ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። በዋናነት የእነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊነት ዉጤት፤ አሁን ተበጣጥሶ የሚገኘውን በገጠር መሬት ላይ የግብርና ውሳኔ መብት በአንጻራዊነት እንዲማከል ማድረጉ ነው። የግብርና ውሳኔ ማለት፥ በአንድ እርሻ ላይ ምን ላምርት? መቼ ላምርት? ምን አይነት እና መጠን ያለው ማዳበሪያ ልጠቀም? ምን አይነት የውሃ ቴኬኖሎጂ ልጠቀም? ምን አይነት ማረሻ፥ ማጨጃ፥ እና መውቂያ ልጠቀም? ምን አይነት የመሬትና አፈር ጥበቃና አስተዳደር አሰራሮችን ልከተል? እና የመሳሰሉት ናቸው። ከግብርና ውሳኔዎች ጋር የሚገናኙ የገበያ ውሳኔዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ ምን ያህል ምርቴን፥ መቼ፥ ለማን ልሽጥ? ምን ያህል ገንዘብ፥ ከማን፥ በምን ያህል ወለድ ልበደር? እነዚህና የመሳሰሉት ገበያ ነክ ውሳኔዎች ካነሳኋቸው ነጥቦች ጋር በቀጥታ አይገናኙም። እኔ ያነሳሁት የግብርና ውሳኔዎችን ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት አይነት መበጣጠሶች ይታያሉ። አንደኛው በቀደመው ጽሁፍ እንዳብራራሁት የመሬት መበጣጠስ አለ። በእርግጥ የመሬት መበጣጠሱ ሁኔታ እንደቦታው ይለያያል። እኔ ያደኩበትን አካባቢ ኢህአዴግ ከደርግ ነጻ እንዳወጣና ደርግን ተክቶ የሕዝብ አስተዳደር ሃላፊነትን ሲወስድ ካደረጋቸው ነገሮች አንደኛው መሬትን መልሶ ማከፋፈል ነው። ለምን? ምክንያቱም ጥቂት ‘አድሃሪያን’ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ጥሩ ጥሩ መሬቱን በብዛት ስለያዙት። እኔ በበኩሌ የመሬት ክፍፍልና ራሱን አልቃወምም። የኔ ነጥብ የዚህ መሬት ክፍፍልና የክፍፍሉ ስልት ስለፈጠረው የመሬት መበጣጠስ ነው። እንደገለጽኩት አንድ ገበሬ ከግማሽ ኳስ ሜዳ ያነሱ፥ ሶስትና አራት እርሻዎች ይኖሩታል። አንደኛው የጓሮ መሬት ሲሆን ሌሎች ከመኖሪያ ጎጆዉ በተለያየ አቅጣጫ በተለያየ እርቀት ይገኛሉ። የመሬት መበጣጠስ የምለው ይሄን ነው። ሁለተኛው አይነት መበጣጠስ፥ የግብርና ውሳኔዎችን የመስጠት መብት መበጣጠስ ነው።
ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል (economy of scale)
የሁለት አይነት መበጣጠሶች፥ መጠን/ስኬል ከሚያስገኘው ጥቅም መጠቀም እንዳንችል ሆኗል። ብዙ አይነት የስኬል ጥቅሞች አሉ። አንደኛው ስኬል የሚባለውና ብዙ የሚታወቀው፥ ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ነው። ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ማለት በብዛት በማምረት የሚገኝ የነፍስ ወከፍ ወጪ መቀነስና የምርት መጨመር ነው።