ዋስትና በሕገ መንግሥትም ሆነ የሕገ መንግሥቱ የበታች በሆኑ በርካታ ሕጎች የታፈረና የተከበረ መሠረታዊው ከሆነው የሰው ልጅ የመዘዋወር ነፃነትና ንፁሕ ሆኖ የመገመት መብት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደፈለገ ለመዘዋወር ሁለት እግሮች የተሰጡት፤ በአንድ ቦታ ተወስኖ እንዳይቀመጥ ሰዋዊ ተፈጥሮ ነፃ አድርጎ የፈጠረው ይህን ተፈጥሮውንም አብዝቶ የሚወድ ነፃ ፍጡር ነው፡፡ ይህ ፍጡር አሳማኝ የሆነ ማስረጃ በማቅረብ አንዳች ወንጀል መፈፀሙ ካልተረጋገጠበት በስተቀር ንፁህ ሆኖ የመቆጠር መብትም አለው፡፡ 

ይህ ከላይ ከፍ ሲል የተገለፀው ነፃ ሰው በሕግ ከመዘዋወር ሊከለከል፤ በአንድ በተለየ ስፍራ ታስሮ ሊቀመጥ የሚችለው ለጠቅላላው ሕዝብ ጥቅም ሲባል፣ የጠቅላላውን ሕዝብ ጥቅም ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ምንአልባት የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ማክበር ይህን የጠቅላላውን ህዝብ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህንን የጠቅላላውን የሕዝብ ጥቅም ለመታደግ ሲባል ብቻ አስቀድሞ በተቀመጠ ሕግ ሊገደብ የሚችል መሠረታዊ መብት ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ መነሻ ከመነሻው የዋስትና መብትን መገደብ ሕገ መንግሥታዊ ነው ወይስ አይደለም የሚል ሳይሆን ክርክርን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ የሚያስችል ሥርዓት (speedy trial) መኖሩን እርግጠኛ ባልተሆነበት ሁኔታ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ወንጀል ፈፅሟል በሚል ክስ ስለቀረበበት ወይም ሊቀርብበት ስለሚችል ብቻ ዋስትና መከልከል ሕገ መንግሥታዊ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡

በኛ ሀገር የሕግ ሥርዓት አንድ ሰው በተጠረጠረበት ወንጀል ሊከሰስ የሚችል ከሆነ ወይም ከተከሰሰ የተከሳሹ ግላዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምንም ከመነሻው ወዲያውኑ ዋስትና የሚያስከለክሉ በርካታ የወንጀል ዓይነቶች አሉ፡፡ ከፍ ሲል የተገለፀውን ጥያቄ ለመመለስ በምሳሌነት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለመጠቀም የወደደው የሙስና ወንጀሎችን ነው፡፡ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882 አንቀጽ 3 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው አንድ ሰው ከ10 አመት ፅኑ እስራት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተያዘ ወይም የተከሰሰ እንደሆነ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በመገኘቱ ብቻ ከፍ ሲል የተገለፀውን መሠረታዊ የዋስትና መብቱን ከጅምሩ ያጣል፡፡

ይህ ሁኔታ ከፍ ሲል የዋስትና መብት ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል ሊገደብ ስለመቻሉ ከተነገረው ጋር የሚስማማ ይሁንም አይሁንም ጉዳዩን በአጭር ጊዜ አይቶ ለመወሰን የሚያስችል የሰው ኃይል አሠራር እና ሥርዓት ስለመኖሩ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አንድን ሰው በሕግ ከጅምሩ የዋስትና መብቱን መከልከል የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 20 እንዲሁም ኢትዮጵያ በመፈረም የሕጓ አካል ያደረገችውን የአለም አቀፉን የሲቪል እና የፖለቲካ ስምምነት (ICCPR) አንቀፅ 14 (3) (ሐ) ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ይሁን የአለም አቀፍ ስምምነቱነቱ አቀራረብ ግልፅ እና ቅልብጭ ያለ ሲሆን ይኸውም ማንኛውም ሰው በአጭር ጊዜ ፍትሕ የማግኘት መብት አለው ወይም ካላስፈላጊ የፍትሕ መዘግየት የተጠበቀ ነው፡፡

ይህ መሠረታዊ መብት ነው እጅግ በተለመደ ሁኔታ የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል (justice delay justice deny) በሚል በሕግ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲገለፅ የሚሰማው፡፡ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ተብሎም ይቀጣል ድርጊቱን አልፈፀመም ተብሎም ነፃ ይለቀቅ መሠረታዊው ነገር ተከሳሹ/ተጠርጣሪው/ ነፃ የወጣውም ሆነ የተቀጣው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው የሚለው ነው? የሰው ልጅ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ የማወቅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ያለው መሆኑን ሳይታበል በጊዜው ያልተሰጠ ፍርድ በተለይ በወንጀል ችሎቶች በሚፈፅሙ ስህተቶች እና መዘግየቶች የካሳ ሥርዓት ባላዘጋጀች እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሀገር ውስጥ ለረዥም ጊዜ ታስረው ነፃ የወጣ ወይም ሊቀጣ ከሚገባው ጊዜ በላይ በእስራት የተቀጣ ሰው ማየት በተለይም በፀረ ሙስና ችሎቶች እየተለመደ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የዚህ ጽሑፍ መነሻም በፀረ ሙስና ችሎቶች ዋስትና ተከልክለው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ተከሳሾች ጉዳያቸው የሚያልቀው እጅግ በተራዘመ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ 

የጽሑፍ አቅራቢ በበርካታ የፀረ ሙስና የክስ ሂደቶች መታዘብ የቻለው አንድ ጉዳይ በትንሹ ከ1 ዓመት እስከ 2 አመት ከ6 ወር ድረስ በአማካኝ ይወስዳል፡፡ የተጠቀሰውን ያህል ጊዜ ታስረው በነፃ የወጡ አንቀጽ ተቀይሮ ወይም በሌላ ምክንያት አነስተኛ ቅጣት ተቀጥተው መቀጣት ከሚገባቸው በላይ የተቀጡ በርካታ ተከሳሾች ያሉ ሲሆን በዚህ ሂደት ከተገኘ ፍርድ ተጠርጣሪው ሊረካ እንደማይችል ጥቅሙ አደጋ ላይ ወድቋል የተባለው ሕዝብም ሆነ ይህንን የጠቅላላውን ሕዝብ ጥቅም በመወከል ሕግ የሚያወጣው ሕግ አውጪም ፍላጎት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡

እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሀሳብ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ የሚያስችል ሥርዓት ባልተዘረጋበት ስለመኖሩም እርግጠኛ ባልተሆነበት የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ከመነሻው ዋስትና የሚያስከለክሉ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ከፍ ሲል የተገለፀውን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚፃረር ተግባር ነው፡፡ የተጠርጣሪው በዋስ የመፍታት መብት ለሕዝቡ ጠቅላላ ጥቅም ሲባል በሕግ የሚገደብ ቢሆንም ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የተገደበን የዋስ መብት ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነና የጠቅላላው ሕዝብም ፍላጎት ባልሆነ የተራዘመ የፍትሕ ሂደት ይበልጥ ተገድቦ እንዲቆይ ማድረግ ፍፁም ሕገ መንግስታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ 
በመሆኑም ከጅምሩ የዋስ መብት በሚከለክሉ ወንጀሎች ሁሉ የተፋጠነ ፍትሕ /የፍርድ ሒደት/ መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር ዋስትና መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም

1. ከጅምሩም የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል፡፡

2. ከመነሻው ሊከለከል የማይገባውን ነገር ግን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በሕግ የተገደበን መብት ለተራዘመ ጊዜ እንደተገደበ ማቆየት በራሱ ፍትሕ አይደለም፡፡

 

3. አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ ታስሮ ቆይቶ በመጨረሻም በሚሰጠው ፍርድ የሚደርስበት ጉዳት ሊካስ የማይችል ቢሆንም በካሳ መልክ ማካካስ ቢቻል እንኳ ይህንን ማድረግ የሚያስችል የሕግ ሥርዓት ባለመኖሩ ከማንኛውም ዋስትና ከሚያስከለክል ወንጀል በፊት የተፋጠነ የፍርድ ሂደት መኖሩ ፍጹም መረጋገጥ አለበት፡፡