መነሻ ነጥብ[1]
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር በ1958 ዓ.ም.በእድርና እቁብ አይነት ቅርጽ የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ በሰዓቱ ከአርባ የማይበልጡ አባላት የነበሩት ሲሆን አባሎቹም በከተማይቱ አዲስ አበባ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ይህ ማህበር የተደራጀና የአባላቱን እንዲሁም የተከበረ ሙያ የሆነውን የጥብቅና ሙያ ለማስጠበቅና ለመጠበቅ ሳይሆን በማህበርተኞች መካከል ለሚፈጥሩ ማህበራዊና ሰዋዊ ችግሮች ለመረዳዳት ተብሎ የተመሰረተ ተቋም ነበር፡፡ ይህ ስብስብ በተመሰረተ በአመቱ ማለትም በ1959 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር የሀገር ግዛት ሚኒስቴር ተመዝግቧል፡፡ ከአብዮቱም በኋላ የኢትዮጵያ የጠበቆች ማህበር የሚለውን ስያሜ የያዘ ሲሆን በማህበሩ ውስጥ ጠበቆች፣ የሕግ መምህራን፣ ዳኞች፣ የሕግ ጉዳይ ፀሐፊዎች እና ሌሎችም አባል ሆነው ይሰሩ ነበር፡፡ ስሙን ቀይሮ የመጣው ማህበር የግብርና የዓላማ ለውጦችንም በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የጥብቅና ሙያ እንዲኖር ግንባር ቀደም ዓላማው አድርጎ ተነሳ፡፡ በወቅቱም ልክ አሁን እንዳለው ተመሳሳይ አሰራር የጥብቅና ፍቃድ በማሳየትና የአባልነት ክፍያ በመክፈል አባል መሆን ይቻል ነበር፡፡
ብዙ ያነጋገረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ ማለትም አዋጅ ቁጥር 621/2000 ከወጣ በኋላም ማህበሩ በድጋሚ ምዝገባ የማህበሩን ስያሜ ከኢትዮጵያ የጠበቆች ባለሙያዎች ማህበር ከሚለው ወደ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ለውጦ ተመዝግቧል፡፡ የስም ለውጡ በሁለት አበይት ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ አንደኛው በክልሎች ላይ የጠበቆች ማህበር የሚለው ስያሜ ስላለና ይህንን ተመሳሳይ ስም ሌላ ማህበር መጠቀም አይችልም በማለት ሲሆን ሁለተኛው ዐብይ ምክንያት ደግሞ ማህበሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አባላት ጠበቆች ብቻ ስላልነበሩ የጠበቆች ሳይሆን የሕግ ባለሙያዎች ቢባል ሁሉንም አካታች ስለሚሆን መልካም ነው በሚል ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ማህበሩ ከሰባት መቶ ያልበለጡ አባሎች ያሉት ሲሆን ወርሀዊ መዋጮውም ሀምሳ ብር ነው፡፡