በሀገራችን ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ሲከሰት መንግሥት በሕግ የተቀመጠለትን መደበኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ፈንታ በስም የተለየ ነገር ግን በአተገባበር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን የሕግ ማስከበር መንገድ ‘ኮማንድ ፖስት’ በሚል ስያሜ እያዘወተረ እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡም ይህንኑ ኮማንድ ፖስት የተባለውን ስያሜ እኩል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አገናኝቶ ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኮማንድ ፖስት መንግሥት በመደበኛ የሕግ ማስከበር መንገድ ሕግን ማስከበር ሲቸገር እየተጠቀመው የሚገኝና በተግባርም የግለሰቦችን መብት የሚገድቡ ክልከላዎችን ጭምር በማውጣት በተግባር ተጠያቂ እያደረገ በመስተዋሉ ነው፡፡ ብዙን ጊዜ ይህንን አዋጅ ሲያውጅ የሚስተዋለው በፌደራል ደረጃ የተዋቀረ ‘ብሔራዊ የፀጥታ ም/ቤት’ የሚባል አካል እነደሆነ ይደመጣል፡፡ ይህ አካል አዋጁን ያውጅ ዘንድ በሕገ-መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው አካል እንዳይደለ መረዳትም ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል እየተዘወተረ የመጣው የክልሎች የጸጥታ መደፍረስን ምክንያት በማድረግ ‘ኮማንድ ፖስት’ እያወጁ የግለሰቦችን መብት መገደብ በብዛት እየተስተዋለ የመጣ ሲሆን ይህ ስልጣን በህገ-መንግስቱ ለነርሱ ያልተሰጠ ሆኖ ሳለ ይኸው ‘ኮማንድ ፖስት’ የተባለው ሲያሜ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው እንመለከታለን፡፡
በዚህ ጽሑፍ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንነት፤ ለምን እንደሚታወጅ፤ ማን እንደሚያውጀው እና ሲታወጅም ይሁን ከታወጀ በኃላ አዋጁንና አፈፃፀሙን በሚመለከት ሊሟሉ የሚገባቸው ይዘታዊም ሆኑ ሥነ-ሥርዓታዊ የሕግ መጠይቆችን እንመለከታለን፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘንም ከላይ ያተትነው ኮማንድ ፖስት የተባለው አዋጅን ከመደበኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጽንሰ ሃሳብ ጋር አገናኝተን እንመለከትና በዚሁ ኢ-መደበኛ አዋጅ ያሉትን ችግሮች ነቅሰን በማውጣት መሆን አለበት የምንላቸውን መፍትሔዎች እናስቀምጣለን፡፡
መግቢያ
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት መንግሥት በመደበኛ ሕግና የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግን የማስከበር አቅሙ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ የሚታወጅ የግለሰቦችን መብት የመገደቢያና የተፈጠረን ችግርን ለመፍታት የሚሰራበት የሕግ ስሪት መንገድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ምንጫቸው ተፈጥሮአዊ (ለምሳሌ፡- የመሬት መደርመስ /መንሸራተት/፤ ያልተጠበቀ ጎርፍ እና የህዘብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተላላፊ በሽታዎች መከሰት ወይም ሰው ሰራሽ (ለምሳሌ፡- የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፤ አመጽ፤ መፈንቅለ መንግሥትና የመሳሰሉት….) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡