰረት መዝገቡን የፍሬ ነገሩ ላይ ሳያከራክር መዝጋት አይችልም በማለት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎቱ አንድን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በማንሣት ስልጣን የለኝም ያለ ፍ/ቤት ጉዳዩ በበላይ ፍ/ቤት ታይቶ በፍሬ ጉዳዩ ላይ እንዲያከራክር ጉዳዩ የተመለሰለት እንደሆነ ሌላ ተጨማሪ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያን መሠረት በማድረግ ጉዳዩን ለማየት አልችልም ማለት አይገባም በማለት በቅፅ 8 በሰ/መ/ቁ.39014 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ወስኗል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የክስ መሻሻል ውጤት
አንዳንድ ጊዜ በፍርድ ቤት በተግባር ክስ ተሰምቶ በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በራሳቸው በተከራካሪዎች ጥያቄ ወይም ደግሞ በፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነት በሚሰጥ ትዕዛዝ ክሱ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ተከሳሹ ሁለት ዓይነት የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን ሊያነሳ ይችላል፡፡ አንደኛው ክሱ ሳይሻሻላ ባቀረበው መልስ ላይ አንስቷቸው የነበሩ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን በድጋሜ ማቅረብ ሲሆን 2ኛው ክሱ ሳይሻሻል (በድሮው ክስ) ያልተነሱ አዳዲስ መቃዎሚያዎችን ማንሳት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በከሳሹ በኩል የሚነሳው መከራከሪያ ክሱ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ተሰጥቶ የነበረ በመሆኑ በድጋሜ የድሮውን ሆነ አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ሊነሳ አይገባም፤ ተከሳሹ መቃዎሚያ ካቀረበም አዳዲስ መቃዎሚያዎችን ማንሳት የማይችል በመሆኑ ክሱ ከመሻሻሉ በፊት ፍርድ ቤቱ መቃዎሚያ ላይ ውድቅ በማድረግ የሰጠው ውሳኔ የፀና ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡
በነገራችን ላይ አልፎ አልፎም ቢሆን ይህ ነጥብ በፍርድ ቤቶች በተግባር ክርክር ሲቀርብበት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ይህንን ነጥብ በተመለከተ በአንድ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በከሳሽ ስኬት ባንከ አ.ማ እና በተከሳሾች እነ ሐጋዚ ሀዱሽ (በቁጥር 3 ሰዎች) በመዝገብ ቁጥር 07993 በነበረ ክርክር ችሎቱ በቀን 18/04/2017 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ በተነሳ መቃዎሚያ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል፡-
ፍርድ ቤቱ… ክሱ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ክሱ ሲሻሻል የፀና ሊሆን ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን መርምሯል፡፡ እንደመረመረውም አንድ ክስ ተሻሻለ ማለት የመጀመሪያው ክስ ሙሉ በሙሉ ቀሪ ሁኖ እንደ አዲስ ሌላ ክስ የሚቀርብበት ሁነት ለመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.91 ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሽም ለተሻሻለው ክስ ከፈለገ የመጀመሪያውን መልሱን በድጋሜ የማቅረብ መብት ያለው ሲሆን ከፈለገ ደግሞ አዲስ መልስ የማቀርብ መብት ያለው ለመሆኑ ከዳበረው የሕግ ሥርዓት እና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.91 እና ከዚህ ድንጋጌ ተቃርኖ ንባብ ለመረዳት ይቻለል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ክስ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች ክሱ ሲሻሻል እንደፀኑ ናቸው ማለት ተከሳሹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን በተመለከተ ክስ ሳይሻሻል ካቀረበው መልስ የተለያ መከራከሪያ ማቅረብ አትችልም በማለት የመከልክል ውጤት ያለው ይሆናል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከላይ በተጠቀሰው መዝገብ ላይ ማለትም በመዝገብ ቁጥር 07993 በነበረ ክርክር ችሎቱ በቀን 18/04/2017 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ከኢፌዴሪ ሕግ-መንግስት ጋር በማያያዝ በመጨረሻም ከሚከተለው መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፡-
አንድ ተከሳሽ የሚያቀርበው መልስ… የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚዎች እና የፍሬ ነገር መልስን አጠቃሎ የሚይዝ ለመሆኑ 234 (1) (ሐ) እና 244 ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ ለተሻሻለው ክስ የተሻሻለ መልስ እንዲያቀርብ ማደርግ የተከሳሹን የመከላከል እና በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 37 ላይ የተቀመጠው ፍትህ የማግኘት መብቱን የማስጠበቅ የፍርድ ቤቶች በኢፌዴሪ ሕ-መንግስት አንቀፅ 13(2) ላይ የተጣለባቸው ግዴታ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህንን የተከሳሽን ሕገ-መንግስታዊ መብት ማስከበር የሚችሉት ደግሞ ክስ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዳልተሰጠ በመቁጠር ተከሳሹ የፍሬ ጉዳይ እና የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ መልሱን ለተሻሻለው ክስ እንዲያቀርብ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የከሳሽ ነገረ-ፈጅ በዚህ ረገድ ያቀረቡት መከራከሪያ ማለትም ክስ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ክስ ተሻሻሎ ሲቀርብ እና ተከሳሹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ሲያቀርብ ክስ ከመሻሻሉ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ የተሰጠው ውሳኔ የሚፀናበት የሕግ ሆነ የአመክኒዮ መሰረት የሌለለው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ ብፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.245 መሰረት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
እንደዚህ መፅሐፍ አዘጋጅ ከሆነ ክሱ ሲሻሻል በተዘዋዋሪ ከክሱ መሻሻል በፊት የተሰጡ ትዕዛዛት፣ ብይን እና ውሳኔዎች በአብዛኛው ቀሪ እንደሚሆኑ ግምት ይወሰዳል፡፡ ከዚህ ላይ የመጽሐፉ አዘጋጅ በአብዛኛው ያለው ተከሳሾቹ ሁለት እና ከዚያ በላይ ከሆኑ እና የተወሰኑ ተከሳሾች ቀርበው የተወሰኑት ካልቀረቡ እና በጋዜጣ ጭምር ጥሪ ተደርጎ በሌሉበት እንዲታይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ክሱ ቢሻሻል በሌሉበት ክርክሩ እንዲቀጥሉ ለተባሉት ተከሳሾች በድጋሜ ለተሻሻለው ክስ ጥሪ ሊደረግ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ስለሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የተሻሻለው ክስ ሌላ እና አዲስ ክስ በመሆኑ በድጋሜ ጥሪ ሊደረግ ይገባል በማለት መከራከር የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ክሱ ቢሻሻልም ክሱ የሚሻሻለው በነባሩ መዝገብ ላይ በመሆኑ አዲስ ክስ እና መዝገብ ባለመሆኑ በድጋሜ ጥሪ ሊደረግ አይገባም በማለት መከራከር የሚቻል በመሆኑ ነው፡፡
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ ለተሻሻለው ክስ ተከሳሹ በድሮ ክሱ ሳይሻሻል ያቀረበውን መቃዎሚያ ሆነ ለተሻሻለው ክስ የሚመጥን ሌላ አዲስ መቃዎሚያዎችን የረሳቸውን ጨምሮ እንዲያቀርብ መፈቀዱ የተከሳሹን ፍትህ የማግኘት እና የመከላከል መብቱን የሚያስጠብቅ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ ክሱን የሚያሻሽለው በራሱ ጥያቄ ፍርድ ቤቱን አስፈቅዶ ከሆነ መጠንቀቅ ያለበት በተከሳሽ ወይም በጣልቃ-ገብ አልያም በፍርድ ቤቱ ክሱን ሊያዘጋ የሚችል የተረሳን የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ሊነሱበት እና ክሱ ውድቅ ሊደረግ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚኖር ክስ ለማሻሻል ከመጠየቁ በፊት በጥንቃቄ ይህንን ነገር ማጤን የግድ ይለዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያና እሱን ለመወሰን መሰረት የሚሆነው ሕግ
በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ፍርድ ቤቱ አከራክሮ በመጨረሻም መቃዎሚያውን ውድቅ በማድረግ ሆነ በመቀበል ተገቢውን ውሳኔ የሚሰጥ ለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.245 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህንን ጉዳይ በዚህ ምዕራፍ ንዑስ ርዕስ በመስጠት ለመቃኘት አስፈላጊ የሆነበት ዋና ምክንያት ፍርድ ቤቱ ለተነሳው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ውሳኔ ለመስጠት የግድ ከሥረ-ነገር ሕጉ ጋር ማገናዘብ አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ከመኖርም በላይ ለተያዘው ጉዳይ ተገቢነት ያለው የሥረ-ነገር ሕግ የትኛው ነው የሚለው አከራከሪ በመሆን እስከ ሰበር ችሎቱ ደርሶ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸው ጉዳዮች ያሉ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አከራከሪ የሚሆነው ከሳሽ ላቀረበው ክስ በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ እና በመጨረሻም በፍሬ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከብዙ የፍትሐብሔር የሥረ-ነገር ሕጎች መካከል ትክክለኛው ተፈጻሚነት ያለውን የሥረ-ነገር ሕግ የትኛው እንደሆነ አወዛጋቢ ጉዳይ ይከሰታል፡፡ ከዚህ ላይ መነሳት ያለበት ነጥብ ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ቀድሞ በማስብ እርግጠኛ መሆን ያለበት ጉዳይ የተያዘውን ጉዳይ በፍሬ ነገር ላይ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ቢኖረው የፍሬ ነገር ጉዳዩን ውሳኔ የሚሰጥበት የሥረ-ነገር ሕግ የትኛው እንደሆነ መለየት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን ላይ ውሳኔ ለመሰጠት መሰረት የሚሆን የሥረ-ነገር ሕግ ሊሆን የሚችለው በመጨረሻ የፍሬ ነገር ጉዳዩን ውሳኔ ሊሰጥበት የሚችለው የሥረ-ነገር ሕግ በመሆኑ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በአንድ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያን ላይ ውሳኔ ለመሰጠት መሰረት ያደረገው የሥረ-ነገር ሕግ እና በመጨረሻ በፍሬ ነገር ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መሰረት ያደረገው የሥረ-ነገር ሕግ ተመሳሳይ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ (ከዚህ ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አለመሆኑ ሊዘነጋ አይገባም) ካልሆነ ፍርድ ቤቱ የውሳኔ እና የሐሳብ መጣረዝ እና መጋጨት የሚያጋጥመው በመሆኑ ታማኝነትን ያጣል፤ የተሳሳተ ፍርድም የሚሰጥ ይሆናል፡፡ከዚህ ላይ ነገሩን ይልጥ ለመረዳት እንዲቻል በምሳሌ እንመለከተው፡፡
ምሳሌ፡- ከሟች ጋር በሟች የውርስ ቤት ውስጥ ይኖር የነበር አንድ በሕጉ መሰረት ወራሽ ያልሆነ ሰው ሟች ሲሞት የሟች ሕጋዊ ወራሽ ቤቱን እንዲለቅ ሟች ከሞተ ከ11 ዓመት በኋላ የወራሽነት ምስክር ወረቀት ሳያወጣ እና የውርስ ማጣራት ሳያደርግ ቆይቶ ቤቱን እንዲለቅ በዚህ ቤቱን በያዘው ወራሽ ባልሆነ ሰው ላይ ክስ አቀረበ እንበል፡፡ ተከሳሹ በመልሱ ላይ የከሳሽ የመውርስ መብት በይርጋ ተግዷል የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ አቀርቦ ከሳሽም በቀረበበት የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ በቃል ክርክር ክስ ያቀረብኩት የማይቀሳቀስ ንብረት የሆነውን ቤት እንዲልቅ በመሆኑ የመፋለም ክስ ስለሆነ በይርጋ ሊታገድ አይገባም የሚል መከራከሪያ አቀረበ እንበል፡፡
በዚህ ምሳሌ ላይ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የከሳሽ የክስ መሰረት የሚሆነው መብት የመነጨው ከወራሽነት በመሆኑ ይህንን ጉዳይ በመጨረሻ ውሳኔ በፍሬ ነገር ላይ የሚሰጥ ቢሆን ከተከሳሹ ይልቅ ከሳሽ ወራሽ በመሆኑ በቤቱ ላይ መብት የሚኖረው እንደሚሆን ቀድሞ ማሰላሰል ይገባዋል፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቱ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው በውርስ ሕጉ እንጅ በንብረት ሕጉ ባለመሆኑ በዚህ የይርጋ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት የሚኖረው የውርስ ሕጉ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የከሳሽ ክስ የወራሽነት ክስ በመሆኑ የከሳሽ መብት በውርስ ሕጉ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1000 እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 6፣ ሰ/መ/ቁ.25664፣ 26422 ፣ 20295 እና ቅፅ 11፣ ሰ/መ/ቁ.52407 በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት አንድ ወራሽ የውርስ ሀብቱን የያዘው ወራሽ ያልሆነ ሰው ከሆነ ከሳሽ/ወራሽ በተከሳሽ (ንብረቱን በያዘው ሰው) ላይ ንብረቱን ለማስመለስ የሚያቀርበው ክስ (a suit of petition hereditatis) በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ካላቀረበ ወራሽ የሆነ ሰው ወራሽ ያልሆነ ሰው ንብረቱን በያዘው ከ10 ዓመት በኋላ ክስ ቢያቀርብበት መብቱ በይርጋ የሚታገድ ስለሆነ የከሳሽ መብት በይርጋ ታግዷል በሚል ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡
በዚህ ምሳሌ ላይ ፍርድ ቤቱ በዚህ መሰረት አንክሮ ሰጥቶ ሳይመለከት ክስ የቀረበበት የቤት ይለቀቅልኝ በመሆኑ የመፋላም ክስ የይርጋ ጊዜ የለውም በሚል ቀድሞ በመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ላይ ውሳኔ ከሰጠ ይህ ውሳኔ በመጨረሻም በፍሬ ነገር ላይ የሚሰጥ ውሳኔን ቀድሞ ያልተነበየ እና ያላገናዘበ በመሆኑ ሥህተት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከዚህ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ሲወስን ታሳቢ ማድረግ ያለበት ወደ ፊት በፍሬ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ለውሳኔው መሰረት የሚሆነውን የሥረ-ነገር ሕግ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅ የሕግ ትርጉምን ለአብነት ያክል ማንሳቱ ነገሩን ይበልጥ ለመገንዘብ የሚቻል ይሆናል፡፡
የሰበሩ ውሳኔ በሰ/መ/ቁ.204288 ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጠው የሕግ አስገዳጅ ትርጉም ላይ ከሳሹ ተከሳሽ በዕቃ ማጓጓዝ ውል መሰረት የተረከበውን ዕቃ በሀሰተኛ ሰነድ ለማይመለከተው አካል በማስረከቡ ጉዳት የደረሰብኝ በመሆኑ የእቃ ዋጋ ሊከፍለኝ ይገባል የሚል ክስ አቅርቧል፡፡ ተከሳሹ ከሳሽ ላቀረበው ክስ የመልቲ-ሞዳል ትርንስፖርት አዋጅ ቁጥር 548/1999 አንቀፅ 40 (1) እና (2) “ን” መሰረት በማድረግ በ6 ወር ይርጋ የከሳሽ መብት ቀሪ ሆኗል የሚል የይርጋ መቃዎሚያ በማንሳታቸው ከሳሽ በቃል ክርክር እስከ ሰበር የሚከራከሩት ተፈጻሚነት ያለው የመልቲ-ሞዳል ትርናስፖርት አዋጅ ቁጥር 548/1999 ሳይሆን ከውል ውጭ ሃላፊነት ሕግ በመሆኑ የይርጋው ጊዜ 2 ዓመት በመሆኑ ክሱ በይርጋ ሊታገድ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምንም እንኳን የከሳሽ ዳኝነት ዕቃውን ባለመረከባቸው ለደረሰባቸው ጉዳት የዕቃውን ዋጋ ተከሳሹ እንዲከፍላቸው ዳኝነት የጠየቁ ቢሆንም በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የነበረው ከውጭ ሃገር ዕቃን አጓጉዞ ሞጆ ደረቅ ወደብ ድረስ አቅርቦ ማስረከብ በመሆኑ ይህ ደግሞ ሊዳኝ የሚገባው በመልቲ-ሞዳል ትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 548/1999 እንጅ ከውል ውጭ ሃላፊነት ሕግ ባለመሆኑ የከሳሽ ክስ በ6 ወር ይርጋ ታግዷል በሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በፍርድ ቤት በራሱ እና በተከራከሪዎች ብቻ የሚነሱ መቃዎሚያዎችን
በዚህ ንዑስ ርዕስ የምናየው ገና ተከሳሹ ሆነ ጣልቃ-ገቡ ሳያነሳው (ተከራካሪዎች ባያነሱትም) በፍርድ ቤቱ በራሱ የሚያነሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን እና በተከራካሪዎች ብቻ የሚነሱ መቃዎሚያዎችን ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በየ ምዕራፉ እንደ ነገሩ ሁኔታ የሚብራራ ሲሆን በዚህ ንዑስ ርዕስ የምንመለከተው ግን ጠቅለል ባለ መልኩ አንባቢዎች አንዳንድ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ገና ተከሳሹ ሆነ ጣልቃ-ገቡ ሳያነሳው (ተከራካሪዎች ባያነሱትም) በፍርድ ቤቱ በራሱ የሚያነሳቸው ያሉ ለመሆኑ እና ፍርድ ቤቱ በራሱ ማንሳት የማይችላቸው በተከራካሪዎች ብቻ የሚነሱ መቃዎሚያዎችን ያሉ ለመሆኑ በመጠቆም ፍንጭ ለመስጠት ነው፡፡
በተከራካሪዎች ብቻ የሚነሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች
እነዚህ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ፍርድ ቤቱ በራሱ የማንሳት ስልጣን የለውም፡፡ ፍር ቤቱ እነዚህ መቃዎሚያ በራሱ አንስቶ ውሳኔ ከሰጠ ከፍርድ ቤቱ ስልጣን ውጭ የተከወነ ድርጊት በመሆኑ በይግባኝ የሚሻር ከመሆኑም በላይ ፍርድ ቤቱ ለአንዱ ተከራካሪ ጠበቃ የመሆን ያከል ሚና ተጫውቷል ተብሎ ውሳኔ የሰጡ ዳኛም በሥነ-ምግባር ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ በመርህ ደረጃ ፍርድ ቤት በራሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ማንሳት የማይችሉ ለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.244 (3) ላይ መቅረብ ከሚገባቸው መቃዎሚያዎች ውስጥ ሳይቀርቡ የቀሩት…ባለጉዳዩ ራሱ ሆን ብሎ ለማቅረብ ባለመፈለጉ እንደተዋቸው ይቆጠራሉ በማለት ካስቀመጠው ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ተከራከሪዎች መቃዎሚያዎችን የማንሳት መብት ያላቸው ለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.234 (1) (ሐ) እና 244 (1) እንዲሁም ከሌሎች የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እና ከበርካት የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት እንደሚቻለው …ተከራካሪ ወገን ላቀረበው ፍርድ ቤቱ ቀድሞ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡
እነዚህ በተከራካሪዎች ብቻ የሚነሱ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በራሱ ማንሳት የማይችላቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች የሥረ-ነገር ሕግ የይርጋ መቃዎሚያ፣ የፍርድ ቤቶች የግዛት ሥልጣን፣ አንደኛው ተከራከሪ ክርክሩ የማይመለከተው ለመሆኑ የሚነሳ መቃዎሚያ ናቸው፡፡
በሌ በኩል በግልግል ዳኝነት ለመጨረስ ስምምነት በተደረገበት ጉዳዩ ላይ ለፍ/ቤት ከሳሹ ክስ ሲያቀረብ ተከሳሹ በግልግል ዳኝነት ለመጨረስ ስምምነት ያላቸው ለመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ለፍ/ቤቱ ሳያቀርብ ሲቀር ጉዳዩን አይተው የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቱ በራሱ ስልጣን የለኝም በማለት ክሱን ውድቅ ማድረግ የማይችል ለመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀፅ 8(3) ላይ ለመረዳት ይቻላል፡፡
ፍርድ ቤቱ በራሱ ሊያነሳቸው የሚችሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች
አንዳንድ የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ተከራካሪዎች ባያነሷቸውም በፍርድ ቤቱ በራሱ ማንሳት የሚችላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መቃዎሚያዎችን የማንሳት ስልጣን የፍርድ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የተከራካሪዎችም ጭምር ማንሳት የሚችላቸውን ናቸው፡፡ ከዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ፍርድ ቤት በራሱ ማንሳት የሚችላቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎችን በሙሉ ተከራካሪዎች የማንሳት መብት ያላቸው ለመሆኑ ነው፡፡
ተከራካሪዎች ባያነሷቸውም በፍርድ ቤቱ በራሱ የሚነሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያዎች ያሉ ለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.244 (3) ላይ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት የሚያሰናክሉ የሆኑ መቃዎሚያዎችን ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፍርድ የፍርድ ቤቶች የሥረ-ነገር ሥልጣን፤ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ይርጋ፤ ጉዳዩ በውሳኔ ያለቀ ነው የሚሉት መቃዎሚያዎች ናቸው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments