1. መግቢያ
ሕገ መንግሥት በባሕርይው ጠቅላላ ድንጋጌዎችን የሚይዝ በመሆኑ፤ ሕገ መንግሥትን ከተለዋወጭ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር ለመጣጣም እና ዘላቂነት ኖሮት ገዚ ሆኖ እንዲኖር ያስችል ዘንድ ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሲባል የተፃፉ ሕገ-መንግሥት ያላቸው ሀገራት በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ማሻሻያ ሥርዓቶችን ወይም ማስተካከያ የሚደረግበት ሂደት የሚደነግጉ አንቀጾችን አካተው ይይዛሉ፡፡ በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥትም እንዴት እንደሚሻሻል የማሻሻያ ሥርዓቶቹን በአንቀጽ 104 እና 105 ስር ተደነግጎ ቢገኝም እስካሁን ድረስ ሥርዓቶቹን ተከትሎ ማሻሻያ ሳይደረግበት ቆይቷል።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴን ታህሳስ 9 2014 ዓ.ም ለቱርኩ አናዶል ኤጀንሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲያጨቃጭቁ የቆዩ ጉዳዪች ላይ ምክክር ማድረግና ለሕዝበ ውሳኔ በማቅረብ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልን ጨምሮ ሁሉን አካታች ሀገራዊ የምምክር መድረክ ለማካሄድ መታቀዱን ተናግረዋል። በተመሳሳይ መልኩ የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድም የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ምክክር እንደሚደረግ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሰረትም አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ የታመነበት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክር ኮሚሽን መቋቋሚ አዋጅ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ነግር ግን የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓቶች እጅግ ውስብስና ጥብቅ (very stringent and rigid) ስለመሆናቸው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡